Sunday, 25 June 2017 00:00

አምባሳደር በቀን 1000 ሙሉ ልብስ ሊያመርት ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

      የመሳሪያ ተከላ ውል ከጃፓንና ኢጣሊያ ኩባንያዎች ጋር ተፈራርሟል
                                 አምባሳደር ፋብሪካ በቀን 1000 (አንድ ሺህ) ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ሙሉ ልብሶች ማምረት የሚያስችለው የመሳሪያ ተከላ ውል፣ ከጃፓንና ኢጣሊያ ኩባንያዎች ጋር ተፈራረመ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተደረገው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት፣ በገላን ከተማ በ25 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ላይ በተሠራው ፋብሪካ፤ ልብስ ማምረቻ መሳሪያውን የሚተክለው ታዋቂው የጃፓኑ ጁኪ (Juki) ሲሆን በስፌቱ ማጠቃለያ ልብሱ አምሮ እንዲወጣ የሚያደርገውን የልብስ ተኩስ (ፕሬሲንግ) መሳሪያ የሚተክለው ታዋቂው የኢጣሊያ ኩባንያ ማክፒ (Macpi) እንደሆነ ታውቋል፡፡
በ350 ሚሊዮን ብር ካፒታል በገላን ፕሮጀክት ማስፋፊያ በጃፓኑና በኢጣሊያው ኩባንያ የሚተከሉት መሳሪያዎች፣ የዘመኑ ሥልጣኔ የደረሰበት የመጨረሻ የቴክኖሎጂ ውጤት (ስቴት ኦፍ አርት) መሆናቸውን የጠቀሱት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ታፈረ፤ የልብስ መስፊያው መሳሪያ በኮምፒዩተር ዲዛይን የሚያደርግና የሚቆርጥ (ኮምፒዩተራይዝ ዲዛይንና ኮምፒዩተራይዝ ካቲን CAD እና CMA) መሳሪያ የተገጠመላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡  የስፌት አሠራሩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የሚያግዙ የኮምፒዩተር ቦርድ አውቶማቲክ ትሪሚንግ መሳሪያ ያላቸው ናቸው ያሉት አቶ ተሾመ፤ ጥሬ ዕቃ መፈተሻ (ፋብሪክ ኳሊቲ ኢንስፔክሽን) መሳሪያና ጨርቁ ለለባሹ ምቹ እንዲሆን የሚያደርግ (ስፖንጂንግ) መሳሪያ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ተሾመ፣ የስፌት የሥራ ሂደት ማጠቃለያ የሙሉ ልብስ ተኩስ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለዚህ ተግባር የኢጣሊያው ኩባንያ ማክፒ የሚተክለው በፕሮግራም የሚሠራ አውቶማቲክ ፕሬሲንግ (የሚተኩስ) መሳሪያ፣ በሰዓት 2000 ኪ.ግ እንፋሎት እያመረተ፣ ከስፍራ ስፍራ የሚዘዋወር አውቶማቲክ ሃንሚንግ ሲስተም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአሁን ወቅት ዓለም አቀፍ ብራንዶች ወደ አገራችን እየገቡ ነው፡፡ በገበያው ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠልና አሁን ያለንን ደረጃ ለማስጠበቅ፣ ድርጅቱ መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ታምኖበታል ያሉት የአምባሳደር ልብስ ስፌት መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሃን፤ ድርጅቱ በአዲስ አደረጃጀትና ማስፋፊያ “አምባሳደር ትሬዲንግ” እና “አምባሳደር ፋብሪካ” በሚል ለአሰራር እንዲያመች ለሁለት መከፈሉን ተናግረዋል፡፡  ከ35 ዓመት በፊት በአንድ ሰው፣በአንድ የስፌት መሳሪያና በ3 ሺህ ብር ካፒታል የተመሰረተው አምባሳደር ልብስ ስፌት፣አሁን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል መድረሱን የጠቀሱት የአምባሳደር ትሬዲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዛና ሺፈራው፤ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው በቀን 500 ሙሉ ልብስ እንደሚያመርት፣ ከምርት ጋር በቀጥታ የተገናኙ 350፣ ከሽያጭ ጋር የተያያዙ 400፣ በአጠቃላይ 750 ሰራተኞች እንዳሉትና ከ6 ወር በኋላ የሙከራ ምርት በሚጀምረው ፋብሪካ፣ ከምርት ጋር በተገናኘ ከ800 በላይ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ገልጸዋል፡፡  
የገላኑ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ከጀመረ አንድ ዓመት በኋላ በ2011 ዓ.ም ተጨማሪ ማስፋፊያ በመስራት ድርጅቱ በቀን የሚያመርተውን ሙሉ ልብስ ብዛት 2000 ለማድረስ መታቀዱንና ከድርጅቱ ሰራተኞች 80 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

Read 3930 times