Monday, 19 June 2017 09:30

የፌስቡክ ጥበበኞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

  “Day and night, throughout their entire lives, men think.” የሰው ልጅ ሕይወቱን ሙሉ፣ መዐልትና ሌቱን ያስባል፣ ያሰላስላልም። እያንዳንድዋ ሽራፊ ሰከንድ፣ ሀሳብና ሕይወት ባንድ ቀንበር ተጣምረው ይኖራሉ፡፡ ጧፉ ይድመቅ አሊያም ይፍዘዝ እንጂ፣ ብርሃን አለው፡፡
ጊልበርት ሃይጌት ስለ ስሌት ሲፅፉ ነው እንዲህ ያሉት፡፡ እኔ ደግሞ ስለ ኪነ ጥበቡ ሳስብ ነው፡፡ ኪነ ጥበብ የመኖር ውጤት፣ የማሰብ ትሩፋት ነው። ምናልባትም የህይወት ልቀትና ከፍታ፣ ውጤት ልንለው እንችላለን፡፡ የምድር ህይወት እርግጠኛ ያልሆነች ድርሰት፣ ሁሌ የምትገለጥ፣ አዳዲስ ገፆች ያሏት ጥራዝ ናት፡፡ ያንን አዲስ፣ ያንን ግርምት፣ እንደ ሽንኩርት መላጥና አዲስ ቀለም ማምጣት ነው - ክየና!
“The mind of the scientists, exploring space and matter, is closely related to the mind of the poet.” ይላሉ ስታንሊ ኩንቲዝ - ህዋ ላይ ሀሰሳ የሚያካሂደውን ሳይንቲስትና በልብ ውስጥ ሀሳብ የሚያስሰውን ገጣሚ በእጅጉ ለማቆራኘት፡፡ እንደኛ ሀገር ዕውቀት ብርቁ, ንባብ ሩቁ ለሆነበት ህዝብ ግን ጥበብ እንደምናምንቴ ይታያል፡፡ የተማርንበትን የምስክር ወረቀት ቆልለን፣ የዕውቀት ቋታችን ኦና እየሆነብን ስለመጣ፣ እንኳን ራቅና ላቅ ወዳለ ጥበብ፣ የተማርነውንም ነገር በቅጡ መፈፀም ዳገት ሆኖብናል፤ ጥሩ ዘመን ያምጣልን ከማለት ውጭ፣ ህልማችን ተሰርቋል፤ ዝም ነው፡፡
ብዙ ጊዜ የጥበብ ሰዎች የሚበዙት ምጥ ሲበዛ ነው ይባላል፡፡ ጦርነት … ረሀብ … የነፃነት ጥማት፣ ሰውን በጥልቀት እንዲያስብና ትርጉም እንዲፈልግ ያስገድዱታል፡፡ ያኔ ደራሲና ገጣሚ፣ በጥቅሉ ከያኒ ይበዛል፡፡ ታዲያ የከያኒ መብዛት፣ ባንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሻማ እንደመለኮስ ስለሆነ፣ ክፋት የለውም። ለተጠቀመበት፣ እንዲያውም ለንቃት፣ ለትጋትና ለስኬት መንገድ ያበጃል፡፡ በፈረሰው ቅርጥም ዘብ ይቆማል፡፡
እኛ ሀገር ያለውን የከያኒ መወለድና ማደግ፣ በወረቀት ላይ ብቻ የምናስስበት ዘመን አልፏል፡፡ ፌስ ቡክ ሌላው የከያንያን መታያና፣ መቀኛ ስፍራ እየሆነ መጥቷል፡፡ ፌስ ቡክ ራሱን የቻለ ሀገር፣ ራሱን የቻለ ዓለምም ነው፡፡ በዚያ መንደር፣ ተሰሚ የሆኑ፣ የታወቁና የታጠቁ ሰዎች አሉ፡፡ ለተኩስ የተዘጋጁ፣ ስድብን አጣጥመው የጠገቡ፣በቀና ልብ ሌሎችን ሊያቀኑ የሚታትሩ፣ ፖለቲካና እምነታቸውን፣ ዘርና ሃይማኖታቸውን እንደ ሰንደቅ ከፍ ያደረጉም ሞልተዋል፡፡ በጥላቻ የተሞሉ፣ ፀያፍና ሀራም ቋንቋ የተጠናወታቸው፣ ስማቸውንና ስብዕናቸው እየቀያየሩ፣ ያልፈለጓቸውን ለማስወገድ፣ በአራቱ ማዕዘናት ቀስት የሚወነጭፉ ብዙ ናቸው፡፡ የቂል ወሬ እያወሩ፣ አርቴፊሻል ዘውድ የጫኑም አሉ፡፡
እንደ ዣክ ሩሶ፤ ንስሃ ለመግባት ልባቸውን ያዘጋጁ፣ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ፍቅር የሚሰብኩ፣ እንደ ሂትለር ጨካኝ ልብ ያላቸው፣ እንደ ክርስቶስ እኔን ባንተ ፋንታ የሚሉም ሞልተዋል፡፡
እኔ አገባቤ፣ የዘገየ ስለሆነ ለሁሉም ነገር እንግዳ ነኝ፡፡ … የሚያስጠሉ ብዙ ነገሮች አይቼ እየሸሸሁ፣ ደግሞ ገና እሸት ልብ ያላቸው፤ገና ለውበት የተገለጡ፣ አበባ ሀሳቦች ያነቦጡ ወጣቶች አየሁ፡፡ እናም እነዚህ ወጣቶች ትንሽ ትንሽ ውሃ ቢያገኙ፣ … የጎደላቸውን ነገር ከእነ ምልአታቸው ብንነግራቸው የሚል ጉጉት ያዘኝ፡፡ በተለይ ገጣሚያኑ ላቅ ያለ አቅምም ያላቸው ናቸውና ተስፋዬ ብዙ ነው፡፡ መጽሐፍ ያሳተሙ፣ ያላሳተሙም አሉ፡፡ ዕውቀት የሚጋሩና፣ ልምድ የሚያካፍሉም እንዲሁ! … ታዲያ ዛሬ ልቤ ያዘነበለው፣ ፌስ ቡክ ላይ ፅፈው ወረቀት ላይ ያልተነበቡትንና፣ … ቀደም ሲል ወረቀት ላይ የታዩትን ገጣሚያን ግጥሞች አብሮ ማየት ነው፡፡
ከአነዚህ ገጣሚያን መካከል ሩቅ ሀገር ነዋሪዋ ሰሚራ አማን አንዷ ናት፡፡ ሰሚራ አጫጭር ታሪኮችና ግጥሞች ትፅፋለች፡፡ ከግጥሞቿ ትንሽ ብናይ ደስ ይለኛል፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም የሰሚራ ኑሮ ሰሜን አሜሪካ ሳይሆን አይቀርም፡፡
የቅርቡን የሩቁን - በምናቤ እያየሁ፣
ቅኔዬን የምቀኝ - ሳላይ ሆኜ እንዳየሁ፣
ገጣሚ እሰኛለሁ፡፡
ፊደላት ደርድሬ - ቃላት አሳክቼ፣
ያልሆንኩትን ኖሬ - ያልሞትኩትን ሞቼ፣  
አዎ ገጣሚ ነኝ - የምዋሽ አብዝቼ፣
ከባህር ሰጥሜ - እንደ ዓሳ ሳልዋኝ፣
የማዕበል ግፊት - ወጀብ የሚሰማኝ፣
ከውሃ ዳር ቆሜ - ውሃ የሚጠማኝ፣
ቅዠት የበዛብኝ - ያልተፈታ ህልሜ፣
ሳያመኝ ያመመኝ - የጠና ህመሜ፣
ሌቱ ያልነጋልኝ - ቀኔ የማይወጣ፣
አቀበት ቁልቁለት - ምዳክር ልወጣ፣
አዎ ገጣሚ ነኝ
*    *    *
ዲያብሎስ በምስጢር - ፍቅር የሚያወጋኝ፣
አምላክ በጥበቡ - ከሁሉ የሚያላጋኝ፣
ሰማይ የቀረበኝ - ምድር የራቀብኝ፣
በምድረ በዳ ላይ - ተስፋን የምዘራ፣
በቃላት ቀረርቶ - በፊደል ድርደራ፣
ባልሞቀ ምድጃ - ምጋግር እንጀራ
ሰሚራ ስለ ገጣሚ ህይወትና አዙሪት ነው የተቀኘችው፡፡ በምናብ ዓለም የሚፈጠረውን ፍልሚያ፣ ሕልምና ተስፋ ነው ያወራችው፡፡ ያንን ህልምና ተስፋ፣ ትዝታና ዑደት መልክ ለመስጠት፣ ምሰላ ለመፍጠር ቃላት ደርዳሪ፣ ቀያሽ መሀንዲስ ነኝ-----እያለች ነው ገፀ ባህሪዋ!
“ሳልታመም - ያመመኝ፣ ያልሆንኩትን የምሆን” ትላለች፡፡ እውነት ነው፡፡ ገጣሚ በሌላ ሰው ገላና ህይወት ውስጥ ገብቶ ይኖራል፡፡ የሌላውን ሰው ጎጆ እያጠነ፣ .. የረሀብተኞችን እንጀራ ለመጋገር ይባትታል፡፡ ያለ ወጉ ዲያብሎስ ስለ ፍቅር ያወራዋል፣ አምላክ ያላጋዋል፡፡
ይሁንና በምድረ በዳ ላይ ተስፋ ይዘራል፡፡ ሰማይ ቅርቡ ምድር ሩቁ ሆኖ፣ ነገሮችን የግሪንቢጥ ያያል፡፡ ሰሚራ በአንደኛ መደብ አንፃር የተረከችው ይህንን ነው፡፡ ቤት አመታትዋ ሸጋ ሆኖ፤ አንዳንዴ አንጓውን በእንጥልጥል ትታ ወደ ሌላ ትሻገራለች፡፡ ይህ የሚሻሻል ነገር ነው፡፡ ትንሽ የሰባኪነት ባህርይም አለው፤ ሙሉ ግጥሙ፡፡ ግና ደሞ ብዙ ነገሮችዋ ጥሩ ናቸው፡፡ ማለፊያ የሚባሉ…
ገፃሚ በላይ በቀለ ደግሞ ፌስ ቡክ ገፁ ላይ እንዲህ ይላል፡-
ልሳምህ አለችኝ ደሞ አለማፈሯ
ኩበት በሚመሥል በደረቅ ከንፈሯ፡፡
 በላይ በቀለ ወያ፤በአተያዩ እጅጉን የራቀና የላቀ ወጣት ገጣሚ ነው፡፡ ‹‹እንቅልፍና ሴት›› በሚለው መጽሐፉ በእጅጉ የሚመሥጡና የሚያረኩ ግጥሞች የፃፈው በላይ፤ፌስ ቡክ ላይም አስገራሚ ግጥሞች አሉት፡፡… (ስስ ጎኖቹን ሳንረሳ) ለምሳሌ ስለ ሆሣዕና የፃፈው ግጥም መሳጭና ገራሚ ነው፡፡
አማኝ ነኝ ያለ፤
የዘንባባ ቅጠል እየገነጠለ
ሆሣዕና እያለ
ስለጌታ መምጣት፣ ጮሆ ይዘምራል
በጌታ መንገድ ላይ፤
ልብሱን ያነጥፋል፤ ቅጠል ይከምራል፤
ይህንን ያየ አይሁድ…
አማኞች መልምለው
ከተውት ግንድ ላይ፤ መስቀልን ይሰራል፡፡
ማን ያውቃል ይህንን
በጌታ መንገድ ላይ፤
ቅጠል ያነጠፈ፤ እየመለመለ
መስቀል ለሚሰራም
እገዛ እንዳረገ፤ ስራ እንዳቃለለ፡፡
ስለ ሆሳዕናና ስቅለት፤ ብዙ ግጥሞች ተፅፈዋል፡፡ ግን ደግሞ እንዲህ አልተፃፉም፤ እንዲህ አልታዩም። የዚህ ወጣት ግጥሞች ሁለት ነገር ያጣምራሉ፡፡ እርካታና እሴት!....
አሥቡት፤ ዘንባባ ዘንጣፊዎች ለመሲሁ በሚያዘጋጁት የክብር ዝግጅት ቀን! ለካስ ዘንባባውን ሲመለምሉ፣ የመስቀሉን ቆረጣ ስራ እያቃለሉ ነው … ይህንን ለማየት መወለድ ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካዊው ፕሮፌሰርና የስነ ግጥም ተመራማሪ እንደሚሉት፤ ገጣሚን አሪፍ ገጣሚ የሚያሰኘው የተለመደውን ጉዳይ አዲስ አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡
በበላይ በቀለ ይህቺን ነገር ግን ማሳበብ እወድዳለሁ፡፡ … የቃላት ከፍታን ለመጨመር፣ ስነ - ቃሎችንና የአማርኛ መዝገበ ቃላትን ማንበብ! … በተረፈ በዚህ ዕድሜው እንዲህ ካሰበና ከፃፈ፣ ወደፊትማ የፌስ ቡክ ክበብ፣ የነገ ታላላቅ ከያኒያን ምንጭ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እሳት መሸሽ ሳይሆን፣ እሳቱን ከማቃጠል፣ ወደ ማብሰል እንዲቀየር ለማድረግ የበኩላችንን ልናዋጣ እንችላለን። … በተለይ ወጣት ከያኒያንን በማበረታታት! ….

Read 3117 times