Sunday, 09 July 2017 00:00

የእናቶችንና የሕፃናትን ሕይወት እየለወጠ ያለው “ሙዳይ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   - 30 ተማሪዎችን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አስመርቋል
                          - የዛሬ ሳምንት 100 እናቶችን በተለያየ ሙያ አስመርቋል
                          - በአሁኑ ወቅት ከ950 በላይ ሰዎች በቀን 3 ጊዜ ምግብ ያቀርባል
                       
     የአብስራ፣ እጆቿ ደረቷ ላይ ሆነው እግሮቿ ተጠላልፈው ነበር ከእናቷ ማህፀን የወጣችው፡፡ ስለዚህ እጅና እግሯን ማንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመጣች በኋላ ወ/ሮ ሙዳይ ተቀብላ እያሳከመች፣ ልዩ መቀመጫ ወንበር አሰርታላት፣ ዩኒፎርም አልብሳት፣ የትምህርት መሳሪያ አሟልታላትና እየመገበች እያስተማረቻት ትገኛለች፡፡ የአብስራ እጆቿ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ የምትጽፈው በጥርሷ ነው፡፡ በጥርሷ የሚያምር ጽሑፍ እየጻፈች ዘንድሮ በ11 ዓመቷ ከመዋለ ህፃናት ትመረቃለች፡፡
“ድሃ ስለሆንኩ እሷን የግል ት/ቤት ከፍዬ ማስተማር አልችልም፡፡ ብችልም የሚቀበላት ት/ቤት የለም” ትላለች፤ እናትና ሞግዚቷ ወ/ሮ ገነት አዱኛ። “ያለኝ አማራጭ ልጅቷን ወደ መንግስት ት/ቤት መውሰድ ነበር፡፡ እዚያም ብወስዳት ለእሷ የሚሆን አስተማሪና ልዩ መቀመጫ የለንም፡፡ በአጠቃላይ ለእሷ የሚሆን የልዩ ፍላጎት ማስተማሪያ ስለሌለን አንቀበላትም” ብለው መለሷት፡፡ ስለዚህ እቤት መልሰናት በር ዘግተንባት ነበር ወደ ስራ የምንሄደው በማለት የልጇን ችግር ገልጻለች፡፡
ወ/ሮ ገነት አዱኛ አዲስ አበባ ውስጥ አንቆርጫ በሚባል አካባቢ ነዋሪ ነበረች፡፡ አብስራን የወለደችው የካቲት ሆስፒታል ነበር፡፡ ሐኪሞቹ ሲያዩዋት ሪፈራል ብለው ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጻፉልኝ፡፡ እዚያም ከአንድ ወር በኋላ አምጫት ብለው መለሷት። ጊዜው ሲደርስ ወሰድኳት፡፡ 15 ቀን አስተኝተው ኦፕራሲዮን አደረጓት፡፡ ከዚያም ጄሶ ታሰረላት፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ለ3 ወር 24 ሰዓት የሚደረግ ጫማ አሰሩላት፡፡ እሱም ምንም አላሻላትም፡፡ በመጨረሻ ሙከራችን ምንም ተስፋ የለውም” በማለት እንዳሰናበቷት በሀዘን ገልጻለች፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር፤ ጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ በልመና የተሰማሩና በሴተኛ አዳሪነት ሕይወታቸውን ሲገፉ የነበሩትን እናቶች፣ ከእነልጆቻቸው ከዚያ አረንቋ ውስጥ አውጥቶ አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ ደርጅት ነው። እናቶችን ከነበሩበት አስከፊ ህይወት አውጥቶ መጠለያ በመከራየት፣ ሙሉ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው፣ በተለያዩ ሙያዎች፣ በሽመና፣ በሸክላ ስራ፣ በጥልፍ፣ በልብስ ስፌት፣ በዕደ ጥበብ ስራዎች አሰልጥኖ ከተመጽዋችነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ይገኛል፡፡
ልጆቻቸው ሙሉ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው፣ ዩኒፎርም ተሰፍቶላቸው፣ የትምህርት መሳሪያዎች እየተሰጣቸው፣ ቁርስ፣ ምሳና እራት እያበሉ እንደየትምህርት ደረጃቸው ሙሉ ወጪያቸው ችሎ፣ በነፃ ከመዋለ ህፃናት እስከ 8ኛ ክፍል ግቢው ውስጥ በሚገኘው “ፍሬሽ ኤንድ ግሪን አካዳሚ” እያስተማረ ነው፡፡ ከ9ኛ ክፍል እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በአቅራቢያው ባሉ ት/ቤቶች እንዲሁም በተመደቡባቸው የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ወጪያቸውን በመሸፈን እንዲማሩ ያደርጋል፡፡
ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ለ430 እናቶች፣ ለ50 አካል ጉዳተኞች፣ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ህፃናትና ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፣ በቀን ሶስት ጊዜ ቁርስ ምሳና ራት እንዲበሉም እያደረገ ነው፡፡ ማኅበሩ ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል በተለያዩ ሙያዎች፡- በሸክላ፣ በሽመና፣ በዕደ ጥበብ፣ በጥልፍ፣ በልብስ ስፌት ያሰለጠናቸውን 100 እናቶችን ያስመረቀ ሲሆን በድጋፍ ስራ ላይ በቆየባቸው 17 ዓመታት ከ1000 በላይ ለሆኑ እናቶች የተለያየ ሥልጠና ሰጥቶና ራሳቸውን ችለው ከማኅበሩ እንዲወጡ አድርጓል። 30 ተማሪዎችን ወጪያቸውን ችሎ በማስተማር፣ ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አስመርቋል። ለ1500 ሰዎች የትራስፖርትና ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎችን ሸፍኖ፣ ወደመጡበት የመኖሪያ አካባቢ እንዲመለሱ ማድረጉም ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል 100 እናቶች በተመረቁበት ወቅት ጥቂቶቹን አነጋግረን ነበር። ዘሪቱ ራፍዬ በወሎ ክፍለ ሀገር የአማራ ሳይንት አካባቢ የቤት እመቤት ነበረች፡፡ አንድ ወንድ ልጅ እንደወለደች ባሏ ይሞትባታል፡፡ ቸግሯት አዲሳባ ወዳሉት ዘመዶቿ ዘንድ ከመጣች 16 ዓመት ሆኗታል፡፡ ገቢዋ በየሰው ቤቱ ልብስ እያጠበችና እንጀራ እየጋገረች የምታገኘው ትንሽ ገንዘብ ነበር። በዚህ መኸል ሌላ ወንድ ተዋውቃ ሴት ልጅ ወለደች። ሁለት ልጆች ማብላቱ ማጠጣቱ ማልበሱ፣ ማስተማሩ በአጠቃላይ ተንከባክቦ ማሳደጉ ትልቅ ፈተና ሆነባትና በጣም ተቸገረች፡፡
ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመጣች አንድ ዓመት ሆኗታል፡፡ አመጣጧም ሰው ጠቁሟት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ሰዎች “ኮተቤ አካባቢ ሙዳይ በጎ አድራጎት የሚባል አለ፡፡ እንኳን አንቺን እንዲህ የተቸገርሽውን ቀርቶ ሌላውንም ይቀበላሉ፡፡ ሄደሽ ጠይቂ” አሏት፡፡ ሄዳ ጠየቀች፡፡ ወ/ሮ ሙዳይም ልታግዛት ፈቃደኛ ሆና ተቀበለቻት፡፡ እሷና ሁለቱ ልጆቿ በሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር መኖር ከጀመሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡
“እዚህ ከመጣሁ አንስቶ ድጋፍ የሚደረግ ነገር ሁሉ ምንም የቀረብኝ የለም፡፡ በጣም ታምሜ ነበር። አሳክማ ለልጆቼ እንድተርፍላቸው አድርጋኛለች። ልብስ በዓመት ሁለቴ ይሰጠናል። በቀን ሶስቴ እንበላለን፤ ቤት ተከራይታልኛለች፡፡ እዚሁ እሰራለሁ፣ በሽመና ሰልጥኜ ባለፈው ሳምንት በሻርፕ ስራ ተመርቄያለሁ፡፡ ሁለቱም ልጆቼ ጫማና ዩኒፎርም ተገዝቶላቸው፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው፣ በቀን ሦስቴ እየተመገቡ፣ 6ኛና 4ኛ ክፍል እየተማሩ ነው፡፡ ተመስጌን ነው የምለው” በማለት ገልጻለች፡፡
የ27 ዓመቷ ራሄል ሽፈራው ትውልዷ ጅማ ነው። ወደ አዲስ አበባ የመጣችው አክስቷ ጋ ሆና ለመማር ነው። አክስቷም እያሳደገች አስተማረቻት። 10ኛ ክፍል ደርሳ ስትፈተን ውጤት ሳይመጣላት ቀረ፡፡ ይኼኔ ከአክስቷ ተጣልታ ከቤት ወጣች፡፡ ካፌ ውስጥ ተቀጥራ መስተንግዶ እየሰራች ስትኖር፣ ከአንድ ወንድ ጋር ተዋውቃ፣ በጓደኝነት አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ አረገዘችና ልጅ ወለደች፡፡ ልጅ ተወልዶ ዓመት ሲሞላው ባል ጥሏት ጠፋ፡፡
ያለ አባት ለብቻልጅ ማሳደግ ከባድ ፈተና ነው ትላለች ራሄል፡ “ትልቅ ስቃይና ችግር ነው ያየሁት። ለልጁ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሁሉ ማድረግ አቅቶኝ ትልቅ ችግር ውስጥ ገባሁ፡፡ አሰሪዬ የቤት ኪራይ ትከፍልልኝ ነበር፡፡ እኔ ገንዘብ ለማግኘት ልብስ አጥብ ነበር፡፡ የማገኘው ገንዘብ ትንሽ ስለነበረ ከአቅሜ በላይ ሆነብኝና ልጄን ማሳደግ አቃተኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች “የተቸገሩ የሚረዳ እንዲህ የሚባል ድርጅት አለ፡፡ እዚያ ሄደሽ ሞክሪ” አሉኝ፡፡
“ይኼ የሆነው በ2005 ነበር፡፡ ሙዳይ በጎ አድራጎት መጥቼ ችግሬን ነግሬ፣ እንድትረዳኝ ወ/ሮ ሙዳይን ጠየኳት፡፡ እሷም ቤቴን ሄዳ አይታ፣ ስለ አኗኗሬ ሰዎች ጠይቃ ተቀበለችኝ፡፡ ልጄ አሁን 4 ዓመቱ ነው፣ መዋለ ህፃናት ገብቷል። እኔን እያሰለጠነች ቤት ተከራየችልኝ፤ ቀለቤንና ወጪዬን የምትችለው እሷ ናት፡፡ ባለፈው ሳምንት የተመረቅሁት በአበባ ማስቀመጫ ስራ ነው፡፡ ሌሎች ሙያዎችም ለማወቅ እጥራለሁ፡፡ ትልቁ ሙያዬ ግን የተመረቅሁበት ነው” በማለት ታሪኳን ገልጻለች፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ቋሚ ገቢ የለውም፡፡ የገቢው ምንጮች የተለያዩ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች የሚያደርጉለት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ከመንግስትና ከግል ተቋማት የሚወሰድ ብድር ነው፡፡ እናቶች የሚሰሯቸው የተለያዩ የእጅ ስራዎች ተሸጠው አነስተኛ ገቢ ያስገኛሉ። ከምንም በላይ ከማኅበሩ ጎን በመሆን በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ታዋቂ ሰዎችና ግለሰቦች ሚና ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡ ስለዚህ “የግል ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ የመንግስት መ/ቤቶች፣ … አቅማችሁ በቻለው ሁሉ ድጋፍ እንድታደርጉልን በተረጂዎቹ ስም እጠይቃለሁ” በማለት ተማፅናለች፤ የማኅበሩ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፡፡    

Read 657 times