Wednesday, 04 April 2012 10:54

“ስፖርት የልማት መሳርያ ነው በሌላ በኩል የልማት ውጤት ነው”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ውድድሩን የምናደርገው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን አንደኛ ዓመት ለማክበር የተዘጋጀ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም በቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ከሚደረገው ጨዋታ ጋር በተያያዘ የከፍተኛ መንግስት ባለስልጣናት ቡድን ከአፍሪካ ዲፕሎማቶች ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡ ምን ተሰማዎት?

የህዳሴ ግንባታ ከተጀመረ አንደኛ ዓመቱን መጋቢት 24 ቀን ሲያከብር በዋዜማው በስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና በህዝብ ተሳትፎ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር መቻላችን የሚያስደስት ነው፡፡ ስፖርት ሁልጊዜ  የህዝብ ተሳትፎን የሚጠይቅ የህዝብ ስሜትን የሚገዛ፤ ህዝብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እያየ እየተዝናና ለጋራ ጥቅም አብሮ ለመስራት ይነሳሳል፡፡ ስለዚህም ስለ ግድቡ አካሄድ እና ግንባታውን ለመጨረስ ወደፊት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የበለጠ ተሳትፎን ለማጠናከር የማስተዋወቂያ መድረክ ሆኖ ክብረ በዓሉ ይዘጋጃል፡፡

የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎችን በዚህ የወዳጅነት ጨዋታ ለማሳተፍ የተፈለገው የህዝብን አደራ ግንባር ቀደም ሆነው የሚሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡ የእነሱን አርዓያ ተመልክቶ ሌላውም ህብረተሰብ  በስፖርት እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ አድርጎ እንዲነቃቃ እና ለአገር ግንባታ እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራትን ለማበረታታት ነው፡፡ የአካል ብቃትን ለማዳበር የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር ለስራ ውጤታማነትና ለጤንነታችንም ጥቅም አለው፡፡ የስራ መደራረብ ባይኖር በተመሳሳይ መንገድ ከስራ በኋላ እንቅስቃሴ ብናደርግ ለአካል ጥንካሬ ለአዕምሮ ደህነነትና ጤንነትም ሊሆን ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ እርስ በራሳችን ያለውን ማህበራዊ ግንኙነት፤ በወዳጅነት ጨዋታው እናከብራለን፡፡ የመንግስት አመራሮች በስራ መደራረብ ብዙ ላይገናኙ ይችላሉ፤ በዚህ አይነት መድረክ ግን እርስበራስ በመገናኘት፤ አብሮ ስፖርትን በመስራት የአካል ብቃትን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

 

አብሮ መስራት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገለጫ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ አሁን ይህን ታላቅ ራእይ ለማክበር ደግሞ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የእግር ኳስ ቡድን አቋቁመው መንቀሳቀሳቸውን በተለይ በኢትዮጵያ የስፖርት እድገት የሚደረጉ ጥረቶችን በማስፋፋት ተመክሮ ሊወሰድበት ይችላል?

የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በዚህ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል በየራሳቸው ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ ከስራ  ሰዓት በኋላ በመሰል ተግባራት ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ በቂ ግዜ በመመደብ መስራት ተገቢ ይሆናል፡፡ ይሁንና የመንግስት አመራሮች ከፍተኛ የስራ መደራረብ አለባቸው፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ወደተለያዩ  ክልሎችና የውጭ አገራት የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን በያዝነው ጅምር የምናስበው ግን ይህን አይነት ተመክሮዎችን በቋሚነት አጠናክረን መስራት እንዳለብን ነው፡፡ ስፖርት አካላዊ ብቃትን በማዳበር ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ግንኙነትና በቡድን ስራ ጠቃሚ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ተመሳሳይ ተሳትፎዎችን ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህም በየስራው ተጨባጭ ሁኔታ እና በእያንዳንዱ ሰው ጥንካሬ ይመሰረታል ብዬ አስባለሁ፡፡  የያዝነው ጅምር መስፋፋት አለበት ያልከው ትክክል ነው፡፡ ሁሉም የየራሱ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በስፖርት የህዝብ ንቅናቄ ለማድረግ አሁን የያዝነው የማንቀሳቀሻ ሃይል አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት የብዙዎች ውክልና የሚኖረው ነው፡፡ ክልሎች በሁለት መዋቅሮች ማለትም በክልል የስፖርት ምክር ቤቶችና የስፖርት ቢሮዎች ይወከላሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 26 የስፖርት ፌደሬሽኖች በፕሬዝዳንቶቻቸው ይወከላሉ፡፡ ታዋቂ የስፖርት ተቋማት የምንላቸው ጤና ጥበቃ፤ ባህልና ቱሪዝም፤ መከላከያ፤ፖሊስ የመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎችና መስርያ ቤቶችም ውክልና ይኖራቸዋል፡፡ሌሎች የሚኒስትር መስርያ ቤቶችም እንዳስፈላጊነቱ ይካተቱበታል፡፡ ዞሮ ዞሮ የስፖርት ምክር ቤቱ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር  ስፖርቱን ከማልማትና ከማስፋፋት አኳያ የራሱን መድረክ ይዞ ስራ የሚሰራበት ህጋዊ ማዕቀፍ ያለው ነው፡፡ ዛሬ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ 1ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር በአጭር ተልዕኮ የመስራት እድሉ መፈጠሩ ዘላቂነት ኖሮት ለጤንነት፤ ለአካል ጥንካሬ፤ ገዢ ለሆነው የእርስ በእርስ ግንኙነት የስፖርት ንቁ ተሳትፎ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ ሁላችንም ዜጎች በስፖርት የመሳተፍ መብት አለን፡፡ ፖሊሲያችን የሚለው ዜጋ፣ ወጣት፣ ወንድ፣ ሴት፣ ሽማግሌ፣ ህፃን፤ አካል ጉዳት ጤናማ ሳይል ሃይማኖትም ሆነ ዘር ሳይለይ ሰው ባለበት ቦታ ስፖርቱን አግኝቶ መሳተፍ አለበት ነው፡፡ በእርግጥ  ከአቅም በተያያዘ፤ ከግንዛቤ መጓደልና እጥረት በተገናኘ፤ በየቦታው የስፖርት ቁሳቁሶችና የስፖርት ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ካለመኖር ችግሮች ጋር በተፈለገው ፍጥነት ማራመድ ባይቻልም እያደግን ስንሄድ የመንግስትም በጀት ሲጨምር፤ የህዝቡ አገልግሎትን የመግዛት የስፖርት አካባቢን ለራሱ የመፍጠር አቅምን በማሳደግ አብሮ የሚጓዝ የለውጥ እንቅስቃሴ እነደሚያስፈልግ የሚታወቅ ነው፡፡ በመፍጠር መስራታችን በቀላሉ በእድገት እንድንጓዝ ያስችላል፡፡

የህዳሴው ግድብ ለስፖርቱ መስክ የሚፈጥረው ተስፋ እና መነቃቃት የሚገልፁት እንዴት ነው?

የህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ምንጭ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ልማት ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ብልፅግናን ያመጣል፤የመብራት ሃይል በተጨማሪ እንድናገኝና እንድናስፋፋ ያደርጋል፡፡ በዚህም በከተማም በገጠርም ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ያግዛል፡፡ በስፖርቱ መስክ ብትወስድ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በመብራት ሃይል ተጠቃሚ በማድረግ አስፈላጊ የሃይል ምንጮችን አቅርቦት በማደጉ የተሟላ ያደርጋቸዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎችን በገጠር እና በወረዳዎች ደረጃ በስፋት በማሰራጨት መስራት የሚቻልበት እድልን መፍጠሩም ለስፖርት መስፋፋት ጉል ሚና ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ ግድቡ መሰራቱ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ ያገለግለናል፡፡ ኢኮኖሚ ሲያድግ ከሃገራዊ ገቢው ለስፖርቱ ዘርፍ ከመንግስት ፈሰስ የሚሆነው በጀት በየጊዜው እያደገ ይሄዳል፡፡ ይህም በስፖርቱ መስክ መሰረተልማቶችን ለማስፋፋት የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማሳደግ ያስችላል፡፡ ይህም ለእድገት ጭላንጭል የሚሆን ተስፋ ያሳድራል፡፡  የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሲያድግ ስፖርቱንለማስፋፋትና ለማሳደግ በቂ አቅም ይፈጠራል፡፡

ስፖርቱን ሊያለለማ የሚችል፤ በስፖርቱ ገበያን ለመፍጠር እንዲሁም ስፖርተኛው ከሙያው በገቢ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆንና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድደሮች በሚኖረው ተሳትፎ እንዲጠናከርም ያደርጋል፡፡ ይህ የህዳሴ ግድብ በተለያየ መንገድ ለስፖርት እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

ስፖርት በአንድ በኩል የልማት መሳርያ ነው በሌላ በኩል የልማት ውጤት ነው፡፡ ስፖርት ጤናማና ብቁ ዜጋን ሲፈጥር የልማት መሳርያ ይሆናል፤ ሰላምን፤ የህዝቦች አንድነትና ፍቅርን ሲያሰፍን ለልማት የተመቻቻ ሁኔታን በመፍጠር ሚና ይኖረዋል፡፡ በሌላ መልኩ ልማትና እድገት ከሌለ ስፖርቱን የትም ማድረስ አትችልም፡፡ ቴክኖሎጂ የሚያገኝና የሚጠቀም ወጣት፤ ጥሩ አሰልጣኝ የሚያገኝ ወጣት፤ ደረጃቸውን የጠበቁና በስፋት የሚኖሩ የስፖርት ማዘውተርያዎች የሚያገኝ ወጣት፤ የተሟላ ትጥቅ፤ የተመጣጠነና በቂ ምግብ አግኝቶ የሚወዳደር ወጣትን ለመፍጠር ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የስፖርት እድገት ስለተመኘነው ብቻ አይመጣም፡፡ የህዳሴ ግድብ ያንን እድገት ለማፋጠን ስፖርታችን አቅም እንዲኖረው ለማድረግ ወሳኝ ይሆናል፡፡

 

 

Read 4335 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 11:00