Print this page
Saturday, 01 July 2017 00:00

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ዋዜማ ላይ...

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ  8 ክለቦች ወደ የሚፎካከሩበት ሩብ ፍፃሜ  ለመግባት  ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ከአምናው ሻምፒዮን የደቡብ አፍሪካው ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ይፋለማል፡፡
በ2009 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላለፉት 4 የውድድር ዘመናት በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ  ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ እስከ 4ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ግጥሚያ 15 ጨዋታዎችን አድርጎ 7 ድል፤ 5 አቻ እና 3 ሽንፈት አስመዝግቧል፡፡ በ9 ጨዋታዎች ግብ ያልተቆጠረበት ሲሆን በአማካይ 1.2 ጎሎች በተጋጣሚው ላይ ሲያገባ 053 ጎሎች ደግሞ ይገባበታል፡፡
ከ2 ሳምንት በፊት በተደረጉት የ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ የምድብ ማጣሪያ 4ኛ ዙር ግጥሚያዎች  በምድብ ሶስት  ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ የተገናኘው ከዲ.ሪ ኮንጎው ኤጎስ ቪታ ክለብ ጋር ሲሆን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። በሌላ በኩል በዚሁም ምድብ በተደረገው 4ኛ ዙር ጨዋታ የቱኒዚያው ኤስፔራንስ በሜዳው የደቡብ አፍሪካ ሜመሎዲ ሰንዳውንስን ጋር ተገናኝቶ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በዚህ መሰረት ከምድብ ማጣሪያው 5ኛ ዙር ጨዋታዎች በፊት ኤስፔራንስ ዴቱኒስ በ4 ጨዋታዎች 10 ነጥብና 5 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ በመሪነቱ ቀጥሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4 ጨዋታ 5 ነጥብና ምንም የግብ ዕዳ ሳያስመዘግብ በ2ኛ ደረጃው ሲቀመጥ፤ የአምናው ሻምፒዮን ሜመሎዲ ሰንዳውንስ በ4 ጨዋታ 4 ነጥብና 3 የግብ ዕዳ በመያዝ ይከተለዋል፡፡ የዶ.ሪ ኮንጎው ኤሴስቪታ ስፖርት ክለብ በ3 ነጥብና በ4 የግብ ዕዳ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ይገኛል፡፡ ሳላዲን ሰኢድ በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ  7 ጎሎችን በማስመዝገብ፤ ኮከብ ግብ አግቢነቱን ከሚመሩት ተርታ መሰለፉም ብዙዎችን አስገርሟል። ከሳምንት በኋላ በሻምፒየንስ ሊጉ የምድብ ማጣርያ 5ኛ ዙር ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያስተናግደው የአምናው ሻምፒዮን ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ሲሆን በቱኒዚያ ደግሞ ኤስፔራንስ ከኤኤስ ቪታ ክለብ ይገናኛሉ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜመሎዲ ሰንዳውንስ በመጀመሪያ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተገናኙበት ወቅት 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሊግ ለተጨዋቾች ዝውውር ብዙ ገንዘብ በማውጣት፤ ምርጥ ወጣት ተጨዋቾችን በማሰባሰብ እና ከተቀናቃኝ ክለቦቹ ተጨዋቾችን በማስኮብለል የሚታወቀው ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ዓመታዊ ገቢው 6.9 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል። ባለፈው የውድድር ዘመን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሆን እስከ 640ሺ ዶላር ወጭ ማድረጉን የሚያመለክቱ መረጃዎች፤ በ2016 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ለመሆን ሲበቃ ከካፍ ያገኘው የገንዘብ ሽልማት 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነና የእግር ኳስ ፌደሬሽኑም 75ሺ ዶላር ማግኘቱን አውስተዋል፡፡ በተጨማሪ የደቡብ አፍሪካ ሊግን በማሸነፉ፤ የአፍሪካ ሱፕር ካፕ በማሸነፉ እና በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ በመሳተፉ በ2016 እኤአ እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ነበረው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድብ ማጣርያው 5ኛ ዙር ግጥሚያ በሜዳው ሜመሎዲ ሰንዳውንስን በማሸነፍ 8 ክለቦች ወደሚገኙበት ሩብ ፍፃሜ ውስጥ ከገባ በአህጉራዊ ውድድሩ የኢትዮጵያ የተሳትፎ ኮታ እንዲጨምር ያስችላል፡፡ ዘንድሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዳዲስ የታሪክ ምዕራፎች በመክፈት ተነቃቅቷል ማለት ይቻላል። የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ ተሳትፎው የመጀመርያው ነው፡፡ በተደራራቢ የጨዋታ መርሃ ግብሮች ተፈትኗል፡፡ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የቲቪ ቻናሎች ስርጭት አግኝቷል፡፡ ተጨዋቾቹ በአፍሪካ ደረጃ በቂ ትኩረት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ከሽልማት ገንዘብ የሚያገኘውን ድርሻ በአጠቃላይ በአህጉሪቱ እግር ኳስ ያለበትን ደረጃም አሳድጓል፡፡ ከሁሉም ደግሞ የክለቡ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ስታድዬም በማራኪ ድጋፎቻቸው እንዲደምቁ ማነሳሳቱ ይጠቀሳል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድቡ 5ኛ ዙር ጨዋታ  አዲስ አበባ ስታድዬም ላይ ሜመሎዲ ሰንዳውንስን ሲያስተናግድ ኡጋንዳዊውን ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦደንኩራ ሊያሰልፍ ይችላል፡፡ ኦደንኩራ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከኤስፔራንስ ጋር 0ለ0 በተለያዩበት ጨዋታ በጉልበቱ ላይ በደረሱበት ጉዳት ከጨዋታዎች ተገልሎ ቆይቷል፡፡  ሜመሎዲ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአፍሪካ ደረጃ 102ኛውን ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን  52 ድል፤ 22 አቻ እንዲሁም 28 ሽንፈት አስመዝግቧል፡፡

Read 1227 times