Sunday, 25 June 2017 00:00

የኢትዮጵያ ቡና አደጋ ተጋርጦበታል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

በአየር ፀባይ ለውጥ ምክንያት “ኮፊ አረቢካ” በሚል መለያ የሚታወቀውን ተወዳጁ የኢትዮጵያ ቡና ጉዳት እያጋጠመው መሆኑን በመጠቆም የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት “ኔቸር ሪሰርች” የተሰኘው ተቋም ባወጣው የጥናት ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ “ኔቸር ፕላንትስ” በተሰኘው መፅሄቱ ላይ ስለ ታዋቂው የኢትዮጵያ ቡና ያሰፈረውን ሰፊ ዘገባ የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያንና ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ጉዳይ አድርገውታል፡፡
በመፅሄቱ በሰፈረው የጥናት ሪፖርት መሰረት “አረቢካ” በሚል በዓለም ዝናን ያተረፈውን የኢትዮጵያ ቡና ከሚያመርቱ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስልሳ በመቶ የሚሆነው በአየር ለውጡ የተነሳ ከእንግዲህ ለቡና ምርት የማይስማማ ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡
ጥናቱን ያከናወኑት ተቀማጭነቱን እንግሊዝ ለንደን ያደረገው ኬው ሮያል ቦታኒካል ጋርደንስ ውስጥ የእፅዋት ምርምር ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አሮን ዲቪሰን እና የኢትዮጵያ የተፈጥሮ አካባቢና የቡና ደን መድረክ ተቋም ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ ወልደማርያም እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕ/ር ሰብስቤ ደምሰው መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በሙቀት መጨመርና በእርጥበት ማነስ ተነሳ በወፍ ዘራሽነቱ የሚታወቀውን “አረቢካ” ቡና ከእንግዲህ የአየር ፀባይ ካልተስተካከለ ለማምረት ይሳናቸዋል ከተባሉ አካባቢዎች ሀረር አንዷ መሆኗ ታውቋል፡፡
አጥኚዎቹ በመላ ኢትዮጵያ 30 ሺህ ኪሎ ሜትር ያካለለ የመስክ ጥናት ማድረጋቸውንና በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቡና አምራች ከሆኑ አካባቢዎች ከ40-60 በመቶ የሚሆኑት በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ቡና ለማብቀል ሊሳናቸው እንደሚችል የሚያመላክት ግኝት ላይ መድረሳቸውተጠቁሟል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ የአየር ፀባይ ለውጥ እየተባባሰ መምጣቱ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ፈታኝ እየሆነ መምጣቱንም ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡
ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ መሆኗን የጠቀሱት የጥናት ቡድኑ አባል ፕ/ር ሰብስቤ ደምሰው፤ “አሁን በኢትዮጵያ ቡና ላይ የተጋረጠው አደጋ በዓለም የቡና ግብርና ላይ የረጅም ጊዜ ጉዳት ያስከትላል” ብለዋል፡፡  

Read 3816 times