Sunday, 02 July 2017 00:00

የመንግስት የውጭ እዳ፣ 23 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(18 votes)

      “ለሚባክነው የድሃ አገር ሃብት፣ ተጠያቂው ማን ነው?” – (የፓርላማ ጥያቄ)
                        “የሚጠየቅ በሙሉ ይጠየቅ። እኔም ልጠየቅ!” (የብረታብረት ኮርፖሬሽን ዋና ሃላፊ)
                            
 • 12 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ የታቀደ ኤክስፖርት
- ከ3 ቢሊዮን ዶላር በታች እየወረደ ነው!
• በዓመት ለወለድ ክፍያ ብቻ፣ 400 ሚሊዮን
ዶላር እየተከፈለ ነው።
ብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት ባክኗል፤ ለዚያውም በብድር
የመጣ ሃብት! ለመሆኑ...
የመንግስት የውጭ ብድር ሸክም፣ ስንት እጥፍ
ጨመረ?
በ2000 ዓ.ም 2.8 ቢሊዮን ዶላር
በ2005 ዓ.ም 11.2 ቢሊዮን ዶላር
በ2009 ዓ.ም 23 ቢሊዮን ዶላር
የውጭ እዳ ለመክፈል የሚውል የውጭ ምንዛሬ -
በዓመት
በ2000 ዓ.ም 89 ሚሊዮን ዶላር
በ2005 ዓ.ም 567 ሚሊዮን ዶላር
በ2009 ዓ.ም 1.2 ቢሊዮን ዶላር
ለወለድ ክፍያ ብቻ የዓመት ክፍያ የት ደረሷል?
በ2000 ዓ.ም 30 ሚሊዮን ዶላር
በ2005 ዓ.ም 140 ሚሊዮን ዶላር
በ2009 ዓ.ም 410 ሚሊዮን ዶላር   

       • የዶላር እዳ የተቆለለበት ሰው ምን ያደርጋል? ከመንግስት በምን ይለያል?
መግቢያ መውጪያ ያጣ ባለእዳ፣ ብር እያተመ፣ ከዚያም ባሰኘው የምንዛሬ ተመን ወደ ዶላር እየቀየረ እዳውን ለመክፈል ይመኝ ይሆናል። አቋራጭ ማምለጫ መንገድ መሆኑ ነው! ነገር ግን፣ “የወንጀል ጥፋት” አልያም “ከንቱ ምኞት” ይሆንበታል።
ለመንግስት ግን፣ አቋራጭ ማምለጫ መንገድ ማለት፣ ‘ወንጀል’ አይደለም። ‘ምኞት’ ብቻም አይሆንበትም። በተግባር ሊፈፅመው ይችላል።...  በእርግጥ፣... ማምለጫ አቋራጭ መንገድ... ውሎ አድሮ፣ “ከጥፋትና ከከንቱ” ትርምስ ያለፈ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል። ቢሆንም... ለጊዜው...  
መንግስት፣ የብር ኖት ማሳተም ይችላል። እንዲያውም፣ ብር የማሳተም ስልጣኑ፣ የሕግ ገደብ አልተበጀለትም። በቃ! እንዳሻው፣ ብር አሳትሞ እያመጣ፣ ወደ ዶላር መመንዘርና የውጭ እዳዎቹን መክፈል ይችላል። ያሰኘውን ያህል ይችላል? ለተወሰነ ጊዜ፤ አዎ የሚችል ይመስላል፤ ይመስለዋል። ግን፣ ለረዥም ጊዜ ሊቀጥል አይችልም።
ለምን? ከእውነታ ጋር የሚያጋጭ፣ አቋራጭ ማምለጫ መንገድ፣ መጨረሻው አያምርም። ብር የማሳተም የመንግስት ስልጣን፣ እስካሁን ሕጋዊ ገደብ ባይበጅለትም፣ ተፈጥሯአዊ ገደብ አለው። በሌላ አነጋገር፣...  የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ውሎ አድሮ፣ ወደ ጥፋት ያመራል። እንዴት?
ያለቅጥ ብር ሲታተም፣ ብር ይረክሳል። ብር ረከሰ ማለት ደግሞ፣ ሌላ ትርጉም የለውም፤ የሸቀጦች ዋጋ ይንራል ማለት ነው። የዚህ ተግባር መዘዞች፣ ቀላል አይደሉም።
በአንድ በኩል፣ ገበያ እየታመሰ፣ የዜጎች ኑሮ ሲናጋ፣ አገሬው በሙሉ ለአደገኛ ትርምስ ይጋለጣል። ይሄ መንግስትንም ሆነ ማንኛውንም ዜጋ ሊያሳስብ የሚገባ፣ ትልቁ ተፈጥሯዊ እውነታ ነው። በሌላ በኩል፣ ብር ረክሶ፣ የሸቀጥ ዋጋ ሲወደድ፤... ያው፤ የዶላር ምንዛሬም ይወደዳል። ይሄም ሌላኛው ለመንግስት የማይጥም እውነታ ነው። ብር ባሳተመ ቁጥር፣ ብር እየረከሰ፣ እንደ ሸቀጦች ዋጋ የዶላር ምንዛሬም ስለሚወደድ፣ መንግስት የአንድ ዶላር እዳ ለመክፈል፣ ብዙ ብር ማውጣት ግድ ይሆንበታል።
ግን፣ ይህንንስ እውነታ ሸውዶ ማለፍ... የዶላር ምንዛሬን እንዳሻው መቆጣጠር አይችልም? ለተወሰነ ጊዜ የሚችል ይመስለናል፣ ይመስለዋል። በእርግጥም፣ የሸቀጦችን ዋጋ መቆጣጠር፣... የመሸጫ ዋጋዎችን በአዋጅ መተመን... ይቻላል። ለአጭር ጊዜም ቢሆን፣ ውጤታማ ሊመስል ይችላል። ግን፣ የዋጋ ቁጥጥር እንደማያዋጣ፣ በተደጋጋሚ አይተነዋል። ብዙም ሳይቆይ፣ የሸቀጦች እጥረት ይፈጠራል። አዳሜ ሲጨንቀው፣ መውጪያ መግቢያ ቀዳዳ መፈለግ ይጀምራል። የጉራንጉር ገበያዎችና የኮንትሮባንድ ንግዶች እየተበራከቱና እየተጠላለፉ፣ አገርን እያባከኑ፣ የዜጎችን ኑሮ ወደሚያዳክሙበት የቁልቁለት ጎዳና ገባን ማለት ነው። ሌሎች አማራጮች፣ በዋጋ ቁጥጥርና በተመን አዋጅ ስለተዘጉ፣ የቁልቁለት ጎዳና ውስጥ የምንገባው። እውነታው ይሄው ነው። የዋጋ ቁጥጥሮች ለረዥም ጊዜ፣ በጤና ሊቀጥሉ አይችሉም።
“ግንኮ፣ የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር፣ ይሄውና ለስንትና ለስንት አመት ሳይቋረጥ ቀጥሏል” ልንል እንችላለን። በእርግጥም፣ መንግስት የውጭ ምንዛሬን እንዳሰኘው የመቆጣጠርና የመወሰን ስልጣን አለው - ለዚያውም ሕጋዊ ገደብ ያልተበጀለት ስልጣን። ግን፣ ያሰኘውን ያህል መቆጣጠርና ከመዘዞች ማምለጥ ይችላል?
• የውጭ ምንዛሬ ቀውስ - ወደ ኤክስፖርት ድንዛዜ
የዛሬውን የዶላር ምንዛሬ ቀውስ፣ በ2002 ዓም ግድም ከነበረው የምንዛሬ ቀውስ ጋር በማነፃፀር እንጀምር።
መቼም የምትረሱት አይመስለኝም። በሚሌኒየሙ መባቻና ማግስት ላይ ነበር፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው የዋጋ ንረት የተፈጠረው። ያው ከፍተኛ የብር ህትመትን ተከትሎ የመጣ አይቀሬ ክስተት ነው። እንደተለመደው፣ የዋጋ ቁጥጥርና ተመን ታወጀ። ነጋዴዎችን የማውገዝና የማሳደድ ዘመቻ ተካሄደ። ግን ውጤት አላስገኘም።
ቀድሞውኑ፣ “የብር ኖት አለቅጥ ከማሳተም መቆጠብ” እንጂ፣ በገፍ እየታተመ ብር ከረከሰ በኋላ፣ የሸቀጥ ዋጋ እንዳይንር መከልከል፣ በአዋጅ መቆጣጠር፣... አያዛልቅም። እናም፣ አይቀሬው መዘዝ መጣ - የሸቀጦች ዋጋ ናረ፤ በሚያስደነግጥ ሁኔታ። መንግስት፣ ለመሰንበቻው ካልሆነ በቀር፣ ለዘለቄታው ሊቆጣጠረው እንደማይችልም በግልፅ ታየ።
ግን “የዶላር ምንዛሬን መቆጣጠር ችሏልኮ” ቢባልስ?
አዎ፣... ለተወሰነ ጊዜ፣ የዶላር ምንዛሬን መቆጣጣርና ደፍጥጦ ማቆየት የቻለ ይመስላል። ለዚያውም በጣም ደፍጥጦ ነበር የያዘው።
“ብር ከረከሰ በኋላ፣ የዶላር ምንዛሬን ደፍጥጦ መያዝ፣ ለዘለቄታው አይጠቅምም” በማለት ምክራቸውን የሰነዘሩ የአለም ባንክ እና የአለም ገንዘብ ድርጅት ሰዎች፤ የዶላር ምንዛሬ በገበያ የሚወሰን ቢሆን ኖሮ፣ ወደ 18 ብር ገደማ ይሆን እንደነበር በወቅቱ እየገለፁ ነበር። መንግስት፣ የዶላር ምንዛሬን ወደ ገበያ ዋጋ ቢያስተካክል እንደሚሻለውም እየመከሩት ነበር። መንግስት ግን፣ ሳያስተካክል ለመቀጠል ሞከረ። በርካታ ወራት አለፉ። ከዓመት በኋላም ምንዛሬው አልተስተካከለም። [ግን፣ በዚህ መዘዙ፣ ኤክስፖርት ተዳከመ ነበር። እያደገ የቆየው የኤክስፖርት ንግድ፣ በ2001 ዓ.ም ባለበት ቆመ!]። የዶላር ምንዛሬ እንደተፈጠጠ ቆየ።
መስከረም 2002፣ የዶላር ምንዛሬ 12.5 ብር ነበር።
ከዚያ በኋላስ? [የዶላር ምንዛሬን ደፍጥጦ መያዝ፣ ኤክስፖርትን እንደሚያደነዝዝ በግልፅ መታየት ሲጀምር፣ መንግስትን ያሳሰበው ይመስላል]።
ጥር 2002 ዓ.ም ላይ፣ የዶላር ምንዛሬ 13.3 ብር እንዲሆን ተወሰነ።
ግን ይህም በቂ አልሆነም። ብር በጣም ረክሷላ - በብር ህትመት ሳቢያ። እናም፣ ከመንፈቅ በኋላ እንደገና የዶላር ምንዛሬ ማስተካከያ መጣ።...
መስከረም 2003፣ የዶላር ምንዛሬ 16.4 ብር እንዲሆን ተደረገ።
በሌላ አነጋገር፣ በዓመት ውስጥ፣ በ30% ማስተካከያ፣ የዶላር ምንዛሬ ከገበያ ዋጋ ጋር ተቀራረበ።
ተደፍጥጦ የቆየው ዶላር ዋጋ፣ እዚያው ተደፍጥጦ እንዲቆይ ማድረግ አያዛልቅም። ትርፉ፣ ከንቱ ልፋትና ጥፋት ነው።
እና፣ በዚያን ጊዜ፣ የ1 ዶላር ምንዛሬ፣  ከ12.5 ብር ወደ 16.4 ብር መስተካከሉ ተገቢ ነበር?
የዚህን ትርጉም፣ ከመንግስት የውጭ እዳ እና ከኤክስፖርት ጋር አያይዘን፣ የቡና ወይም የወርቅ አምራቾችንም በምሳሌነት እየጠቀስን እንመልከት።
• በዶላር ምንዛሬ ቁጥጥር - የቢሊዮን ብሮች ኪሳራ!
በ2002 ዓም፣ መንግስት የውጭ እዳዎቹን ለማቃለል፣ 110 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል። ዶላሩን ከየት ያገኛል። ሁነኛው ምንጭ፣ ከኤክስፖርት የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ አይደል? እናም፣ መንግስት፣ ከኤክስፖርተሮች 110 ሚሊዮን ዶላር ወስዶ የውጭ እዳውን ይከፍላል።
መንግስት፣ ከኤክስፖርተሮች ዶላር የሚወስድባቸውም፣ በ12.5 ብር የምንዛሬ ሂሳብ፣ 1400 ሚሊዮን ብር ብቻ በመክፈል ነበር።
በ2002 ዓም፣ የዶላር ምንዛሬ ቢስተካከል ኖሮስ?
መንግስት፣ 110 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት፣ ለኤክስፖርተሮች፣ በ16.4 ብር የምንዛሬ ሂሳብ፣ 1800 ሚሊዮን ብር መክፈል ይኖርበት ነበር።
በሌላ አነጋገር፣ የዶላር ምንዛሬን እንዳሰኘው መቆጣጠርና ደፍጥጦ ማቆየት ስለሚችል፤ ወጪውን በ400 ሚሊዮን ብር ቀነሷል ማለት ይቻላል (ከ1800 ሚሊዮን ብር ወደ 1400 ሚሊዮን ብር)። ግን፣ በዚያው ልክ፣ የወርቅ፣ የቡና፣ የሰሊጥ አምራቾችና ኤክስፖርተሮች ይከስራሉ።
የወርቅ ኤክስፖርትን ተመልከቱ። 890 ኩንታል ወርቅ ኤክስፖርት በተደረገበት በዚያው ዓመት፣ የወርቅ አምራቾችና ላኪዎች፣ ለአንድ ግራም በ31.57 ዶላር ሂሳብ፣ 280 ሚሊዮን ዶላር አግኝተዋል። ዶላሩን ለመንግስት ማስረከብ ግዴታ ሲሆንባቸው ነው፣ ችግር የሚፈጠረው።
መንግስት 280 ሚሊዮን ዶላሩን ወስዶ፣ በ12.5 ብር መንዝሮ ሲሰጣቸው፤ 3.5 ቢሊዮን ብር ይደርሳቸዋል።
የዶላር ምንዛሬ ቢስተካከል ደግሞ፣ 16.4 ብር መንዝሮ ሲሰጣቸው፣ 4.6 ቢሊዮን ብር ይደርሳቸዋል።
የአንድ ቢሊዮን ብር ልዩነት አለው። የዶላር ምንዛሬ በቁጥጥር ተደፍጥጦ መቆየቱና እንዲስተካከል መፈቀዱ፣ ለወርቅ አምራቾችና ኤክስፖርተሮች፣ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው አያችሁ? ማግኘት ከሚገባቸው ገቢ ውስጥ ሲሶ ያህሉን የማጣት ጉዳይ ነው ትርጉሙ (ከ30% በላይ)።
የዚህን ያህል ገቢ፣ በምንዛሬ ቁጥጥር አማካኝነት የሚነጠቅ አምራቾችና ኤክስፖርተሮች፣ ቀስ በቀስ ቢዳከሙና በምትካቸው ቀስ በቀስ የኮንትሮባንድ ግብይቶች ቢበራከቱ ምን ይገርማል?
የዶላር ምንዛሬ ከተስተካከለ ግን፣ አምራቾችና ኤክስፖርተሮች፣ በአግባቡ ገቢያቸውን እያገኙ ይጠናከራሉ፤ ይበራከታሉ። በተቃራኒውም፣ ወደ ጉራንጉር ገበያና ወደ ኮንትሮባንድ ጥልፍልፍ ልፋት የሚገባ ሰው ይቀንሳል።
በእርግጥም፣ የዶላር ምንዛሬ ከተስተካከለ በኋላ፣ በሦስት ዓመታት ልዩነት የኤክስፖርት ገቢ በእጥፍ አድጓል።
በ2001 ዓ.ም የኤክስፖርት ገቢ = 1.5 ቢሊዮን ዶላር
በ2004 ዓ.ም የኤክስፖርት ገቢ = 3.1 ቢሊዮን ደላር
ነገር ግን፣ የኤክስፖርት እድገት በዚሁ አቅጣጫ አልቀጠለም። እዚያው ላይ ደነዘዘ። ከ2006 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ፣ ጭራሽ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በታች ወርዷል።
የ2008 ዓ.ም የኤክስፖርት ገቢ = 2.9 ቢሊዮን ዶላር
የ2009 ዓ.ም የኤክስፖርት ገቢስ?... 2.7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ!
• pለምን? ሰበቡ፣ ድብቅ እንቆቅልሽ አይደለም!
እንደ ሚሌኒየሙ መባቻ ባይሆንም፣ ከዓመት ዓመት በሚካሄድ የብር ህትመት ሳቢያ፣ በየዓመቱ ብር መርከሱ አልቀረም። የሸቀጦች ዋጋም፣ በየአመቱ በ10% ገደማ እየናረ ቆይቷል። የዶላር የምንዛሬ ዋጋ ግን፣ ገበያውን ተከትሎ በዚያው መጠን እንዳይስተካከል፣ በመንግስት ቁጥጥር ተደፍጥጦ ተይዟል።
የአለም ባንክ እና የአለም ገንዘብ ድርጅት ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፣ የዶላር ምንዛሬ፣ እንደ 2002 ዓ.ም መስተካከል አለበት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ቢሆን፣ የዶላር ምንዛሬ በጣም ተደፍጥጦ እንደተያዘ አይክድም። ምንዛሬው በገበያ የሚወሰን ቢሆን ኖሮ፣ ልዩነቱ ከፍተኛ እንደሆነ፣ በቁጥር ይገልፀዋል። ምናለፋችሁ፣ አነሰ ቢባል፣ የዶላር ምንዛሬ በ30% መስተካከል ይገባው ነበር። መንግስት ግን ዳተኛ ሆኗል።
• የ1 ዶላር ምንዛሬ፣ ከ24 ብር፣... ቢያንስ ቢያንስ ወደ 30 ብር!
የዶላር ምንዛሬ ቢስተካከል፣ ለመንግስት ችግር አለው? አዎ አለው።
መንግስት በየአመቱ፣ ለብድር ክፍያ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይፈልጋል - አሁን ባለው ምንዛሬ የ24 ቢሊዮን ብር ወጪ ማለት ነው።
የዶላር ምንዛሬ፣ ወደ 30 ብር ከተስተካከለስ?
መንግስት በዓመት ውስጥ የ1 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ ለመክፈል፣ 30 ቢሊዮን ብር ማውጣት ሊኖርበት ነው። 6 ቢሊዮን ተጨማሪ ወጪ ማለት ነው። እና ምን ይሻላል? የዶላር ምንዛሬን፣ እዚያው ባለበት ደፍጥጦ ማቆየት?
ግን፣ በዚያው ልክ፣ የቡና፣ የወርቅ፣ የሰሊጥ ወዘተ አምራቾችና ኤክስፖርተሮች ሊያገኙት ከሚገባ ገቢ፣ ሲሶውን ያህል እንደመንጠቅ መሆኑን አንርሳ። ታዲያ፣ በርካታ ቢሊዮን ብር ገቢ እየተቀነሰባቸውና እየተወሰደባቸው፤ እንዴት ኤክስፖርት ያድጋል? እንዴትስ ላይዳከም ይችላል?
የንግድ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ በአነስተኛ ተቋማትና ግለሰቦች አማካኝነት እየተሰበሰበ ለኤክስፖርት ይቀርብ የነበረ ወርቅ፣ ባለፉት አራት ዓመታት በግማሽ ቀንሷል።
• በአነስተኛ አምራቾች አማካኝነት የሚቀርብ የኤክስፖርት ወርቅ
ከሦስት አመት በፊት፣ ከ7000 ኪሎግራም በላይ ወርቅ ለኤክስፖርት ይቀርብ ነበር።
አምናስ? ከ3500 ኪሎግራም በታች ሆኗል።
ዘንድሮስ? 2000 ኪሎግራም ገደማ ይሆናል።
የዚህ መንስኤዎች ድብቅ አይደሉም። መፍትሄዎቹም ሚስጥር ሊሆኑ አይችሉም። ከጥፋት ለመዳን፣ በመፍትሄ ጎዳና መራመድ እንጀመር።
1 የስኳር ፕሮጀክቶችንና ፋብሪካዎችን በመሳሰሉ የመንግስት ድርጅቶች አማካኝነት የድሃ አገር ሃብት እንዳባክን፣ መንግስት ወደ ቢዝነስ ስራዎች ከመግባት እንዲቆጠብ ማድረግ!
2 መንግስት እስከ ዛሬ የገባባቸውን ቢዝነሶች፣ ቀስ በቀስ ለግል ኢንቨስትመንት መተው!
3 መንግስት ከቢዝነስ ስራ እስኪወጣ ድረስ ደግሞ፣... ቢያንስ ቢያንስ ግንባታዎችን በስራ ተቋራጭ ኩባንያዎች አማካኝነት እንዲካሄዱ ማጫረት!
4 የሃብት ብክነትን እንዲህ በማስቀረት፣ የውጭ እዳ እንዳይከመር መከላከል ይቻላል። ሌላስ?
5 አለቅጥ የብር ኖት ከማተምና ብርን ከማርከስ መቆጠብ!
6 ብር በገፍ ከታተመና ከረከሰ ግን፣... የዶላር ምንዛሬን ደፍጥጦ ለመያዝ አለመሞከር! 

Read 4894 times