Sunday, 02 July 2017 00:00

ሽማግሌው

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(15 votes)


       (ደራሲ አዳም ረታን ጨምሮ ሌሎች ዕውቅ ጸሐፍያን ከተሳተፉበትና ዛሬ ለንባብ ከበቃው “አማሌሌ እና ሌሎች” ከተሰኘ መድበል ውስጥ ለዛሬ የሌሊሳ ግርማን እንዲህ አቅርበናል)
ሀገሪቱ አድጋለች የሚባለው ለካ እውነትም በቁመት ነው!. . . ሠላሳኛው ፎቅ ላይ ነው ሼባው የሚኖረው፡፡ ዛሬ መብራት በመጥፋቱ ምክኒያት የህንጻው አሳንሰር መስራት አቁሟል፡፡ ታዲያ ሼባው በወጣበት መውረድ ቢያቅተው፣ ስልክ ደወለልኝ፡፡
‹‹ተ. . . ተ. . . ተሻገር. . . እባክህ!  የ. . . የ. . . ሚበላ ነገር ይዘህልኝ ና›› ብሎ ዘጋ፡፡ አለቃዬ ነው፡፡ እኔ ብዙ አልቀርበውም፡፡ ዘበኛና ሠራተኛ የሚቀራረበውን ያኽል ጠዋት ጎብጦ ሲገባም ሰላም ይለኛል፡፡ በእጁ የሚያንጠለጥለውን ቦርሳ ተቀብየው ከኋላ ኋላው እከተላለሁ፡፡ ቢሮው በር ላይ ሲደርስ ቀና ብሎ፣ አፍንጫውን አጨማድዶ የቢሮውን ቁጥር ያያል። ከዚያ ቁልፉን ከጀርባው ይመዛል፡፡ የቁልፉ መዓት ይገርመኛል። የድሮ ሣጥን ቁልፍ ሁሉ አለው፡፡ በሦስት ሙከራ ትክክለኛውን ቁልፍ ያገኘው አንድ ቀን ብቻ ነበር፡፡ ትክክለኛውን ቁልፍ ሲያገኝ የሚደሰተውን ያኽል በሌላ በምንም ነገር አይደሰትም፡፡ ለደሞዝ ቀን ፊቱ ይጨፈግጋል፡፡
የቢሮው ጠረን ደስ አይልም፡፡ የወረቀቶቹ ክምር ከኮርኒሱ ገጥሟል፡፡ አቧራው ወደ ነፍሳት ተቀይሯል፡፡ ቦርሳውን ጠረጴዛው ላይ ሳስቀምጥለት ኪሱን መዳበስ ይጀምራል፡፡ ሳንቲም ለመቀበል እንዳልሆነ ብነግረው በዚያ መነጽሩ እንዳያፈጥብኝ እፈራለሁ፡፡ በ’ርግጠኝነት ለማኝ እንኳ ሃምሳ ሣንቲም እንደማይቀበል አልሰማም፤ የሆነ ዘመን ላይ ቆሟል፡፡ አዲሱ ዘመን የሚታየውም አይመስለኝም፡፡ ስልክ አይይዝም፤ ጠረጴዛው ላይ የፖስታ ደብዳቤ አይጠፋም፡፡ ያለቁ ስክሪቢቶዎች በኩባያ ውስጥ አበባ መስለው ተቀምጠዋል፡፡ እያስነጠሰኝ ሃምሳ ሣንቲሜን አመስግኜ እረከባለሁ፡፡
አንዳንዴ በትልቁ ስልክ ዘበኛ ቤት ደውሎ ሻይ ያዘኛል፡፡ የሻይ ትዕዛዙ ረጅም ነው፡፡ በሚንተባተብ አንደበቱ ቁልፎቹን የሚፈልግበትን ያኽል በትዕግሥት አደምጠዋለሁ፡፡ የጦስኙን፣ የስኳሩን፣ ሎሚ ግማሹን፣ የሻዩን ቅጥነት ገልጾልኝ ስልኩን ዘጋ፡፡
እኔ ወደሻይ ቤቱ ደውዬ ያን ሁሉ ገለጻ ወደሁለት ቃሎች አወርደዋለሁ፡- ‹‹ለአቶ ዘካርያስ አንድ ሻይ›› . . .  በቃ፡፡
እንግዲህ ይሄው ነው ትውውቃችን፡፡ እና ድንገት ደውሎ፣ ‹‹ተ. . . ተ. . . ተሻገር›› ሲለኝ ግራ ገባኝ፡፡ ወደ አስተዳደሩ ሔጄ እንደተደወለልኝ ነገርኩት፡፡ አስተዳደሩ አራዳ ነው፡፡ ችግሩ ከአትክልተኞቹ ጋ እንጂ፣ ከዘቦች ጋ ሽርክ ነው፡፡ ይዞ የሚገባውን ሰው ሳንመረምር እናስገባለታለን፡፡ የሚያወጣቸው ዕቃዎችም ካሉ እንተባበራለን፡፡ እና ነገርኩት፡፡ ድንገት ሐሳብ ገባው፡፡
‹‹አይ፣ ጋሽ ዘካርያስ በጣም ቢያመው ነው፡፡ ደግሞ’ኮ የቀፎራ ሕንፃ ሠላሳኛው ፎቅ ላይ ነው ተከራይቶ የሚኖረው፡፡ የልቡ ሕመም ተነስቶበት ይሆናል፡፡ ቆይ አንዴ. . . ›› አለኝ፡፡ የጠቀሰኝ መሰለኝ፡፡ በኃላፊነት ያለ ሰው አራዳ ሲሆን መዝናናቴን ይነሳኛል፡፡ ስልክ ደወለ። ገና ሲነሳ፣ ‹‹መኪናውን አስነሳ. . . የት ነህ?›› አለ፡፡ አትክልተኞችን ብቻ ሳይሆን፣ ሾፌሮችንም አይወድም መሰል፡፡ በዛኛው ጫፍ የሚለማመጥ ድምፅ ይሰማኛል፡፡
‹‹በል በሩ ጋ እጠብቅሃለሁ፡፡ . . . እኔና ማን? ምን ቸገረህ! አንተ መኪናህን ይዘህ ውጣ፤ ፔሬድ!›› አለው፡፡
እኔና አስተዳዳሪው ወደ አቶ ዘካርያስ ፎቅ ከሾፌሩ ጋ ከነፍን፡፡
ሾፌሩና አስተዳዳሪው በዕድሜ አይገጣጠሙም። አለቅየው ወጣት ነው፤ ሾፌሩ እንደወጣት ለመሆን የሚሞክር ነው፡፡ ከምሥራቅ ቅርንጫፍ ዕቃ ግዢ ክፍል ተቀንሶ ነው ሾፌር የሆነው፡፡ አስተዳዳሪው ደ’ሞ ከዚያው ቅርንጫፍ ጠቅላላ አገልግሎት ክፍል በዕድገት የመጣ ነው፡፡
ስለ አቶ ዘካርያስ ምንም መረጃ የለኝም፡፡ ምሑር ነው ይባላል፡፡ አብዷልም፣ ኢሕአፓም ነበረ የሚሉ አሉ፤ ኢሕአፓነቱን አይበሉባው ላይ ባየሁት ጉርብርብታና ጠባሳ አረጋግጫለሁ፡፡ ያለጠባሳ አብዮተኛነት የለም ባይ ነኝ፡፡
አስተዳዳሪው የአለቅነትን አቀማመጥ ችሎበታል፡፡ ሰውነቱ ግን ሥልጣኑን አልሞላለትም፡፡ የሾፌሩ ሰውነት ግን የሞላ ነው፡፡ ድኃ ሳይቀነስ፣ የሞላውን ቀንሶ አሁን ላለበት ሥራ መመጠን አለበት፡፡ ያልበዋል፤ ማጅራቱንና ግንባሩን በመኃረብ ይጠራርጋል፡፡ በሰውነቱ ላይ እንዳካበተው ጥሪት በቤቱ ውስጥም የሚቀልጥ ጮማ እንደንብረት ሳይኖረው አይቀርም፤ ወይም በባንክም ቢሆን፡፡ ግን እኔ ምናገባኝ? ከተግባረ-ዕድ ስመረቅ ለቅቄ መሔዴ አይቀር፡፡
ከአስተዳደሩ ጋ፣ ዓይናችን በመስታወት ይጋጭና ወደተለያየ አቅጣጫ እናፈናጥቃለን፡፡ ስለ አቶ ዘካርያስ መረጃ እየፈለግኹ ነበር፡፡ እንደጠበቅኹት አስተዳዳሪው ማውራት ጀመረ፡፡
‹‹አይ ጋሽ ዘካርያስ! እንዲሁ እንዳኮረፈ፣ ሕመሙን እንደደበቀ፣ በቃ. . . መጨረሻው እንዲህ ሆነ፡፡ ልጆቹ የልብ ሕመሙን ሊያሳክሙት ቢሉ፣ ‹‹ታንቄ ብሞት ይሻለኛል›› ብሎ አሻፈረኝ አለ፡፡
‹‹በኢሕአፓ ጊዜ ከመሪዎቹ ማኽል ነበር፡፡ መጻሕፍትም ጽፏል፤ በብዕር ስም፡፡ ዘካርያስ ራሱ የትግል ስሙ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይገርማል፤ ምቾትን ይጸየፋል! ከቀበሌ ቤት ባያስለቅቁት ፎቁ ላይ ባልገባ ነበር፡፡ እንግዲህ መብራት ሲጠፋ በ’ግሩ ወጥቶ ነው ልቡ የፈነዳው ማለት ነው፡፡››
‹‹እንዴ! ጋሽ ዘካርያስ አረፈ እንዴ! ለኔ’ኮ፣ ‹ምግብ ይዛችሁልኝ ኑ› ብቻ ነው ያለኝ፡፡››
‹‹አይ፣ ዘካርያስ እንዲህ ካለ አስከሬኔን አንሱ ማለቱ ነው፡፡ እ’ሱ መች ምግብ ይርበዋል? ያውም ርቦት ሰው ሊያስቸግር. . . አሁን ዘመዶቹን እንዴት ማግኘት ይቻላል? ከራሱ በስተቀር ማንም ቤተ-ዘመዶቹን አያውቅም፡፡ አድራሻ ቢገኝ ራሱ ዘመን ያለፈበት ይሆናል፡፡ የቤቱን በር ሰብረን መግባታችን አይቀርም፡፡ ብረት ሠራተኛ መያዝ አለብን፡፡ እንደው እኔ ግን ቤቱ ምን እንደሚመስል ለማየት ነው የጓጓሁት፡፡ ማንንም’ኮ አያቀርብም፡፡ ምናልባት አሁንም የማጭድና መዶሻ ባንዲራ ከቤቱ አይጠፋም። እነሱ’ኮ ጉንዳኖች ናቸው፤ ዓላማቸውን አይቀይሩም። ‹ዴሞክራሲያ› እና ‹የሰፊው ሕዝብ ድምፅ› ዕትሞችን እያነበበ ይሆናል፡፡ ጉድ እኮ ነው!... እንዴት እናድርግ? ፖሊስ ይዘን እንሒድ? ደ’ሞ የሆነ ወንጀል. . . የሆነ ማስረጃ ቢያገኙበትስ?. . . ብቻ ስልክ እንምታለት፡፡››
ተንቀሳቃሽ ስልኩን አውጥቶ ደወለ፡፡ ይጠራል፤ አይነሳም፡፡ የድሮው ስልክ ነው፤ ስድስት አኃዞች ብቻ ያሉት፡፡
ሾፌሩና አስተዳደሩ ድሮ በነበሩበት ቅርንጫፍ ሸሪኮች እንደነበሩ የሆነ ነገር ሹክ አለኝ፡፡ አብረው የሠረቁትና የደበቁት የሆነ የሙስና አፅም አለ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ-ቤት የተለመደ ነው፡፡ የመንግሥት ጆሮ ሩቅ ነው፤ ስለዚህ የራሱ እጆች በራሱ ኪስ ገብተው ይሰርቃሉ። ኪስ ውስጥ እንዳለ የተያዘ እጅ ከደረጃው ይቀነሳል፤ ያልተያዘው ይሾማል፡፡ አስተዳዳሪው ተሾሟል፡፡ ሾፌሩ ወዙን እንዲጠቀምበት ለአስተዳዳሪው ማዋስ አለበት። ከዕለታት አንድ ቀን ደ’ሞ ቦታ የሚለዋወጡበት ጊዜ ይመጣል፡፡ አስተዳዳሪው አትክልተኛ፣ አትክልተኛው ግምጃ ቤት፣. . . ሾፌሩ ደ’ሞ ዋና ሥራ-አስኪያጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ማንም በነበረበት አይዘልቅም፤ ከአቶ ዘካርያስ በቀር፡፡ ግን፣ አቶ ዘካርያስ ከሞተ ዘላቂነት ሕልም ነው እንጂ... እምነትም ቢሆን ብቁ አይደለም ማለትም አይደለ?
‹‹እስኪ ጎማውን ወጥተህ ተመልከተው›› አለ ሾፌሩ። የተናገረው ሳያስብ ነው፡፡ ወደ አስተዳዳሪው አቅጣጫ ዞረ፡፡ የአስተዳዳሪው ፊት በድንገት ተነፈሰ፡፡ ባለበት ሆኖ ቦታ የተለዋወጠ መሰለኝ፤ አፍንጫው በከንፈሩ ቦታ. . . ግን የሆነ ነገር ብቻ ሆኗል፡፡ ከዚያ ከንፈሩ ከሌላው ፊቱ ተለይቶ ወደ ኋላ ቀረ. . .
ሾፌሩ በሠራው ስህተት ደነገጠ፡፡ ‹‹ይቅርታ እሱን ማለቴ ነው›› አለ፡፡
እኔን ማለቱ ነው፡፡ እኔ፣ የጋሽ ዘካርያስን ቦርሳ ስሸከም አይቶኝ ተላላኪ መስዬው እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ከእ’ሱ ትዕዛዝን አልቀበልም፡፡ ‹‹ጆብ ዲስክሪፕሺን ያለኝ ሰው ነኝ፤ ራስህ ወጥተህ ተመልከት›› አልኩት፡፡
በ’ኔ ምላሽ አስተዳዳሪው ተደሰተ፤ ድንጋጤውም መለስ አለለት፡፡ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ሁለቱም ትናንሽ ሰዎች ናቸው፡፡
የአቶ ዘካርያስ ዘመን ሰዎች ናፈቁኝ፤ ባላውቃቸውም ናፈቁኝ፡፡ እኔ ራሴ የየቱ ዘመን ሰው እንደሆንኩ በ’ርግጥ አላውቀውም፡፡ ምናልባት፣ ሰው የሚመደበው በዘመን ሳይሆን በሰፈር ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ወደ መገናኛ አካካቢ በመወለዴ ከእነ’ሱ መሻሌን እንዴት አውቃለሁ? እነ’ሱ የመርካቶ ልጆች ሆነው የሚቀሩ ናቸው፤ የማያድጉ መሰሉኝ፡፡ አቶ ዘካርያስ፣ የአብዮቱ ዘመን ሰው ናቸው። የትም ሰፈር ቢኖሩ፣ ከየትም ቀበሌ ቤት ቢባረሩ፣ በሠላሳኛው ፎቅ ላይ ቢሰቀሉ፣ ተሰቅለውም ያለደራሽና ያለዘመድ ቢሞቱም፣ ከ’ኔና ከእነዚህ ሁለቱ ይበልጣሉ፡፡ ዘመናችን ሰፈር. . . ማንነታችን በዘር. . . እውነታችን ብር ከሆንነው ይሻላሉ፡፡
ፎቁ ጋ ደርሰን ከመኪናው ወረድን፡፡ አመነታን. . . ለማጣራት ቀስ ብለን ወደ ዘበኛው ተጠጋን፡፡ ‹ዘበኛውን የሚያናግረው ዘበኛ ነው› የተባለ ይመስል ሾፌሩና አስተዳደሩ ይጠብቁኝ ጀመር፡፡ ቋንቋ ከብሔር ጋ ብቻ ሳይሆን ከሥራ መደብም ጋ መያያዙ ገረመኝ፡፡ ከመጠየቄ በፊት፣ ቅድም አስተዳዳሪው በሾፌሩ ጥያቄ ተከፍቼ ስመልስ የሳቀው ሳቅ ድንገት መጣብኝ፡፡ ለካ እንግሊዘኛ በመቀላቀሌ ነው፡፡ እንደ እንግሊዘኛ የሚፈራው ነገር የለም ይባላል፡፡ ፈረንጆች ወደ መሥርያ-ቤቱ የሚመጡት እ’ሱን ለማዋረድ ስለሚመስለው፣ ፈረንጅን ሀገር ከሚቀሙ ወራሪዎች ጋ አገናኝቶ ማውራት ይቀናዋል፡፡ ቋንቋ አለመቻል ለካስ፣ የአድዋ ጦርነትን በመሥርያ-ቤት ውሰጥ ለመቀስቀስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ንዴቴን ውጬ፣ ዘበኛውን ስለ አቶ ዘካርያስ ጠየቅኩት፡፡
‹‹አሁን ወደ ሥራ ሄዱ፣ ከ. . . አስር ደቂቃ በፊት›› አለኝ፤ ደስታ ተሰማኝ፡፡ ተነፈስኩ፡፡ ‹‹ሰሞኑን መብራት ጠፍቶ ነበር?›› አልኩት ዘበኛውን፣ በዘበኛ ቋንቋ፡፡    
‹‹አዎ፣ ሁለት ቀን መብራት ጠፍቶ ነበር፡፡ አቶ ዘካርያስም ጠፍተው ዛሬ ተከሠቱ፡፡ መብራት ከሌለ ሌላ ቦታ ሄደው ይኖራሉ መሰለኝ›› አለ፡፡
እ’ሱ ተጠያቂነቱን በመሰለኝ ከራሱ ትከሻ አውርዷል። መሰለኝ የግድ-የለሽ ትውልድ ቋንቋ ናት፡፡ ቋንቋ ከሆነች ደ’ሞ ብሔርም፣ ሰፈርም ይኖራታል፡፡ ሰውየው ከሠላሳኛ ፎቅ ላይ መውረድ አቅቷቸው፣ መብራት እስኪመጣ በባዶ አፋቸው ሁለት ቀን እንደተቀመጡ አላወቀም፡፡ ዘበኛውን አመስግኜ ከመሄዴ በፊት አንድ ጥያቄ ሰነዘርኩ።
‹‹ጋሽ ዘካርያስ ቦርሳቸውን ይዘዋል?›› አልኩት፡፡
‹‹አዎ. . . አዎ፣›› አለ፡፡
‹‹ርግጠኛ ነህ?›› አልኩት፡፡
ርግጠኛ አልነበረም፤ መስሎታል፡፡ የእውነት ነው ደ’ሞ የመሰለው፡፡ መኪና ይዘው ቢሆን ኖሮ በደንብ ያያቸው ነበር፡፡ እ’ሱም የእኛው ትውልድ አባል አይደል?
ለአስተዳዳሪው መልካሙን ዜና ስነግረው ብዙም የተደሰተ አይመስልም፡፡ ሾፌሩን መቆጣት ጀመረ። የቤንዚን ብክነት ምናምን ላይ፡፡ ቺፍቼ  ይባባላሉ፡፡ ይግባባሉ፡፡
ወደመሥርያ-ቤት ስንመለስ፣ ወደ አቶ ዘካርያስ ቢሮ አመራሁ፡፡ በሩን አንኳኩቼ ጠበቅሁ፡፡ በሩ ሲከፈት ደስታዬ ርግጠኛ ሆነ፡፡ ሰውየው እንደወትሮው ናቸው፡፡
‹‹ተ. . . ተ. . . ተሻገር. . . እ. . . መብራት ሲመጣ፣ በቃ. . . ራሴ ወርጄ መጣሁ፡፡ የለም. . . ምንም ችግር የለም። እንደው እርጅና መጣና ሰግቼ መሰለኝ የደወልኩልህ፡፡ ለማንኛውም እግዜር ይስጥልኝ›› አሉ፡፡ ጠረጴዛቸው ላይ የድሮ መጽሔት አለ፤ ግን ቢያንስ በአዲሱ መንግሥት ዘመን የታተመ ነው፡፡ እኔ የተወለድኩበት ዘመን በመጽሔቱ ግርጌ ላይ ተጽፏል፡፡ ብቻ ይሻላል፡፡ በዛ ላይ የእግዜርን ስም በምስጋና ሲጠሩ ሰማኋቸው አይደል?. . . ወይንስ የመሰለኝ ትውልድ ያስበቀለ ጆሮዬ ነው?. . . ከአብዮቱ የራዲዬሽን ሐሩር ይሆን?. . .ግን ሲያገግሙ ማንን ይሆኑ ይኾን?. . . አንድ ተራ ሽማግሌ ይሆኑ ይኾን?. . . ግን ተራ ሽማግሌ ብሎ ነገር የለም. . . ተራ ሽማግሌ በማን ዘመን?. . . በንጉሡ ዘመን ያለ፣ ቤተስክያን የሚስም ሽማግሌ?. . . ወይንስ በአሁኑ ዘመን ያለ፣ ኮረዳ የሚያማግጥ ሽማግሌ. . . ወይንስ ሌላ?
የሽማግሌ ዓይነትን በሰፈር ማወቅ ይቻላል? ወይንም የሽማግሌ ዓይነትን በብሔር? ርግጠኛ አይደለሁም፡፡
የሚቆረጥሙትን ሽንብራ ከኮት ኪሳቸው አፍሰው ሰጡኝ፡፡ የፍቅር መግለጫ መሆኑ ነው፡፡ አባቴ መሰሉኝ። ከሳንቲም ቲፕ፣ የአሹቅ ቆሎው ተሻለኝ፡፡ በራቸውን ዘግቼ ወጣሁ፡፡
ደረጃው ላይ አስተዳዳሪው ገጠመኝ፤ ገላምጦኝ አለፈ፡፡ አለቅነት የሚሰጠውን የጠባይ ዩኒፎርም ለውጧል ማለት ነው፡፡ የሚሄደው ወደ አቶ ዘካርያስ ቢሮ መሆኑ ታውቆኛል፡፡ አኳኋኑ ሊቆጣቸው ይመስላል፡፡ ግን እንደማይዳፈር አውቃለሁ፡፡ እንዴት ድመት ተራራን ይቆጣል? ቢቆጣስ ተራራው ‹‹ሚያ-ው!›› ቢባል መች ይሰማል?
ግን እንደው ሊቆጣቸው ቢችል ምን ይላቸው ነበር? ‹‹ለምን ሳይሞቱ ቀርተው፣ የመሥርያ-ቤት መኪና አገልግሎትና ነዳጅ አስባከኑኝ?›› ይል ይሆን ?. . . ቆሎዬን መቆርጠም ያስፈልገኛል፡፡

Read 4816 times