Monday, 19 June 2017 10:19

ህግና ሥርዓት ያልጎበኘው፤ ሥልጣኔ የራቀው - ”ፓሲፊክ ኢንዱስትሪ”? ሠራተኞች ምን አሉ?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ጊዜው ያለፈበት ክሎሪንና ፍሌቨር ለጁስ ምርት ይውላል 20 ዓመት ያለፋቸው የሳሙና ኬሚካሎች ተገኝተዋል
    ምርቶቹ የሚሸጡት ከመዲናዋ በራቁ አካባቢዎች ነው ሠራተኛን መስደብ፣ ማዋረድና ማሸማቀቅ የተለመደ ነው
           ከጋዜጣው ሪፖርተር

       በሰበታ ከተማ የሚገኘው ፓስፊክ ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግል ማህበር፤ አቶ መፍቱህ አብዱልጋፋር በተባሉ ባለሀብት ባለቤትነት የሚመራ ፋብሪካ ነው። ፓስፊክ ኢንዱስትሪ፤ ሦስት የተለያዩ ምርቶችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል - ‹‹ማሩቲ፣ ዊኒስታርና ክላሲክ›› የተባለ የልብስ ሳሙና፣ ‹‹ፕሮሚስ›› የተባለ የታሸገ ውሃ እና “ማርች ኦሬንጅና ማርች ማንጎ” የተባሉ ጁሶች ናቸው። ምርቶቹ በሙሉ የሚሸጡት ግን ከአዲስ አበባ በራቁ ክልሎች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ከድርጅቱ በቅርቡ የተባረሩ ሠራተኞች ለአዲስ አድማስ በዝርዝር እንደገለጹት፤ ”ሦስቱም ምርቶች የሚሠሩት ጊዜያቸው ባለፈ (ኤክስፓየር ባደረገ) ጥሬ ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባና አካባቢው ለገበያ አይቀርቡም፤ ራቅ ወዳሉ የክፍለ ሀገር ከተሞች ተወስደው ነው የሚሸጡት”
ሠራተኞች አይበረክትለትም እየተባለ በሚነገርለት ፓስፊክ ኢንዱስትሪ፤ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎችና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች ለምርት እንደሚውሉ በቅርቡ ከድርጅቱ የለቀቁና የተባረሩ ሰራተኞች አጋልጠዋል፡፡ በአንድ ጊዜ ስቶር ሱፐር ቫይዘርም፣ ካሸርም፣ ፐርሶኔልም፣ ነዳጅ ቀጂም ሆና ትሰራ እንደነበር የገለጸችው የቀድሞ ሠራተኛ፤ በተቀጠረች በአንድ ወር ከ15 ቀኗ መባረሯን ትናገራለች፡፡ በዚህች አጭር ቆይታዋ ግን ጊዜያቸው ያለፈባቸው ጥሬ እቃዎች በፋብሪካው ውስጥ መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን ለጁስና ለታሸገ ውሃ ምርት ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ማረጋገጧን ጠቁማለች፡፡  
“እዚህ ግቢ ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈ (ኤክስፓየር ያደረገ) ክሎሪን አለ፡፡ መጋዘኑን የምናውቀው ሁለት ሰው ብቻ ነን፣ እኔና የሚደባልቀው (ሚክስ የሚያደርገው) ልጅ ብቻ። ለረዥም ጊዜ በመቆየቱ ጊዜው ያለፈበትን ይህን ክሎሪን፤ ለውሃም ለጁሱም ምርት ይጠቀሙበታል። አንድ ቀን ወደ ክሎሪኑ ጠጋ ስል ሽታው አልተመቸኝም፡፡ ልጁን፤ እስቲ ይህን ክሎሪን አውጣልኝና የመጠቀሚያ ጊዜውን ልየው አልኩት፤ አወጣልኝና አየሁት፡፡ በ2012 ኤክስፓየር ያደርጋል- ይላል፤ አሁን 2017 ነው፤ ኤክስፓየር ካደረገ 5 ዓመት አልፎታል ማለት ነው፡፡”
በዚሁ የመጠቀሚያ ጊዜው ባለፈበት ክሎሪን የተነሳም ከባለቤቱ ጋር ፍጥጫ ውስጥ እንደገባችና እውነቱን ፊት ለፊት እንደነገረቻቸው ይህችው የቀድሞ ሰራተኛ ለአዲስ አድማስ አስረድታለች - የተለወጠ ነገር ባይኖርም፡፡
“የፋብሪካው ሰራተኞች ውሃ ከሚመረትበት ክፍል መጥተው፤ ክሎሪን ስጪን አሉኝ፤ አልሰጥም አልኳቸው፡፡ ለባለቤቱ ነገሩት፤ ስልክ ደውሎ ጮኸብኝ፡፡ ‹‹ያለመስጠት የእኔ ኃላፊነት ነው፤ መጥተህ አነጋግረኝ›› አልኩት፤ መጣ ‹‹ይህን ውሃ‘ኮ የሚጠቀሙት ሕፃናት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ምናልባትም ያንተም ልጆች ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል፤ ከ5 ዓመት በፊት ኤክስፓየር ያደረገ ክሎሪን እንዴት ትጠቀማለህ?!” አልኩት፤ ‹‹በቃ ነገ ወደ ታች ግቢ ይጫናል›› ብሎኝ ሄደ፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ ወር ቆይቼ ነው የወጣሁት፤ እስከዚያ ጊዜ ድረስ  ታች  ወደተባለው ግቢ አልተጫነም፤ አሁንም እየተጠቀሙበት ሊሆን ይችላል” ስትል ጥርጣሬዋንና ግምቷን ተንፍሳለች፡፡
“የዛገ ዕቃ፤ ለምግብ ቀርቶ ለመለዋወጫ መጠቀም ክልክል ነው፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ የሚጠቀሙት መለዋወጫ በሙሉ የዛገ ነው፡፡” ያለችው የድርጅቱ የቀድሞ ሰራተኛ፤ በጁስ ምርት ውስጥ የሚጨመረው ፍሌቨርም ጊዜው ያለፈበት መሆኑን እንዴት እንደደረሰችበት ለአዲስ አድማስ ጠቁማለች፡፡
“ፍሌቨሩ ከየት አገር እንደሚመጣ በፍፁም አናውቅም፤ ፍሌቨሩን ሌሊት መጥቶ የሚጨምረው ራሱ ነው፤ ቀምማችሁ ጠብቁኝ የሚል ትዕዛዝ ይሰጣል፤ ተቀምሞ፣ ስኳር ተደርጎበት ይጠብቀዋል፤ ሌሊት መጥቶ ፍሌቨሩን ጨምሮ፣ ያመጣበትን መያዣ ዕቃ ይዞ ይሄዳል። ይህን የጁስ አሠራር ማንም ሠራተኛ እንዳያይ የተደረገበት ምሥጢር ምንድን ነው? አንድ ቀን በአጋጣሚ ፍሌቨሩ የመጣበትን ዕቃ አግኝቼ ሳይ፣ ፍሌቨሩ ራሱ ኤክስፓየር ያደረገ መሆኑን ተረዳሁ”  
የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበትን ክሎሪን ባጋለጠችበት ጊዜ፤ ም/ሥራ አስኪያጁ አቶ ሸረፋ ከማል ‹‹ይሄ አንቺን አይመለከትሽም፤ ከእሱ ጋር መጋፈጥ ማለት ከግድግዳ ጋር መጋጨት ነው›› ሲል ሊያስፈራራት እንደሞከረ አስታውሳ፤ እሷም በበኩሏ፤ ‹ይቅርታ አድርግልኝ! እኔ ፈሪ ትውልድ አይደለሁም›› በማለት እንደመለሰች ተናግራለች፡፡
ድርጅቱ በአጠቃላይ ከባድ ችግሮች አሉበት ያለችው ደግሞ የ”ፕሮሚስ ውሃ” የፋይናንስ ሰራተኛ በመሆን ለ10 ወራት ገደማ ከሰራች በኋላ፣ ባለቤቱና ም/ሥራ አስኪያጁ ከባድ ዕዳ ፈጥረው፣ በዋስትና ያስያዘችውን የአሮጊት እናቷን መኖርያ ቤት እንዳያሸጧት ፈርታ፣ ሥራዋን በገዛ ፍቃዷ የለቀቀችው የድርጅቱ የቀድሞ ሠራተኛ ናት፡፡ ድርጅቱ ለጁስና የታሸገ ውሃ ምርት የሚጠቀምባቸውን ጊዜ ያለፈባቸው ጥሬ ዕቃዎች በዝርዝር ታውቃለች፡፡ እንደውም በቆጠራ ወቅት የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ፍሌቨሮችና ስታርቾች አግኝተው፣ ለአስተዳደሩ ሪፖርት ማድረጋቸውን ጠቁማለች፡፡   
“እኔ በዚያ ድርጅት የሠራሁት 10 ወር ያህል ነው፡፡ በመጨረሻ ልወጣ አካባቢ ንብረት ቆጠራ ገብቼ ነበር፡፡ እንዳየሁት ከሆነ፣ የሚመረተው ውሃም ሆነ ጁስ በትክክል ችግር አለበት፡፡ የንብረት ቆጠራውን ያደረግነው እኔና የአስተዳደር ሠራተኛው ነበርን፡፡ ለምሳሌ፣ የሳሙና ኬሚካል የሚቀመጥበት ክፍል ውስጥ 20 ዓመት ያለፋቸው ኬሚካሎች፣ ኤክስፓየር ያደረጉ 40 ጀሪካን የጁስ ፍሌቨርና ስታርቶች አግኝተናል፡፡ እኔና የአስተዳደር ሰራተኛው፤ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ጥሬ ዕቃዎች በሙሉ መወገድ አለባቸው ብለን የጻፍነው ደብዳቤ በእጄ ይገኛል”
አዲስ አበባ አፍንጫ ስር በሰበታ ከተማ እንዲህ ያለ የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዳ፣  የተቀነባበረ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈፀም፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት እንዴት ሳይደርሱበት ቀሩ? ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ሠራተኞች እንደሚናገሩት፤ የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት በየጊዜው ይመጣሉ ግን እንዴት እንደሆነ አይታወቅም፤ ሰውየው ‹‹ውሃ አድርጎ” አሳምኖ ይመልሳቸዋል፡፡
በካሸርነትና በስቶር ሱፐርቫይዘርነት የሰራችው የቀድሞ የድርጅቱ ተቀጣሪ፤ ‹‹እሱ እጁ ረዥም ነው፤ በትክክለኛ መንገድ 300 ሺህ ብር ከሚከፍል በሕገ-ወጥ መንገድ 3 ሚሊዮን ብር ቢያወጣ ይቀለዋል›› ብላለች፡፡
በፋብሪካ የሚመረት የምግብ ሸቀጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤ ነገር ግን ድርጅቱ ከእንደዚህ ዓይነቱ ሥልጣኔም ሆነ የሠራተኞች ደህንነት አጠባበቅ ጉዳዮች ጋር አይተዋወቅም ብላለች- የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኛ፡፡
“በዚህ ፋብሪካ የሚሠሩ ልጆች ጓንት አይጠቀሙም፤ አይሰጣቸውማ! በክሎሪንና በሶዳ ዕቃ ያጥባሉ፤ በዚያው እጃቸው ጁስ ምርት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ክሎሪንና ሶዳው ወደፊት፣ በእጃቸው ላይ በሽታ ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡ የመቶ ብር ጓንት ገዝቶ ቢሰጣቸው ምን ችግር አለበት? የሚገርምህ ነገር እኔ ነኝ በመቶ ብር ጓንት ገዝቼ የሰጠኋቸው። ይህንን ያደረኩበት ምክንያት እህቶቼ ናቸው ብዬ ነው፤ ችግር ነው እዚያ ቦታ የጣላቸው”
“ላቦራቶሪውም ራሱ ብዙ ችግሮች አሉበት” ትላለች - ይህቺው ሠራተኛ፡፡ እዚያ የሚሠሩ ሠራተኞችም ችግሩን እንደሚያውቁት ትናገራለች።
“ነገር ግን እየፈሩ አይናገሩም፡፡ አንዳንዶቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸው፤ ሌሎች ደግሞ የዕለት ጉርስ ማግኛቸው ስለሆነ ‹‹ነገ ብባረርስ?›› በማለት ስህተቱን ለመናገር ይፈራሉ፡፡ ይህን ሕገ-ወጥ አሠራር፣ የሠራተኞችን ጭቆናና ግፍ፤ መንግሥት በጥንቃቄ ቢከታተለው በጣም ደስ ይለኛል፡፡” ስትል አስተያየቷን ሰንዝራለች፡፡
“እውነቴን ነው የምለው እዚያ ግቢ ስገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን አረብ አገር ወይም ሌላ የባርነት ሥርዓት የተንሰራፋበት አገር ያለሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ ሽንት ቤት እንድትሄድ አይፈቀድልህም፣ ስልክ ተደውሎልህ ማንሳት አትችልም፡፡ ጧት ገብተህ እንደተዘጋብህ ትውላለህ። ሁለተኛው ጓንታናሞ ያለው ፓሲፊክ ኢንዱስትሪ ግቢ ነው፡፡ አንድ ጸሐፊ አለች፤ የኩላሊት በሽተኛ ስለሆነች ሐኪሟ ብዙ ውሃ ጠጪ ብሏታል፡፡ ብዙ ውሃ ስለምትጠጣና ሽንቷ ቶሎ ቶሎ ስለሚመጣባት ሽንት ቤት ትመላለሳለች። ‹‹አንቺ ለሽንትሽ ጊዜ የለሽም እንዴ?›› ተብላለች። ይህን ያህል ሰብአዊ መብት የሚጣስበትና ሕግ የሌለበት ድርጅት ነው።” ብላለች - ሠራተኛዋ፡፡
ስድስት ወር ያገለገለው የድርጅቱ ሰራተኛ የተባረረበት ምክንያት ይገርማል፡፡ ‹‹የድርጅቱ ባለቤት፣ ሥራ አስኪያጅ፣ አስተዳደር… ሁሉም ነገር ባለቤቱ ራሱ ነው›› ይላል - ሠራተኛው፡፡
‹‹ድርጅቱ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ነው፡፡ በሥራዬ አጋጣሚ 224 ሺህ ብር ዕዳ አለባችሁ›› የሚል ደብዳቤ  ደረሰኝና ያንን ደብዳቤ ለባለቤቱ ሰጠሁ። ባለቤቱም “አንተን እዚህ ውስጥ ምን አገባህ? ለምንድነው ያመጣኻው?” በማለት ፀብ ተፈጠረ፡፡ የሰራሁበትን ደሞዝና አበል ሳይከፍለኝ ውጣ ብሎ ሰድቦ አባረረኝ›› ብሏል፡፡
ይኸው ሠራተኛ፤ ሌሎች ውሃ አምራች ድርጅቶች በቲቪ፣ በሬዲዮና በጋዜጣ ሲያስተዋውቁ አይቶ ‹‹እኛስ ፕሮሚስን ለምን አናስተዋውቅም?›› የሚል ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ባለቤቱ ‹‹ዝም ብለህ ተቀመጥ፤ ይኼ አይሠራም፤ የማያገባህ ነገር ውስጥ አትግባ›› በማለት እንዳሸማቀቁት ተናግሯል፡፡  
የድርጅቱ ሌላው ችግር፣ ሠራተኛ ሲቀጥር ውል አይዋዋልም፡፡ ይሄ ደግሞ ሠራተኞች መብታቸውን እንዳይጠይቁ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲደርስባቸው እንዳደረጋቸው ተናግረዋል - የድርጅቱ ሠራተኞች፡፡ በሆነው ባልሆነው የሰራተኛውን ክብር አዋርዶ ከሥራ ማባረር፣ ደሞዝ መቆራረጥና ከእነአካቴው መከልከልም ለፓስፊክ ኢንዱስትሪ በጣም የተለመደ ተግባር መሆኑን ሠራተኞች ጠቁመዋል፡፡   
“ውል ስንጠይቅ፤ እኛ ሥራችሁ ላይ ገደብ (ሊሚት) እንዲኖርባችሁ አንፈልግም፤ ይላሉ። ነገር ግን እነሱ በፈለጉት ጊዜ ተነስተው፤ ‹‹ሥራህን ልቀቅ፣ ተባረሃል›› እያሉ ለአንዳንዶች ደብዳቤ ይሰጣሉ፡፡ ብዙዎች ግን ‹‹ዓይንህን እንዳላየው፤ ከነገ ጀምሮ እዚህ ግቢ እንዳትመጣ፤ ምንም መሥራት አትችልም አቅም የለህም፣…›› በማለት ባለቤቱ ሠራተኛውን አዋርዶ ያባርራል። አንድ ሠራተኛ 30 ቀን ሰርቶ ደሞዝ ሲወጣ ቀርቶ፣ በሁለተኛው ቀን ቢመጣ፣ ወር ሙሉ የሠራበት ደሞዙ አይከፈለውም፡፡ ‹‹ደሞዛቸው እንዳይከፈል››፣ “የዚህ ቀን ደሞዛቸው ይቆረጥ” የሚል የመከልከያ ደብዳቤ ለፋይናንስ ይጻፋል፤ በዚህ ዓይነት ደሞዛቸው ሳይከፈል ተመላሽ የሆነባቸው ብዙ ሠራተኞች አሉ”
የክፍለ ሀገር የሳሙና ሽያጭ ሠራተኛው ደግሞ 8 ወር ሰርቶ መባረሩን ተናግሯል፡፡ ‹‹ሰራተኛ ሲባረር ቀርቶ ሲቀጠርም ደብዳቤ አይሰጠውም። ‹አንተ ሌባ ነህ፤ ግቢዬን ለቀህ ውጣልኝ› ነው የሚባለው። የዚህ ዓይነት ስድብና አባባል በተደጋጋሚ ስሰማ ቆይቼ በመጨረሻም በእኔ ላይ ደረሰ፤ ሠራተኛ በግፍ የሚባረርበት መ/ቤት ፓሲፊክ ኢንዱስት ነው›› ብሏል፡፡
“አንድ ሰራተኛ በድርጅቱ ቆየ ቢባል 3 ወር ነው። እኔ 8 ወር ሰርቼ ነው የወጣሁት፤ የሚያውቁኝ ጓደኞቼ ይህን ያህል መቆየቴን ሲሰሙ ይገረማሉ። የባለቤቱ ሰላይ (ጆሮ ጠቢ ነህ) የሚሉኝም አሉ። እኔ የምሸጠው ሳሙና ማሩቲ ክላሲክ ይባላል። ሳሙናው ገበያ ላይ ካሉትና በትልቅነቱ ምርጥ ከሚባሉት አንዱ ነው። ዋጋውም በጣም ርካሽ ነው፡፡ ስለዚህ ገበያውም ውስጥ ገብቷል፡፡ የሚሸጠው ደግሞ ከአዲስ አበባ  ርቀው በሚገኙት  እንደ ሻሸመኔ፣ ዲላ፣ ይርጋጨፌ፣ ጂማ፣ አጋሮ፣ ጌራ፣… በተባሉ ራቅ ራቅ ባሉ የገክልል ከተሞች ነው፡፡ ነጋዴዎቹን ‹‹ይህ ሳሙና ተወዳጅ የሆነው ለምንድነው?›› በማለት ጠይቄአቸው ነበር፡፡ የሰጡኝ መልስ፤ የኅብረተሰቡ የኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ ስለሆነ ዋጋው ረከስ ያለ ምርት ስለሚመርጡ ነው እንጂ የጥራት ደረጃው ዝቅተኛ እንደሆነ እናውቃለን፤ ብለውኛል፡፡ እኔም አገልግሎት ጊዜው ባለፈ ጥሬ ዕቃ ስለሚሰራ ጥራቱን የጠበቀ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡” ብሏል የቀድሞው የሽያጭ ሠራተኛ፡፡
የፓሲፊክ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ መፍቱህ አብዱልጋፋር በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የአገልግሎት ጊዜው ባለፈበት ጥሬ ዕቃ ይጠቀማል የሚለውን የሠራተኞች ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ‹‹ይኼ‘ኮ የሀገር ሀብት ነው፤ ለ30 ዓመት የሰራ ፋብሪካ እንዴት እንዲህ ያደርጋል? በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው››
የድርጅቱ ሠራተኞች ተፈፅሞብናል የሚሉትን በደል በተመለከተም ተጠይቀው ሲመልሱ፤ ‹‹ሰራተኛው ላይም ምንም በደል አይፈጸምም፤ ሰራተኛ ሲያጠፋ ከመቶ አንድ ሊኖር ይችላል እንጂ በማንም ላብ ላይ በደል አይፈጸምም፡፡ ደሞዙን ከአንድ ዳቦ ወደ ሁለት ዳቦ ለማሳደግ ከመጣር በስተቀር በሰራተኛው ላይ የሚደረግ ጭቆና የለም›› ብለዋል፡፡  

Read 1669 times