Sunday, 25 June 2017 00:00

“ዘፈን በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ከተለቀቀ ያስከፍላል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 በ1996 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ የጋራ መብት አዋጅ በ2007 ዓ.ም እንደገና ተሻሽሎ ከወጣ በኋላ በተለያዩ የኪነ - ጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፤ መብቶቻቸውን ለማስከበር ማህበሩ የሚመሰረትበትን መተዳደሪያ ደንቦች ሲያረቁ፣ ሲያፈርሱና ሲከልሱ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ሂደትም ብዙ ውዝግቦች፣  ቅሬታዎችና ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ ከ12ቱ የኪነ-ጥበብ ማህበራት የ50 ዓመት እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር፤ የመተዳደርያ ፅሁፉን አብሮ ሲያረቅና ሀሳብ ሲያመነጭ ቢቆይም የማታ ማታ፣ “የተረቀቀው የማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ፣ መብት የሌላቸውን ባለመብት ያደርጋል” በሚል ራሱን ያገለለ ሲሆን 10 የኪነ-ጥበብ ዘርፎችን የጋራ መብት የሚያስተዳድረው “የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ የጋራ መብት አስተዳደር ማህበር” ባለፈው እሁድ በካፒታል ሆቴል ተመስርቷል፡፡ የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫም ተካሂዷል፡፡ በዚህም መሰረትም፤ የወቅቱ የደራሲያን
ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ የቦርዱ ሰብሳቢ፣ የህግ ባለሙያና ድምፃዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳ ም/ሰብሳቢ፤ የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ም/ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉና ደራሲ አበረ አዳሙ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ሆነው ሲመረጡ፤ ሌሎችም ከተለያዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች የሥራ አስፈፃሚ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በምርጫው ሂደት፣ እስከ ዛሬ በነበረው ውዝግብና ማህበሩ ሊሰራቸው ባቀዳቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች አንዱ ከሆነው አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች።

      ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ማህበሩ ተቋቁሟል፡፡ የምርጫው ሂደት እንዴት ነበር?
እውነት ነው፤ ብዙ ውጣ ውረዶች፣ብዙ ክርክሮች ተካሂደዋል፡፡ በዚህ ሂደት ግለሰቦች ለብዙኃኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ተያያዥ መብት ላላቸው አካላት መብትና ጥቅም መከበር ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በመጨረሻ ግልፅና ተዓማኒ ምርጫ ተካሂዶ፣ ብዙ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አንጋፋ የኪነ -ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከየክልሉ የመጡ ባለመብቶችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ማህበሩ ተመስርቶ፣ ተመራጮችም ኃላፊነት ተረክበዋል፡፡ ይሄ የብዙዎች ህልም ነበር፤ እውን ሆኗል፡፡
ግልፅ ምርጫ ተካሂዷል ስትል እንዴት ነው? ሂደቱን ልትገልጽልኝ ትችላለህ?
በጣም ግልፅና ተዓማኒ ምርጫ ነበር፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያት ምርጫው እዚያው ፊት ለፊት ነው የተካሄደው፤ ኮሮጆ የደበቀም በጓሮ ያዞረም የለም። ለምርጫው 26 ሰዎች ተጠቁመዋል። ምርጫው በስድስት ዘርፎች ነው የተካሄደው። ለምሳሌ ከሙዚቃና ከድምፅ ሪከርዲንግ 8 እጩዎች ቀርበው አራቱ አልፈዋል፣ከስነፅሁፍና ከህትመት ስድስት ቀርበው ሶስት ተመርጠዋል፣ ከኦዲዮ ቪዥዋልና ፊልም ዘርፍ (እኔ ያለሁበት ዘርፍ ማለት ነው) እንዲሁ 6 ቀርበው ሶስታችን አልፈናል። ከቴአትርና ድራማ ዘርፍ 4 ቀርበው ሁለት አልፈዋል። ይሄ የተካሄደው መተዳደሪያ ደንቡ በሚያዘው መሰረት በግልፅ ነው፡፡ ምርጫው በጣም ደስ የሚል፤ ጉርምርምታ የሌለበት ነው፡፡ እንደውም “የዚህ ማህበር የምርጫ ሂደት ብዙ ለምንታማበት አገር አቀፍ ምርጫ ትልቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው” ሲባል ነበር፡፡
በተለይ አንተ ያገኘኸው ከፍተኛ ውጤት አነጋጋሪ ሆኗል ሲባል ነበር፤ ለመሆኑ ስንት ድምፅ አገኘህ?
የእኔ ያልተጠበቀና የሚገርም ውጤት ነው፤ 302 ሰው ነው የመረጠኝ፡፡ ሁለተኛ ትልቅ ድምፅ ያገኘችው ፀደንያ ገ/ማርቆስ 129 ድምፅ ነው ያገኘችው፤ እና በጣም የሚገርም ነው፡፡
ይህንን ማህበር ለመመስረት በተደረገው ትግል ብዙ የለፉ፣ ህግና ደንብ ሲቀርጹ የነበሩ የአደራጅ ኮሚቴ አባላት ይመረጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ያልተመረጡ መኖራቸው ቅሬታ አላስነሳም?
እውነት ነው፤ ለዚህ ማህበር መመስረት ደም የሰጡ የአደራጅ ኮሚቴ አባላት አሉ፤ በምርጫው ተጠቁመው አልፈልግም ያሉም አሉ፡፡ ለምሳሌ ለዚህ ማህበር እውን መሆን ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ከነበሩት መካከል አንዱ ሀይላይ ታደሰ ሲሆን መመረጡን አልፈልግም፤ ልረፍ ብሎ ነው የቀረው፡፡ ነገር ግን ከአደራጅ ኮሚቴው ውስጥም ከባለመብቶችም ተጠቁመው፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውስጥ የተካተቱ አሉ፡፡
ማህበሩን ለመመስረት ብዙ ስምምነቶች ላይ ከተደረሰና መተዳደሪያ ደንቡ ከተቀረፀ በኋላ “ባለሙያ ያልሆኑ ግን የባለሙያውን ፈጠራ አትመው የሚሸጡ ነጋዴዎች ተካትተዋል፤ ይሄ ትክክል አይደለም” በሚል ውዝግብ ተነስቶ ነበር፡፡ ውዝግቡ በምን ተቋጭቶ ነው ማህበሩ የተመሰረተው?
ይሄ የግንዛቤ ማነስ ይመስለኛል፡፡ ወይም ደግሞ የማህበሩን መመስረት ዓላማ ካለማወቅ የመነጨ ይመስለኛል፤ ነጋዴዎች እስከዛሬ የተለያዩ የሌሎች የፈጠራ ስራዎችን ተጠቅመው ሳይከፍሉ ኖረዋል፤ በርካታ ፊልሞችን፣ በርካታ ሙዚቃዎችን፣ በርካታ የመፅሐፍ ትረካዎችንና ግጥሞችን ተጠቅመው አልከፈሉም፤ ነገር ግን በሌላ በኩል ባለመብትም ናቸው፡፡
እንዴት ባለመብት ይሆናሉ?
እየውልሽ፤ እነሱንም ባለመብት የሚያደርጋቸው የፈጠራ ስራዎች ያመርታሉ፡፡ ለምሳሌ ቴሌቪዥን ከዜናዎች ባለፈ፣ ባለ መብት ሆኖ ዘጋቢ ፊልሞችን ያመርታል፣ ፊቸር ፊልሞችን ሊያመርት ይችላል። ስለዚህ በመከወን፣ በመፍጠርና በማምረት ሌላው የጣቢያውን ስራዎች ሲጠቀም ተከፋይ ይሆናል፤ ተጠቃሚው ለዚህ ጣቢያ ከፋይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነጋዴ ባለግዴታም ባለመብትም ነው። ለምሳሌ ‹‹እንቁጣጣሽ›› የሚለው የዘሪቱን ዘፈን እንውሰድ፤ ሬዲዮው፣ ቴሌቪዥኑ፣ ማስታወቂያ አስነጋሪው ሳይቀር ዘፈኑን ይጠቀማል፤ እዚያ ውስጥ የድምፃዊቷ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲው፣ የሪከርዲንግ ባለቤትና የብዙዎች መብት አለ፤ እስከ ዛሬ እነዚህ ተገልጋዮች ለባለመብቶች ቢከፍሉ ባለሙያዎቹ በድህነት አይኖሩም ነበር፡፡ እንደዚህም ሆኖ ነጋዴዎቹም ጣቢያዎችም ከላይ በገለፅኩልሽ መልኩ ባለመብት የሚሆኑበት ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ ነጋዴ መሆናቸውና ማትረፋቸው ባለመብት አይደሉም አያስብልም፤ የግንዛቤ ማጣት ካልሆነ በስተቀር፡፡ የፈጠራ ባለሙያውም እኮ ስራውን ገዝቶ የሚያተርፍ ነጋዴ ከሌለ መኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን ነጋዴው አልበም ወይ መፅሀፍ ለማሳተምና ለመሸጥ ሲስማማ፣ በተስማማበት የጊዜ ገደብ መሆን አለበት፤ ዋናው ነገር ይሄ ነው፡፡ የፈጠራ ባለሙያው አንዴ ሸጦልኛልና እያባዛሁ እየሸጥኩ እኖራለሁ፤ የሚለው የእስከዛሬው ብሂል ግን አይሰራም፡፡ ለምሳሌ አንድን መፅሀፍ ለሁለተኛ ጊዜ ለማሳተም፣ ከፈጠራ ባለሙያው ጋር ሌላ አዲስ ውል መፈራረም አለበት አበቃ!
ህጉን በማርቀቅና ሀሳብ በማዋጣት አብሯችሁ የቆየው የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር “ሙዚቃ 24 ሰዓት በየትኛውም ቦታ የሚሰራበት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ራሱን ችሎ መመስረት አለበት፣ በኪነ ጥበቡ ብዙ የማይንቀሳቀሱ ስራዎች በሙዚቃው ገቢ ብቻ ይተዳደራሉ፤ስለዚህ አንድ ላይ መመስረት የለበትም” በሚል ራሱን ከማህበሩ የጋራ ምስረታ አግልሏል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው?
አሁንም ከግንዛቤ ማነስ የመጣ ነው ባይ ነኝ፤ ምክንያቱን ደግሞ ላስረዳሽ፡፡ ማህበሩ አንድ ላይ መመስረቱ በየትኛውም አለም የሚሰራበትና የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ማህበሩ አንድ ላይ ተመሰረተ ማለት ሙዚቃ በሚያስገኘው ገቢ ሰዓሊያን ወይም ደራሲያን ይጠቀማሉ ማለት አይደለም ወይም ፊልም ባመጣው ገቢ የቴአትር ባለሙያው ይጠቀማል ማለትም አይደለም፡፡ ማህበሩ በውስጡ የራሱ መዋቅሮችና አስተዳደር ክፍሎች አሉት፡፡
ለምሳሌ?
በጣም ጥሩ፡፡ በጋራ መብት አስተዳደሩ ውስጥ ወደ የሚጠጉ አስተዳደር ክፍሎች አሉ፡፡ አንደኛው፤ የሙዚቃ፣ የከዋኞችና የድምፅ ሪከርዲንግ ክፍል ነው፤ ከዚህ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ይመራል ይቆጣጠራል፡፡ ሌላው የስነ ፅሁፍና ተያያዥ ስራዎች አስተዳደር ክፍል ሲሆን የኦዲዮ ቪዥዋልና የፊልም ስራዎች አስተዳደር እንዲሁም የቴአትርና የድራማ ሰሪዎች አስተዳደር፣ የስነ ጥበብና የፎቶግራፊ ስራዎች አስተዳደር የተሰኘና የብሮድካስቲንግና የተያያዥ ስራዎች አስተዳደር የሚባሉ ከፍሎች አሉ፡፡ እነዚህ አስተዳደር ክፍሎች የየዘርፎቹን ስራዎች ይሰራሉ እንጂ የአንዱ ዘርፍ ከሌላው ዘርፍ ተደበላልቆ፣ የአንዱ ገቢ ሌላውን ተሸክሞ የሚሄድበት አንድም አሰራር የለም። ይሄን መጠየቅ መመካከር መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደውም አንድ አርቲስት ተናገረ በተባለው ነገር በጣም አዝኛለሁ፡፡ “ሙዚቃውን ከሌሎቹ ጋር አብሮ መመስረት፣ እግር ኳስንና ገበጣን እንደማወዳደር ነው” ነው ያለው፡፡ በመሰረቱ አንድን ሙያ ከሌላው ሙያ አኮስሶ ማየት ነውር ነው፡፡ የኪነ ጥበብ ሰው በመጀመሪያ ትሁት መሆንም አለበት። በዚህ ሰው አነጋገር ሙዚቃ ከስዕል፣ ከቴአትር፣ ከፊልም፣ ከግጥም ወይም ከሌላው የጥበብ ሰራ ይበልጣል ለማለት ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ለመሆኑ ሙዚቃ ከሌሎቹ ስራዎች ተነጥሎ ብቻውን ምንድን ነው፡፡ አንድን ሙዚቃ፣ ሙዚቃ የሚያስብለው ምንድን ነው? አንዱ ግጥም ነው፤ ግጥም የደራሲ (የገጣሚ) ስራ ነው፤ በመሳሪያ ይታጀባል ይቀናበራል፤ የከዋኝ ሰራ ነው፣ ቪዲዮ ክሊፕ ይሰራለታል፤ ይሄ ደግሞ የፊልምና የኦዲዮ ቪዥዋል ስራ ነው፤ ስለዚህ ሙዚቃ የሁሉም ኪነ ጥበቦች ውጤት ነው፡፡  
አንዱ ከአንዱ የተቆራኘ ነው፤ ሌላው ቀርቶ የሙዚቃ ቪዲዮ ሲሰራ ስክሪፕት ይፃፍለታል እኮ! ፊልምን ፊልም የሚያሰኘውስ ምንድን ነው? ድርሰት፣ ከዋኝ፣ ኦዲዮ ቪዥዋል፣ የማጀቢያ ሙዚቃና ስኮር-----ሌላም ሌላም ነገር አይደለም? ስለዚህ አንዱ ለአንዱ መቆም ዋስትና በሆነበት ኪነ-ጥበብ ውስጥ “ሙዚቃ ብዙ ገቢ አለው፤ ስነ-ፅሁፍ የለውም፤ በእኛ ገቢ ሌላው ተጠቃሚ ይሆናል” የሚል አስተሳሰብ ምንድን ነው? ይሄ በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡ ተመልከቺ፤ ፊልም ሳያሳይ የሚውልና የሚያድር፣ በየቤቱ ፊልም የማያይ ማን ነው? ብዙ ገቢ ያስገኛል እኮ፡፡ ጠቅለል ስናደርገው፣ የማንንም ድካም ማንም አይወስድም፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡
አሁን የተገነጠለው ቡድን ተመልሶ በዚህ ማህበር ውስጥ ልካተት ቢል የሚያግደው ነገር አለ?
በፍፁም! በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር፣ ለዚህ ማህበር መመስረት ከደከሙና ከለፉት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜም አብረውን ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም በጋራ መብት አስተዳደሩ ውስጥ የተካተቱ ብዙ ሙዚቀኞች አሉ፤ በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት የተመረጡም አሉ፡፡ አሁንም ቢሆን ማህበሩ የተቋቋመው ለኢትዮጵያ ባለመብቶች ነው። በዚህ ማህበር ውስጥ የፈጠራ ስራ ያለው ከዋኝ፣ ደራሲ፣ አሳታሚ፣ ሰዓሊ፣ ቀራፂ----ሁሉ ባለመብት ነው፤ ስለዚህ ማንኛውም የሙዚቀኞች ማህበር አባል ባለመብት ነው። ባለመብት የሚያደርጋቸው ሰው ሳይሆን ህጉ ነው፤ አዋጁ ነው መብት ለባለሙያዎች የሰጠው። እንደነገርኩሽ ሙዚቀኞች ማህበር፣ ለዚህ ማህበር መመስረት ከሌሎች የጥበብ ዘርፎች ጋር ላለፉት 20 ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አሁንም በህጉ መሰረት የሙዚቀኞች ማህበር መጥቶ መብቱን ማስበር ይችላል፡፡ ከምስረታው በፊት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ሚኒስትሮችና በርካታ ምሁራን በተገኙበት በተደረገው ውይይት፣ አደረጃጀቱንና ሙዚቃ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት እንዳለው ከተረዱ በኋላ ዳዊት ይፍሩም ሆነ ሰርፀፍሬ ስብሀት አብሮ መመስረቱ የተሻለ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ አሁንም እድሉ ክፍት ነው፡፡
የሙዚቀኞች ማህበርን ለማግባባት ሞክራችሁ ነበር?
ብዙ ተሞክሯል፡፡ አብረን እንሁን፤ የሚሻለው አንድ መሆናችን ነው ተብሎ ተጠይቀዋል፡፡ ቅድም እንደነገርኩሽ፣ የአንዳችን ሙያ ከሌላው የተሰናኘ ነው፡፡ ሆኖም እነሱ በእምቢታቸው ነው የቀጠሉት። አሁንም ግን አብረን መቀጠል እንችላለን፤ በህጉና በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ማለቴ ነው፡፡ እዚህም እዚያም የጋራ መብት አስተዳደር መመስረት ለአሰራርም አያመችም። በሮያሊቲ ክፍያ እያንዳንዱ እንደየስራው ጥቅም ያገኛል፤ ለየብቻ ከተበታተንን ምኑን የጋራ ተባለ?
ሌላው ሰው ብቻ ሳይሆን ራሱ ባለሙያውም በጋራ መብት አስተዳደርና በሮያሊታ ክፍያ ላይ ብዥታ አለው ይባላል፡፡ ይሔን ብዥታ ለማጥራት ምን አስባችኋል?
ሌላው ሰው ሳይሆን ከአንድ ሚሊዮን የማያንሰው ባለመብቱም በዚህ የሮያሊቲ ክፍያ መብቱን እንዴት ማስከበር እንዳለበት፣ የፈጠራ ባለሙያዎችን ስራ እንደፈለጉ የሚጠቀሙ ተቋማትም ያለባቸውን ግዴታ አያውቁም፡፡ ስለዚህ ይህን ለማሳወቅ ማህበሩ ብዙ ስራ ይጠብቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን 50ኛ ዓመት ሊከበር ሲል፣ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያው ትልቅ ኃላፊ ያለኝ ነገር በጣም አስቂኝ ነው፡፡ “እስከ ዛሬ ያለ ክፍያ 50 ዓመት የሌሎችን ፈጠራ ተጠቅማችኋል፤ እስኪ 50ኛ ዓመት በዓላችሁን ስታከብሩ በራሳችሁ ተነሳሽነት ሮያሊቲ ክፍያ ጀምሩ፤ ምክንያቱም ይህን የሚያስገድድ አዋጅ ወጥቷል” አልኩት፡፡ “ለምን?” አለኝ “ሙዚቃ ፊልም፣ ስታሳዩ ማለቴ ነው” ስለው “እንዴት እኛ እንከፍላለን፤ እንደተለመደው ለጣቢያው ነው መከፈል ያለበት፤ እኛ የእነሱን ስራ ለህዝብ ባስተዋወቅን እንዴት እንከፍላለን ነው” ያለኝ፡፡ ይሄ ከመግረም አልፎ ያስቃል፤ከአንድ ትልቅ ባለስልጣን ስለማይጠበቅ ማለቴ ነው፡፡ ይሄ ሰው እንዲህ ካሰበ፣ ሌላው ህዝብና ባለሙያው እንዴት ያውቃል? ስለዚህ ማህበሩ ዋናውና የመጀመሪያው ስራ፣ በህዝቡም ሆነ በባለሙያው ትልቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት ነው፡፡
ግን እኮ አንድን ስራ ለማስተዋወቅ የፈጠራ ባለሙያዎች ሙዚቀኞችን ብንወስድ የፕሮሞሽን መክፈላቸው ይቀራል?
ይሄ አይቻልም፤ የተቋቋመው ማህበር እንኳን የዚህን አገር የውጭውንም የሮያሊቲ ክፍያ ይሰበስባል። የትኛውም ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሙዚቃ በለቀቀ ቁጥር ይከፍላል፤ ውስጥ ለውስጥ የፕሮሞሽን ስራ ሊሰራ ይችላል፤ ዘፈን በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ከተለቀቀ ያስከፍላል፡፡ የውጭ ዘፈን ነው የማጫውተው አልከፍልም አይሰራም። እኛም ከዚህ ሰብስበን ለውጭው የጋራ መብት አስተዳደር እንልካለን፤እነሱም ለእኛ ይልካሉ አለቀ፡፡
በሌላው ዓለም ይሄ አሰራር በጣም የቆየ ነው፤ለምን እዚህ አገር ዘገየ?
አንደኛ አገሪቱ ህግ አልነበራትም፤ በ1996 ዓ.ም ህጉ ቢወጣም በ2007 እንደተሻሻለው የሚያሰራ አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ ሂደቱን ጀመርን፤ ይሄው ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ ተሳክቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህ ህልም እውን እንዲሆን ለለፉ አደራጅ ኮሚቴዎች፡- ሀይላይ ታደሰ፣ ፀደንያ ገ/ማርቆስ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ አበበ በየነ፣ ስዩም አያሌው፣ አክሊሉ አያሌውና ቴዎድሮስ ሞሲሳ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤትንና ሌሎች የተባበሩንን ሁሉ በማህበሩ ባለመብቶች ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

Read 2465 times