Monday, 19 June 2017 09:51

ዳልች

Written by  በአለማየሁ ጌትነት (ኢብታ)
Rate this item
(7 votes)

 ዳልች፤ እንጢጥ ያለ ጥጋበኛ ነው፡፡  ....የሰው ማሳ ገብቶ ሰብል ሲያወድም፤ ሴት ወይም ጉብል ሊከለክለው ከመጣ፣ ቀጥ ያሉ ጆሮዎቹን ወደ ጋማው ልጎ፣ ወደ አባራሪው ይንደረደራል፡፡ . . . እንግዲህ እየጮሁ መሮጥ የአባራሪው ፋንታ ይሆናል፡፡  ደሞ ክፋቱ መንጋውን የመምራት ሀይሉ ነው፡፡ ከተከተሉት በለምለሙ ማሳ ያውላቸዋል፤ ካልተከተሉት እያክላላ ...አንዱን በንክሻ .....ሌላውን በእርግጫ እያለ ያብጣቸዋል፡፡ ...ዙሪያቸውን እንደ ውረንጭላ እየፈነጠዘ ያባርራቸዋል ... ያስጎፋቸዋል ......ይከበክባቸዋል፡፡ ማስኩ ትንሽ ታገስ የሚለው አባ አያል ጉዳይ ኑራቸው የጫኑት እንደሁ ብቻ ነው፡፡
አንዳ”ንዴ ባለቤታቸው ጋጠ-ወጥነቱ ትዝ ሲላቸው አባ አያልን፤ “አንቱዬ አሁን አያርገውና እርስዎ አንድ ነገር ቢሆኑ ይሄ ፈረስ ምን ይሆናል;” ይሏቸዋል አባ አያል፤ “ኪኪኪኪኪ አርነት ይወጣላ የኔ ዳልች” ይላሉ፣ በብረታቸው “ንኮ የሱን ያህል አይኮሩም፡፡
አንዴ አባያል ተአፋፍ ጩኃት ሰሙና እየጋለቡ ቢወጡ፤ ምን የመሰለችትን ጊደር ጅብ በቀን ገልብጦታል።
“እግዞ ክፉ ዘመን! እርጉም ጊዜ....” አሉ ያ ጅብ በቀን ይወጣ የነበረበት የራብ ወቅት ፊታቸው መጥቶ ሲደቀን ዝግንን ብሏቸው፤ ለጥቀውም ውርጋጡን ይዘው ወደ ላይ ወጡ......ጅቡ ገባበት የተባለውን ዋሻ እየጠቆሙ መመሪያ ሰጡ፡፡
“አሁን ተዚያ ዋሻ ጀርባ ትሄዱና ትደበቃላችሁ፤ በሗላ እኛ ያዘው ያዘው ስንል ወጥታችሁ ዋሻውን ትዘጉባታላችሁ” ወጣቶቹ ትዕዛዙን ተቀበሉ ....አባ አያል በባህር ከዘራቸውና ዳልች እየታገዙ ቀሪውን ሰው ከጊደሮ አርቀው ....ፈንጠር ብለው አደፈጡ፡፡ .....ተጠበቀ .......ተጠበቀ .....እልህ አስጨራሽ ጥበቃ ......ብቅ አለ። ........ከዋሻው ጊደሮ ጋር ለመድረስ ደግሞ ሌላ አመት የሚያካክል ጥበቃ!
 በመጨረሻ አባ አያል ዳልችን ኮለኮሉት....  ከዘራቸው ሽቅብ ተወደረ.......  ጅቡ ፈረጠጠ “ያዘው!... ያዘው!.... በለው!... በለው!....” በርቀት የሚመለከተው ሁሉ ሰው ተንጫጫ  ....... ወጣቶቹ ዋሻው ላይ ተገጠገጡ፡፡ .......ጅቡ መግቢያ ቀዳዳ በማጣቱ፣ ቁልቁል ተፈተለከ። ከእሮጩ ሁሉ አመለጠ፡፡ ........ዳልች ግን አባ አያልን እንዳንቀረቀበ መስኩ መሀል ደረሰበት  ........አባ አያል ጎንበስ ብለው በከዘራ ዠለጡት .......ዳልች እንደተቆጣ አልፎት ሄደ፡፡  ........ ልጓሙ ተሳበ - በፍጥነት ዞረ፡፡
.....ጅቡ ወደመጣበት እየተመለሰ ነው፡፡ .......ወደ ዳገቱ ከመድረሱ በፊት ዳልች ደረሰበት፡፡ .....ሊያስጓፋው አፉን ከፈተበት-ወይ ፍንክች!  ....ሽማግሌው እንደገና ዝቅ በማለት ጆሮ ግንዱ ግድም ለጠጡትና አለፉ፡፡  .....የበረቱ ማቲወች መስኩን እረገጡ .....ጅቡ ተመልሶ መስኩን ለማቆረጥ ወደ ሽገዛ ወንዝ ሸመጠጠ፡፡
የተቆጣው ዳልች ለሶስተኛ ጊዜ ደረሰበት፤ አባአያል..... እንሆ በረከት አሉት፡፡ .....ጅቡ .....ወደቀ  ....ተነሳ ....ዞረበት .....መሂጃው ጠፍቶት ተደናበረ፡፡
ቀልጣፋው ዳልች ተመልሶ አጠገቡ ደረሰ...... ሌላ ሸጋ የባህር ከዘራ በረከት፡፡  ወደቀ፡፡ ማቲዎቹ ደረሱ፡፡  ........ ሽማግሌው ዳለች፤ የባህር ከዘራቸው ከአካባቢው ተሰወሩ፡፡
ሌላ ቀን ከገበያ ሲመለሱ፤
 “በላት!... በላት!...” ይባላል “ቡርእርእርእርእእ.......” ዳለች ድምጽ አሰማ፤ አይ ሁከት ሲወድ!
“ቸ.....” አሉት፤ አባ አያል ጨሞጋ መስክ ላይ  … ወደል ሚዳቆ ሽቅብ ሽቅብ ትዘላለች፡፡
....መስኩ ደለል ስለተኛበት፤ ሚዳቆዋ ደከም ስላለች፣ ዳልች ፈጣን ስለሆነ ደረሰባት፡፡ ....አባ አያል፤ ገበያ ሲወጡ ምንሽራቸውን እነጅ ዱላ እንደልያዙ ምንሽራቸውን ደግሞ ሎሌው እንዳነገተው፤ እጃቸው ጋ አለንጋ ብቻ እንደሚገኝ ያስተዋሉት ገና አሁን ነው፤  ፈገግ ካሉ በሆላ “ገረፍኮት” ብለው ለመቀለድ አለንጋቸውን ከፍ ሲያደርጉ    ........ያልጠበቁት ሆነ፡፡  
......ሽማግሌው አለንጋቸውን ከመሰንዘራቸው በፊት ዳልች በፊት እግሩ ለጋት ...ተንከባለለች፡፡ .....የታደኑ አራዊትን ከመሸከም ልምዱ ሳይታወቅ የማደን ጥበብን ተምሮ በተገኘው ፈረሳቸው የተገረሙት አዛውንት፤ ልጎሙን ለቀው ጋማውን በመያዝ የሚሆነውን ያያሉ.......
.......ዳልች ዞሮ ተመለሰ ......ሚዳቆዋ አቅጣጫዋን ቀየረች .....ተከትሎ ደገማት ....ሰለሳት ....አደከመ አደከመና ጣላት፡፡ ...ረመረማት፡፡ ..ልጓሙን ከአፉ አወጡለት፡፡  አክላላ.... እስከ ሰማየ ሰማያት የሚሰማ መክላላት አክላላ .....ብቻውን ጋለበ .... በማያውቀው መስክ ያሉ ፈረሶችን መረበሽ ጀመረ..
በአባ አያል ሲጠራ...... መጣ፡፡   ግዳዩን በአግራሞት የተወጡት ሽማግሌ ጭነውት መራመድ ጀመሩ.......... ተከተላቸው፡፡
ዳልች የሚገርም ባህሪ አለው (እንስት ጌታውን የሚያስጨንቅ) ሽማግሌው በፈለጉ ሰዓት ሊይዙ ሊጋልቡት ሲችሉ ከሳቸው ውጭ ግን ማንም አይቀመጠውም፤ ማንም የታሰረበትን ጠፍር ጎትቶ ዳልችን ማንቀሳቀስ አይችልም .......መጀመሪያ የፊት እግሩን ገትሮ ወደ ኋላ በመለጠጥ አሻፈረኝ ይላል፡፡ ሰውየው በጉተታው ከበረታ አይኑን አፍጦ፤
“እህህህህ....” ሲል ያጉረመርማል፤ ጎታቹ ካልተወው ወይም እንዲንቀሳቀስ ከመታው፤ ጆሮውን ልጎ፤ ጥርሱን አግጦ የመልስ ምት .....እንዴት ያን ግዙፍ ሰውነቱን እንዳዞረ ሳይታውቅ በርግጫ እንካ ቅመስ፡፡ .....ለነገሩ ሚደፍረውም የለ!፡፡
አንዴ ግን ለሌላ ሰው  ተጋለበ አባአያል ከከተማ ሲመለሱ፣ በስካር ጨርቅ ሁነው ኑሮ ድንገት ከፈረሱ ወደቁ፤ ዳልች አጉተመተመ ሊቀሰቅሳቸው ታገለ በልባቸው ከተዘረሩበት መሬት ሊገለብጣቸው ባፍንጫው እየገፋ ሞከረ፤ አልተሳካለትም፤ ተሽከረከራቸው፤ አይሰሙም አይለሙም  .... ሽምጥ ጋልቦ ...ቤቱ ደረሰ፡፡    ልጎሙ አላስጮህ ቢለው ሁለት እግሩን ሽቅብ እያነሳ ዘለለ፡፡
...... የአባአያል ባለቤት ገባቸው፡፡
“እኛ ሰውዮ አንድ ነገር ሆነዋል፤ እባክህ ሂድ ......” አሉት የበኩር ልጃቸውን፡፡
“ምን ሆነ ናና”
“እንጃ! ገለዋቸው ይሆን፤ ተው ሲሏቸው አይሰሙ” እንባ ፊታቸውን ሞላ፡፡
“አሃ! ምን ያስለቅስሻል፤ አብጌን ማን ወንድ ነው “የሚነካው፤ ለሰው ሰጥቶት ወይ በጥሶ የሌለ መስሎት መጥቶይሆናል እይ....”
እነሱ ይሄን ሲባባሉ፣ ዳለች ወርዶ ሄዷል፡፡
እናት፤ “የለም፤ ዳልች በደናው እንዲህ አይቆጣም”
“እና ምን ተሸለ;”
“ተከተለው...”
“ማንን?”
“ዳልችን ነዋ!”
“መች እደርስበታለሁ”
............ዳልች  ተመልሶ መጣ..........   ወደ ሴትየዋ ተጠጋ..........
“ውጣው!”
“ዋ!.ዋ!... ይሄን እብድ”
የአባያል ባለቤት ልጃቸውን እያበረቱ፣ ሲናር ይዘው ወደ ፈረሱ ተጠጉ፡፡
“ና..ና.. ችኢችኢችኢ.... ና.ና.. አለሜ ና....”....ዳልች  ሰውነቱ ሁሉ እንደጋለ ባለበት ቆሞ ጠበቃቸው፡፡ ....ያዙት፡፡ .....እንዲበላ ልጓሙን አወለቁለት፡፡ ....... ናፍቆት የነበረውን ሚስጥር በጩኸት ዘረገፈው “በል ውጣው፤ ይዠልሃለሁ” ..... ልጅ ፈራው...........
“በል እንጅ!;” .....ወደ ጀርባው ሲቀርብ ዳልች አንገቱን አቅንቶ የጎሪጥ አየው፡፡  ........የዋለ ፍርሃት ተባባሰ፡፡  ......እናት ሁለቱንም መለማመጥ ጀመሩ፡፡
“እባክህ ... የኔ ልጅ በነፍሱ ብትደርስ ደፈር በል..  ወንድ አይደለህ፤ ያውም የጀግናው አባያል ልጅ .........ዳልች አለሜ የኔ አንበሳ፤ የዛሬን ውለደኝ......... የዛሬን ብቻ!!” አንገቱን እያሻሹ ግንባሩን እየደባበሱ ሲለማመጡት ......የሚሰማ ይመስል፤ ለስለስ ይልና ይቆጣል...... ይለመናል ይለሰልሳል ........መልሶ ይቆጣል.... በመጨረሻ እንዲወጣ ፈቀደለት፤ ልጓሙን መጉረስ ግን አሻፈረኝ አለ። የአባአያል ባለቤት ልጃቸው ጋማውን ጨምድዶ መያዙን ሲያረጋግጡ፣ አቅፈው ይዘውት የነበረውን የዳለች አንገት ለቀቁት..... በቁጣ ተሽቀንጥሮ ተፈተለከ.......፡፡
........ከቆይታዎች በሆላ የተጨነቁት እናት፤ በርቀት የባላቸው ጌጥ ሲያክላላ ሰሙት፡፡ ወዲያውም ሽማግሌውን ጭኖ ወጣቱን በእግሩ እየነዳ ከተፍ አለ...... ሳተናው ዳለች!!
*   *   *
ግና…. ዳልች ሳተና ነቱ ሳይጠፋ፣ ወኔው ሳይቀዘቅዝ ጊዜ ጣለው፤ መጋኛ አጠናገረው ወይም እንደ ቄሶች ጥናት ጋኔን ሰፈረበት፤ ገላው አልታዘዝ አለ ያዞር ይጥለው ጀመር .....በይደር ይሻለዋል፤ ተባለ ....ጠበል ተረጨ - ባሰበት፤ የኋላ እግሩ ከትዛዙ ውጭ ሆነ፤ ስንት ኮተት ዝተት ተሸካሚ ጀርባው ይዞታውን ጠብቆ መዘርጋት ተስኖት ቁልቁል ተቆለመመ፡፡ እልኩና ጨፋሪ የፊት እግሮቹ ብቻ ቀሩት የትም ሊያደርሱት ግን አልቻሉም ቀኑን ሙሉ ሊነሳባቸው ይታገላል  .....አንገቱን ቀና ያደርጋል። .....የፊት እግሮቹ መሬቱን ተጭነው ይገፉታል ........ደረቱ እየተነፋ ከፍ ይላል ........ተመልካች ያፈጣል ......... ኋላው  ይጎትተዋል .....ወደ ቀኝ ሲጎትተው፣ ወደ ግራ ጋደል ብሎ ለመነሳት ይፍጨረጨራል ወደ አጋደለበት ከመነሳቱ በፊት ይወድቃል ወይም ኋላው ሲበረታበት አዙሮ ይደፋዋል፡፡
በሱ ተስፋ ተቆረጠ ይልቅ  ጋኔኑን ወደ ሰው እንዳያጋባ ወይም ወደ መሰሎቹ እንዳያዛምት ስለተሰጋ ቤተሰቡ በሊቃነ ቄሶች መሪነት እንዲጣል አመነ፡፡  
...........አባአያል ግን አሻፈረኝ አሉ፡፡
“ልጅ ጋኔን ቢይዘው እጥለዋለሁ፤” ሲሉ ሙግት ገጠሙ ዳልች እኮ ፈረሳቸው አይደለም ልጃቸው ነው!!!፡፡
........አጋጣሚው የኮርቻ ፈረሳቸው በእርጅና ደከም ያለበት ጊዜ ነበር፡፡ በርግጥ ቤት ውስጥ ሁለት በመገራት ላይ ያሉ እና አንድ የተገራ ፈረስ ነበራቸው፤ ይሄ ፈረስ ሰጋር ቢሆንም ቀዝቃዛ ስለሆነ አይኮሩበትም በወጣቶች ላይ የነበራቸው ተስፋ ደግሞ ሲገሩ አይተው ተሞጠጠ፡፡ ...በቅሎ ደግሞ ጥሎባቸው አይወዱም ስለዚ ክብራቸውን የሚመጥን ፈረስ ፍለጋ ገበያ ወጡ  ……..አይን እሚሞላ የለም!!!!!
“የመሳ መሳማ ቀዝቃዜ ምን አለኝ” ብለው....ገበያውን ሊለቁ ሲጣደፉ፣ አንድ ባላገር አንዳች የሚያህል ፈረስ እየጎተተ ሲገባ ተገጣጠሙ ......ይሄን የሚያክል ፈረስ አይተውም ሰምተውም አያውቁ፡፡ ....ሰውየው ግመል እንጅ ፈረስ ሚጎትት አይመስልም ......ተጠግተው አዩት፤ ቁጡ ቢጤ ናት  ...በክብድና እንዲህ ንቁ መሆኖ ገረማቸው፣ ድንገት ደግሞ ወንድ ብትወልድ ብለው አሰቡ፤ አስበው አልቀሩም፤ የዚችን ጠብደል-ጠብደል ግልገል፤ የዚችን ንቁ-ንቁ ልጅ መጋለብ አማራቸው አሁን አሁን አላቸው፡፡
.......ውድ በሚባል ዋጋ በደንብ ሳያዮት በቃ እንደ ፈተን የለሽ እንስሳ (አህያ) ያለፈተን ገዞት ከጥቂት ቀን በኋላ ግን ችግር እንዳለባት ታወቀ፡፡  ..... አዎ አይኖ ችግር አለበት በጣም ንቁ ብትሆንም በተለይ ከርቀት አይታያትም አባአያል ግን ቁብም አልሰጣቸው የሳቸው ጉዳይ ከግልገሎቾ አንዳች አንዳች ከሚያክሉት ልጆቾ ...ለዚህ ማረጋገጫ ይመስልም ዘመዶቻቸው፤         “እንዲያው ይችን ፈረስ ዝም ብለው ያዩታል ምን አለ አንድ ቢሎት” ሲሏቸው  የተለመደች ሳቃቸውን በልግጥ አስቀድመው፤ “ኪኪኪኪ.. ድንብስ ብያታለሁ” ይላሉ፤ የነገሩን ርዕስ ለመለወጥ....በደንባሳ ነቶ ድንብስ የሚለውን ስም የወሰደችው ድንብስም ሲመሽ ሎሌዎችን ማስጨነቅ የሰርክ ልማዶ ሆኖ ነበር፡፡ .......ሁሉ እንስሳ ከተከተተ በኋላ የፈረሶች መግቢያ ይደርሳል .......ፈረሶች በሰዎች ተከበው እየተከበከቡ ወደ ጋጥ ይነዳሉ፤ ነባሯ እናት ፈረስ ትገባለች... ተከታይ ይቀጥላል..... ይቀጥላል...... ዙሪያቸውን የከበቡ ወንዶች “ቸ!.. ግባ.....” ይላሉ ሴቶችም፤ በቀጫጫ ድምጻቸው ለማስገደድ “ቸ!.... ግቢ ሲሉ ይጮሀሉ ..... ይገባሉ ....... ይገባሉ....... ድንብስ የመጨረሻውን ፈረስ ጭራ ተከትላ በርጋታ ትደርሳለች .... የተከፈተው በር ከሌላው ጠቁሮ ይታያታል ..... ትጎፋለች ---- ተፈናጥራ ወደ ጎን ስትሸሽ ድምጹን ብቻ ትሰማው የነበረ ሰው ፊቶ ላይ ድቅን ይላል ወደ ሆላዋ ትፈረጥጣለች፤ ኩታ ወገቧ ጋ ያገለደመች ሴት፤ “ተይ ወሽ” ስትል ትፋጠጣታለች፤ ጫጫታው ይደምቃል  ...አምልጬ እሄዳለሁ .......ትጋቢያለሽ ግብ ግቡ ይጦፋል፣ አባአያል የሚወዱትን በሬ/ዳመናን/ እያሻሹ፤ በረቱ ጥግ ቆመው ይስቃሉ.......ግብ ግቡ ያዝናናቸዋል፡፡
....ከብት ከጠፉ የጎደለ እንስሳ ካለ፣ ቤተኛው ሰርቶ ማጠናቀቅ ያለበት ስራ ከኖረ ግን መሪ ተዋናይ ይሆናሉ፤ ጠጋ ብለው ትዕዛዝ ይሰጣሉ በዘዴ ስለሚያስከብቧትም በፍጥነት ትገባለች፡፡ .......ዳልችን ከተገላገላች በሆላ ግን ሰውነቷ ሲቀላት ጊዜ ፍጹም አመጸኛ ሆነች፤ የሀገሩ ተባቶች በሙሉ ቢሰበሰቡን”ኮ ጥሳ ከማለፍ የሚያግዳት ጠፋ፤ ቂጥ ቂጧን የሚሮጠው ውርንጭላዋ ደግሞ ጥሩ አፈራጣጭ ሆናት፡፡
በዛ በተለከፉ ውሾች፤ ሰፈሩ በታመሰበት ርጉም ቀንም አልገባ ብላ ቤቱን ታጥብ ጀመር፡፡ አባአያል በረቱ ጋር ቆመው ያዩታል፤ በተለይ በማያውቀው መንተል መንተል የሚለው ውርንጭላዋ አሳዘናቸው፡፡ ......ሁኔታዋ አበሳጫቸው፡፡ የተለከፉ ውሾችን ለመግደል የያዙትን ሽፍዳ/አራት መአዘን ጦር/ ዝቅ ብለው ተመለከቱት፤ ጫፉ እግራቸው መሀል ነው ጠበቅ አርገው ያዙና ወደ ታች ገፉት፤ ወደ ውስጥ ጠለቀ፤ ማንም ባያውቅላቸውም ከራሳቸው ጋር ሙግት ገጥመዋል......
እሁድ ከቤተ-እግዚያር ተመልሰው፣ ታሁን አሁን ደረሰ እያሉ፣ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውን የሰንበት ቡና ዱቄት አንዲት መንቃራ ቄብ ዶሮ በመድፋቶ በያዙት ከዘራ አስቀርተዋት ስላልረኩ ቀሪ ዶሮዎችን ደጅ ለደጅ እያባረሩ የጨፈጨፉ ለት .....ንዴታቸው ይቅር ብሏቸው ሲሄድ የእግዜርን ፍጥረት መግደል አልነበረብኝም፤ ሁለተኛ በእንስሳት ላይ እጄን አላነሳም ሲሉ የገቡትን መሃላ ላለማጠፍ እየታገሉ ነው.... በርግጥ ስሪያ ይዘው አንገታቸውን  በፍጥነት ወደ ታችና ላይ እያንቀሳቀሱ ሰው እንዲከለክላቸው ባለ መመቸት የተሰጣውን በርበሬ ዶግ አመድ ያርጉትን አህዮች ለመበተን መድሀኒቱ ሴቶን ማባረር ነው ብለው በሽመል ጆሮዋ ግድም ጠብሰው ከገደሉት ገና ወር አልሞላትም፤ ያኔም ተጸጽተው ነበር፡፡      
....መድገም አልፈለጉም እንደሚደግሙት ግን ታውቆቸዋል ምክንያቱም እሳቸው ሲበሳጩ እራሳቸውን መቆጣጠር አይችሉም....
ዛሬ ደግሞ ቁጣቸው ነዳለች፡፡
ድንገት ዞር በሉ ዞር በሉ አሉ፤ ሽፍዳውን ወረወሩ፤ ጦሩ የድንብስን ጎን አጥንት በጥቶ ሳንባዋ ውስጥ ተቀበቀበ፡፡ ድንብስ ተብረከረከች፤ የሁለት ወር ግልገሏ ተቅበዘበዘ፤ የባሰ አሳዘናቸው፡፡ ሀዘኑ የናቱን ቦታ ለመሸፈን አስወሰናቸው - አደረጉትም እንደ ልጅ አሳደጉት፤ ሌላ ሰው አልቀርብም ቢል  በጉልምስና ገሩት፤ ዳልችም እጀ ሰባራ አላደረጋቸውም፤ ባንዴ ሰጋር፤ ጨፋሪ፤ ንቁ፤ ሲጋለብ ፈረስ ለምን ተከተለኝ ብሎ የሚቆጣ ሆነ - የሚጋለብ ልጅ ወጣው፡፡
ሙግቱ ግን አልያዘላቸውም፤ ከስንት እና ስንት ጉነጭ አልፋ ንግግር በኋላ ተረቱ፡፡ ዳለች የመጣሉ ነገር እርግጥ ሆነ፡፡
....ተኮሳትረው ለማየት ይፈሩት የነበሩ የውለታ ቢሱ ዘር ውርጋጦች ዳልችን እየተራገሙ፣ በተዘጋጀለት እንጨት የወሳንሳ ቡዙ እና ቡዙ ሆነው እንደ ቆጥኝ ከብዶቸው በመሸከም ....ባደገበት፤ በጎረመሰበት፤ በጎለመሰበት፤ ሴት ፈረሶችን ባማገጠበት፤ ወንዶችን ደንብቆ በጣለበት፤ ጅብ በገደለበት መስክ ጣሉት፡፡
*   *   *
ዳልች ህመሙን ማስታመሚያው ታዛ  ....ያባአያል የቁልምጫ ጥሪ ......በፍቅር የሚያሻሹት  ....በኮለላ  የሚቀርብለት የገብስ ና እንግዶ ቅልቅል ናፍቆት .....ተስፋ መቁረጥ ልቡን አልደፍር አለው፡፡
እንዴት ተስፋ ይቁረጥ?   ትርጉሙን የማያውቀው የአባአያል “እንዴት ነው ....ዛሬም አልተሻለውም?!” የሚል ንግግር እየቀሰቀሰው ...የሀዘኔታና ፍቅር ቅይጡ አስተያየታቸው እየጠራው፤
እንዴት ተስፋ ይቁረጥ? ........እንዴትስ ይንቀሳቀስ?
…..አንዳች ጠብ ላይል፣ ለአቅመ-መቆም ላይበቃ፣ በመታገል ሳለ መሽቶ፣ የጨለማ ልጆች/ጅቦች/ ድምጽ መሰማት ጀመረ.....
አይ መያዝ ድንግጥ አለ!!  ...ለወትሮው ከጠፉ ፈረሶች መካከል ዳልች ካለ ማንም አይጨነቅም ነበር .....ጅቦች ሲጠጉት ቂጡን ያዞርና ይቆማል፤ ሌሎች ፈረሶችም አንገታቸውን ከሱ ጋር አቆላልፈው፤ ቂጣቸውን አዙረው እንደሱ በተጠንቀቅ ይቆማሉ    ….እቀርባለሁ ያለ ደፋር ካለ፣ ማላመጫው ግድም ከባድ እርግጫ ይጠብቀዋል፡፡
......ዳልች ሁሉን ይቆጣጠራል፤ ከሱ በተቃራኒ ሌላውን ሲቀርብ ካየ፣
“ቡርእርእርእርእእ.......” ይልና በፊት እግሩ መሬቱን በሀይል ይደልቀዋል  ጅቦች በድንጋጤ ሲሸሹ፤ ፈረሶች ነቃ ይላሉ፤ እንዲ እንደ መላዕክ ሲጠብቃቸው ያነጋል፡፡
ዛሬ ግን ለእራሱም ጠባቂ ይፈልጋል.....
መጀመሪያ ዳልችን ያየው ጅብ፤ ግዙፍ ሰውነቱና ህያውነቱ ስላስፈራው አፉን መሬት ጋ በመስፋት “አውው......ው!” ሲል የእርዳታ ጥሪ ጀመረ... መነሳቱ ተስፋ ያስቆረጠው ዳለች፤ እርዳታ ፍለጋ በጥቂት እርቀት ወደ ሚገኙት ጭጨት መኞች ለመንፏቀቅ መውተርተር ጀመረ......... ጅቡ የእርዳታ ጥሪውን ቀጠለ......... ለዳለች በሁለት መቶ እርምጃ የማይርቁት የለሊት ተረኛ ከብት ጠባቂዎች የሰማይ ያህል እራቁበት.......
የጅቦች ቁጥር ሁለት ደረሰ  ........ፊቱን በመፍራት ወደ ሆላው ጠጋ ሲሉ በፍጥነት አንገቱን አዞሮ በቁጣ መልክ፤
“ቡርእርእርእርእእ....” ይላል፡፡ ....ይደናበራሉ  ....ወደ ጭጨቱ ለመንፋቀቅ ይታገላል ......ጅቦች እየተቀባበሉ “አውው...........ው!” ይላሉ....... ይቆጣል..... “አውው.........ው!”
ምርር ያለው የዳልች ንጭንጭ ያሳዘነው ወጣት፤ በዳልች አንጻር ያለ ባልንጀራውን ጠርቶ፤
“ምንም መጋዣ ቢሆን ለቀደመ ክብሩ ንሳ እርዳው ባክህ!!” አለው ወጣቱ “ታለክስ አንጀቴን በልቶታል” ብሎ ወደፊት በመንደርደር “የታበህ አንተ ቅዘናም!!!” ሲል ጮሆ የያዘውን ገሳ ና ደበሎ ነረተው .....ጅቦች አካባቢውን ለቀው ሄዱ ....ብዙም ግን አልራቁም .....ጥሪያቸውን አሞሙቀው ቀጠሉ.... “...አውው.....ው! ...”
ዳልች እስከቻለው ወደ ጭጨቱ ተንፏቀቀ...... ሁለቱ የለሊት ተረኛ ጠባቂ ወጣቶች ክብ እንዲሰሩ ተደርገው በተኙት ከብቶች መድረስ ግን ተሳነው ....... እንዲያውም ጠላቶቹ እሰኪመለሱ ሁለት እርምጃ በቅጡ አልተጠጋም.........
የቀደሙ የሌሊት ግልገሎች፤ ጥንድ ጥንድ የጅ ባትሪ የሚመስሉ አይኖቻቸውን እያብለጨለጩ ብዙ አጃቢ በማስከተል መጡ...... .....ወጣቶቹ እንኳን ለዳለች ለከብቶቻቸውና ነፍሳቸው ሰጉ፡፡ .....ዳልች በጅብ መንጋ ተከበበ፡፡
ጅቦች በአንተ ጀምር አንተ ጀምር..... የሚለካኩ ይመስል ዙሪያውን በጉምዠታ የሚዝረበረብ ልሀጫቸውን እያንጠባጠቡ ይዞሩታል .....የሚዞሩትን በንቃት ይከታተላቸዋል... ወደ ኋላው ቀረት ወይም ጠጋ የሚሉትን ደግሞ በፍጥነት አንገቱን ቆልሞ ያንባርቅባቸዋል..... ጅቦች  ሀይለኛ ድምጹን ሲሰሙ ብድግ “የሚል እየመሰላቸው መለስ ይላሉ........ ወደ ፊቱ ጠጋ ብለውም  “ያዝንህ!.....”  ይሉታል ጆሮውን ልጎ ጥርሱን አግጦ “ወንድ ነህ!!!” ይላል.....  ፉክክሩ ለረዥም ሰዓት ቀጠለ....... በመጨረሻ ኋላውን መቆጣጠር እንደ ማይችል ተረዱ፡፡   ........ሰፈሩበት!!!
  *   *   *                                                                       
ጨረቃዋ አሳዛኙን ትዕይንት ለወጣቶች አሳየቻቸው--- ዳልች ሁለቱ ጭኖቹ ከሞላ ጎደል ተበልተው፤ አንገቱን ቀና በማድርግ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት   “ቡርእርእርእርእእ......” ይላል .......የሆድ እቃው ተዘርግፎ፣  ጭንቅላቱ እንደ ምረግ በመክበድ ላይንቀሳቀስ ከመስኩ ተለጥፎ፤   
“አፉ..ፉ...ፉ...ፉ......” ሲል ጥልቅ የሆነው ትንፋሹ ይሰማል፡፡

Read 4336 times