Sunday, 02 July 2017 00:00

800ሺ ብር የፈጀው ‹‹አንድ ክለብ አንድ ቤተሰብ›› ዛሬ ለገበያ ይቀርባል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የመጀመርያ እና ፈርቀዳጅ የሚሆን የስታድዬም ማስጨፈርያ ዜማዎችና የደጋፊ መዝሙሮች የተሰባሰቡበት ልዩ አልበም ዛሬ ለገበያ ይቀርባል፡፡ አልበሙ “አንድ ክለብ አንድ ቤተሰብ” የሚል ርእስ ያለው ነው፡፡ የሙዚቃ አልበሙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የሚመለከቱ 12 ዘፈኖች ያሉበት ሲሆን ሙዚቃዎቹ በይዘታቸው የክለቡን ታሪክ፤ ለነፃነት ያደረገውን አርበኝነትና ተጋድሎ፤ የደጋፊዎችን መዋደድ እና አንድነት፤ ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚዳስሱ ይገኙበታል፡፡
የአልበሙን ግጥምና ዜማዎች በመድረስ እና አጠቃላይ ስራዎችን በማስተባበር የሰራው በቀኝ ጥላ ፎቅ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አስጨፋሪ የሆነውና በሳክስፎን የሙዚቃ መሳርያ ተጨዋችነቱ የሚታወቀው እዮብ እድሉ ነው፡፡ እዮብ ሳንጃው አበባ በሚለው ቅፅል ስሙ የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮ በስታድዬም የሚታየውን የክለቡ ደጋፊዎች አስደናቂ የድጋፍ አሰጣጥ ትርኢት እንዳቀጣጠለ ይታወቃል፡፡ የአንድ ክለብ አንድ ለቤተሰብ አልበም ዜማና ግጥም ስራዎችን ጨምሮ የማስተሪንግ፤ የቅንብር እና የማሳተሚያ እና ሌሎች ህትመቶች በድምሩ 800ሺ ብር ወጭ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቅላፄ ባንድ አባል ሆኖ የሚሰራው እዮብ እድሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ የአባልነት መታወቂያ ከ1996 ዓም ጀምሮ የያዘ ሲሆን፤ ከታላላቅ ሙዚቀኞች እነ መሃሙድ፤ ፀሃዬ ዮሃንስ እና ጌታቸው ካሳ ጋር በመስራት ልምድ አለው፡፡ ሳክስፎን የሙዚቃ መሳርያን በቲኤምኤስ እና በጃዝ አምባ ተምሯል፡፡
አንድ ክለብ አንድ ቤተሰብ የሙዚቃ አልበም የመጀመርያው እትም 15ሺ ቅጂዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድዬም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ በ15 ብር በይፋ ለገበያ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ የአልበሙ ሽያጭ ሙለሙሉ ገቢው ለክለቡ እንደሚሆንም ታውቋል፡፡ የአልበሙ መታሰቢያነት  በ2005 ዓም የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታን ለማየት ሲጓዙ የመኪና አደጋ ገጥሟቸው ህይወታቸው ላለፈው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች  መሃሪ፤ ዞላና ቤቢ እንደሆነ ታውቋል፡፡

Read 1977 times