Monday, 19 June 2017 10:15

የግርማ በየነ ኮንሰርት ተደነቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 አዲስ አልበሙን አስተዋወቀ

     በኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን ለ25 ዓመታት በልዩ ብቃት ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎችን ለአድማጮች ያቀረበው ከያኒ ግርማ በየነ ባለፈው ማክሰኞ በብሔራዊ ቴአትር ከ ‹‹አካሌ ውቤ›› ባንድ ጋር ያቀረበው ኮንሰርት አስደሳችና አዝናኝ እንደነበር ታዳሚያን ገለፁ፡፡ ድምፃዊ፣ የሙዚቃ ቀማሪና አቀናባሪ እንዲሁም የፒያኖ ተጫዋች የሆነውና ለረጅም አመታት በአሜሪካ በስደት የቆየው አንጋፋው ከያኒ፤ ከሙዚቃው ተራርቆ የከረመ ሲሆን ወደ ሙዚቃው የተመለሰው ከሁለት ዓመት ወዲህ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በታዋቂው የሙዚቃ ሰው ፍራንሲስ ፋልሴቶ አነሳሽነት በግንቦት 2016 ፓሪስ በሚገኘው ‹‹ላ ኤሪ ቴጅ›› የተባለ ስቱዲዮ ግርማ በየነ ‹‹አካሌ ውቤ›› ከተሰኘው የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ቡድን ጋር ‹‹ኢትዮፒክስ 30 ሚስቴክስ ኦን ፐርፐዝ›› የተሰኘውንና 14 ዘፈኖችን ያካተተው አልበሙን ያሳተመ ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ ያቀረበው ኮንሰርትም ይህንኑ አልበም ለማስተዋወቅ ያለመ እንደነበር ታውቋል፡፡ ለአርቲስቱ የመጀመሪያው ሙሉ አልበሙ ነው ተብሏል፡፡ ግርማ አልበሙን ለማስተዋወቅ ባዘጋጀው ኮንሰርት፤ ከ‹‹አካሌ ውቤ›› ባንድ ጋር አስደናቂ ትርኢት ያሳዩ ሲሆን በተለይ ግርማ በድምፅ ብቻ ሳይሆን በፒያኖ ችሎታውም ብዙዎችን አስደንቋል፡፡ አርቲስቱ በ1960ዎቹ፣ ከ60 በላይ የሙዚቃ ቅንብሮችን የሰራ ሲሆን ግሩም የግጥምና ዜማ ደራሲም ጭምር እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በብሔራዊ ትያትር ቤት ባቀረበው ኮንሰርት ‹‹እንከን የሌለሽ››፣ ‹‹ካንቺ ወዲያ ሴት አላምንም››፣ ‹‹ፍቅር እንደክራር››፣ ‹‹ፅጌረዳ››፣ ‹‹መስሎን ነበር››፣ ‹‹ሙዚቃዊ ስልት›› የተሰኙትን ጨምሮ በርካታ ስራዎቹን በመጫወት አድናቆት የተቸረው ሲሆን ‹‹የድምፁ አለማርጀት›› ለብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ አምሽቷል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ ስለፍቅር አብዝቶ የሰበከው ድምፃዊው፤ ከኢትዮጵያ ሴት ድምፃዊያን ሄለን በርኼ በተለይ ‹‹አታስፈራራኝ›› ለሚለው ዘፈኗ ያለውን አድናቆት በአደባባይ ገልጿል፡፡
ግርማ በየነ ከዚህ ቀደም ‹‹ዘራፍ››፣ ‹‹ጋይድ ቱ ሚዩዚክ ኦፍ ኢትዮጵያ››፣ እ.ኤ.አ በ2004 ‹‹በወርልድ ሚዩዚክ ጌት ወርክ›› አሳታሚነት ‹‹ኢትዮፒክስ ቁጥር 8››፣ ‹‹ስዊን ጊንግ አዲስ››፣ በቡዳ ሚዩዚክ አሳታሚነት ደግሞ ‹‹ኢትዮፒክስ 22›› በተሰኙ አልበሞች ላይ ተሳትፏል፡፡ አርቲስት ግርማን ያጀበው ‹‹አካሌ ውቤ›› የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ቡድን፤ በፈረንሳይ ሙዚቀኞች የተደራጀ ሲሆን ከ74 በላይ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በዓለም ዙሪያ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ ከወራት በፊትም በፈረንሣይ ከታዋቂው የፒያኖ ተጫዋች ሀይሉ መርጊያ ጋር በ ‹‹ስቱዲዩ ዴላ ኤል ሚቴጅ›› ታላቅ የሙዚቃ ዝግጅት ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡

Read 2387 times