Sunday, 25 June 2017 00:00

የሙስናው ግልገል አሳዳጊዎች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 ለማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ዕድገት ማለት ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ብቻ ሳይሆን የስነ ልቡናዊና ማህበራዊ ጉዳዮችንም አብሮ ያጣምራል፡፡ ይህም የሀብት ክፍፍሉ በማህበረሰቡ ውስጥ ምን ያህልና እንዴት ነው? የሚል ትኩረትም ይሰጣል፡፡ እነዚህ ደግሞ ከድህነት፣ከሃብት ልዩነትና ከስራ አጥነት ጋር ይያያዛሉ፡፡
ለምጣኔ ሀብት ምሁራን ደግሞ ነገሩ ሌላ ነው። ለእነሱ ዕድገት የምጣኔ ሀብት ከፍታና የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው፡፡ ታዲያ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ድህነትና ስራ አጥነት እንዲቀንስና ብልፅግና ወደ እያንዳንዱ ጎጆ እንዲገባ ሲታሰብ፣ በምኞት ብቻ ሰማይ አይደረስም፡፡ በጎዳናው ላይ በርካታ እንቅፋቶች አሉ፡፡ እነዚህ እንቅፋቶች ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራኑ እንደሚሉት፤ከስነ ልቡናዊ ቅርጻችንና መልካችን ጋር ይያያዛል። ካዳበርነው ባህል፣ እምነት፣ ልማድ ወዘተ-- ይተጋገዛል፡፡
ሙስና ከእነዚህ የዕድገት ዕንቅፋቶች ዋነኛውና ሥር የሰደደ፣ ሺህ ዓመታት ያስቆጠረ በሽታ ነው። ይሁንና ይህን እንቅፋት ለማስወገድ የታተሩ የእምነትም ሆነ የተረት ምሳሌዎች፣ የታሪክ ሰነድ ውስጥ በእውነታ የሚታሰቡ ምስክሮች አሉት። እኔም ሁልጊዜ ፀረ ሙስና አቋም ያለው አንድ ሰው ይታሰበኛል፡፡ ምድር ቀና አጥታ፣የተቀደሱት ረክሰው፤ የተጠበቁት ቁም ነገር ጠፍቶባቸው በነበረ ጊዜ፣ የአንዲት መካን ማህፀን ያፈራው፣አንድ እውነተኛ ሰው ተወልዶ ነበር - ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የአፉ ቃል ጠብ የማይለው ነቢዩ ሳሙኤል፡፡
ነቢዩ ሳሙኤል በሙስና ጉዳይ ከሺህዎች ዓመታት በፊት በህዝብ መሃል ራሱን ለግምገማ ያቀረበ ንፁህ ሰው ነው፡፡ በተለይ ስራውን እያጠናቀቀ ሲመጣ፣ ያመነውን አምላኩን ስም ለማስከበርና፣ የራሱን አርአያነት ለትውልድና ለታሪክ መዝገብ ፀአዳ አድርጎ ሊያስቀምጥ ሲሻ፤ “ከእናንተ ውስጥ እጅ መንሻ የተቀበልኩት፣ በሀሰት የዳኘሁት አለ ወይ? ብሎ ህዝቡን በጉባኤ የጠየቀ ጎበዝና ደፋር ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ባሳለፋቸው የኃላፊነት ዘመናት የነበረው ንፅህናና ፍትህ የሰጠው ድፍረት ነበር፡፡ መቸም ቢሆን ንፁህ ሰው ኮሽ ባለ ቁጥር አይደነብርም፤ አደባባይ ላይ ሳይሳቀቅ ይንጎማለላል። የንፁሃን አይኖች ሽሽት፣ አይኖቹ መግቢያ አያጡም። ውስጡን የድሆች ጩኸት አያሽረውም፡፡ ከሕፃናት ጉሮሮ የነጠቀው ርዳታ፣ እንደ ጅራፍ ጆሮው ላይ አይጮህም፤ እዬዬአቸው አይከተለውም፡፡ በረሀብና በዕጦት ለሞቱ ወገኖቹ የሚመታው ደረት ህሊናው ላይ እንደ ከበሮ አይጮህም፤የተረጋጋና ነፃ ነው፡፡
በዓለማችን ላይ እንደ ሳሙኤል ያሉ ሰዎች ብዙም ባይሆኑ አሉ፡፡ አንዳንድ ሀገራት ላይ መዋቅሩ በራሱ የሙስናን ቀዳዳዎች ስለሚደፍን ሰዎች ብዙ ፈተና አይገጥማቸውም፡፡ አንዳንዱ ጋ ደግሞ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም የሚሰጣቸው ፅናት ሙስናን እንዲፀየፉት ያደርጋቸዋል፡፡ “እግዚአብሄር የለም!” የሚል ድፍን ጥላቻና እምነት ዓለምን እንደ ደመና በከበበ ዘመን እንኳ ያለምንም ዓይነት አምላክ ሆነው ራሳቸውን ከሙስና የጠበቁና ያራራቁ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምናልባትም “እግዚአብሔርን እናመልካለን” ከሚሉት ምዕራባውያን ይልቅ ምስራቃውያኑ በዚህ ፀዳ ያሉ ነበሩ፡፡
ስለዚህ ሳነሳ ትዝ የሚለኝ ጆሴፍ ስታሊን ነው፡፡ ስታሊን በእጅጉ ጨካኝ ተብሎ በአረመኔዎች ሰልፍ የተመደበውን ያህል ትግሉን በጀመረ ጊዜም በነበረው ፅናትና ስልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ በነበረው ከሙስና የፀዳ ኑሮ ይወደሳል፡፡ … ይህ ደግሞ ከሚኖርበት አፓርትመንት ይጀምራል፡፡ ሶቪየትን የሚያህል ታላቅ ሀገር የሚመራ ሰው ሊኖርበት የሚችለውን ቤትና አኗኗር፤ የቀደመው መንግስት መለኪያ ያኖረለት ቢሆንም ስታሊን ግን በነርሱ የተንደላቀቀ ፓላስ መኖርን አልፈለገም፡፡ ምክኒያቱም ራሱን ከጭቁኖች ብዙ ማራቅ አልወደደምና!
ያ ብቻ አይደለም፤ የወለዳቸው ሁለት ልጆቹ (ከሁለተኛ ሚስቱ ይመስለኛል) እንደ ማንኛውም ዜጋ የአየር ኃይል ፓይለትና ከዚያ ያልዘለለ ስራ ነበር የተሰጣቸው፡፡ የኛው ሀገር ኮሎኔል መንግስቱም ለቤተሰቦቻቸውና ለራሳቸው የተለየ ጥቅም ያልነበራቸው፣ እህትና ወንድሞቻቸው ማንኛውም ዜጋ በሚማርበት ተራ ትምህርት ቤት የሚማሩ፣ በቀበሌያቸው እንደ ሌሎቹ ሁሉ ለስኳርና ጨው የሚሰለፉ እንደነበሩ በቅርቡ በደራው ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ሰምተናል፡፡
እንደኔ እንደኔ ሙስና እንቁላሉን የሚጥለው በገዛ ጎጆዋችን ነው፡፡ የሚፈለፈለው ምናልባት ጎረቤት ቢሆን፣ አድጎ ክንፍ የሚያወጣው አደባባይ ላይ ይሆናል፡፡ ቀላል የሚመስሉን ልምዶች ናቸው አድገው፣ ግዙፍ ሆነው፣ ካቅማችን በላይ ሆነው የሚያንጠራሩን፡፡ ሰፈር ውስጥ ካስለመድናቸው ትንንሽ ጉርሻዎች ጀምሮ ወደ ሙስና የሚያድጉ ብዙ ልምዶች ናቸው፡፡ ስጋ ቤት የተመረጠ ስጋ እንዲቆርጥልን በኪሱ አስርና ሃያ ብር ከምንወሽቅለት ስጋ ቆራጭ፣ ይነሳል፤ ጉቦ! … ይህን ጉርሻ የለመደ ሰው ታዲያ አድልዎ ቢፈጥር፣ላልሰጡት ጥሩ ባይቆርጥ ጥፋቱ የማን ሊሆን ነው? … የኛ የራሳችን ነው፡፡
ካፊቴሪያና ሬስቶራንት ውስጥ ጠቀም ያለ ቲፕ ስንሰጥስ? … በየትኛው ዝንባሌ ይሆን? … “ልጆቹ/ሰዎቹ ለአገልግሎታቸው ይገባቸዋል?” በሚል ወይስ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ለእኛ በቶሎና በጥሩ ሁኔታ እንዲታዘዙን? … ለማኪያቶ ባሬስታ ጉርሻ ስንሰጥስ? … በቀና መንፈስ ወይስ ለኛ ጨምሮ እፍታውን እንዲያወርድ? በአዲስ ቡና ጠብደሉን እንዲያጠጣን? … የተለያዩ ቦታዎች በሚኖር ወረፋና ሰልፍም ይህ ግልገል ሙስና አለ፡፡ ዛሬ ማጣፊያው ያጠረን ራሳችን፣ በጎጆዋችን አሳድገነው ነው፡፡
ሀገር መውደድና ለወገን ማገልገልን ከማስተማር ይልቅ ስለ ብልፅግና ያለ ድንበር በማውራት ስድ አደግ ትውልድ ፈጥረናል፡፡ ለመብላት ሲሮጥ፣ ሰዎችን እንደ አውዳመት ቄጠማ እየረገጠ ሲያልፍ ቅር የማይለው ዓይነት ሰው በዝቷል፡፡ … ግን ይህ ሁሉ የዘራነው ዘር ነው፡፡ በዚህ ዘመን የሙሰኛው ቁጥር እጅግ በርክቷል፡፡ ምናልባት አንድ ሙሰኛ ልንፈትሽ ብንሄድ ከጀርባ ሌሎች ተመሳሳይ ሺዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አርነስት ሔሚንግዌይ በጻፈው አጭር ልብ ወለድ ድርሰት ላይ ከልጁ ጋር ተቀያይሞ የነበረው አባት፤ያወጣው ማስታወቂያ እንዲህ ተፅፏል፡-
“ውድ ፓኮ፣ ነገ ከሰዓት በኋላ ከማድሪድ ጋዜጣ ዝግጅት ቢሮ ፊት ለፊት ናና እንገናኝ፡፡ ሁሉንም ነገር ይቅር ብያለሁ፡፡ እወድሃለሁ”
በማግስቱ ግን የሆነው ሌላ ነበር፤ 800 ታዳጊ ወጣቶች ነበር በስፍራው የተገኙት፡፡ የኛም ሙስና እንዲህ ነው፤ ከገመትነው በላይ፡፡ በጥቅሉ ስናየው የኛ ባህል ለሙስና የተመቻቸና ክብር የሚሰጥ ነው። ለስጋ ሻጩ ሳንቲም ከማጉረስ ጀምሮ ለዳኝነት፣ ለፍትህ ሰጪና ለሌሎችም የሚዘረጋ መሰላል እስከ ላይ ይዘልቃል፡፡
ሌላ ቀላል ምሳሌ ላምጣላችሁ፣ … በታክሲ ሰልፍ እንኳ ሀገር በፀሐይ እየነደደ ሳለ፣ ቀሚሷ አጠር ያለ፣ ቆንጆ ሴት ስትመጣ ተራ አስከባሪው የሙስናን ፈተና ይወድቃል፡፡ ያለ ተራዋ ያስገባታል፤ እሷም ያልተገባ ጥቅም ተጠቀመች፡፡ ሰልፍ መያዝ ሲገባት፣ በውበቷ አማልላ ሰልፉን ሰበረች ማለት ነው፡፡ ይሄኔ ነው የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ቤተሰቦች የማደንቀው፡፡ እንደ ሀገሬው ሰው ልማድ፣”የሹም ቤተሰብ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ” ሆኖ ሳለ ያንን ሰብረው፣ ከህዝብ ጋር ሰልፍ ይዞ፣ ስኳርና ጨው መውሰድ የሚጠቀስ ስነ ምግባራዊ አርአያነት ነው፡፡
“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል!” የሚል ብሂል ያለን ኢትዮጵያውያን፤ወደ ሌሎች ጣት እንጠነቁላለን እንጂ ሁላችንም እንዳቅማችን ተነካክተናል፡፡ ለምሳሌ መምህራንን ስለሚያካትተው ሙስናም የተለያዩ ቦታዎች የሰማሁት ምሬት አለ፡፡
አንድ መምህር ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች አንዱን በግል ተከፍሎት የሚያስጠና ከሆነ፣ ያ ልጅ በርሱ ጥናት ውጤቱ እንደተቀየረ ለማስመሰል፣ ያላመጣውን ውጤት በመጨመር፤ ከሌሎች ጓደኞቹ እንዲበልጥ፣ ሌሎቹ ላይ አድልዎ ይደረጋል። በዚህ ምክንያት በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሯቸውን በተለይ ስም ጠሪ የሆኑበት ክፍል፣ ተማሪ በግል፣ በክፍያ እንዳያስጠኑ ከልክለዋል፡፡
እንግዲህ ሙስና ይህ ነው፡፡
የጥበቃ ሰራተኞችም ይሞስናሉ፡፡ ለምሳሌ መኪና ማቆሚያ ስፍራ እያለ “ቦታ የለም!” ብለው የማያውቁትን ሰው ይመልሱና ጉርሻ የሚሰጣቸው ሰው ሲመጣ ተሽቆጥቁጠው፣ ቦታ ይሰጡታል። መዝገብ ቤት፣ ፀሐፊ ወዘተ--- ለምናውቀውና ለሚቀርበን ሰው እናደላለን፡፡ ሙስና ማለትም ይህ ነው፡፡ ያልተነካካ የለም፡፡
 በሌላ በኩል “ሙሰኞች” ብለን የምንሰድባቸውን ሰዎች ስለሰሩት ፀያፍ ስራ አናገልላቸውም፤ ወይም አንንቃቸውም፡፡ ይልቅስ ለጥ ብለን እጅ እንነሳቸዋለን፡፡ ቆንጆ መኪና፣ ቆንጆ ቤት ያለው ሰው ይከበራል፤ እንጂ ቆንጆ ስነ ምግባር ያለው ሰው አይከበርም፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ “ለራሱ አያውቅም፤ ምን ያደርጋል!” ይባላል፡፡
እኔ በይፋ የማውቃቸውና በሚሰሩበት አካባቢ የሚታወቁ ሁለት የሙስና ጠላት የሆኑ ወዳጆች አሉኝ፡፡ አንደኛው እጅግ በጣም ጓደኛዬ ነው። እምነቱ ሙስሊም ሆኖ፣ የህግ ሰው ነው። ሌላኛው የግብርና ባለሙያ ሆኖ ማኔጅመንትም ተምሯል። የማኔጅመንቱ ሰው የወረዳ አስተዳዳሪ ሆኖ ለዓመታት ሰርቶ ነበር፤ ግና አሁን ዘርፉን ከቀየረ በኋላ በኑሮው ላይ ለውጥ የለም፤ መኖሪያ ቤት አልሰራም፤ አንዳች ሀብት አላከበተም፡፡ በዚያው ዓይነት ኑሮ፣ በአንድ ቢሮ ውስጥ የፀረ ሙስና መኮንን ሆኖ ይሰራል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ንፅህናው ማህበረሰቡ አያከብረውም፡፡ በተደጋጋሚ ስለ እርሱ የሰማሁት ነገር ቢኖር ህዝባችን ከንፅህና ይልቅ ሙስናን እንደሚያደንቅ ነው፡፡
‹‹የማይረባ ሰው ነው፣ ሥልጣን በያዘበት ጊዜ ለልጆቹ እንኳ የመኖሪያ ቤት ሳይሠራ ይወርዳል?... እርሱማ ከንቱ ሰው ነው!” ሲሉ በጆሮዬ ሰምቻለሁ። ይህንን የሚሉት ደግሞ ጉሮሮዋቸው እስኪደርቅ ድረስ ሙስናን የሚቃወሙ ሰዎች ናቸው፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው!›› ነው ነገሩ፡፡ ምንም አድርጎ ሰው ገንዘብ ይዞ መገኘት አለበት የሚል በሽታ አለብን፡፡
ይህ ጉዳይ አሁን አሁን ባሰ እንጂ በንጉሠ ነገሥቱም ዘመን እጅግ የተስፋፋ እንደነበር “የንጉሱ ወጥ ቤት ሃላፊ” መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ያኔ የትም ቦታ፣ የትም ቢሮ ያለ እጅ መንሻ አይገባም ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ መነሻው አስተሳሰብ ነው፡፡ ከህሊና ነፃነት ይልቅ ሆድን መውደድ!
ከላይ ከጠቀስኳቸው ሁለት ወዳጆቼ ውስጥ የመጀመሪያው ሙስሊሙ፣ ከሌሎቻችን ጠንከር ያለ አቋም አለው፡፡ ብዙ ሠዎች በዚህ ፀባዩ  እንደ ደካማ ቆጥረው ከንፈር ቢመጡለትም እርሱ ግን በነፃነት ቀና ብሎ መሄዱን ከሁሉ በላይ ይኮራበታል። ለኔም የነገረኝ ይህንኑ ነበር፡፡ አንዴ በነበረበት ወረዳ ከፍተኛ ግምገማና የፀረ-ሙስና ፍተሻ ሲደረግ፣ እጃቸው የነካካው ሰማይ ሲደፋባቸው፣ እርሱ ግን እየሣቀ አደባባይ ላይ ይንጎማለል ነበር፡፡ ንፅህና ክብር ነው! ብሎ፡፡
እኔ የሁለቱም አድናቂ ነኝ፡፡ በባህር መሀል እንደሚነድድ እሣት ናቸው፤ በሙስኞች መሀል ጤነኛ ሆኖ መገኘት ታላቅ ድል ነው፡፡ በነፃነት- በልክ መኖር! ሕብረተሰቡ ግን አሁንም የሙሰኞች ቲፎዞ ነው። በአንድ ጉንጩ የምሬት እንባ እያፈሰሰ፤ በሌላው ዐይኑ በአድናቆት ይሥቃል፡፡ መጽሐፉ እንደሚለው፤ ”ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን›› ማለት ይህ ይሆን?
ገጣሚት ሜሮን ጌትነት ‹‹ዙረት›› በሚለው መጽሐፏ የተካተተው ግጥም፣ይህ በሽታችን ያመጣብንን ጣጣ ይነግረናል፡-
‹‹ተበላችሁ›› ይላል ርዕሱ
የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም
በርታ ተማር ብላችሁ
ያሳደጋችሁት ልጃችሁ
የብሂሉን ልክነት አረጋግጦ
ተምሮ ተምሮ ስልጣኑን ጨብጦ
ውለታ ይመልሳል፤ ሕዝብ ያገለግላል
ብላችሁ እናንተ ምላሽ ስትጠብቁ
እውቀቱን መች አጣት አጅሬ ጥንቁቁ
ዞሮ የናንተኑ ሀብታችሁን ግጦ
የቀረውን ሽጦ
ቅርፍጥ አርጎ በላ የሀገር አደራ
ብላችሁት የለ አይወድቅም የበላ፡፡
ሙስና በሚገዛው መኪና፣ በሚሠራው ቪላ በኩል ካየነው ያሥጎመዥል፡፡ በሌላው ጥላ በኩል ስንቃኘው ግን ይዘገንናል፡፡ ያ የሚዘረፍ ገንዘብ፣ በሚያሠራው፤ ሆስፒታል፣ የሚድኑ ሰዎች እንደሚሞቱ፤… በዚያ ገንዘብ ጎዳና የሚወድቁ ልጆች ተነሥተው፤ ተምረውና አድገው፤ ለሀገር መጥቀም ሲችሉ፣ መውደቃቸውን ካሰብን ያምማል፡፡
ብዙ ሰዎች በበሽታና ረሀብ በሚሰቃዩበት ሀገር፣ ከድሆች አፍ ነጥቆ፣ የተንቀባረረ ኑሮ፤ ልክ የሌለው ቅንጦት ውስጥ መግባት መሆኑን ከልጅነት ጀምሮ ያላስተማረች ሀገር፣ በምንም ተዐምር ከሙስና አትወጣም!... ሙስና የሚጣፍጠው አእምሮዋችን በውሸት ተቃኝቶ ሲያድግ ነው፡፡ ቄሱና ሼሁ፣ ወይም ፓስተሩ ይህን ካላስተማሩ፤ ነገም ከዚህ ማጥ ውስጥ አንወጣም፡፡

Read 1890 times