Sunday, 02 July 2017 00:00

ዳያስፖራዎች ሀገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ወርሃዊ ወጪ የሚሸፍኑበት አሰራር ተጀመረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  ከ3 ሚ. በላይ ዳያስፖራዎች፣ በዓመት እስከ 3 ቢ. ዶላር ይልካሉ
                           
     ዳያስፖራዎች ሀገር ቤት ላሉ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ወርሃዊ የቤት ወጪዎች ክፍያን በቀጥታ የሚፈፅሙበት ስርአት መዘርጋቱ ተገለፀ፡፡
“ማስተር ካርድ” የተሰኘው አለማቀፍ የገንዘብ አዘዋዋሪ ድርጅትና “ክፍያ” በጋራ የጀመሩት አገልግሎት፤ የውሃ፣ የመብራትና የስልክ የመሳሰሉ ወጪዎችን ዳያስፖራዎች፣ ኮምፒውተራቸውንና ሞባይል ስልኮችን በመጠቀም ብቻ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሀገር ቤት ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እንዲከፍሉላቸው ያስችላል ተብሏል፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) መዘጋጀቱን ኩባንያዎቹ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ኩባንያዎች የጋራ ቅንጅት ይተገበራል የተባለው አዲስ አሰራር ለአፍሪካውያን የተዘጋጀ አገልግሎት መሆኑንና የሚጀመረውም በኢትዮጵያ እንደሆነ ታውቋል፡፡ “ክፍያ” የተሰኘው ኩባንያ ስርአቱን በኢትዮጵያ ለመጀመር እንዲያስችል በአሜሪካን ሀገር በሚኖሩ አፍሪካውያን ዳያስፖራዎች ላይ ባደረገው ጥናት፤ አፍሪካውያኑ ዳያስፖራዎች ሀገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ወርሃዊ የቤትና የማህበራዊ ተግዳሮት ወጪዎችን ለመጋራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ወጪን የመክፈል አገልግሎት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ሳይንገላቱ በዴቢት፣ በክሬዲት ካርድ እንዲሁም በመኒ ሞባይል በባንክ በኩል አገልግሎቱን በማግኘት ጭምር ከየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው በሀገር ቤት ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የቤት ወጪ እንዲሸፍኑ ያደርጋል፤ ይህ የሚሆነውም ማስተር ካርድ በሚዘረጋው ደህንነቱ የተረጋገጠ የመክፈያ መረብ አማካኝነት ነው ተብሏል፡፡
ለጊዜው በቤት ውስጥ ወጪዎች የተጀመረው የክፍያ አገልግሎት፤ በቀጣይ የመድህን ኢንሹራንስ፣ የትምህርትና የሆስፒታል ወጪዎችን እንዲሁም የዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪ አገልግሎቶችንም ለመክፈል እንደሚያስችል ታውቋል፡፡  በአሁን ወቅት ከ3 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገር እንደሚኖሩ ይገመታል ያለው የኩባንያዎቹ መግለጫ፤ አገሪቱ በዓመት በሐዋላ ብቻ ከ2 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከዳያስፖራዎች እንደምታገኝ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ ገቢ ውስጥ 2 ቢሊዮን ያህሉ ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከዳያስፖራ ዜጎቻቸው በዓመት 36 ቢሊዮን ዶላር የሚያገኙ ሲሆን ናይጄሪያ ቀዳሚ ገቢ ሰብሳቢ መሆኗንና የጠቆመው የዓለም ባንክ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በ2ኛነት እንደምትከተል ይገልፃል፡፡
ይህን አገልግሎት የጀመሩት “ክፍያ” በገንዘብ ክፍያ ዝውውር ጉዳይ ላይ የሚሰራ ኩባንያ ሲሆን “ማስተር ካርድ” የተሰኘው አለማቀፍ ኩባንያ ተመሳሳይ አገልግሎቶችን በ201 የዓለም ሀገራት እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡

Read 3181 times