Monday, 19 June 2017 10:35

PMTCT…ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እንደውጭው አቆጣጠር ከ2011-2015 ድረስ የቆየ ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ በተለያዩ መስተዳድሮች ከሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት ጋር ሰፊ ስራ ሰርቶአል። በዚህ እትም በማህበሩ ስር ከአምስት አመታት በላይ ኤችአይ ቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይለተላለፍ የሚያስችለውን ፕሮግራም በተመረጡ የግል የጤና ተቋማት ሲሰጥ መቆየቱንና ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ እንደነበረ ይታወሳል። በዘሬው ፕሮግራማችን የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ፕሮጀክቱ በምን ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ለአንባቢዎች ለማድረስ የፕጀክቱ አስተባባሪ ከነበሩት ዶ/ር እያሱ መስፍን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ተቋም መምህር ማብራሪያ ጠይቀናል። የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክቶም በውጭው አቆጣጠር 2016 በወጣው ረፖርት ከተካተቱት እውነታዎችም ለአንባቢዎች ጠቅላላ ግንዛቤ እንዲረዳ ለንባብ ብለነዋል።
ኤችአይቪ ለመጀመሪያ ጊዜ መኖሩ ከታወቀበት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1984 አመተ ምህረት ጀምሮ በአለም ላይ ከፍተኛ የጤና እክል መሆኑን የፕሮጀክቱ ሪፖርት ያስታውሳል። በዚህ የጤና እክል ደግሞ ከፍተኛው ጉዳት የደረሰባቸው እንደ ኢትዮጲያ ያሉ የከፊል ሰሃራ አገራት ናቸው። በተጨማም የበሽታው የስርጭት ሂደት በ2008 አም 1.1 በመቶ መሆኑን እና ከዚህም መሀከል 0.7 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 1.4 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ሪፖርቱ በመግቢያው የስታውሳል። የበሽታው ስርጭት በገጠርና ከተማ እንዲሁ የሚለያይ ሲሆን በገጠር 0.5 በመቶ ሲሆን በከተማ ደግሞ 3.2 በመቶ እንደሆነ የ2007 መረጃን ጠቅሶ ያሳያል። በ2008 ዓም በኢትዮጲያ ከ730 ሺህ በላይ የሚሆኑ አዋቂዎች እንደሚኖሩ አስታውሶ ከነዚህም ውስጥ በተመሳሳይ አመት ከ27 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከእናት ወደልጅ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ የሚሰጠው አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ሴቶች አንዳሉ ይጠቅሳል።
በአገሪቱ ከሚኖሩ ህዝቦች መካከል አብዛኛው የሚኖረው በገጠራማው የአገሪቱ አካባቢዎች መሆኑን አውስቶ በከተማው የሚኖረው ህዝብ ግን በሂደት የግል የጤና ተቋማትን አያዘወተረ መምጣቱን እና በዚህም ምክንያት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረግ የጤና ፕሮግራም እነዚህን የግል የጤና ተቋማት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንደሚገባው ሪፖርቱ ይመክራል። ከነዚህ ፕሮግራሞች አንዱ ደግሞ ይህ ቫይረሱ ከእናቶች ወደልጆች እንዳይተላለፍ የሚሰራው ፕሮግራም PMTCT መሆኑን ይገልጸል።
ኤችአይቪ ወደህጻናት ከሚተላለፍባቸው ዋንኛ መንገዶች ጥቂቶቹ በእርግዝና፤ በምጥ፤ በወሊድ ወቅትና እና በጡት ማጥባት እንደሆነ ይታወቃል። ቫይረሱ ከእናት ወደልጅ የመተላለፍ እድሉ ባደጉት አገራት ውስጥ ከ15-25 % ሲደርስ ባላደጉት አገራት ውስጥ ግን ለ25-35 % እንደሚደርስ ያብራራል። ቫይረሱ ከእናቶች ወደልጆች እንዳይተላለፍ ታቅዶ ሲሰራበት የነበረው እና በእንግሊዘኛ ምህጻረ ቃል PMTCT በመባል የሚታወቀው አገልግሎት ወደህጻናት የሚተላለፈውን ቫይረስ ለመቀነስ ብሎም ለማቆም የላቀ ሚና እንዳለው የፕሮጀክቱን ማብቃት የሚያወሳው ሪፖርት ያስነብባል።
PMTCT የምንለው ፕሮግራም እንግዲህ በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል፤- እነዚህም፤- ኢችአይቪ ምርመራ፤ ጥራቱን የጠበቀ እና በጥንቃቄ የሚከናወን የማዋለድ አገልግሎት፤ የኢችአይቪ መድሃኒቶችን ማቅረብ፤ የልጆችን አመጋገብ የተመለከተ፤ የቤተሰብ እቅድ የምክር አገልግሎት እንዲሁም የሪፈራል ትስስርን መፍጠር ናቸው። በዚህ የ PMTCT አገልግሎት ጥራትም ሆነ ተደራሽነት ኢትዮጲያ ከከፊል የሰሃራ አገራትም ሆነ በፕሬዝዳንት ኦባማ አስተዳደር ስር በተቋቋመው እና ፔፕፋር በተባው ፕሮጀክት ከሚደገፉ 15 አገራት ጋር ሲነጻጸር ደካማ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነ እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ2020 ከኤችአይቪ የጸዳ ትውልድን ለመፍጠር ከአገር ውስጥ እና ከሃገር ውጪ ካሉ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር አገልግሎቱን በጥራት ለማዳረስ እየሰራ እንደሚገኝ የ PMTCT ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር እያሱ ማብራሪያ ከሆነ የግል የጤና ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፉ ነው። የ2000ዓም መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ በአጠቃላይ 149 ሆስፒታሎች የነበሩ ሲሆን ከነዚህ መሃል 40 ያህሉ የግል ተቋማት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም 371 ከፍተኛ እና 1155 ልዩ ክሊኒኮች የነበሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም 13ኛ የሚሆኑት የጽንስና ማህጸን ባለሞያዎች የሚገኙት በነዚህ የግል ተቋማት ሲሆን ከነዚህ መሃል አብዛኛዎቹ ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው። ፒኤምቲሲቲን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው ተጨማሪ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ተጨማሪ ስራ ሊሰራባቸው ይገባል ከተባሉት አካባቢዎች ደግሞ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በተለያየ ምክንያት በሚያዘወትሯቸው የግል የጤና ተቋማት ላይ ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ ነው እንግዲህ ፕሮጀክቱ አላማውን (PMTCT) ከእናት ወደልጅ ኤችአይቪ እንዳይተላለፍ ለማድረግ በአገር ደረጃ የሚሰጠውን አገልግሎት በግል ዘርፉ ማስፋፋት እና የመንግስትን እና የግሉን ዘርፍ ትብብር ለማጠናከር በሚል የተጀመረው።
 ዶ/ር እያሱ መስፍን እንደሚሉት ፒኤምቲሲቲ የተባለው ፕሮጀክት ማህበሩ በዋናነት ሲሰራባቸው ከነበሩት ፕጀክቶች ዋንኛው ሲሆን ለአምስት አመታትም ቆይቶአል። ከእናት ወደልጅ ኤችአይቪ እንዳይተላለፍ ለማስቻል የሚሰጠውን አገልግሎት ኢትዮጲያ ውስጥ በሚገኙ የግል የጤና ተቋማት ውስጥ ማስፋፋት በሚል ርዕስ ሲሰራበት የነበረውን ፕሮጀክትም ሲደገፍ የነበረው CDC እና PEPFAR በተባሉት ሁለት የአሜሪካ መንግስት የጤና ቁጥጥር ኤጀንሲዎች ነበር። በተጨማም ፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ የክልል ጤና ቢሮዎች፤ HAPCO - PFSA ፤ መንግስታዊ የሆኑና እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የግል የጤና ተቋማትም ጭምር በትግበራው ላይ ተሳትፈዋል ።
የግል የጤና ተቋማት ኤችአይቪን ለመከላከል ያላቸው ሚና ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ እንደመጣ ይታወቃል። እነዚህ ተቋማት የማዋለድና ተያያዥ አገልግሎቶችን ሲሰጡ የነበሩ ቢሆንም ፒኤምቲሲቲን አስመልክቶ አልፎ አልፎ ከሚሰጧቸው ስልጠናዎች በዘለለ በሀገር አቀፉ ፕግራም ውስጥ የነበራቸው ድርሻ ውስን ነበር።
በአገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይቪን መስፋፋት ለመግታት ሲደረግ ለነበረው እንቅስቃሴ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2007 አም በኢትዮጲያ የማበረሰብ ጤና ማህበር በኩል ከሲዲሲ ጋር በተደረገ ስምምነት የፒኤምቲሲቲ አገልግሎትን በግል የጤና ተቋማት ውስጥ ማስፋፋት ሲጀምርም መነሻ ያደረገው የፒኤምቲሲቲ አተገባበርን፤ ጠቅላላ ግንዛቤና አመለካከትን በግል ሆስፒታሎችና በእናቶችና ህጻናት ልዩ ክሊኒኮች ውስጥ ለመለካት በተደረገ ዳሰሳ ነበር። በዚሁ ከጥር እስከ መጋቢት 2008 በተደረገው ዳሰሳ የግል ሆሰፒታሎችም ሆነ ክሊኒኮች በወቅቱ ባልነበራቸው እንደ ቤንሻንጉል ጉምዝ፤ ጋምቤላ እና አፋር ክልሎች በስተቀር በሌሎች ሁሉም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 39 የጤና ተቋማት ተካተዋል። በዳሰሳውም ከተገኙት ውጤቶች መካከል፡-
በጥናት የተካተቱት የግል ተቋማትPMTCTአገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ሲሰጡ እንዳልነበር፤
አብዛኛዎቹ ባለሞያዎች ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚያስችል ሙያዊ ክህሎት ስልጠና የተሰጣቸው እንዳልነበሩ፤
አብዛኛዎቹ ተቋማት ለ PMTCT የተሟላ ቁሳቁሶች ያልነበራቸው እንደነበሩ፤
በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤችአይቪ ምርመራን፤ PMTCT የቤተሰብ እቅድን፤ እና ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ጨቅላ ህጻናት ሊደረግ የሚገባ እንክብካቤን በተመለከተ የጤና ተቋማቱ ሳይጠቀሙባቸው ያለፏዋቸው መልካም አጋጣሚዎች እንደነበሩ፤
ያለምንም ስልጠና አገልግሎቱን ሲሰጡ የነበሩ ባለሞያዎች እንደነበሩ፤
ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እርጉዝ ሴቶች የቫይረሱ መድሃኒት አጠቃቀም ከሚጠበቀው በታች እንደነበር፤
አብዛናዎቹ ተቋማት ግን ፕግራሙን ለማስጀመርም ሆነ ለማጠናከር ፈቃደኛ አንደነበሩ፤
ሁሉም ተቋማት ማለት ይቻላል ለሰራተኞቻቸው ስልጠናዎች ቢመቻቹላቸው ሰራተኞቻቸው የሚካፈሉበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ተስማምተው እንደነበር፤
ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሁሉም ሰራተኞች እንዲህ አይነት ስልጠናዎች ቢመቻቹላቸው ለመሳተፍ እና በፒኤምቲሲቲ አገልግሎት ዙሪያ እውቀታቸውን ለማዳበር ፍቃደኞች እንደነበሩ፤
አግባብ ባለው አካል በቂ የሆነ ክትትል እንዳልነበር…ወዘተ
የሚሉት እና ሌሎችንም ግኝቶች የተደረገው ዳሰሳ አስገኝቶ እንደነበር ሪፖርቱ ያስነብባል።
ይቀጥላል

Read 1185 times