Sunday, 25 June 2017 00:00

“ዳንጎቴ ሲሚንቶ ችግሮቹ ካልተፈቱ ፋብሪካውን ሊዘጋ እንደሚችል አስታወቀ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

    የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሲሚንቶ ለማምረት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ግብአቶችን የማውጣትና የማቅረቡን ሥራ ለወጣቶች እንዲያስረክቡ ያወጣውን ትዕዛዝ ካልሰረዘ፣ ዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካውን ሊዘጋ እንደሚችል መግለፁን ብሉምበርግ የዘገበ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ ከዳንጎቴ ጋር የተፈጠረ አለመግባባት እንደሌለ አስታውቆ፤ ዘገባውን ያሰራጩት “ለሆዳቸው ያደሩ ጋዜጠኞች” ናቸው ሲል አስተባብሏል፡፡
በአፍሪካ ቀዳሚ ባለሀብት እንደሆነ የሚነገርለት ናይጄሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ፤ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ከአዲስ አበባ በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሙገር ከተማ አካባቢ ከጥቂት ዓመታት በፊት የገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ምርት ከጀመረ በኋላ የአገሪቱ የሲሚንቶ እጥረት መቃለሉንና ዋጋ መውረዱን የጠቆሙት ምንጮች፤ የፋብሪካው መዘጋት በአገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ለዳንጎቴ ሲሚንቶ የፃፈው ደብዳቤ እንደደረሰው የጠቀሰው ብሉምበርግ፤ “ፋብሪካው የፑሚስ፣ አሸዋና ኖራ ምርቱን ለወጣቶች አሳልፎ ካልሰጠ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነቱን እንደሚወሰድ” የሚያሳስብ ነው ብሏል፡፡
ብሉምበርግ ያነጋገራቸው የዳንጎቴ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር ኤድዊን ዴቫኩማር፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ለችግሩ መፍትሄ እንዲያበጅ የሚያሳስብ ደብዳቤ እንደሚፅፉ ጠቁመው፣ መፍትሄ ካልተገኘ ግን ፋብሪካውን እስከመዝጋት ሊያደርሳቸው እንደሚችል መግለፃቸው ተዘግቧል፡፡
በስልክ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትራንስፖርት ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ተክሌ ኡማ ለብሉምበርግ በሰጡት ምላሽ፤ ዳንጎቴ በክልሉና በአገሪቱ ህግና ደንብ መሰረት እስከሰራ ድረስ “የትኛውንም ኢንቨስትመንት የማፈናቀል ፍላጎት የለንም” ብለዋል፡፡ ማንኛውም አካል በክልሉ መንግስት ላይ ቅሬታ ካለው ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ‹‹ማንኛውም ኢንቨስትመንት ይመጣል፤ ማንኛውም ኢንቨስትመንት ይሄዳል›› ማለታቸውንም ዘገባው ጠቅሷል፡፡
የማዕድን፣ ነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሣ በበኩላቸው ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ምንም ዓይነት  ቅሬታ ለቢሮአቸው እንዳልቀረበላቸው አስረድተዋል፡፡
ስማቸውን መጥቀስ አልፈለጉም ያላቸው አንድ የፌደራል መንግስቱ ሚኒስትር፤ ጉዳዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን ጠቁመው፤ ኩባንያው ቅሬታውን ወደ ሚዲያ ይዞ ከመሄዱ በፊት የሚመለከታቸውንየመንግስት አካላት ማነጋገር እንደነበረበት አስታውቀዋል ብሏል ብሉምበርግ፡፡
ትናንት ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የብሉምበርግ ዘገባን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ከኩባንያው ጋር የተፈጠረ ምንም ዓይነት ቅራኔ እንደሌለ ጠቁመው፣ዘገባውን ያሰራጩት ለጥቅማቸው ያደሩ ጋዜጠኞች ናቸው፤ ጉዳዩም ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በማህበራዊ ድረ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ምላሽ፤ ዘገባው መሰረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጠቁመው፣ የፑሚስና የአሸዋ ምርትን ለወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚነት ማዋልን በተመለከተ ዳንጎቴ ሲሚንቶን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከስምምነት ላይ ደርሰው ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡
ዳንጎቴም ሆነ ሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ስራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆኑንና ከክልሉ መንግስት ጋርም ምንም የተፈጠረ አለመግባባት አለመኖሩንም ኃላፊው አክለው ገልፀዋል - በፃፉት ማስተባበያ፡፡
በኦሮሚያ ለሁለት ዓመታት ገደማ የዘለቀውን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ፣ የክልሉ መንግስት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከዘየዳቸው መላዎች መካከል የድንጋይ፣ ጠጠር እና አሸዋ መሳሰሉ የማዕድን ማውጫ ጉድጓዶችን ከባለሀብቶች ላይ ወስዶ ለተደራጁ ወጣቶች መስጠትን እንደሚጨምር ተዘግቧል፡፡

Read 11414 times