Monday, 19 June 2017 10:01

ስትሞት አትቅበሯት!

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(5 votes)

 ብዙዎች በልባቸው ይዘው ከሚዞሩት፣ ጥቂቶች ደግሞ በርትተው - ሁኔታዎችም ፈቅደውላቸው ከሚፅፏቸው የሕይወታቸው መጻሕፍት መሀል ብርቱካን አላምረው በቀለ “ስሞት አትቅበሩኝ”ን ጽፋለች፡፡ ይህን መጽሐፍ በ3 ተከታታይ ቅጾች አሳትማም ለአንባቢያን አድርሳለች፡፡ በቅድሚያ የሚነሳው ጥያቄ፣ ብርቱካን አላምረው ማን ናት? የሚል ነው፡፡ ማን ስለሆነች ነው ግለ-ታሪኳን ፅፋ ለማስነበብ የበቃችው? የሚለው ጥያቄ ተገቢም መልስ ያለውም ነው፡፡ ብርቱካን ማንም አይደለችም። በህይወት መንገድ ላይ ሽቅብ ቁልቁል የምትል፣ በሕይወቷ መስክ ላይ ክረምትና በጋ፣ ፀሐይና ቁር የተፈራረቁባት አንዲት እንስት፡፡ በቃ! ይህች ናት ብርቱካን፡፡
ግለ - ታሪክን ጽፎ ለማስነበብ ስምና ዝና መነሻ ከሆነ፣ ብርቱካን ከመጠሪያነት ባለፈ ብዙ ሰው ጋር ያደረሰ ስም አልነበራትም፡፡ ዝናዋ ሳይሆን “ስሞት አትቅበሩኝ”ን ያፃፋት፤ መጽሐፉ ነው ዝና ያመጣላት። ከሦስቱ ተከታታይ ቅጾች በፊት “የአፍሪካ ፈረስ” የሚል የግጥም፣ የልብ-ወለድና አፈ-ታሪክ መጽሐፍ አላት፡፡ እሱም ስም አልሆናትም፡፡ የትግል መነሻ ነው የሆናት፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 26 ቀን 2009 የ“ስሞት አትቅበሩኝ”ን ቁጥር 3 ምረቃ፤ በሀዋሳ “ዳግም ጅምናዚየም” አዳራሽ አሰናድታ እንግዶች ጋብዛለች - ብርቱካን አላምረው፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ 15 የሚሆኑ የስነ ጽሑፍና ብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎችን ጠርታለች፡፡ በምቹዎቹ አውቶብሶች ከአዲስ አበባ ሀዋሳ፣ የሁለት ቀን ምግብና መኝታ፣ በሶስተኛው ቀን ከሀዋሳ ወደ ሸገር - ይህ ሁሉ ለመጽሐፍ ምረቃ መሆኑ ያልተለመደ ነው፡፡ መጽሐፍ መጻፍ (በእኛ ሀገር) ታሪክን ወደ አንባቢ ከማድረስ ፍላጎት አልፎ ይህን ያህል ወጪ የሚመደብለት፣ ገቢውም የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በእኛ ሀገር ሁኔታ መጽሐፍ መጻፍ (ይዘቱ ምንም ይሁን)፣ በራስ አቅም ማሳተም፣ ሸጦ ወጪውን መመለስና ማትረፍ፣ በትርፉ መኖር----መታደልን የመሰለ ብርታት ይጠይቃል፡፡
በዚያ ላይ ሴት ሆኖ ይህን ሁሉ ማድረግ ድርብ ትዕግስት፣ ድርብ ብርታት ይፈልጋል፡፡ ብርቱካን አላምረው እሱን ነው ያደረገችው፡፡ የእኛን መጓጓዣና መቆያ የተለያዩ ድርጅቶችን በማናገር (ስፖንሰር) ያሟላችው ነው፡፡ ለነገሩ መጻሕፍቶቿን የሰነደችበት፣ ያሳተመችበትና ለአንባቢ ያደረሰችበት መንገድ ሲታይ፣ ብዙዎቹ ፀሐፍት ፈጥነው የሚደክሙበት፣ ሌላ የታጋይነት አቅም እንዳላት ያመለክታል፡፡ በሦስቱ ቅጾች ያሰፈረችው ጨለምተኝነት፣ ውጣ ውረድ የበዛበት ህይወቷ ይህን ጥንካሬ ቢሰጣት አይደንቅም፡፡ ብርቱካን ሕይወቷ የልፋት ነው። ምናልባት ድካሙን፣ ግራጫውን፣ አዘቅቱን የሕይቷን ጎን ስባ ማውጣት ለምዶባት ይሁን ወይም ችግርና መከራ ከያሉበት እየተጠራሩባት አይታወቅም፣ የደራሲዋ ህይወት ጥልፍልፍ ነው፤ መውጫው ጠፍቶባት ግራ የተጋባች እስክትመስል ድረስ፡፡ ይህን ነው፤ በድምሩ 479 ገፅ የሆነውን ታሪክ ሦስት ቦታ ከፍላ ያሳተመችው፡፡
ብርቱካን በ“ስሞት አትቅበሩኝ” ከሕይወቷ በላይ ምሬቷ ትኩረቷን የሳበው ይመስላል፡፡ በየመሀሉ ፈካ ያለ ሕይወቷን ብትሞክር እንኳ ፈጥና ወደ አዘቅቷ ጎትታ ታስገባናለች ወይም አዘቅቱ ጎትቶ ያሰምጣታል፡፡ ይህ ሊያነጋግር ይችላል፡፡ የ“ግማሹ ባዶና ግማሹ ውሀ” ፍልስፍና ሊነሳ ይችላል፡፡ ደራሲ የቱን የሕይወት ክፍል ነው ለአንባቢው ማስጎብኘት ያለበት? ግን ደግሞ ከሌለስ ከየት ይመጣል? “ስሞት አትቅበሩኝ” ልብ ወለድ ሳይሆን እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ብርቱካን ገና በቅጽ አንድ “መግባቢያ”ዋ ላይ እንዲህ ትላለች፡-
“ከከበበኝ ፀለምተኛ አየር፣ የጥላቻን መረቅ ፉት እያለ ከሚያጣጥመው ባህሪዬ የተነሳ ሲበዛ ቂመኛ ነኝ፤ ገፄ በበደል ምሬት የጎመዘዘ … ጨፈገግ … ጨፍጋጋ …፤ አንደበቴ አዋዝቶ የማይሰጥ ድንቅፍቅፍ … ግራ ገብ … ተብታባ …፤ አእምሮዬ በራሱ ምርጫ ሳይሆን በሌሎች ፍላጎት ተበጃጅቶ …. ተደራጅቶ የነገሮችን ይሁንታ አዛብቶ የመዘገበ … እንግዲህ እኔ እንዲህ ነኝ!”
በቅጽ ሦስት መጽሐፏ ጀርባ ላይ የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህሩ ወንደሰን በየነ በጻፈው ማስተዋወቂያ ገለፃው መጨረሻ ላይ፤ “… በቀጣይ የህይወትን መልካም ጎን ፅፋ እንደምታቀርብልን ተስፋ አለን” ላለበቱ የድጋፍ ድምፄን እሰጠዋለሁ፡፡
እምብዛም የእንስቶች ተሳትፎ ደምቆ በማይታይበት የስነ ጽሑፍ ድርሰቱ ዓለም፤ ከ2002 ጀምሮ በ”አፍሪካዊ ፈረስ” የተቀላቀለችው ብርቱካን፤ በብዙ መልኩ አርአያነቷ የጎላ ነው፡፡ መፃፍ የተሰጥኦና ጀምሮ የመጨረስ ትዕግስት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ብርቱካን ግን ከዚህ በእጅጉ ታልፋለች። ቀዳሚ ስራዋ የሆነው “አፍሪካዊ ፈረስ” ለስድስት ጊዜ (በአጠቃላይ 17,500 ቅጂዎች) ሲታተም፣ 15,000 የሚሆኑትን በጀርባዋ አዝላ፣ ከሸከፈችበት ሻንጣ እያወጣች፣ በእጇ እንደሸጠቻቸው በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተናግራለች፡፡
15,000 የሚሆኑት ቅጂዎችን የሸጠቻቸው ደግሞ በመጻሕፍት መሸጫ መደብር ውስጥ ሆኖ፣ ድካም ሲሰማት ማኪያቶ ፉት እያለች አይደለም። በቅድሚያ በሀዋሳ፣ በኋላም በተለያዩ ከተሞች አውቶብስ መናኸሪያዎች እንደ ተሳፋሪ እየገባችና አውቶብስ ውስጥ ባለው ክፍት ቦታ ተቀምጣ፣ ተሳፋሪውን በማናገርና በማሳመን ነበር። ፀሐይ፣ ንፋስ፣ ዝናብ ጓደኞቿ ሆነዋል፡፡ ከዚያ በላይ አስቸጋሪው ግን ከመጽሐፉ መሸጫ ዋጋ በላይ ጨምሮ በመስጠት የሚያበረታታት የመኖሩን ያህል ቀንሳ እንድትሸጥ የሚጠይቃትና የሚያንጓጥጣት መኖሩ ነው፡፡ ወደ 25,000 ቅጂ ከታተሙት የ“ስሞት አትቅበሩኝ” ሦስት ቅጾች፣ 20,000 የሚሆኑትን የጨረሰችው በተመሳሳይ ሁኔታ በጀርባዋ አዝላ፣ ከከተማ ከተማ ተዘዋውራ፣ በመሸጥ ነው፡፡
ሀዋሳ ከተማ ሄዳችሁ መንገደኛውንና የባጃጁን ሹፌር፤ “ብርቱካን የምትባል የዚህ ከተማ ነዋሪ ደራሲ…” ብትሉት “እ! … መናኸሪያ የምትሸጠው?” ይላችኋል፡፡ መጻሕፍቷን ገዝተው ያላነበቡም ባልተለመደ የሽያጭ ስልቷ፣ በጥንካሬዋ፣ እንዲሁም ብዙዎችን የሚደንቀውና መጀመሪያ ላይ የማያምኑት፣ በጀርባዋ አዝላ የምትሸጠው የራሷን ታሪክና የፈጠራ ስራ መሆኑን ነው፡፡ ብርቱካን ስም ባትጠቅስም አዲስ አበባ መጥታ፣ ወደ አንድ መጻሕፍት መደብር ጎራ ብላ የምታነበውን መጽሐፍ ልትገዛ ስትል፣ በጻፋቸው መጽሐፍት አንቱ የተባለ ደራሲ አግኝቷት፤ “አንቺ! መጽሐፍ በጀርባሽ አዝለሽ በየመንገዱ በመሸጥ የደራሲያንን ስም ታስጠፊያለሽ?” እንዳላት ስትገልጽ፤ ሳግ ተናንቋት ንግግሯን አቋርጣለች፡፡ ብርቱካን ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ አዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት፣ ሻሸመኔ፣ ጅማ፣ ዲላ፣ አለታወንዶ፣ ወላይታ፣ አርባ ምንጭ (ተርጫ)፣ ሆሳዕና፣ መቀሌና ባህርዳር በባዛርና በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ እየተገኘች መጻሕፍቷን ሸጣለች። አሁን ላይ ግን ይህን ሁሉ ለማድረግ ጉልበቷ መድከሙን፣ አቅሟ መሟጠጡን ትናገራለች፡፡ ትግሏ ግን ቀጥሏል፡፡
የመጽሐፍ ምረቃው 8፡00 ሰዓት ይጀመራል የሚል መርሀ ግብር ቢወጣለትም ፕሮግራሙ እስከ 9፡30 አካባቢ አልተጀመረም፡፡ ላለመጀመሩ ዋናው ምክንያትም ለቀናት በከተማው ስለ ፕሮግራሙ ቢቀሰቀስም በአዳራሹ የተገኙት እንግዶች ቁጥር ማነሱ ነበር፡፡ ሰዓት አለማክበር ድንቃችን አይደለም። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ም/ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ደራሲ አያልነህ ሙላት፣ የዕለቱን ፕሮግራም በከፈቱ ወቅት ያሰሙት ንግግር ይህንኑ ቅሬታ የሚገልፅ ነው፡- “ብርቱካን አላምረው ከአዲስ አበባ ወደ 15 የሚሆኑ እንግዶች አምጥታለች። ከሀዋሳ የመጣችሁት ግን ከእኛ ብዙም በቁጥር አትበልጡም፡፡ ለምን? ይህ ሊታሰብበት ይገባል። የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ከዓመታት በፊት ሀዋሳን ለመኖሪያና መስሪያ ከተማነት መርጠዋታል። አሁን ምንድነው የጠፋው? ፖለቲካው ቢሰፋ፣ መንገዶች ቢያምሩ፣ ህንፃዎች ቢሰሩ ያለ ኪነጥበብ ሀገር ልታድግ አትችልም፡፡ አሜሪካውያን የ9/11 አደጋ የደረሰባቸው ጊዜ በማግስቱ ያደረጉት የሆሊውድን ሰዎች ሰብስበው ማናገር ነው፡፡---”
ደራሲ አያልነህ በማስከተልም፤ ከቀናት በኋላ በሀዋሳ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንደሚከፈትና ከእንግዲህ ብርቱካን ብቻዋን እንደማትደክም በመግለጽ አበረታተዋታል፡፡ ይሁንና ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ፣ በአዳራሹ የተገኙ እንግዶች ቁጥርም እየጨመረ ሄዷል፡፡
የመጽሀፍ ምረቃው ፕሮግራም በምልዐት እንዲሳካ በከተማዋ ያሉ የተለያዩ መኝታና ምግብ ቤቶች ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የከተማው መስተዳድር የመጨረሻውን ራት ጓብዟል፡፡ ብዙው እገዛ የተደረገው የብርቱካንን ብርቱ ጥረት በመረዳት ይመስላል፡፡ ከሁሉም የድጋፍ አይነት በአዳራሽ ውስጥ የነበርነውን በተመሳሳይ ስሜት ያስደሰተን፣ ብርቱካን ከእንግዲህ መፃህፍቶቿን በጀርባዋ አዝላ መሸጧ መቅረቱ ነው፡፡ ከ2003-2006 ለአራት ዓመታት በሀዋሳ መናኸሪያ፣ ከ2007-2009 ደግሞ በባዛር ገበያዎች አለማቋረጥ መጻሐፍት ያዘለችበት ጀርባዋና ትከሻዋ በደቀቀበት፣ ጉልበቷ በዛለበት በዚህ ወቅት እዚያው ሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የ“ኔትወርክ ካፌና ሬስቶራንት” ባለቤት አቶ አብይ ለማ፤ ዙሪያውን በመስታወት የተሰራን አነስተኛ መደብር አለምንም ክፍያ ሰጥተው፣ አርፋ እንድትሸጥ ማድረጋቸውን በገለፀች ጊዜ ሁሉም በደስታ ቆሞ ነው ያጨበጨበው፡፡ አሁን ብርቱካን በፀሐይና በዝናብ መጽሐፍት አዝላ ከወዲያ ወዲህ አትንከራተትም፡፡ ረጋ ብላ መጽሐፏን እየሸጠች፣ በተገኘው ጊዜ ሁሉ እዚያው መደብሯ መጽሐፍ ስታነብና የመጣላትን ስትፅፍ ትውላለች፡፡ የደራሲያንና ጋዜጠኞች ቡድኑ፤ አዲሱ የብርቱካን መጻሕፍት መደብር ያለበት ድረስ በመሄድ የጎበኘ ሲሆን ለኔትወርክ ካፌና ሬስቶራት ባለቤት አቶ አብይ የተሰማውን አድናቆትም ገልጿል።
ብርቱካን “ስሞት አትቅበሩኝ” ያለችበቱ ምክንያት ግልፅ ነው፡፡ ሁላችንም በዘልማድ የምንለው ነው። “… ስሞት በድኔን ለመቅበር አትምጡ፡፡ ያንንማ በአቅራቢያዬ ያየ ማንም ዘወር ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ በይሉኝታ አትልፉ፤ አትድከሙ…! ዘለላ እንባም ጠብ እንደማይላችሁ አውቃለሁ፡፡ እኔም “አያስፈልገኝም” ብያችኋለሁ፡፡ በቁሜ ከአጠገቤ ካጣኋችሁ! ከሞትኩ በኋላ ምን ትሰራላችሁ? ብላለች- የመጀመሪያው ቅጽ ላይ፡፡
በሕይወቷ ላይ የተጋረጡባትን ሁሉ አንድም ሳታስቀር በሦስቱ ቅጾቿ ዘርዝራለች፡፡ “የእኔ” ለምትላቸው ሰዎች “ስሞት አትቅበሩኝ” ያለችበቱን ጉዘት አጠናቃለች፡፡ ይህን ስሜት ሁላችንም እንጋራዋለን፡፡ ለዚያም ነው “ስትሞት አትቅበሯት” የምንለው፡፡ በቀጣይ መምህር ወንደሰን በየነ እንዳለው፤ ብርቱካን የራሷንም ባይሆን የሕይወትን ጀንበር ሳይሆን ጮራን ታሳየን ዘንድ እንመኝላታለን። ብርቱካን ራሷ ዘር፣ ራሷ አፈር፣ ራሷ ውሃ፣ ራሷ አየር፣ ራሷ ፍሬ ሆና ለሌሎችም ተርፋለች፡፡ ብርሃን ከእርሷ ጋር ይሁን፡፡

Read 1769 times