Sunday, 25 June 2017 00:00

ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች አሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 በፓርቲዎች ድርድር ላይ ኢህአዴግ በአገሪቱ የፖለቲካ እስረኞች አሉ ብሎ ስለማያምን፣ ተቃዋሚዎች በፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ለመደራደር ያቀረቡትን አጀንዳ እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቅ የጀመሩት ዛሬ አይደለም፤ ለበርካታ ዓመታት ጠይቀዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችም መንግስትን ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ከእስር እንዲፈታ በየጊዜው ይጠይቃሉ፡፡ መንግስት ሁሌም መልሱ አንድ ነው - “በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች የሉም” የሚል፡፡ እውነቱ የትኛው ነው? ተቃዋሚዎች “የፖለቲካ እስረኞች” ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? የህግ ባለሙያዎችስ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በጉዳዩ ላይ የህግ ባለሙያዎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሮ ሀሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ አጀንዳው ለውይይት ክፍት ነው፡፡

          “የፖለቲካ እስረኛ አለ የምንለው ከሚከሰሱበት ህግ በመነሳት ነው”
                አቶ አመሃ መኮንን (የህግ ባለሙያ)

    የፖለቲካ እስረኛ ምን ማለት ነው ለሚለው፣ በሀገራችን ቀጥተኛ ትርጉም የሚያስቀምጥ ህግ የለም፡፡ መንግስት ይሄን ትርጉም የሚሰጥ ህግ ያወጣል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም ይሄን ህግ አወጣ ማለት፣ የፖለቲካ እስረኛ እንደሚኖር አመነ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፖለቲካ እስረኛ የሚል ትርጉም ያለው የህግ ቋንቋ የለም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንዲሁ በተለምዶ የፖለቲካ እስረኛ የምንለው የትኛው ነው? ከሌላው እስረኛ በምን ይለያል? የሚለውን በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ማሳያዎች ጠቅሶ ማስረዳት ይቻላል፡፡
በሀገራችን ከህገ መንግስቱ ቀጥሎ የሚመጡ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የመሳሰሉ አሉ፡፡ እነዚህ ህጎች ሰዎች እንዳይፈፅሟቸው የሚከለክሏቸውና የሚፈቅዷቸው ነገሮች አሉ፡፡ እንዳይፈፀሙ የተከለከሉ ነገሮች ሲጣሱ፣ እነዚህን ህጎች መጣስ ተፈፀመ ወይም ወንጀል ተፈፀመ ተብሎ ሰው ይታሰራል፡፡ በመሰረቱ ሁሉም ሰው የሚከሰሰው የሀገሪቱን ህግ ጣሰ ተብሎ ነው፡፡ የሚከሰሰው ሰው የፖለቲካ እስረኛ ነው ወይስ ሌላ ወንጀል ነው የፈፀመው? የሚለውን መረዳት የምንችለው በክሱ ወደተጠቀሱበት ህጎችና አንቀፆች ስንሄድ ነው። ህጎቹ ምን አይነት ሰዎችን ነው የሚያስጠይቁት የሚለውን ስናይ ነው፣ ግለሰቡ የምን እስረኛ ነው የሚለውን የምንረዳው፡፡ ለምሳሌ ደረቅ ወንጀል አለ፡- አስገድዶ መድፈር፣ መስረቅ፣ ሰውን መደብደብ፣ የሰውን ስም ማጥፋት የመሳሰሉትን የሚከለክሉ ህጎች አሉ። እነዚህ ተጠቅሶባቸው የሚታሰሩ ሰዎች የደረቅ ወንጀል ተከሳሾች ይባላሉ፡፡
የሀገርን ሰላምና ፀጥታ መናድ፣ የመንግስትን ስም ማጥፋት፣ መንግስትን በሀሰት መወንጀል፣ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ መንቀሳቀስ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ተቋማት የተሰጣቸውን ስራ እንዳይሰሩ ማደናቀፍ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ ለሽብርተኛ ደርጅት ማገዝ፣ ድጋፍ መስጠት የሚሉ ህጎች ደግሞ አሉ፡፡ እነዚህ ህጎች እነማንን ነው ትኩረት የሚያደርጉት? የሚለውን ለመመለስ ስንሞክር ነው፤ የፖለቲካ እስረኞች አሉ የሉም የሚሉትን መረዳት የሚቻለው፡፡ በእነዚህ ህጎች የሚከሰሱት በገሃድ እንደሚታየው፤ መንግስትን በመተቸት የሚታወቁ፣ በጋዜጠኝነት ወይም በፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና አመራርነት ተሰልፈው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ናቸው፡፡
በመሰረቱ መንግስትን መቃወም፣ መተቸት፣ ወንጀል አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች በህጋዊ መንገድ የተፈቀደላቸውን ስራ ሲሰሩ መንግስትን ይተቻሉ፤ ይቃወማሉ፡፡ የተቃውሞ ደረጃውም ይለያያል። አስተያየት በመስጠት ደረጃ አሊያም በፓርቲ ተደራጅቶ ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ ሊኖር ይችላል። እዚህ ላይ ነው በእነዚህ አካላትና በመንግስት መሃል አለመግባባት ሊፈጠር የሚችለው፡፡
በአንድ በኩል፤ እነዚህ ወገኖች ህጋዊ ስራ እየሰራን ነው ብለው ያምናሉ፡፡ መንግስት ደግሞ፤ “አይ ይሄ ለሀገርም ለመንግስትም ህልውና አደጋ ነው” ብሎ ይነሳል፡፡ “ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል የመናድ ሙከራ ነው” ወይም “ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ማድረግ ነው፤ መርዳት ነው” በሚል ወንጀል ፈፅማችኋል ይባላል፡፡ ከዚያም እስር ይመጣል፤ ክስ ይመሰረታል፤ ፍርድም እየተፈረደ እናያለን፡፡
እነዚህ ሰዎች ሠርቀው ወይ ደፍረው አሊያም ነፍስ አጥፍተው አይደለም የሚከሰሱት፤ የሚታሰሩት፣ የሚፈረድባቸው፡፡ መንግስት ከሚከተለው አቋም የተለየ አቋም ይዘው መንግስትን በመገዳደራቸውና በመተቸታቸው ነው። ከዚህ አንፃር ነው የመታሰራቸው፣ የመከሰሳቸውና ጥፋተኛ የመባላቸው መነሻ ከመንግስት የተለየ አቋም መያዛቸው ነው የሚባለው፡፡  ይሄ ደግሞ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ ህግ ጥሠው ነው ከተባለ፣ ሁሉም ህግ ጥሰዋል ተብለው ነው የሚከሰሱት። ህግን ጥሰዋል የሚባሉበት አግባብ ግን የፖለቲካ እስረኞች ያስብላቸዋል፡፡ እንዲህ ያለ አረዳድ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሃገራት ያለ ነው። ግን ህግ እነዚህን ሰዎች የፖለቲካ እስረኞች ብሎ አይፈርጃቸውም ወይም አይለያቸውም፡፡
እነዚህ ሰዎች በቀጥታ በግለሰብ ላይ ወንጀል ፈፅማችኋል ተብለው አይደለም የሚታሠሩት። ረቂቅ በሆነው በመንግስት፣ በሃገር ላይ ወንጀል ፈፅማችኋል በሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ከሞራል ወይም ከማህበረሰብ ስነ ምግባር ጥሰት ጋርም አይገናኝም ጉዳያቸው፡፡ ለምሳሌ መስረቅ አስገድዶ መድፈር፣ ሰው መግደል… የሞራል ጉዳይ አለበት፣ የሰብዕና መውረድ አለበት፡፡ የእነዚህ ሰዎች ግን የዚህ አይነት ነገር የለበትም፡፡ እንደውም በማህበረሰቡ ዘንድ በሰብዕናቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ የፖለቲካ እስረኞችን ከሌላው ይለያቸዋል፡፡
እኔ በበኩሌ፤ መንግስት “አዎ! የፖለቲካና የህሊና እስረኞች አሉን” እንዲል አልጠብቅም፡፡ እውቅና ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እኔ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዳሉ በግሌ አምናለሁ፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት ግን አሉ ብለው እንዲያምኑ አልጠብቅም፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የየትኛውም ሃገር መንግስትም የፖለቲካ እስረኞች አሉኝ ብሎ አያምንም፡፡

----------------

                       “መንግሥት የፖለቲካ እስረኞች አሉ ብሎ እንዲያምን አይጠበቅም”
                      አቶ አዲሱ ጌታነህ (የህግ ባለሙያ)

      የፖለቲካና የህሊና እስረኛ ምን ማለት ነው ለሚለው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸውና በአስተሳሰባቸው በግለሰቦች ላይ የሚደርሰው እስራት ነው ማሳያው፡፡ አንድ ሰው የፖለቲካ አስተሳሰብ በማራመዱና ሀሳብን በነፃነት በመግለፁ ወይም በጋራም ሆነ በተናጠል መብቶቹን ለማስከበር በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የሚወሰድበትን እርምጃ ተንተርሰን ነው ሰዎችን የፖለቲካ ወይም የህሊና እስረኛ ብለን የምንፈርጀው፡፡
ከዚህ በመነሳት ለእነዚህ ዜጎች ማሰሪያነት እየዋሉ ያሉ ህጎችን ስናይ፣ከውጪ ሀገር ቃል በቃል የተቀዱ ናቸው ይባላል፡፡ እነዚህ ህጎችን ስለጣሱ ነው የታሰሩት ነው የሚለው መንግስት፡፡ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን ለመለየት በቀላሉ የሚታሰሩ ሰዎችን ማንነት፣ አያያዛቸውን፣ የፍርድ ሂደቱንና በመጨረሻ የሚመጣውን ውጤት ማየት አለብን፡፡ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሰዎች በማህበረሰቡ ተሰሚነት ያላቸው፣ ምንም ዓይነት የደረቅ ወንጀል ሪኮርድ የሌለባቸው፤ የእስሩና የተጠረጠሩበት ሁኔታም ሀሳባቸውን በነፃ በመግለፃቸው መሆኑን እንረዳለን። ለምሳሌ ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬን ብንወስድ፤ “ፌስ ቡክ ላይ ሃሳቡን በመግለፁ ነው” የክሱ ጭብጥ የሚለው፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም በተመሳሳይ፤ እውቅና ተሰጥቶት፣ ፍቃድ አውጥቶ ጋዜጣ የሚያሳትም የነበረና በፃፈው ፅሁፍ ተከስሶ፣ 3 ዓመት የተፈረደበት ግለሰብ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ በ”ኢሳት” እና “ኦኤምኤን” ተናግረዋል በሚል ተከሰዋል፡፡ ይሄ ማለት ደረቅ ወንጀል አይደለም። ሀሳባቸውን በመግለፃቸው ነው የተከሰሱት፡፡ ሀሳብን መግለፅ ደግሞ ፖለቲካዊ መብት ነው፡፡ እነ አግባው ሰጠኝ የታሰሩት “የጎንደር መሬት ለሱዳን ተቆርሶ ተሰጥቷል” ብለዋል በሚል ነው፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች ስንመለከት፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ናቸው። ከዚህ በመነሳት ነው የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በኢትዮጵያ አሉ የምንለው፡፡
በተከሳሾቹ ላይ የሚቀርቡ ማስረጃዎችም ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከማራመድ ጋር የተገናኙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይሄ ግልፅ ነው። መንግስት የፖለቲካና የህሊና እስረኞች አሉኝ ብሎ እንዲያምንም አይጠበቅም፡፡

-----------------

                         “የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲኖሩ የሚፈቅዱ ህጎች አሉን”
                        አቶ ተማም አባቡልጉ (የህግ ባለሙያ)

      የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ማለት በተናገሩት በፃፉት፣ በተቃወሙት ጉዳይ የታሰሩ ሰዎች ማለት ነው፡፡ መቼም በእነዚህ ምክንያቶች የታሰሩ ሰዎች ስለመኖራቸው ህዝብ በግልፅ ያውቀዋል፡፡ በዚያው ልክ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኝነትን የሚፈቅዱ ህጎችም አሉ፡፡ የፀረ ሽብር ህግ፣ የፕሬስ አዋጅ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ስለ ፕሬስና ሀገር መክዳት የተፃፉ ህጎች ሁሉ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲኖሩ የሚፈቅዱ ናቸው፡፡
በደረቅ ወንጀል ማለትም ሰው በመግደል፣ በመስረቅ፣ በአስገድዶ መድፈርና በመሳሰሉት ሳይሆን መንግስትን በተለያየ አግባብ በመቃወም፣ መንግስት የማይመቸውን ነገር በመፃፍ የታሰሩ ሰዎች በሙሉ፤ በድርጊት የሚገለፅ ወንጀል ሳይኖር እንዲሁ በአስተሳሰባቸው የተነሳ የታሰሩ የህሊና እስረኞች ብለን ነው የምንፈርጃቸው፡፡ ለምሳሌ፡- እነ ዶ/ር መረራ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የመሣሠሉት የቀረበባቸው ክስና ማስረጃ ከፃፉት፣ ከተናገሩት ነገር ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ይሄ ታዲያ ምን ትርጉም ነው ሊሰጠው የሚችለው? በፀረ ሽብር አዋጁ የተመሠረቱ ክሶችና እስሮችን በሙሉ የፖለቲካ እስረኞች ነው ልንል የምንችለው፡፡ የፀረ ሽብር ህግ ሃገርን መጠበቂያ እንጂ ዜጉችን ከመንግስት ላይ መጠበቂያ አይደለም። ይሄን ስንመለከት ግማሽ ያህሉ በኢትዮጵያ ያሉ እስረኞች፤ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ናቸው ለማለት ያስደፍረናል፡፡
ማነሣሣት፣መናገር፣መቀስቀስ የመሳሰሉት የፖለቲካ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በድርጊታቸው ሣይሆን በአስተሣሠባቸው፣ ገና ውጤቱ ሣይመጣ የተከሰሱና የታሠሩ በሙሉ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች ናቸው፡፡ በህጎች ላይ የፖለቲካ እስረኞች የሚል ቃል ባይኖርም የሚከሰሱት ሰዎች ማንነትና ፈፅመዋል የተባለው ድርጊት ነው የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ብለን እንድንለይ የሚያግዘን፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች የሉም ማለት በገሃድ የሚታይን ሃቅ መካድ ነው፡፡

-------------------

                              “የፖለቲካ እስረኞች የሉም ብሎ መካድ ከእውነታው መጣላት ነው”
                            ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

      ለሀገራቸው ችግር የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልጋል ብለው የተነሱ ሰዎችን ማሰርና “የታሰሩት በሰሩት ወንጀል ነው” ብሎ ማጭበርበር፣ በዓለም ላይ ያሉ የአምባገነን ገዥዎች ባህርይ ነው፡፡ ነገሩን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካየነው፣ ኔልሰን ማንዴላም በአንድ ውቅት አሸባሪ ነበሩ፤ ወንጀለኛ ነበሩ፤ ድርጅታቸው ሽብርተኛ ድርጅት ነበር፡፡ የበርማዋ የነፃነት ታጋይም ስልጣን ላይ በነበረው ስርአት ወንጀለኛ ተደርጋ ለረዥም አመታት የቁም እስረኛ ነበረች፡፡ ይሄ የአምባገነን ገዢዎች የቆየ ባህርይ ነው፡፡ በኛ ሀገር ሁኔታም እነ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ እነ ዶ/ር መረራ፣ እነ ዮናታን ተስፋዬና ሌሎችም የታሰሩ ፖለቲከኞች፤ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው እንደታሰሩ አለም የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡
መንግስት መቼም እነዚህን ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው አሰርኳቸው ሊል አይችልም፡፡ ይሄን ካለማ ከራሱ ፖለቲካ ጋር ተጋጨ ማለት ነው። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ፈፅሞ የፖለቲካ እስረኞች አይደሉም ብሎ ሸምጥጦ መካድ የሚያሳየን፣ አሁንም ኢህአዴግ ለፖለቲካ መፍትሄ ዝግጁ አለመሆኑን ነው፡፡ እውነተኛ ችግሮችን ለይቶ፣ ለችግሮቹ መፍትሄ ለመስጠት የዝግጁነት ችግር እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ እንዲሁ እየገዛ በስልጣን መቆየት መፈለጉን የሚያሳይ ነው፡፡ “በህግ ነው ያሰርነው” እየተባለ መተጣጠፍ የተለመደ የአምባገነን መንግስታት ባህሪ ነው፡፡ ያለአግባብ እዳ እየከፈሉ ያሉ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ትልቅ እርምጃ ነበር፡፡ የሉም ብሎ መካድ ከእውነታው መጣላት ነው፡፡

-------------------

                        “እንደ ፀሐይ በርቶ የሚታይ ሃቅ መካድ ነው”
                     ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (ፖለቲከኛ)

     የፖለቲካና የህሊና እስረኞች የሉም ማለት፣ እንደ ፀሐይ በርቶ የሚታየውን ነገር መካድ ነው። በኢትዮጵያና በዓለም ህዝብ ፊት ይሄን ሃቅ መካድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
ፖለቲከኛውን ለማጥቃት ሲፈልጉ ክስ ይመሰርታሉ፤ ከዚያም በፖለቲከኛነቱ አይደለም የከሰስነው ይላሉ፡፡ ይሄ የተለመደ የኢህአዴግ ፀባይ ነው፡፡ እነ ዶ/ር መረራ ምን ስላደረጉ ነው የታሰሩት? ይሄ ክህደት አመክንዮ የሌለው ነው፡፡
ዓለም የሚያውቀውን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀውን ሃቅ መካድ ነው፤ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች የሉም ማለት፡፡ ሰው በሙስና፣ በማጭበርበር ይታሰራል፤ የእነዚህ የፖለቲካ አላማ አራማጆች ጉዳይስ በየትኛው ዘርፍ ነው የሚካተተው? የሰው ቤት ዘርፈዋል? ህዝብ መቀስቀስ ወይም ማሰለፍ በሚል ከተጠረጠሩ ያው ፖለቲካ አይደለም እንዴ?!

Read 2243 times