Print this page
Saturday, 24 June 2017 11:30

PMTCT ፕሮጀክት (2011-2015)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን (PMTCT) ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ለአምስት አመታት ያህል ከ2011-2015 ድረስ ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን ተጠናቆአል። ፕሮጀክቱ በስራ ላይ በነበረበት ወቅት ስራው በሚከናወንባቸው ስፍራዎች ሁሉ በመገኘት በስፍራው ያሉ ባለሙያዎችን እንዲ ሁም ተጠቃሚዎችን እያነጋገርን ለንባብ ማለታችን ይታወሳል። በዚህም መሰረት ባለፈው እትም (PMTCT) ፕሮጀክቱ በምን መልክ ተጠናቀቀ? ቀጣዮቹስ ሁኔታዎች ምን መልክ ይኖራቸዋል? በሚል የፕሮጀክቱን ዋና ተቆጣጠሪ የዶ/ር እያሱ መስፍንን ማብራሪያ እና የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ ምክንያት በማድረግ የወጣውን ሪፖርት በመጠኑ አስነብበናችሁዋል። ዶ/ር እያሱ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው።
ዶ/ር እያሱ መስፍን እንዳብራሩት የ(PMTCT) ፕሮጀክት ግብ የነበረው በብሔራዊ ደረጃ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይሰራጭ ለሚደረገው እንቅስቃሴ እገዛ ከማድረግ አኩዋያ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው እናቶችን እና ቤተሰባቸውን ተገቢ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነበር። የተጠቀሰው ግብ ተግባራዊ እንዲሆን የመከላከል እርምጃውን በስፋት ማዳረስና በተጠናከረና ቀጣይነት ባለው መንገድ የተቀናጀ የ(PMTCT) አገልግሎት በኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት በተመረጡ በግል የህክምና ተቋማት አገልግሎቱ እንዲዳረስ ማስቻል ሲሆን እነዚህን የግል የህክምና ተቋማት ኤችቸአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ በሚሰሩት ስራ ጠቃሚ መሆናቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ነው።
የ (PMTCT) ፕሮጀክት በአምስት አመት ቆይታው ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ በተቀናጀ እና ቀጣይነት ባለው መልክ በግል የህክምና ተቋማት አገልግሎቱ እንዲዳረስ ከማድ ረግም ባሻገር ለሁሉም እናቶች እና ቤተሰባቸው የኤችአይቪ ምርመራ እና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ በፕሮጀክቱ በተካተቱ የግል የህክምና ተቋማት ውስጥ ስራ ተሰርቶአል። እናቶች ጸረ ኤችአይቪ እንዲያገኙ ማድረግ እና ጨቅላዎቻቸውም ከቫይረሱ ነጻ የሚሆኑበትን መንገድ በመከተል ለእናቶቻቸው እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸው ክትትል እና የምክር አገልግሎት መስጠትም በፕሮጀክቱ የተካተተ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአጋር ድርጅቶች በሚገኘው ድጋፍ እየታገዘ ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲመክራሲያዊ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ለክልል የጤና ቢሮዎች ሙያዊ እገዛ ሲያደርግ ቆይቶአል። የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በጠቅላላው ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው መስተዳድሮች በሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ስራዎችን የመከታተል ግዴታውን ተወጥቶአል። በአመት ሁለት ጊዜ በሚደረገው የስራ ግምገማም የክልል ጤና ቢሮዎችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ባለፈው ምን ተሰራ?ጉድለቱ እና ጥንካሬው ምን ነበር? ወደፊትስ እንዴት እንቀጥል? የሚል ሁሉንም ያማከለ የምክክር ስብሰባ ያደርግ ነበር። በዚህም በስራ ከተሰማሩ ባለሙያዎች ትክክለኛውን አስተያየት እየተቀበለ ተገቢውን አሰራር ለመቀየስ ይጠቀምበት እንደነበርም ዶ/ር እያሱ መስፍን ገልጸዋል። ስራው ከሚሰራባቸወ ከተለያዩ መስተዳድሮች የግል የህክምና ተቋማት በሚገኙ ምላሾች በመመስረትም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፡-
ስራውን በሚመለከት የሚመለከታቸው አካላት የተጠናከረ ግንኙነትና በስራው መደማመጥ እንዲቻል እንዲሁም አንዳንድ አላስፈላጊ የሆኑ ድግግሞሽን ማስወገድና ፒኤምቲሲቲን በመተግበር ረገድ ጥሩው የሆነውን ተግባር ሌሎችም የግል የህክምና ተቋማት እንዲቀጥሉበት ማስቻል
ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ ጨቅላዎች የህክምና ክትትላቸው እንዳይቋረጥ እና በጊዜው ምርመራ እንዲያደርጉ ክትትል ማድረግ
ኤችአይቪ በደማቸው ያሉ እርጉዝ ሴቶች በተገቢው መንገድ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተደርጎአል። ፡
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የተሰራው ፕሮጀክት በአምስት አመት ቆይ ታው አብዛኛዎች በእቅድ የተያዙ ስራዎች ተከናውነዋል እንደ ፕሮጀክቱ ሪፖርት። ስራው የተከናወነባቸው አካባቢዎችም አዲስ አበባ፣ አማራ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ሕዝቦች፣ ድሬደዋ፣ ሃራሪ እና ሶማሊ ክልል ሲሆኑ በእነዚህ ስፍራዎች የሚገኙ 78 የግል የህክምና ተቋማት በፕሮጀክቱ ታቅ ፈው ሲሰሩ ቆይተዋል። የህክምና ተቋማቱም ጠቅላላ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒ ኮችና የእናቶችና የህጻናት ሆስፒታሎች ሲሆኑ ሁሉም የጽንስና ማህጸን ሕክምና የሚሰጡ ተቋማት ናቸው። ፕሮጀክቱ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ከሚያስችሉ ስራዎች ውስጥ ባለሙያዎችን ማሰልጠን አንዱ እቅዱ የነበረ ሲሆን በዚህም ፕሮጀክቱ ከሚከናወንባቸው የህክምና ተቋማት በድምሩ 982 የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ማግኘታቸውን ዶ/ር እያሱ መስፍን ገልጸዋል። ከሰለጠኑት ውስጥ ወደ 61% በመቶ የሚሆኑት ነርሶች ናቸው። የህክምና ባለሙያዎቹን ስልጠና በተመለከተ ግን ምንም እንኩዋን ወደ 47% የሚሆኑት የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ቢሆኑም ቁጥራቸው ከነርሶቹ አነስ ያለበት ምክንያት አብዛኞቹ ቀደምት ሐኪም በመሆናቸው ወይንም ቀደም ሲል እውቀቱን በተለያዩ ድርጅቶች አማካኝነት የጨበጡ በመሆናቸው ነው። ሆኖም ከ2 3ኛ በላይ የሚሆኑት የሰለጠኑ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ የግል የህክምና ተቋማት የተወከሉ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያትታል።
በ (PMTCT) ፕሮጀክት ቆይታ እንደታየው ከሆነ በፕሮጀክቱ በታቀፉት የግል የህክምና ተቋማት ክትትል ያደረጉና የኤችአይቪ ሁኔታን ያወቁ ደንበኞች በ2011 82.6% የነበሩ ሲሆን በ2015 ደግሞ 93.5% ናቸው። በአጠቃላይም ሲታይ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ በአማካይ የኤችአ ይቪ ምርመራ ያደረጉት አዲስ ታካሚዎች 88.4% ናቸው። ከዚህ እውነታ በመነሳት ሁኔታው ሲታይ የኤችአይቪ ቫይረስ በደም ውስጥ መኖር በ2011 2.6% የነበረ ሲሆን በ2015 ግን 1.8% ሆኖአል። በፕሮጀክቱ የአምስት አመት ቆይታ የኤችአይቪ ቫይረስ በደም ውስጥ መኖር ወደ 2.4% ነው። ባጠቃላይ ፕሮጀክቱ ይደግፋቸው በነበሩ የግል የህክምና ተቋማት 168346 እናቶች አዲስ የእርግዝና ክትትል በማድረግ ኤችአይቪ በደማቸው ይኑር አይኑር ለማወቅ ፈቃደኛ በመሆን ምርመራውን ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም 3/4ኛ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው ከዚህ ምርመራም 3965 እናቶች ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚኖር አረጋግጠው በክትትሉ ወቅት ከወሊድ በፊት አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት እና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጎአል።
(PMTCT) ማለትም ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ሲሰራ የቆየው ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በተሳካ ጎዳና ተጉዞአል ማለት አይቻልም እንደ ዶ/ር እያሱ መስፍን። አንዳንድ ችግሮች ማጋጠማቸው አልቀረም።
የመጀመሪያው የተጠናከረና የተሙዋላ አገልግሎት በመስጠቱ ረገድ የግል የህክምና ተቋማቱ ዝግጁነት ወይንም ልምድ ማነስ ነው።
በመቀጠል እንደ አንድ ችግር የተቆጠረው አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ የአደረጃጀትና ለምክር አገልግሎቱ በቂ ስፍራ አለመኖር እንዲሁም በቂ የሆነ የሰው ኃይል አለመኖር ነው።
ፕሮጀክቱ ለአምስት አመታት በቆየባቸው ጊዜያት አልፎ አልፎ ናሙና መውሰጃዎች ወይንም ለምርመራ የሚያገለግሉ የህክምና መገልገያዎች እጥረት እንደ አንድ ችግር የሚቆጠር ነበር።
ሌላው ችግር የትዳር አጋሮች (ባሎች) ሚስቶቻቸው የእርግዝና ክትትል ለማድረግ ወደሆስፒ ታል ሲሄዱ አብረው ለመገኘት አለመቻላቸው ነው። በተለይም እርጉዝዋ ሴት በደምዋ ውስጥ ቫይረሱ ሲገኝ ባለቤትዋ አብሮአት ወደሆስፒታል እንዲመጣ እንድታደርግ ሲነገር ብዙ ጊዜ ወንዶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ፈቃደኛ አይሆኑም። በእርግጥ በ(PMTCT) ፕሮጀክት የአምስት አመት ቆይታ ብዙ ወንዶች ፈቃደኛ ሆነው ከሚስቶቻቸው ጋር በሕክምና ተቋም ተገኝተው የምርመራ ውጤታቸውን በማወቃቸው ቤተሰባቸው ጥሩ ሕይወት እንዲኖረው እድል ፈጥሮ አል። እንደ ዶ/ር እያሱ መስፍን ማብራሪያ።
ይህ ፕሮጀክት ቢያበቃም እንኩዋን በቀጣይነት ስራው ሲሰራባቸው በነበሩ የግል ሕክምና ተቋማት እንደሚቀጥል እሙን ነው። ከዚህ ፕሮጀክት ወደ 179700 እናቶችና ቤተሰባቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሎአቸዋል ብለዋል ዶ/ር እያሱ መስፍን።

Read 946 times