Sunday, 02 July 2017 00:00

በፍ/ቤቶች የሀሰት ማስረጃዎችና ምስክሮች መበራከታቸው ተገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

      የመዝገቦች መጨመር ዳኞች ላይ ጫና ፈጥሯል
                      የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ችሎቶችን አጓታል
       የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ዳኜ መላኩ፤ ሰሞኑን የፌደራል ፍ/ቤቶች የ11 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡ ሲሆን የምክር ቤት አባላትም በዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት፣ ለደንበኞች በሚሰጥ አገልግሎት፣ በፍትህ መጓተትና በዳኞች ስነ ምግባር የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
በተለያዩ ንዑስ ርዕሶች ተከፋፍሎ ከቀረበው የአቶ ዳኜ መላኩ ሪፖርት መካከል የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት በተመለከተ የቀረበው ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ በርከት ያሉ ጥያቄዎችንም አስተናግዷል። ከህዝብ የተሰበሰቡ ናቸው ተብለው በአንድ የፓርላማ ተወካይ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከልም የዳኞች ነፃነትና ገለልተኛነት እንዲሁም ስነ ምግባር ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡
አቶ ዳኜ በሪፖታቸው የዳኝኘት አካሉን ነፃነት ለማረጋገጥ የበጀት ምንጩ እንዲቀየር ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ የፌደራል ፍ/ቤቶችን ተቋማዊ ነፃነት ለማረጋገጥ በጀት ከአስፈፃሚው አካል ሙሉ ለሙሉ ተላቆ፣ በቀጥታ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል እንዲፈቀድ የሚያስችል ጥያቄ መቅረቡን አውስተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይም ከሚመለከታቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚ/ር ኃላፊዎች ጋር ውይይት መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡
የዳኞችን ግለሰባዊ ነፃነት ለማስከበርም የተሽከርካሪ አቅርቦትን ለማሟላትና የመኖሪያ ቤት ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የዳኞች ገለልተኝነትን ለማስጠበቅ በፌደራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት. በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በዚህ ዓመት ከሁለት መቶ ያላነሱ ተደጋጋሚ የችሎት ቅኝቶች መደረጋቸውን፤ በ1 ሺህ 570 መዛግብት ላይም ምርመራ መካሄዱንና በገለልተኝነት የዳኝነት አገልግሎት አልሰጡም የተባሉ አካላትን ከስራ እስከማሰናበት የደረሱ የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውን አቶ ዳኜ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
ከተገልጋዮች በቀረቡ አቤቱታዎች መነሻም የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ፤ ለአንድ ዳኛ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን፣ አራት ዳኞችን በስነ ምግባር ጉድለት ማሰናበቱም ተመልክቷል፡፡ በዳኝነት ስራው ላይ በደል ላደረሱ 12 ዳኞች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱም ተጠቅሷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ጥያቄና አስተያየት የሰነዘሩት አንድ የህዝብ ተወካይ ም/ቤት አባል በበኩላቸው፤ አንድ ዳኝ የስነ ምግባርም ሆነ ሌሎች እንከኖች ሲገኙበት የመጨረሻው ቅጣት ከስራ መባረር መሆኑ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ ከዚህ ያለፈ ቅጣት ሊጣልበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ አንድ ዳኛ በፍትህ ላይ ባደረሰው በደልና ባዛባው ፍትህ ልክ ከስራ ከመሰናበት ባሻገር በህግ ሊጠየቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ሌላ የፓርላማ አባልም፣ ከአንድ ፍ/ቤት በህግ ጥሰት የተሰናበተ ዳኛ፤ በሌላ ፍ/ቤት የሚሰራበት ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ አሰራሩ ሊፈተሽ ይገባዋል ብለዋል፡፡
በጥያቄና አስተያየቶቹ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የጠ/ፍቤት ፕሬዚዳንት ዳኜ መላኩ በበኩላቸው፤ ዳኝነቱ ነፃ ሆኖ መስራት አለበት የሚለው መርህን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ጠቅሰው፣ ችግር ያለባቸው ዳኞች ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነ ዜጎችን የሚያጉላሉና የሚያንገላቱ ዳኞችም የዲሲፒሊን ቅጣት እየተጣለባቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ በአጠቃላይ ዳኝነቱ ሊመራበት የሚችል የዳኝነት ፖሊሲ ለመቅረፅ እቅድ መያዙን አስታውቀዋል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የፌ/ከ/ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት፤ ችግር ያለባቸውን ጥቂት ዳኞች በመለየት ወደ ተጠያቂነት ለማምጣት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የፍ/ቤቶች ሰራተኞችን ስነ ምግባር ለማረቅም ግድፈት በሚፈፅሙት ላይ ከደመወዝ ቅጣት ጀምሮ ከስራና ደመወዝ እስከማገድ የደረሱ እርምጃዎች መወሰዳቸው በሪፖርቱ ተወስቷል፡፡
ኢ-ስነ ምግባራዊ ድርጊቶች በፈፀሙ የፍ/ቤት ሰራተኞች ላይ ከዲሲፒሊን ቅጣቱ ጎን ለጎን በወንጀልም ክስ እየቀረበባቸው መሆኑ ተመልክቷል - በሪፖርቱ፡፡ ባለፉት 11 ወራትም የጠቅላይ ፍ/ቤት ሶስት የስራ ኃላፊዎች ከደረጃቸው ዝቅ መደረጋቸውንና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቡድን መሪ በፈፀሙት የወንጀል ድርጊት፣ በፌደራል ፖሊሲ ኮሚሽን የሙስና ክስ እንዲመሰረትባቸው መደረጉን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በበኩላቸው፤ በፍ/ቤቶች አካባቢ ይታያሉ ያሏቸውን ስነ ምግባር ጥሰቶች በመዘርዘር የተወሰደው እርምጃ በቂ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል።
ሌላው በሪፖርቱ ጎልቶ የታየው ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ በሶስቱ ፍ/ቤቶች ማለትም በፌ/ጠ/ፍ/ቤት 17ሺ 10፣ በፌ/ከ/ፍ/ቤት 22 ሺህ 527፣ በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት 144 ሺህ የክስ መዛግብት ሲታዩ የከረሙ ሲሆን ከነዚህ መዛግብት ውስጥ በአጠቃላይ 92 በመቶ ለሚሆኑት እልባት ተሰጥቷል ተብሏል፡፡ መዝገቦቹ ውሳኔ ያገኙት በ40 የጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኞች፣ በ87 የከፍተኛ ፍ/ቤት፣ በ148 የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ዳኞች መሆኑን በመጥቀስ የመዛግብቱ ብዛትና በጥቂት የሰው ኃይል የተሰጠውን እልባት በማገናዘብ አፈፃፀማችን መልካም ነው ብለዋል - የሶስቱም ፍ/ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፡፡
ፕሬዚዳንቶች ይህን ይበሉ እንጂ ከተወካዮች ም/ቤት አባላት አፈፃፀማችሁ የሚበረታታ ቢሆንም አሁንም ገና ይቀራችኋል? ለምን ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተሳናችሁ? የሚሉ ጥያቄዎች አስከትለዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያለውን አጠቃላይ ገፅታ በማስረዳት ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በአሁን ወቅት በቀን ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ የሚደርሱ ባለጉዳዮችን እያስተናገደ እንደሚገኝ በመጥቀስ፤ እነዚህን ሁሉ እያስተናገዱ ያሉት በፈረቃ የሚሰሩ 46 ችሎቶች ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከዛሬ 56 ዓመት በፊት በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የተገነባው የልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ 10 ችሎቶችን ብቻ እንዲያስተናግድ ተብሎ በወቅቱ መዋቀሩን ያስረዱት ኃላፊው፤ ቁጥሩ እየጨመረ በመጣው ተገልጋይ ልክ ለችሎት የሚሆኑ ህንፃዎችን መገንባት አለመቻሉ፣ በ46 ችሎቶች ደንበኞችን በፈረቃ ለማስተናገድ ማስገደዱን ተናግርል፡፡
ለ46 ችሎቶች 12 ፀሐፊዎች ብቻ መኖራቸውን በመጥቀስም የስራ ብዛትና የሰው ኃይሉ አለመጣጣሙ ለቀጣይ አገልግሎት ተግዳሮት እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲና በአራዳ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ህንፃዎችም ለችሎት አገልግሎት የሚመጥኑ አይደሉም ብለዋል፡፡ በተለይ የአራዳ ችሎት ማስቻያ መንገድ ዳር በመሆኑ፣ ለችሎት አገልግሎት ፈፅሞ የማይመች መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ለችሎት የሚሆን ህንፃ ተፈልጎ መታጣቱን፣ በቀጣይ በተገጣጣሚ ህንፃዎችን ለመገንባት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በ2009 አገልግሎት እንዲሰጡ ከተመደቡ 103 ዳኞች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች 20 ዳኞች በስራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው በዓመቱ ተይዞ የነበረውን እቅድ በ83 ዳኞች ብቻ ለመወጣት መገደዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ይህም በቀልጣፋ ፍትህ አሰጣጥ ላይ ተግዳሮት ሆኗል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የእሳት ቃጠሎ የችሎት ጉዳዮችን በ3 ወራት ያህል ማራዘሙ በኃላፊዎቹ ተጠቁሟል፡፡ በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋትም በፍ/ቤቶች ጉዳይ ላይ ተደማሪ ሆኗል፣ ምስክሮችን የመስሚያ ጊዜያትንም አጓቷል ተብሏል፡፡  ሌላው የፍትህ ሂደቶችን እያጓተተ፣ ተገልጋዮችን ለምሬት ዳርጓል ተብሎ የተጠቀሰው ምክንያት በችሎት የሚደረጉ ክርክሮች በድምፅ ከተቀረፁ በኋላ በሰው ኃይል ወደ ፅሁፍ ለመገልበጥ የሚወስደው ጊዜ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሄ በሚልም የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን ወደ ፅሁፍ ሊቀይር የሚችል ሶፍትዌር ለማዘጋጀት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተጠና ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ኮምፒውተር ላይ ንግግሮችን መፃፍ የሚችሉ ባለሙያዎችን በየችሎቱ ለማሰማራት እቅድ መያዙም ተጠቅሷል፡፡ ዳኞችም ከወረቀት ላይ ፅሁፍ ራሳቸው በኮምፒውተር ላይ እንዲተይቡ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከፍ/ቤቶች አገልግሎት ጋር በተገናኘ ከፓርላማ አባላቱ የተነሳው ሌላው ጥያቄ፤ የሽንት ቤቶች ችግር ሲሆን ለዚህ ችግር ሽንት ቤቶች ተገንብተው በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ውስጥ ከተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር ባልተናነሰ “የጠባብነት” እና “ትምክህተኝነት” ችግር መኖሩንም የፍ/ቤቱ ፕሬዚዳንት ጠቁመዋል አመራሩ ከእነዚህ ጋር እየታገለ መሆኑን በመግለፅ፡፡
በየዓመቱ በፍ/ቤቶች የሚቀርቡ የክስ መዝገቦች ፍሰት እየጨመረ መምጣት ባሉት ጥቂት ዳኞች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸውም ተመልክቷል - በሪፖርቱ፡፡ የክሶች መብዛትና የፍ/ቤቶች አገልግሎት አለመጣጣም በፍትህ አሰጣጡ ላይ ጫና አሳርፏል ተብሏል፡፡ ለዚህም ተጨማሪ ህንፃዎች ከማስፈለጋቸውም በላይ ተጨማሪ ዳኞች እንዲሾሙ ተጠይቋል፡፡
የሀሰተኛ ማስረጃና ምስክርነት በከፍተኛ መጠን በሀገሪቱ እየተስፋፋ መምጣቱም የፍትህ አሰጣጡን አስቸጋሪ እንዳደረገው የጠቀሱት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ በሀገሪቱ የህክምና ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሀሰተኛ ማስረጃዎችን መስጠታቸው ለፍትህ አሰጣጡ ፈተና ሆኗል ተብሏል፡፡ “የትምህርት ተቋማት፣ ቀበሌዎች፣ አዋዋዮች የሀሰት ማስረጃ እየሰጡ ነው፡፡ ሀሰተኛ ምስክሮችም ተበራክተዋል” ተብሏል፡፡
አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርአትን ለመዘርጋት ሲባል በሶስቱም ፍ/ቤቶች፣ ከፍ/ቤቶች ጋር የተያያዙ የማስማሚያ ፍ/ቤቶችን (Court Annexed Mediation) በመክፈት የአስማሚነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀት፣ በቀጣይ ዓመት ይመቻቻል ተብሏል - በሪፖርቱ፡፡  

Read 1340 times