Print this page
Sunday, 09 July 2017 00:00

ሰሞኑን በአዲስ አበባ 5 ሰዎች በጎርፍ ተወስደዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

- የ ሦስቱ አስክሬን አልተገኘም ተብሏል
• ‹‹ከ18 አካባቢዎች ነዋሪዎችን ከጎርፍ አደጋ ማሸሽ ያስፈልጋል››

በአዲስ አበባ ሰሞኑን የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ 5 ሰዎች ተወስደው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በክረምቱ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው የተባሉ አካባቢዎች በጥናት መለየታቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ እሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ሰሞኑን በአዲስ አበባ የጣለው ዝናብ ያስከተላቸውን አደጋዎች በተመለከተ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሠጡት ማብራሪያ፤ ሰኔ 25 እና 26 ቀን 2009 ዓ.ም በመዲናዋ የጣለው ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ፤ የ5 ሰዎች ህይወት መቅጠፉንና የ3ቱ አስክሬን አለመገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
አንደኛው የጎርፍ አደጋ የደረሰው ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ፣ ሃና ማሪያም አካባቢ ሲሆን 4 ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ሲሞቱ፣ የሁለቱ አስክሬን ብቻ ሊገኝ ችሏል፡፡ የሁለቱን አስክሬን የማፈላለግ ስራ መቀጠሉንም አቶ ንጋቱ አስረድተዋል፡፡ ሌላኛው የጎርፍ አደጋ ቦሌ፣ ወረዳ 7 ጃክሮስ አካባቢ የተከሰተ ሲሆን አንዲት ሴት በጎርፉ መወሰዷንና አስክሬኑም አለመገኘቱ ተገልጿል፡፡
ከጎርፍ ጋር ተያይዞ በንብረት ላይ የደረሰው አደጋ እጅግ በርካታ መሆኑን የገለፁት አቶ ንጋቱ፤ በተደጋጋሚም በንብረት ላይ አደጋው እየደረሰ ነው ብለዋል፡፡
በክረምት ለጎርፍ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የታሠቡ አካባቢዎች ላይ ኮሚሽኑ ጥናት ማካሄዱን የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው፤ አካባቢዎችን ለአደጋው ባላቸው የተጋላጭነት መጠን በሶስት መክፈሉን ያስረዳሉ፡፡
ጥናቱ 18 የከተማዋ አካባቢዎች በጣም ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ተጋላጭ በመሆናቸው ነዋሪዎችን ከአካባቢዎቹ የማሸሽና ወደተለዋጭ ቦታ መውሰድ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ተረጋግጧል ያሉት ባለሙያው፤ 54 አካባቢዎች  ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው፣  34 አካባቢዎች ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆናቸው በጥናቱ ተጠቁሟል ብለዋል፡፡
በጥናቱን በመመርኮዝ የአደጋ መከላከሉን ተግባር እንዲያከናውን በከተማ ደረጃ ለተቋቋመውና በየወረዳው ንዑስ ኮሚቴዎች ላደራጀው የጎርፍ አስወጋጅ ቢሮ መቅረቡን የጠቀሱት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው፤ ቢሮው በዚሁ መሰረት በተለይ አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል በተባሉት 18 አካባቢዎች ላይ መፍትሄ ያበጃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የአካባቢዎቹን ስም መጥቀሡ በነዋሪዎች ላይ የስነ ልቦና ጫና ሊያሣርፍ ስለሚችል ከመግለፅ የተቆጠቡት አቶ ንጋቱ፤ የጎርፍ አስወጋጅ ቢሮ ዝርዝሩ ተሠጥቶታል፤ አስፈላጊውን ተግባርም ያከናውናል ብለዋል፡፡
የከተማዋን ጎርፍ ጉዳይ መላ ያበጃል ተብሎ የሚጠበቀው የጎርፍ አስወጋጅ ቢሮ ሃላፊን በስልክ አግኝተን ስለጉዳዩ  ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ስልኩ ባለመነሳቱ ሊሣካልን አልቻለም፡፡
የክረምቱ ዝናብ አዲስ አበባን ጨምሮ በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመቱን ብሄራዊ ሜትሮሎጂ በድረ ገፁ ያመለከተ ሲሆን አብዛኛውን የሃገሪቱ አካባቢዎችም ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ ቀድሞ ሊወጣ ይችላል ተብሏል፡፡





Read 4696 times