Sunday, 25 June 2017 00:00

“ድርቅ በተከሰተ ቁጥር እርዳታ መቀበልን የመሰለ አሳፋሪ ነገር የለም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አዲስ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል
      ከሳምንት በፊት አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ባወጣው የሀገራት የኢንቨስትመንት መለኪያ ሠንጠረዥ፤ ኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ከቬትናም ቀጥሎ በዓለም 2ኛ፣ በአፍሪካ 1ኛ ደረጃ መያዟን አስታውቋል፡፡
ሀገሪቱ ይህን ደረጃ ያገኘችው መንግስት በተለይ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው በሰጠው ትኩረት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በዋናነት ጨርቃ ጨርቅን መሰረት በማድረግ፣ እ.ኤ.አ በ2025 የአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለቤት ለመሆን ተወጥኗል- ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን በጎበኙበት ወቅት፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሊቀመንበርና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የኢኮኖሚ እቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አርከበ እቁባይ በበኩላቸው፤ ሀገሪቷ ከእንግዲህ ዋስትናዋ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ነው ብለዋል። “ድርቅ በተከሰተ ቁጥር እርዳታ ላለመቀበል ከተፈለገም ኢንዱስትሪዎች በሀገሪቱ ማስፋፋት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው” ብለዋል-ዶ/ር አርከበ፡፡
ሀገሪቱ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ በተያዘው ውጥን መሰረትም፣ 15 ግዙፍ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከ2 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ዶ/ር አርከበ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፋት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ እየተገነቡ ያሉ ሰፋፊ ፓርኮችም በከፍተኛ ርብርብና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ የሚጠቀሰው በዘጠኝ ወር ግንባታ የተጠናቀቀው በ1.4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የሃዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን በተያዘው ወር መጨረሻም የመቀሌና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይመረቃሉ ተብሏል፡፡ ከሶስት ወራት በኋላ ደግሞ የአዳማና ድሬደዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ይመረቃሉ ተብሏል፡፡
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዙሪያ የተገነባው የለሚ-ቦሌ ቁጥር 1 ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመርቆ፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኩባንያዎች፣ ፋብሪካዎቻቸውን እየከፈቱበት ሲሆን ቁጥር 2 ፕሮጀክቱም በመጪው ዓመት ጥር ወር ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ የጅማና የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮች በቀጣይ አመት ግንቦት ወር ይጠናቀቃሉ የተባለ ሲሆን የአረርቲና የደብረ ብርሃን ፓርኮችም በሰኔ ይጠናቀቃሉ ብለዋል - ዶ/ር አርከበ፡፡
የአላጌ (ዝዋይ)፣ የአይሽ (ሶማሌ ክልል) እና የሁናን አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ በቀጣይ ዓመት ግንባታቸው ይጀመራል፤ አፋር - ሰመራ ላይም የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማ    ቋቋም የአዋጪነት ጥናት እየተጠና ነው ተብሏል፡፡
በዓይነቱ የተለየ እንደሆነ የተነገረለት በአዲስ አበባ ቂሊንጦ የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ደግሞ መድኃኒትና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ብቻ የሚስተናግድበት ግዙፍ የፋርማሲዩቲካል ማዕከል ይሆናል፤ ግንባታውም በመጪው ጥር 2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል ብለዋል፤ ዶ/ር አርከበ፡፡
አብዛኞቹን ፓርኮች እየገነቡ ያሉት ደግሞ የቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ፓርኮቹ ሲገነቡ በማዕከላቱ ኢንቨስት ሊያደርጉ ይችላሉ የተባሉ ዓለማቀፍ ኩባንያዎች ተመልምለው፣ እነሱ በሚፈልጉት ዲዛይን የፋብሪካ መጠለያዎች (ሼድ) ግንባታዎች እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
መንግስት በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ምርጥ ኩባንያዎችን በመመልመል ስራ ላይ መጠመዱን የጠቆሙት ዶ/ር አርከበ፤ ወደ ኢንዱስትሪ ማዕከላቱ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ በቅርቡ ጠ    ቅላይ ሚኒስትሩ በቻይና የሚገኙ 12 ግዙፍ ኩባንያዎችን ሲያግባቡ እንደሰነበቱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
መንግስት በራሱ ወጪ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመገንባቱ ሚስጥርም ባለሀብቶች መሬት ለማግኘት፣ መሰረተ ልማት ለማሟላት፣ ህንፃ ለመገንባት የሚወስድባቸውን ጊዜና ገንዘብ ለመቀነስ መሆኑን ዶ/ር አርከበ አስረድተዋል፡፡ ፋብሪካዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ከማቋቋም ይልቅ በአንድ ማዕከል ማሰባሰብም መንግስት ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያወጣውን ወጪ በከፍተኛ መጠን ይቀንስለታል ተብሏል፡፡ እያንዳንዱ ፓርክ የየራሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማጠራቀሚያ ቋት እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡
መንግስት ሀገሪቱን ከችግር ለማውጣት መፍትሄ ነው ያለውን ኢንዱስትሪ ለማስፋፋትና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግም ዶ/ር አርከበ ተናግረዋል። ለምሳሌ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገቡ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች፤ ሁሉንም የመንግስት ቢሮዎች አገልግሎት በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ ተደርጓል የሚሉት ዶ/ር አርከበ፤ ለውጪ ዜጎች ቪዛ ሳይቀር በፓርኩ በተቋቋመው ማዕከል እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ የጉምሩክና የባንክ የመሳሰሉ አገልግሎቶች በፓርኩ በተቋቋመ አንድ ማዕከል ይኖራሉ፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሳተፉም የተለየ ማበረታቻ አዘጋጅተናል ይላሉ። “የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የፋይናንስ፣ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂና የገበያ ውስንነቶችና ማነቆዎች እንዳሉባቸው ይታወቃል” ያሉት ዶ/ር አርከበ፤ የፋይናንስ ችግራቸውን ለመፍታት መንግስት እስከ 85 በመቶ የብድር አቅርቦት ስርአት ማመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ለማስመጣትም ሆነ ሰራተኞቻቸውን በውጭ ሀገራት ለማሰልጠን እንዲችሉም መንግስት እስከ 5 ዓመት የሚደርስ የወጪ መጋራት ስርአት ማበጀቱም ተገልጿል፡፡ ባለሀብቶች በመጀመሪያ ዓመት የስራ እንቅስቃሴያቸው 85 በመቶ ብድር፣ በሁለተኛው ዓመት 75 በመቶ፣ በሶስተኛው ዓመት 50 በመቶ፣ በአራተኛው ዓመት 25 በመቶ፣ በ5ኛው ዓመት ምንም ድጋፍ ሳይደረግላቸው ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡
“በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀዳሚ መሆን ይኖርብናል” ያሉት ዶ/ር አርከበ፤ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ከተንቀሳቀሰ ይህን ውጥን ለማሳካት የሚችል ቁመና እና አቅሙ አለን ብለዋል፡፡ ማኑፋክቸሪንግ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ያለው ድርሻ ከ5 በመቶ በታች ነው፤ የቀጠረው የሰው ኃይልም 380 ሺህ ያህል ብቻ ነው፤ ማኑፋክቸሪንግ ለሀገሪቱ የውጪ ገበያ ያለው አስተዋፅኦ ከግብርና ውጤቶች አንፃር 12 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ይህን አካሄድ ለመቀየርና በቀጣይ 10 ዓመት ማኑፋክቸሪንጉ አስተዋፅኦው ከፍተኛ እንዲሆን በኢኮኖሚው ያለው ድርሻ በ4 እጥፍ ማደግና እስከ 2 ሚሊዮን ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም በውጭ ገበያ አቅርቦት ያለው ድርሻም በ4 እጥፍ አድጎ ግማሽ ያህል ገቢ ከማኑፋክቸሪንግ ውጤት መገኘት አለበት ተብሏል፡፡ ማኑፋክቸሪንግ (የፋብሪካ ምርት) ሲስፋፋም አሁን በጥሬው እየተላኩ ያሉ የግብርና ውጤቶችንም ወደ ፋብሪካ ምርት ቀይሮ መላክ ይቻላል - ብለዋል፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች መገኘት እንዳለበትና ለዚህም ሲባል ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገቡ ባለሀብቶች ትኩረታቸው የውጪ ገበያ ላይ እንዲሆን ይፈልጋል ተብሏል፡፡
በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲዎች ለሚመረቁ እስከ 1 ሚሊዮን ለሚደርሱ ወጣቶች ግብርናው ብቻ የስራ ዕድል እንደማይፈጥር ያወሱት ዶ/ር አርከበ፤ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሰፊ የስራ እድል መስጠት አለበት፡፡ አለበለዚያ ሀገሪቱን የማዘመን ጉዞ ቅዠት እንደሚሆን አስምረውበታል፡፡ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ 2 ሚሊዮን የስራ ዕድል ተፈጥሮ፣ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በቀጥታ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መጠቀም እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን የማምጣት ግብ እንዲሳካም ከዝናብ ጠባቂነት ወደተላቀቀ የመስኖ ግብርና መሻገር እንደሚገባ ዶ/ር አርከበ አስምረውበታል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ የግብርና ዘርፉም ተመጋጋቢ ሆኖ መተሳሰር እንዳለበት ተወስቷል፡፡
 “አንድን ሀገር የሚያሳፍር ነገር ካለ ድርቅ በተከሰተ ጊዜ እርዳታ መቀበል ነው፣ እርዳታን መቀበል የመሰለ አሳፋሪ ስራ የለም” ያሉት ዶ/ር አርከበ፤ “ከዚህ መውጣት አለብን፤ ከዚህ መውጣት የምንችለው ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን አሳድገን፣ የሀገሪቱን አጠቃላይ ምርት ማሳደግ ስንችል ነው ብለዋል፡፡ መንግስት በአሁን ወቅት የውጭ ኢንቨስተሮች ላይ   ማተኮርን የመረጠውም ይሄን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሁን ወቅት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የማኑፋክቸሪንግ የመሰረተ ልማት መሟላትን ስለሚፈልጉ ወጪያቸው ከፍተኛ መሆኑን ታሳቢ አድርገው “ትርፉ ኪሳራ ነው” በሚል እንደሚሸሹ የጠቆሙት ዶ/ር አርከበ፤ ቀጣዩ የመንግስት እቅድ ግን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ኢትዮጵያውያን የፋብሪካ ባለቤቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በተነደፈው አዲስ ፖሊሲ መሰረትም፤ 85 በመቶ የባንክ ብድር ተመቻችቶላቸው፣ በእያንዳንዱ ፓርክ ከ15-30 በመቶ ቦታ  ይመደባል ብለዋል፡፡
በፓርኩ የጋዜጠኞች ጉብኝት  ወቅት በጨርቃ ጨርቅ ምርትና በአልባሣት ምርት ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች ደሞዛቸውን ተጠይቀው፤ በወር ከ600 እስከ 1200 ብር መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ‹‹ይሄ ጉልበት ብዝበዛ አይደለም ወይ›› በሚል የተጠየቁት ዶ/ር አርከበ፤ ‹‹አሁን ትኩረታችን ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩ ላይ ነው›› የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል፡፡
ባለፉት 50 አመታት በሃገሪቱ የተዘረጋውና ያዝ ለቀቅ የሚያደርገው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው መፍጠር የቻለው የስራ እድል ለ53 ሺህ ሰዎች ብቻ ሲሆን አሁን ያለው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪም በአመት እስከ መቶ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ኤክስፖርት የሚያደርገው፡፡ በሚቀጥለው ሁለት አመታት ግን ገቢውን በ10 እጥፍ በማሳደግ 1 ቢሊዮን ዶላር በአመት ለማስገባት ነው እቅዳችን ይላሉ- ዶ/ር አርከበ፡፡ ይህ ገቢም ከሐዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ የሚገኝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በ10 ዓመት ውስጥ የፋብሪካ ሠራተኞችን አሁን ካለው 50 ሺህ ገደማ ወደ 2 ሚሊዮን ለማሳደግም ብቸኛውም መንገድ አስራ አምስቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማቋቋም መሆኑን ዶ/ር አርከበ አስምረውበታል፡፡

Read 1532 times