Sunday, 09 July 2017 00:00

“በግምት የሚጣለው ግብር ማን ላይ ሊጣጣ ነው?!”

Written by  ተአምር ተክለብርሃን
Rate this item
(5 votes)

   “የ50 ሣንቲም ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ሄደች”  አሉ፤ በመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ተስፋ አድርገው  ሿሿ የተሰራባቸው አንድ ጎልማሳ፤ መንግስት ያዘጋጀው “ሀገራዊ የተሀድሶ መድረክን”ተጠቅመው፡፡
እቺን ተረት በመድረኩ ላይ ስሰማት የ2009 ዓ.ም የመንግስት ሰራተኞችን የደሞዝ ጭማሪ ነገር ሊገልፅ የሚችል ሌላ ነገር ሁላ የሚያስፈልግ አልመሰለኝም፡፡
ተረቱን ስሰማ በምናቤ ዶሮዋ በቀኝ እግሯ እራሷን እየጠቆመች በማጓጓት፣ የመንግስት ሰራተኞችን ነባር ደሞዝ (ጭማሪውን ጠቅልላ እንዳትወስድ ከየት አግኝታው) በግራ እግሯ በታሰረ ገመድ ላይ እየጎተተች ስትሄድ ትታየኛለች፡፡
የ2009ኙ የደሞዝ ጭማሪ እጄ እስከገባበት ቀን ድረስ መንግስት ከአፉ አምልጦት የተናገረ ሁላ ነበር የመሰለኝ። እንደዛ ባይሆንማ ስለ ደሞዝ ጭማሪው እርግጡን ለማወቅ እንደዛ ጊዜ ባልፈጀብን ነበር፡፡ እኛም ጭማሪው ቀርቶ ይሆን፣ ይመጣ ይሆን እያልን በጉጉትና በሰቀቀን ባልከረምን፡፡
በወቅቱ ስለ ደሞዝ ጭማሪው፤ “የእርከን ማስተካከያ ነው አልኩ እኮ፣ አትሰሙም እንዴ?” ሲል ነበር መንግስት (..ይቅርታ የእርከን ማስተካከያ እያልኩ ለመቀጠል እሞክራለሁ ከቻልኩ) ታዲያ በወቅቱ ጭማሪው ሲዘገይ፤ “መንግስት ከጥር አንድ ጀምሮ የእርከን ማስተካከያ አደርጋለሁ አለ እንጂ በ2009 ጥር ይሁን ወይም በ2025 ሀገሪቷ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ስትመደብ፣ ያኔ አንደኛዬን ጥር 1 ቀን ደሞዝ እጨምራለሁ ይበል ብዬ መጨነቅ የለብኝም” እያልኩ አስብ ነበር፡፡ (በሰዓቱ ስንት ኪሎ ቀንሼ እንደነበር እኔ ነኝ የማውቀው..)
ቢሆንም ከጥር አንድ ጀምሮ የሚለው መረጃ ከደሞዙ ቀድሞ ወሬው እንደ ወረርሺኝ በሀገሪቷ በመንሰራፋቱ (ግልፅነትና ተጠያቂነት ከማስፈን አንፃር) እንደ ተራቹ ግለሰብ ገለፃ፤ የነጋዴ ሲሳይ አድርጎን ነበር፡፡ እናም ነጋዴው እቺን እድል ተጠቅሞ፣ በጀሶ እንጀራ ሲያደርቀን ቆይቶ፣ ባልበላነው ደሞዝ ጭማሪ ሲያቃጥለን መሰንበቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ (አልረሳውም ስቀልድ ነው) ብቻ ነጋዴና ኪራይ ሰብሳቢ ማለቴ አከራዮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሲጥሉብን ነበር፡፡ (ነጋዴዎች ስል በጅምላ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ)
በጭማሪ ተስፋ ላይ እንዲህ ኑሮ ከተወደደ፣ ገንዘቡ  ጥር አንድ ባይሆንም የደረሰው ወር ላይ የምር እጃችን ሲገባ ለመገብየት አቅማችን የሚፈቅደው የጀሶ እንጀራ እና ኮንዶም ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፡፡ (ያው ኮንዶም በዲኬቲ ኢትዮጵያ አማካኝነት በነፃ ይታደላል፤ ሱቅ ላይም ቢሆን አቅም አይጠይቅም በሚል ነው) ከዚህ በኋላ ኮንዶሚኒየምና ሰፊው ህዝብ  በድጎማም ቢሆን አይደራረሱም ብዬ ነው፡፡ (ተመዝግቦ አየሁሽ አይነት ጫወታ ለመጫወትና ባለሀብቱ ሲያስመርቅ ጥሪ ተጠርቶ ለማየት ካልሆነ)
ነጋዴ “ጭማሪ” የሚባል ነገር ሲሰማ ጠላት ሀገርን የወረረ ይመስለዋል መሰለኝ ሆ ብሎ ይነሳል፡፡ በደህናው ጊዜ ደህና አድርጎ በጀሶ እንጀራ አድርቆናል፤ ይቺን ወሬ ሲሰማ ነዳጅ ሳይጨምር ያቃጥለናል፡፡ ብቻ ደሞዙ ሲጨመር ከነጋዴ ጋር ብጋራህ ተባብለን እኩል እንደተካፈልን ታውቃላችሁ፡፡ ሳስበው ሳስበው እኛ ኢትዮጵያውያን ወሬያችን ስለ ፍቅር ተግባራችን ግን ለየቅል ይመስለኛል፡፡
ህዝብ ተዋዶ ተፋቅሮ የሚኖርባት ሀገር ኢትዮጵያ ከየት እንደተመሰረተች ይገርመኛል፡፡ ወይም በልቦለድ አሊያም በፊልም ታሪክ ያለች እስኪመስለኝ ያለ ጠላት መኖር የማንችል ህዝብን ተሸክማ፣ ወገን ለወገን ከማሰብ ይልቅ ከራስ በላይ ንፋስ ሲያልፍም ሰማይ ብቻ የሚመስለው ህዝብ ጋር እየኖርን ስብከታችንና ህይወታችን ይምታታብኛል፡፡
ያው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊው ነጋዴንና ሰፊው ህዝብን የሚያገናኘው ዜግነት አሊያም አንድነት ሳይሆን የገዢና ሻጭ ግንኙነት ብቻ እየመሰለኝ ነው፡፡ የመተሳሰብ ሃይኮፒ እንደ ቻይና እቃ ኢትዮጵያን ወሯታል፡፡ ቻይና እንደ ሰማሁት ከሆነ፤ ሃይኮፒ እና ኦርጂናል እቃ የምትሸጥለትን ዜጋዋን አይደለም ሀገር ትለያለች አሉ፡፡ when I was in china ብዬ እንዳላወራ ለ1 ሳምንት እንኳ የመሄድ እድል አላጋጠመኝም ግን ሰምቻለሁ፡፡ ነገሩ ለአንድ ሳምንት “ብላክ ቻይና ውጡልኝ” የሚል አዋጅ ካላወጣችና ነይ ተብዬ በኢቢሲ ካልተለመንኩ አልመጣም ነበር። ይሄኔ እኮ ኑ ብሎ ከሚጣራው ውስጥ  “ወገን” ሲሄድ አራጣ አበድሮ የላከ  አይጠፋም፡፡ (በኢቢሲ ኑ እያሉ ተደርድረው ወገን ከሳኡዲ የሚጠሩት አርቲስቶች፤ ጎን ለጎን ምን እንደግፋቸው ብለው እንዲያስቡ ልቦና ይስጣቸው!)
ኢትዮጵያ ውስጥ ነጋዴ ወገኑን እንደ ደንበኛ ሳይሆን የሚመለከተው አዲስ ነገር እንደ መሞከሪያ አይጥ ሆኗል። ስለምንበላው ነገር ምንነት እራሱ የምናውቀው የሆነ ግዜ “ወንጀለኞቹ ተያዙ” ተብሎ ሲወራ ነገርዬውን ሰውነታችን ከተላመደው በኋላ ነው፡፡ አሁን አሁንማ ሳስበው “ነጋዴዎች” ተሰብስበው፤ “አንድ ፈረሱላ ጤፍ ከስንት ፈረሱላ ጀሶ ጋር ብንደባልቅ ትርፋማ እንሆናለን?” ብለው የሚማከሩ ሁሉ ይመስለኝ ጀምሯል፡፡ (አንዳንድ ነጋዴዎች እያላችሁ አንብቡት)
ከመሀል አንድ ህሊና ያለው ነጋዴ ደሞ ተነስቶ፤”ፍትሀዊ መሆን አለብን፤ ጤፍ ውስጥ ስንደባልቅ በርበሬስ? እግረ መንገዳችንን በአንድ ፈረሱላ በርበሬ ምን ያህል የተፈጨ ሸክላ አሊያም ቀይ አፈር መደባለቅ እንዳለብን መመካከር ያስፈልጋል” የሚል ሃሳብ የሚሰነዝር ይመስለኛል፡፡
ብቻ ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡትን ነገር ዘይት ፣ቅቤ ሃሃ--- ዶሮ (የሞተ) በማቅረብ ብቻ--- ማንኛውንም ነገር በዚህ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ መድረክ ይዘው ተወያይተው የሚወስኑ ---  እናም በሰው ጤና ላይ ወጪ ሳያወጡ ትርፋማ የመሆን ስልት እየተከተሉ ያሉ ምናምን ሁሉ እየመሰለኝ መጥቷል፡፡ 1ለ5 አደረጃጀት ሁላ ሳይኖራቸው ይቀራል?
ብቻ የተጠቃሚና የተጎጂ ግንኙነት ተንሰራፍቷል። እንዲህ በባዕድ ነገር ሽያጭ ጉድ የሰሩን ሳያንስ የደሞዝ ጭማሪን ሲሰሙ ለምን እንዲህ የሚይዙት የሚጨብጡት እንደሚጠፋቸው ግርም ይለኛል፡፡ “ነጋዴውም እኛው፣ ባለመብቶችም እኛው” የሚል ፈሊጥ ይዘው ይፈልጡናል። የደሞዝን ሰሞን እንዲህ ለመንደድ ዝግጁ ባደረገን የሰጋቱራ ልዩ እንጀራ ተመቻችተን ስንቃጠል ከረምን፤ አሁን ደሞ ምን ብሰማ ጥሩ ነው? ለንግዱ ማህበረሰብ የቀን ገቢ ተመን ተሰራ፤ እናስ በቅርቤ ያለ ጉልት ቀመስ ኮንቴነሮች የመጣባቸውን የቀን ተመን ሰማሁ፡፡ እውነት እላችኋለሁ “እሰይ” ብዬ ተደስቼ አልያም፤ ለጌታም ጌታ አለው ብዬ አንጀቴ ቂቤ ጠጥቶ አይደለም፤ ብቻ ሳቄን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ ለምን አትሉም? እንደው የቀን ገቢ ተመን ተብሎ የመጣባቸውን ገንዘብ በወር ማግኘት ከቻሉ፣ ከምላሴ ላይ ፀጉር (አትጓጉ፤ ምላሴ ላይ ፀጉር የለም) ነጋዴው በተቻለው አቅም እቃ አሽሽቶ ለተመኑ የሚመጡ እንግዶቹን በባዶ ሱቅ በተገቢው ቢቀበልም ተማኞቹ እቴ…..
ግን እኔን የሚያሳስበኝ የቀን ተመንን ተመርኩዞ የሚጣለው ግብር ማን ላይ ይጣጣል የሚለው ነው፡፡ እሱ እስኪደርስ እንደለመድኩት መሳቀቁ ጀምሮኛል፡፡ የቼዝ ጠጠር አደረጉን እኮ መሀል ቤት…
ወደ መንደሬ ጉልት ቀመስ ኮንቴነር የንግድ ቦታ ስገባላችሁ ---- ሃሃሃ ሳቄን ለመቆጣጠር አቅሙ የለኝም፡፡ እናላችሁ ከአንዲት እናት ልጀምርና ሴትየዋ ውፍረታቸውን ልነግራችሁ አልችልም (ስለ ቀን ተመን እንጂ ስለ ውፍረታቸው ምን አገባሽ አትሉኝም!) የቀን ተመኑ የመጣላቸው ከውፍረታቸው ጋር በተያያዘ እንጂ ቀቅለው ከሚሸጡት በቆሎ ጋር በተያያዘ ስለማይመስል ነዋ፡፡
እኝህ እመቤት ክረምትን ጠብቀው በቆሎ ቀቅለው ይሸጣሉ፤ ከዛም ባለፈ አልፎ አልፎ በርበሬ ሲሸጡ አውቃለሁ እዛ ስለማዘወትር (ደሞ እንዲህ ስላችሁ ሳታዩ የበርበሬ ማሳ አላቸው ብላችሁ እንዳትደመድሙ፤ ነገሩ ያዩትም እንዲህ እየተመኑ…እንደፈለጋችሁ ገምቱ) ስለ በርበሬው ስታስቡ ግን ጉሊት ላይ ተመድቦ የሚሸጥ በርበሬ አስቡ እና በቀን ስንት ያስገባሉ ተብለው ደብዳቤ ቢደርሳቸው ጥሩ ነው? 3ሺብር! ሃሃሃ በዚህ የሚበቃ መሰላችሁ፤ የንግድ ስማቸው የደረቅ ምርቶች ማቀነባበርና መፈብረክ! አስቡት-- ይሄ መፈብረኪያ በቀን 3ሺ ብር ለማስገባት 750 የተቀቀለ በቆሎ መፈብረክና ገዢዎችን ማቀነባበር ያለበት ይመስለኛል፡፡
አንድ የተቀደደ አልባሳትን የሚጠግን ደግሞ እዛው መስመር አለላችሁ፤ ተማኞቹ ከልብስ ስፌት ትመና ሲመለሱ ወደሱ ይምጡ አልያም የልብስ ስፌት መኪናው ከአይሱዙ ገልባጭ መኪና ጋር ይመሳሰልባቸው አላውቅም፤ የልብስ ጥገና የሚሰራውን ሰውዬ በቀን 1800 ብር ታስገባለህ ብለው እርፍ፡፡ እንደሚመስለኝ ግን እነሱ ቁጭ ብለው ሳለ፣ አንድ በ20 ብር ሱሪውን እያስጠገነ ያለ የመንግስት ሰራተኛ ገጥሟቸው የሱን ደሞዝ ሰምተው የገመቱ  ይመስለኛል፡፡ (ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው በወር የሚያገኘውን ነው ያልኩት፤ አንድ ነጋዴ ይሄን አንብቦ በቀን ይሄን ያህል ብሎ ብቻ የሰጋቱራ ልዩ እንጀራውን እላይ እንዳይሰቅላት)
ብቻ ተዟዙሬ ባላይም የዛች መንደር የቀን ገቢ ትመና በጣም አዝናንቶኛል፤ ሁሉንም ብነግራችሁ ደስ ይለኝ ነበር፤ግን ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡ መንግስት ምን አስባለኝ… መሰላችሁ? ገቢዎችና ነጋዴዎች አይጥና ድመት በተጫወቱ ቁጥር ቀዳማዊ ተጎጂ እመቤቶች (ግለሰቦች) እኛ ነን፤ በሚያቀርቡልን እህል ውስጣችንን፣ በመሳቀቅ ቆዳችንን ጨረስን፡፡


Read 1900 times