Sunday, 25 June 2017 00:00

ባለ 10 እና ባለ 5 ብር የሞባይል ካርድ የጠፋው ተጠቃሚ በመብዛቱ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በአዲስ አበባ ባለ 5 እና ባለ 10 ብር ካርድ እጥረት የተፈጠረው በከተማዋ የካርድ ተጠቃሚዎች በመበራከታቸው መሆኑን ኢትዮ- ቴሌኮም አስታወቀ፡፡ ለካርዶቹ መጥፋት ከተጠቃሚው መብዛት ባሻገር የስርጭት ችግር መኖሩን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የኢትዮ-ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ፤ አከፋፋዮች እጥረት አለ ሲባል አጋጣሚውን ተጠቅመው ዋጋ ለመጨመር ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠራቸውን ገልፀዋል፡፡
በሳምንት 50 ሚሊዮን  የባለ 5 እና 10 ብር ካርዶች ፍጆታ ላይ ይውሉ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አብዱራሂም፤ በአሁን ወቅት ከ100 ሚሊዮን በላይ ካርድ እንደሚቀርብ ሰው ሰራሽ እጥረቱን ማሳያም ነው ብለዋል፡፡
ችግሩን በአፋጣኝ ለማቃለል 140 ሚሊዮን ባለ 5 እና 140 ሚሊዮን ባለ 10 ብር ካርዶች በውጭ ሀገር አሳትሞ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዱራሂም፤  ችግሩ ከሰኞ ጀምሮ እንደሚቀረፍም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከ89 ዋና የካርድ አከፋፋዮች፣ 600 ንኡስ አከፋፋዮችና ከ120 ሺህ ቸርቻሪዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ካርዶቹን ለተጠቃሚዎች እንደሚያደርስ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡  
ከሠሞኑ በአዲስ አበባ በርካታ አካባቢዎች ባለ 5 እና ባለ 10 ብር የሞባይል ካርዶችን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሠጡ ተጠቃሚዎች አስታውቀዋል፡፡

Read 3894 times