Sunday, 09 July 2017 00:00

በነጋዴዎች ላይ የተጣለው የገቢ ግብር ግምት በአስቸኳይ እንዲሻሻል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

     ሠሞኑን በከተማዋ ነጋዴዎች ላይ የተጣለው የገቢ ግብር ግምት የከተማዋን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የገለፁት “ሰማያዊ” እና “መኢአድ” የገቢ ግብር ግምቱ በአስቸኳይ እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ “በአዲስ አበባ ነጋዴዎች ላይ የተተመነው ከአቅም በላይ የሆነ የግብር ዕዳ እንዲሻሻል አጥብቀን እንጠይቃለን” በሚል መሪ ቃል በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የገቢ ግብሩ ግመታ እውቀትንና ክህሎትን ያጣመረ ዘዴን በመጠቀም በባለሙያዎች በአዲስ መልክ እንደገና እንዲሰራ ጠቁመዋል፡፡
አሁን በነጋዴዎቹ ላይ የተወሰነው የገቢ ግብር ዜጎች በሀገራቸው ነግደው ለማደር ያላቸውን ተስፋ የሚያሟጥጥና ለስደት የሚዳርግ፤ በስደት ላይ ያሉ ወገኖችንም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፍቃደኛ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
በተመሳሳይ ነጋዴዎቹ በተጣለባቸው ያልተመጣጠነ የግብር ዕዳ የተነሳ ከንግድ ስራ ለመውጣት በማሰብ የንግድ ፍቃዳቸውን ለመመለስ ያቀረቡት ጥያቄም በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
የንግድ ፍቃድ ለመመለስ የሚፈልጉ እስከ ጥቅምት 2010 ዓ.ም ድረስ እንዲቆዩ መደረጉ ያለምንም ስራ ተጨማሪ ግብር እንዲከፍሉ የሚያስገድድ በመሆኑ አሰራሩ ተቀባይነት እንደሌለውና አስቸኳይ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡

Read 3169 times