Print this page
Saturday, 01 July 2017 14:46

ሕጻናቱ ስለኤችአይቪ መረጃ ያገኛሉ?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ኤችአይቪ ዛሬም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑ እሙን ነው። የስርጭት አድማሱም ወደነበረበት እንዳይመለስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል የሚለውን ሁሉም የሚስማማበት ነው። ለመሆኑ ሕጻናቱ በየትምህርት ቤታቸው በምን መንገድ ስለኤችአይቪ ይማራሉ ስንል በአዲስ አበባ ካራቆሬ ረጲ የሚባለው አካባቢ የሚገኘውን አትላስ አጸደ ሕጻናት ‘የመጀመሪያ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የመሰናዶ ትምህርት ቤትን አሰራር ለንባብ ብለናል። በቅድሚያ ማብራሪያቸውን የሰጡን የትምህርትቤቱ ምክትል ርእሰ መምህር አቶ ፋሲል ገቢሳ ናቸው።
“በትምህርት ቤቱ በስነተዋልዶ ጤና እና ኤችአይቪን በሚመለከት ለተማሪቹ ተገቢውን መረጃ ለመስጠት እንዲቻል የተዋቀረ ክለብ አለ። ከ4ኛ - 12ኛ ክፍል ድረስ እንደየክፍሉ ደረጃው ቢለያ ይም በትምህርት መልክ ይሰጣል። እንዲሁም የተዋቀረው ክለብ በሰልፍ ላይ ጭምር ተማ ሪዎች ስለኤችአይቪ የተለያዩ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ያደርጋል። ይህ የመረጃ ልውውጥ ሂደት ከትምህርት ሚኒስቴር ጀምሮ በወረዳ የትምህርት ቢሮዎች በየደረጃው በመዋቅር የሚታ ወቅና አሰራሩንም በተለያዩ ጊዜ ከወረዳ እየመጡ የሚመለከቱት ነው። ”
መምህርት ስሜነሽ መንግስቱ እና መምህርት ቤተልሄም ፀጋዬ የክለቡ አስተባባሪዎች ናቸው። እነሱ እንደገለጹት አስተባባሪዎቹ ወይንም የቡድኑ አባላት ተማሪዎቹን ይመሩዋቸዋል። በሰልፍ ላይ በትምህርትቤቱ ሚድያ የሚገልጹትን ነገር ያያይዙዋቸዋል። ለዚህም ምንጭ የሚያደርጉት ከተለያዩ መጣጥፎች ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ የሚወጡ የመገናኛ ብዙሀን ውጤቶችን በመጠቀም ነው። የክለቡ አባላት አስተማሪዎችን ጨምሮ ወደ 40 ይጠጋሉ። ክለቡ ሲዋቀር በቅድሚያ በፈቃደኝነት ሲሆን በእድሜያቸው ከፍ ያሉትን ተማሪዎችን ግን በተለይ እየመረጥን በቡድኑ እናካትታቸዋለን ብለዋል መምህርቶቹ። ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎቹ ኤችአይቪ ኤይድስን በሚመለከት ወደቤተሰባቸውም ሲሄዱ ግልጽ ውይይት እንዲያደርጉና የተማሩትን እንዲገልጹላቸው ለተማሪዎቹ እንነግራቸዋለን ብለዋል።
የአትላስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጠዋት ጠዋት ወደትምህርታቸው ከመግባታቸው በፊት በሚያደርጉት ሰልፍ ላይ ኤችአይቪን በሚመለከት ለግንዛቤ የሚረዳ ግጥምና መነባንብ ያቀርባሉ። ተማሪዎቹ ከሚያቀርቡዋቸው ግጥሞች መካከል የሚከተሉትን ለንባብ ብለናል።
ኤችአይቪ ኤይድስን እንከላከለው፣
ሕዝብን እየጎዳ እየጨረሰ ነው።
ኤይድስን ለመከላከል...መተላለፉን አውቀን፣
እባካችሁ ሰዎች እንኑር ተጠንቅቀን፣
እንከላከለው አብረን በጋራ ሁነን።
---//////---
የሚከተለው ግጥም ደግሞ የገሊላ እና ዲቦራ ነው።
የሰው ጠላት የሆነው ብዙዎችን የገደለው፣
ቀንደኛ ጠላታችን ኤችአይቪ ኤይድስ ነው።
ኤችአይቪ ጎጂ ነው …ሰዎችን ይገድላል፣
በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳክማል፣
የሀገር እድገትንም ያደናቅፋል።
ከላይ ያነበባችሁዋቸው ግጥሞች ፀሐፊዎችና አቅራቢዎች የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ሕጻናት ናቸው። ይህ ግጥም የእራሳቸው በመሆኑ ተማሪዎቹ ስለኤችአይቪ በአቅማቸው እውቀቱ አላቸው ያሰኛል። መምህራኖቹ እንደገለጹት ልጆቹ ትምህርቱ የሚሰጣቸው በእነሱ እድሜና ደረጃ አስፈላጊ በሆነው ደረጃ እንጂ ትላልቅ ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች ወይም ድርጊቶች አይደለም።
በማስከተል የምታነቡት አንድ (Welcome to do something) የምትችሉትን ለማድረግ እንኩዋን በደህና መጣችሁ በሚል ስሜት የተከፈተ ድህረ ገጽ ያስነበበውን እውነታ ይሆናል። ድረገጹ በመከፈቱም በአለማችን ወደ 5.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች በጎ ስራን እንዲሰሩ እና ሰዎች እንዲድኑበት ምክንያት ሆኖአል ይላል መረጃው። በዚህ ድረ ገጽ ስለኤችአይቪ ኤይድስ አንዳንድ እውነታዎች በሚል ተመዝግቦአል።
በአለማችን ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው መኖሩ ከተረጋገጠባቸው ሰዎች መካከል 69% የሚሆኑት የሚገኙት ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ነው። ይህም ማለት 23.8 ሚሊየን ያህል በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ሰዎች ናቸው።
በአለማችን የኤችአይቪ ቨይረስ በደማቸው ካለባቸው ሕጻናት መካከል 91 % የሚሆኑት የሚገኙት በአፍሪካ ነው።
በየአመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ትላልቅ ሰዎችና ሕጻናት በኤችአይቪ ምክንያት በአፍሪካ ይሞታሉ። በ2011 በአለም አቀፍ ደረጃ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች በኤይድስ ምክንያት ማለፋቸው አይዘነጋም።
ኤችአይቪ በአለማችን ከ75 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለመታመም ምክንያት የሆነና ከ36 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ለሕልፈት መዳረግ ምክንያት ነው።
71 % የሚሆኑት በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች አፍሪካውያን ነበሩ።
የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት የቫይረሱን ስርጭት መፋጠን ለመገደብ እና በቫይረሱ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ እንደሚረዳ ተረጋግጦአል። በዚህም ምክንያት መድሀኒቱን የሚወስዱ ሰዎች ጤናማ እና መደበኛ ሕይወታቸውን ለመቀጠል ማስቻሉ ተረጋግጦአል።
ነገር ግን በየሀገራቱ በተስተካከለና ብቃት ባለው ደረጃ አቅርቦቱ ባለመኖሩ ምክንያት በ2010 በአፍሪካ ከ10 ሚሊዮን መድሀኒቱን ማግኘት ከነበረባቸው ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝባቸው ሰዎች ውስጥ 5 ሚሊየን ያህሉ ብቻ አግኝተዋል።
ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በኤችአይቪ ኤይድስ ምክንያት አማካይ እድሜ 54.4 ሲሆን በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ከ49 አመት በታች መሆኑ ተረጋግጦአል።
ኤችአይቪ ኤይድስ በአፍሪካ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ለመማርም ሆነ ለመስራት አቅም ስለማይኖራቸው አምራችነታቸውን ተፈታትኖታል። በዚህም ሳቢያ የኢኮኖሚ እድገቱን ወደሁዋላ ጎትቶታል። እርጉዝ ሴት አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ ካላገኘች የምትወልደው ጨቅላ በእርግዝና ወቅት ከ20-45 % ያህል በቫይረሱ የመያዝ እድል ሊገጥመው ይችላል። 59% የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ያለ ሰዎች በአፍሪካ ያሉ ሲሆኑ በአብላጫውም ቫይረሱ በደማቸው የተገኘ ሕጻናት ከእናታቸው የተላለፈባቸው ናቸው።
ይህ መረጃ በምንጭነት የጠቀሳቸው እውነታዎች በ2011 ዓ/ም የተሰሩ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ያለውን እውነታ ለመገመት ያስችላል የሚል ግምት አለ። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በቫይረሱ ምክንያት የሚታመሙ ሰዎች በተለይም በገጠሩ ክፍል ብዙ ግንዛቤ በሌለበት ሁኔታ የባህላዊ መድሀኒቶችና እምነት ቦታዎችን ብቻ እንደመድሀኒት በመጠቀም ለሕልፈት የሚዳረጉ ብዙ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ። ነገር ግን “ሸማ በየፈርጁ” እንደ ሚባለው ቫይረሱ በደማቸው የተገኘ ሰዎች በሕክምናው ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት እየተጠ ቀሙ ሌላውን መንገድ እንደየፍላጎታቸው ቢያደርጉት መልካም መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ። ይህ የሚያሳየው የኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ ያለ ሰው በመንም ምክንያት ከሕክምናው መዘናጋት እንደሌለበት ነው።

Read 1410 times