Tuesday, 20 June 2017 00:00

የኢራኑ የሃይማኖት መሪ፤ አይሲስን የፈጠረችው አሜሪካ ናት አሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ሳኡዲን በመካከለኛው ምስራቅና በምዕራቡ አለም ሽብር ወንጅለዋል

    የኢራኑ የሃይማኖት መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ፤”አሸባሪውን ቡድን አይሲስን የፈጠረቺው አሜሪካ ናት፤ አይሲስንና ሌሎች አሸባሪዎችን እየተዋጋሁ ነው የምትለውም ውሸቷን ነው” ሲሉ መናገራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
አሜሪካ አይሲስንና አሸባሪዎችን እየተዋጋሁ ነው በማለት የምታሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ያሉት አያቶላህ አሊ ካሚኒ፤ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት አለመረጋጋት እንዲፈጠር አድርጋለች በማለትም አሜሪካን ወቅሰዋል፡፡
“የአሜሪካ መንግስት ኢራን ራሷን የቻለች አገር ሆና እንዳትቀጥል ይፈልጋል፤ በሁለቱ አገራት መካከል የተከሰቱት አብዛኞቹ ችግሮችም መፍትሄ የማይገኝላቸው ናቸው” ሲሉ ሰሞኑን ከኢራን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ መናገራቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
የኢራኑ የሃይማኖት መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ፤ አሜሪካና ወዳጇ የሆነቺው ሳኡዲ አረቢያ አይሲስን ጨምሮ በኢራን የሽብር ጥቃት በመፈጸም የሚታወቁ ሌሎች አሸባሪ ቡድኖችን በገንዘብ ይደግፋሉ ሲሉም ወቅሰዋል፡፡  በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ ጃቫድ ዛሪፍ፤ ሳኡዲ አረቢያ በመካከለኛው ምስራቅና በምዕራቡ አለም እየተፈጸሙ ለሚገኙ የሽብር ጥቃቶች ድጋፍ ትሰጣለች በሚል መውቀሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። እ.ኤ.አ በ1979 የተከሰተውን የኢራን እስላማዊ አብዮት ተከትሎ፣ ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕም ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት የኦባማ አስተዳደር ከኢራን ጋር የተቋረጠውን ግንኙነት ለማደስ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንደሚያቋርጡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ መደመጣቸውን ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በእስራኤል ባደረጉት ጉብኝት፣ “ኢራን ሽብርተኞችን በገንዘብና በስልጠና መደገፏን ልታቆም ይገባል” ሲሉ መናገራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 3361 times