Sunday, 02 July 2017 00:00

ኢትዮጵያና ውኃ

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

  የሰው ፍጥረቱ ከውኃ ጋር እጅግ የተቆራኘ ነው፡፡ ለነገሩ ሰው ብቻ ሳይሆን መላ ህይወት ያለው ፍጥረት ከውሃ ውጭ መኖር አይችልም፡፡ ከምድራችን ክፍል ውስጥም የላቀውን ድርሻ የሚይዘው ውሃ ነው እንጅ የብሱ ሲሶ ያህል ቢሆን ነው፡፡ ከውቅያኖሶች ላይ የነበረ ውሃ በሙቀት ኃይል ወደ እንፋሎት ተቀይሮ ወደ ሰማይ ያርጋል፤ ከውቅያኖስ እንደተካካደ ሁሉ ከሰማይም ይካካድና ዝናም ሆኖ ይዘንብብናል፤ ሰውና ውኃ እጅግ ይዋደዳሉና፡፡
ከፍጥረት ዓለም አስቀድሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በውሆች ላይ ሰፍሮ ነበር ይላል፤ ታላቁ መጽሐፍ። በኢትዮጵያውያን ጥንታዊ እውቀት መሰረት፤ የውኃ ፍጥረቱ እንደዚህ ነው። በሰኞ ዕለት ፍጥረታት፤ ውኃ ለአራት ክፍል ተከፈለ። አንዱን ክፍል ሰማይ አደረገው፤ ሁለተኛው ክፍል ሐኖስ ይባላል፣ ይኸውም ከጠፈር በላይ ነው፤ ሦስተኛው ውቅያኖስ ይባላል፤አራተኛው ክፍል ደግሞ ከምድር በታች ያለው ነው። ከሰው ልጅ አስቀድመው ከተፈጠሩት ውስጥ አንዱ ፍጡር ውሃ ነው፡፡ ግዙፍም ቀላልም ነው፤ ህይወትም ሞትም ይሆናል። በቀላሉ በእጃችን ስንይዘው፤ ያለ ቦቴ ተሽከርካሪ አጋዠነት ደግሞ መያዝ የማንችልበት መጠን አለው። በብርጭቆ በጥቂቱ እየጠጣን ህይወታችንን ማደስ ስንችል፤ የሞላ የወንዝ ውሃ እያዳፋና እያላጋ ሊገድለን ይችላል፡፡ ፈጣሪ መፍጠር በጀመረበት በሁለተኛው ቀን የተፈጠረው ውሃ፤ እንዲህ አግራሞት የሚጭር ፍጡር ነው፡፡
ሰው በሥጋውና በነፍሱ ሰባት ባህሪያት አሉት /‹ሰብ› ተብሎ የተሰየመው ሰባቱን ባህሪያት ለማስታወስ ነው ይላሉ ሊቃውንቱ/፤ በሥጋው አራት፣ በነፍሱ ደግሞ ሦስት። ውኃ፣ ነፋስ፣ እሳትና መሬት የሥጋ ባህሪያት ሲሆኑ፤ መናገር፣ ማሰብና ህያውነት ደግሞ የነፍስ ባህሪያት ናቸው። ውኃም የራሱ ሦስት ባህሪያት አሉት፤ እርጥብነት፣ ግዙፍነትና ብርሃናዊነት። ሰውን ከውኃ ለየነው ማለት ሦስቱን የውኃ ባህሪያት ያልናቸውን እርጥብነትን፣ ግዙፍነትንና ብርሃናዊነትን ማሳጣት ማለት ነው። ሰው ያለ ውኃ እርጥብነት ደርቆ የቆመ፣ ቁርበት የለበሰ አጥንት ማለት ነው፤ ያለ ውኃ ብርሃናዊነት የቆዳ ጸዳልና ፍካት ከቶ አይገኝም፤ያለ ውኃ ግዙፍነት ደግሞ አካሉ መንምኖ ገለባ ይሆናል  /ከሰውነታችን ክብደት ስልሳ በመቶው ውኃ እንደ ሆነ ሳይንሳችንም ይነግረናል/።
አሁን አሁን የሚመጡ የሳይንስ ግኝቶች ደግሞ ውሃ ይሰማል ይላሉ፤ እነ ኳንተም ሳይንስ በዚህ ረገድ አዳዲስ ፍልስፍናዎችን ይዘውልን ብቅ እያሉ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ቃላት ጋር የውኃ ሞለኪሎች ቅርጻቸውን ሲቀያይሩ በማይክሮስኮፕ ፎቶግራፍ ተነስተዋል፡፡ ስለ ፍቅር ሲወራ አንድ አይነት ቅርጽ ይዘው የነበሩ የውኃ ሞለኪውሎች፤ ስለ ጥላቻ ሲወራ ደግሞ ሌላ አይነት ቅርጽ ሲይዙ ታይተዋል፡፡ ለነገሩ የኛም አባቶች ውሃ እንደሚሰማ ስለሚያውቁ ይፀልዩበትና ኳንተም ሳይሆን ፀበል ብለው ይረጩናል፡፡ ‹‹ከውሃ ዳግም ካልተወለዳችሁ የዘላለም ህይወትን አታገኙም›› እንዲል ታላቁ መምህር፡፡
‹‹ማዬ ገቦ›› ይሉታል ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን የተገኘውን ውኃ፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ዓለምን ለማዳን ተላልፎ የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በመስቀል ተሰቅሎ ሳለ፣ ሌንጊኖስ የተባለ ወዳጁ ስቃዩንና ስቅለቱን ላለማየት ከከተማ ሸሽቶ ከዋለ በኋላ፤ አይሁድ እንዳይቆጡ አመሻሽ ላይ ወደ ቀራንዮ በመመለስ ‹ይህ ወንበዴ ተሰቀለ አይደል› ብሎ በፈረስ ላይ ሆኖ የክርስቶስን ግራ ጎን በጦር ወጋው፤ የዚያን ጊዜ በ‹ለ› ቅርጽ ከጎኑ ደምና ውኃ ተቀላቅሎ ፈሰሰ፤ ትንሽዬ ፍንጣቂ ፊቱ ላይ ጠብ አለችበትና የሌንጊኖስ አንድ ዓይናነት ታሪክ ሆኖ ባለሁለት ዓይን ሆነ፡፡ ይህ ውኃ  ነው ዛሬ እኛ የቅዳሴ ጸበል እያልን ዳግም ከውኃ ለመወለድ የምንጠጣው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ በመላው ኢትዮጵያ ይህ ማዬ ገቦ በደጋውም፣ በቆላውም ያለማቋረጥ ይፈሳል፡፡ ሰውና ውኃ እንዲህ ይዋደዳሉ፡፡
ኢትዮጵያችን በተከዜ፣ በዓባይ፣ በአዋሽ፣ በዋቢ ሸበሌ፣ በባሮ፣ በፊንጫና ዠማ ወንዞቿ የከበረች የታፈረች ‹‹የውኃ ማማ›› ተብላ የምትቆላመጥ ናት፡፡ ከፍጥረታት ሚስጥርና ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር እጅግ መቆራኘቷን በወንዞቿና በከርሰ ምድር ውኃዎቿ ብዛት መረጃነት መመስከር እንችላለን፡፡ የፍጥረት እንቆቅልሽ መፍቻ የሆነችው ሃገራችን የፈጣሪ ሚስጢራት ማከማቻ ውድ ግምጃ ቤት ናት፡፡ ኢትዮጵያና ውኃ እንዲህ ይዋደዳሉ፡፡ ሰውና ውኃም እጅግ እንደሚዋደዱ ከኢትዮጵያችን በላይ ማስረጃ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የሰው ልጅ ውኃን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ፥ በባህር ዳርቻዎች መዝናናትን ያዘወትራል፤ ባህር ባጠገቡ ቢያጣ እንኳ የቧንቧ ፏፏቴ ሰርቶ ዳርዳሩን ይኮለኮላል፡፡
ከፍጥረት አስቀድሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍሮ ነበር ተብለናል፤ እና እኛ እንዴት እንደ ተፈጠርን ምስክር ሊሆን የሚችል ንጥረ ነገር ነው ውኃ፡፡ ግዮን ወንዛችንን በዚህ መነጽር ነው ማየት ያለብን፤ ከዘፍጥረት ጀምሮ ምስክርና ቅርስ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ የኢትዮጵያ የጥንት ግዛቷ እስከ ታንዛኒያ ነበር፤ ግብፆችንም አስገብረዋል ሲባል እውነት መሆኑን ምስክር የሚሆነን የዓባይና የዓባይ ተፋሰስ መልክአምድር ነው፡፡ የዓባይ ተፋሰስ ሃገራትን እርስ በርስ የሚያስተሳስርና የሚያቀራርብ በጣም ብዙ ባህላዊና የቋንቋ መመሳሰሎችን እናይባቸዋለን፡፡ የመልክአምድራዊ ገጽታቸውም የሚያቀራርብ እንጂ የሚያለያይ ገጽታ የለውም፤ ታሪካቸውም እርስ በርስ የተሳሰሩ የነበሩና ጥንታዊያን መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚመሰክር ነው፡፡ /አስተዋይ ልቦና ከተገኘ፥ የዓባይ ተፋሰስ ሃገራት ወደ አንድነት ማምጣት ይቻላል፡፡/
የውኃዋ እመቤት ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ፤ የስጋዋንና የነፍሷን ቅራኔዎች ለማስታረቅ ሱባየ የገባችው ውኃ ውስጥ ነበር፤ ያውም ዓባይና ጣና በሚቀላቀሉበት ውኃ፡፡ ሰውነቷ ተበጣጥሶ ዓሳዎች በሰውነቷ ውስጥ ይመላለሱ ነበር ይሉናል አባቶቻችን፡፡ እርሷም፣ዓሳውም፣ ውኃውም የአንድ ፈጣሪ ፍጡሮች ናቸውና ለአንድዬ ምን ይሳነዋል ብለን እንቀበለዋለን፡፡ በኢትዮጵያችን ሰው ከውኃ በእንደዚህ ያለ አኗኗርም ይተዋወቃሉ፡፡ የአባታችን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገድልም ይህንንኑ ትረካችንን የሚያዳብር የዝቋላ ተራራ ላይ የእሳተ ጎመራ ሐይቅ መረጃ ነው፡፡
‹‹ዓባይ አረጀ አሉ ሽበት ቀላቀለ፤ አንድ ሰው ብቻውን ይሻገር ጀመረ›› ይላል ያገሬ ሰው፤ መተርጎም፣ መተንተን፣ ማብራራት ጭንቅ ሆኖ ሃቅ ደግሞ ምርግት ሆኖ ሲተናነቀው። ዓባይ ሽበት እንደ ሰው አያበቅልም፤ አንድ ሰው ብቻውንም ሊሻገረው አይችልም፤ ታዲያ እንዲህ ያለ ማጣፊያው የሚሳጥር ነገር ሲገጥመው፥ ያገሬ ሰው ይኼው ነው እንጉርጉሮው፡፡
ጀምስ ብሩስ በዘመኑ ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ያስገደደው አንዱ ምክንያት የግዮን ምስጢራዊነት ነው። ምንም እንኳን አባቶቻችን ቀለብ ሰፍረው መንገድ መሪ መድበው እግዮን ምንጭ ድረስ ወስደው ቢያስጎበኙትም እኛ ልጆቻቸው ግን የግዮንን ምንጭ ያገኘው ጀምስ ብሩስ ይባላል እየተባልን ተማርን። ግዮን ከዕጸ ህይወት ሥር መመንጨቱ በእውነተኛው በዘላለማዊው ዓለመ ህላዌ የመኖሩ ምስክርነት የምንረዳው መጽሐፍ ቅዱሳችን የገነትን ደጆች ከሚያጠጡ አራት ወንዞች መካከል አንዱ የተጠቀሰው ግዮን በመሆኑ ነው። ዕጸ ህይወት ፍሬዋን የበላን እንደሆን ሞትን ድል አድርገን ለዘላለም መኖር የምታስችለን ዛፍ ናት። እንዳለመታደል ሆኖ ሳይሆን ቀረ እንጅ ቀዳማዊ አዳም በገነት ውስጥ ትዕዛዝ ጠብቆ ሳይስት ለአንድ ሺህ አመት ቢኖር ኖሮ፣ ከዕጸ ህይወት ፍሬ ተመግቦ ዘላለማዊ አዲስ ህይወት እንዲመራ ይፈቀድለት ነበር። /ኢትዮጵያ ናት ግዮን ወይስ ግዮን ነው ኢትዮጵያ?/
ግዮን ብንጠጣው የሚያድሰን፣ ብንታጠብበት የሚፈውሰን የዘላለማዊነታችን ወንዝ ነው የምንለው፥ ከዕጸ ህይወት ሥር በመመንጨቱ ነው። እንግዲህ እኛ ኢትዮጵያዊያንን፥ ፈጣሪ ሲፈጥረን፥ ከግዮን ጨልፎ በወሰደው ውኃ ስለሆነ፥ ግዮንንና ኢትዮጵያዊን መለያየት ከፍጥረት ህግ በተቃራኒው እንደ መሆን ነው።
ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ከሞት በኋላ ህይወት ስለ መኖሩም ጥሩ መረጃ የሚሆነን ይኸው ግዮን ነው፤ ምነው ቢሉ የገነት ደጆች ያጠጣሉ ከተባሉት አራት አፍላጋት ውስጥ አንዱ የእኛው ግዮን ነውና። ለግብጻዊያን አባይ ህይወት ሊሆን ይችላል፤ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ግን የሰብዕናችን፣ የኅላዌነታችን፣ የደምና የወዛችን፣ ከሞት በኋላ ላለንም ህይወት ምስክራችን ነው ግዮን፡፡

Read 3684 times