Print this page
Monday, 19 June 2017 10:28

ፎርብስ የአመቱን የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች ይፋ አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ 6ኛ ደረጃን ይዟል

     ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤ የ2017 የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ 100 ዝነኞችን ዝርዝር ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አምና በ22ኛነት ደረጃ ላይ የነበረው ታዋቂው ድምጻዊ ሻን ዲዲ ኮምብስ፣ ባለፉት 12 ወራት፣ የ130 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ዘንድሮ የአንደኛነት ደረጃን ይዟል፡፡
ባለፈው አመት በ34ኛ ደረጃ ላይ የነበረቺው ታዋቂዋ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፣ ዘንድሮ 105 ሚሊዮን ዶላር በማፍራት  የሁለተኛነት ደረጃን ስትይዝ፣ በአመቱ በድምሩ 95 ሚሊዮን ዶላር ያፈራቺው እንግሊዛዊቷ የ”ሃሪ ፖተር” መጽሃፍት ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ በበኩሏ የሶስተኛነቱን ደረጃ ይዛለች፡፡
ካናዳዊው የሂፕ ሆፕ አቀንቃኝ ድሬክ በ94 ሚሊዮን ዶላር፣ የአለማችን የወቅቱ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ93 ሚሊዮን ዶላር አራተኛና አምስተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን፣ በአለም የሙዚቃ መድረክ እጅግ ደምቆ የወጣው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ በበኩሉ፤ በአመቱ 92 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የአለማችን ስድስተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ሆኗል፡፡
ሙዚቀኞች፣ የፊልም ተዋንያን፣ ስፖርተኞች፣ ደራሲያንና በሌሎች መስኮች አለማቀፍ ዕውቅናን ያተረፉ ዝነኞች  በተካተቱበት በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ 100 ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ፣ 16 ሴቶች ብቻ እንደተካተቱ የጠቆመው ፎርብስ፤ ከፍተኛውን ገቢ ያገኘቺው ቢዮንሴ ኖውልስ መሆኗንም አመልክቷል፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት የአመቱ የአለማችን ዝነኞች ባለፉት 12 ወራት ያፈሩት ሃብት በድምሩ ከግብር በፊት 5.15 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ፎርብስ አስታውቋል፡፡

Read 3769 times
Administrator

Latest from Administrator