Sunday, 09 July 2017 00:00

የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ

Written by  ከኑረዲን ዒሣ፤ ዒሻራ የሥነ ግጥም ስብስብ
Rate this item
(4 votes)

   (በህገ መንግስት ጉባኤ ውስጥ የነበረ ክርክር)
                     
     “አንድ ትልቅ ሀገር በትንሽ መንደር ላይ፣
ተጣጥፎ ተኝቶ፣
 ሲጨናነቅ አየሁ፣ ለእግሮቹ መዘርጊያ፣
 ሽራፊ ቦታ አጥቶ፡፡”
በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ካሉት ግልጽነት የሚጎድላቸው አንቀጾች መካከል በአንቀጽ 49 (5) ላይ ያለው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ስለሚኖረው ልዩ ጥቅም የሚመለከተው ድንጋጌ አንዱ ነው፡፡ ንዑስ አንቀጹ የያዘው ሐሳብ እንዲህ የሚል ነው፡-
“የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፤ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡”
ሕገ መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ሕግ ይወጣል ቢልም፣ ለሃያ አምስት ዓመታት ያህል ሳይወጣ ቀርቶ ለብዙ ሐሜቶችና አለመግባባቶች ምክንያት ሆነዋል፡፡ በሕገ መንግስቱ ጉባኤ ላይ ብዙ ጉዳዮች በዝርዝር ሕግ ይወሰናል እየተባለ ታልፈዋል። ታዲያ ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ በወቅቱ አንድ ትንቢት የሚመስል ነገር ተናግረው ነበር፣ መንግሥት እምነት ሊጣልበት የማይችል መሆኑን ከረጅም የሕይወት ልምዳቸው እንደተገነዘቡ ገልፀው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ “ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ተብሎ ቢቀመጥ እንኳን ሕጉ መውጣቱና የሚወጣው ሕግም ለሕዝቡ የሚስማማ መሆኑ ስለማያስተማምን ይኼ “ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” የሚሉትን ነገር እንዲቀር ጠይቀው ነበር፡፡
በዚህ አንቀፅ ላይ በሕገ መንግሥት ጉባኤው ውስጥ የነበረው የክርክር መንፈስ እንደ ሚከተለው ይመስል ነበር። ለምሳሌ በወቅቱ ከፍተኛ የህወሀት ባለስልጣን የነበሩት፣ አቶ ሙሉጌታ ገ/ሕይወት በሰጡት ማብራሪያ፤የፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ መሆኗን፣ ከተማዋ እንደ ክልል ባትወሰድም በዝርዝር ሕግ የሚወሰን ራሷን በራሷ የማስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግሥት እንደሚሆን ካብራሩ በኋላ፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ከክልሉ ጋር ሊያገናኙ የሚችሉ በርካታ የአገልግሎት፣ የአቅርቦትና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን የሚመለከቱ ችግሮች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ፣ እነዚህን ችግሮች ሊፈታ በሚችል መልኩ፤ ኦሮሚያ ሁለቱን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ ያለው ልዩ ጥቅም እንደሚከበርለትና ይህም በዝርዝር ሕግ እንደሚወሰን መቀመጡ አግባብ ነው ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የተቃውሞ ሐሳብ ያቀረቡት ከአዲስ አበባ በግል የተወከሉ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ አንቀጹ ግልፅነት የሚጎድለው ከመሆኑም በላይ ተገቢነቱንም ጥያቄ ውስጥ አስገብተው ተከራክረዋል፡፡ ለምሳሌ አቶ አዳሙ ደገፉ በሰጡት አስተያየት፣
“አዲስ አበባ ከሁሉም አካባቢዎች የሚመጡ ብዙ ብሔረሰቦች መኖሪያ በመሆኑ፣ ቢያድግ ለጥቂቶች ሳይሆን ለሁሉም የጋራ ሀብት መሆን የሚችል ሆኖ ሳለ፣ ለኦሮሚያ ክልል ብቻ ነጥሎ የተለየ ጥቅም ያገኛል መባሉ፤ ይህ የተባለው ጥቅም ደግሞ ግብርም ሊሆን ስለሚችል፣ እንዲህ ዓይነቱ አንቀጹ በሕገ መንግሥቱ መቀመጡ አግባብ ስለማይሆን እንዲወጣ” አበክረው ጠይቀው እንደነበር በቃለ ጉባኤው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል የሆኑትት አቶ ተሰማ ጋዲሳ ከላይ ለቀረበው ሐሳብ የተቃውሞ መልስ የሰጡ ሲሆን የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይጠበቃል ሲባል በጽሕፈት ቤት አቅርቦትና በመሳሰለው እንጂ እንደ ተባለው በግብር የመሰብሰብ ጉዳይ እንዳልሆነ፣ አዲስ አበባ ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት፣ በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የሚስተናገዱባት ከተማ ብትሆንም፣ ከተማዋ ያለችበት መሬት ግን የኦሮሚያ መሆኑን የመሰረቷት ነፍጠኞች ሳይቀር እንደሚገነዘቡት ጠቅሰው፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ እምብርት በመሆኗ የክልሉ ምክር ቤት ሌላ ውሳኔ ካልወሰነ በስተቀር የፌዴራሉ መንግሥት ብቻ ሳትሆን የክልሉም ርዕሰ ከተማ መሆኗን፤ ከዚህም ባሻገር በከተማዋ መስፋፋት ረገድ ከኦሮሚያ ጋር የተቆራኘች በመሆኑ ነው ይህ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ድንጋጌ ያስፈለገው ብለዋል፡፡
ከአማራ ክልል የተወከሉት አቶ ደመቀ መኮንን በሰጡት አስተያየት ደግሞ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ በልዩ ሁኔታ ዝርዝሩ በሕግ የሚወሰን ራሱን የማስተዳደር ሥልጣን መሰጠቱና ነዋሪዎቹም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጥንቅር እንደመሆናቸው መጠን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው መደረጉ አግባብ እንደሆነ በመግለፅ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም የሚገባው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ እንደ ሆነና የከተማዋ መስፋትም የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚነካ በመሆኑ እንደሆነ፣ ከዚህም በላይ ደግሞ፣ ቀደም ሲል እንደተባለው በተፈጥሮ ሀብትና በመሳሰሉት ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ በረቂቁ እንዳለው መቀመጡ ለሁለቱም የልማት እንቅስቃሴ የሚበጅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም የአቶ አዳሙ ደገፉን ሐሳብ ተቃውመው አስተያየት የሰጡት አቶ ሙሉጌታ ገ/ሕይወት፣ “አዲስ አበባ የሁሉም ናት፤ ዕድገቷም የሚጠቅመው ለሁሉም ነው” የሚለው አባባል በጥቅሉ ሲታይ የሚጠቅም እንደሚመስል፣ ግን ችግር ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ያለመግባባቶችና የጥቅም ግጭቶች ለማስወገድ መሰል ነገሮች መልክ የሚይዙበትና የሚፈቱበት፤ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም የሚጠበቅበትን መንገድ የያዘ ዝርዝር ሕግ እንደሚወጣ መደንገጉ አግባብ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን እንደሚሉት፣ ከሆነ ደግሞ፣ አንቀጹ በራሱ ግልፅነት የሌለው ከመሆኑም በላይ፣ ባለፉት የሩብ ክፍለ ዘመን የኢሕአዴግ ዘመን ይወጣል የተባለው ዝርዝር ሕግ ያለመውጣቱ፤ የኦሮሚያ ርዕሰ ከተማነት ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እንዲዛወር መደረጉ፣ እንደገና ደግሞ የቅንጅት በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ማሸነፍን ተከትሎ እንደገና ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ መደረጉ፣የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤቶች ሳይመክሩበት የፌደራል መንግሥት አዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች በኢኮኖሚ በአስተዳደር የሚያስተሣሥር ነው የተባለለት ማስተር ፕላን ማውጣቱ፣ ይህን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ሲታይ ችግሩን ምን ያህል እንዳወሳሰበው መረዳት የሚቻል ነው፡፡
ችግሩ ያለው ሕገ መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ካሰፈረው ጽንሰ ሀሳብ ጀምሮ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ። ለምሳሌ አቶ ተስፋዬ ንዋይ፤ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ እንደሚኖረው ቢደነግግም “ልዩ ጥቅም” ለሚለው ሐረግ የተሰጠው ትርጉም ግን የለም ይሉና ከልማዳዊው የሕግ አተረጓጎም በመነሳት ልዩ ጥቅም የሚለውን ሀረግ  እንደሚከተለው ትርጓሜ   ሰጥተውታል፡-
“ልዩ የሚለው ቃል ከአንድ ነገር ጋር የተያያዘ እና ከተለመደው ወጣ ያለ ሁኔታ የሚገልፅ ሲሆን ጥቅም የሚለው ደግሞ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው አንድ ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችለውን መብት የሚያመለክት እንደሆነ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ስለሆነም ክልላዊ መንግሥቱ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለው ሲባል፣ ተለይቶ የሚታወቅ ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሚያጎናጽፍ ጥቅም አለው ተብሎ ይወሰዳል፡፡”19
በሕገ መንግሥቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሊኖረው የሚገባው ልዩ ጥቅም “አገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ነው” ቢልም፣ “የመሳሰሉት” የሚለው አገላለፅ ድንበሩ የት ድረስ ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሆነ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ይናገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ በሕገ መንግሥት ድንጋጌ ውስጥ “ሌሎች”፣ “ተመሳሳይ”፣ ወዘተ. የሚሉ እጅግ ጥቅል የሆኑ ድንጋጌዎችን ማስቀመጥ ያልተለመደ ከመሆኑም በላይ፣ በዚህ ምክንያት የተሰጠው ልዩ ጥቅም ሊንጸባረቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምንነት በግልፅ ለመረዳት እንደሚያስቸግር አብራርተዋል፡፡
ይህ ሁኔታ አስቀድሞ ሕጋዊ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ ከዚህ የባሰ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ለመረዳት ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ ይህ ልዩ ጥቅም የተባለውን ነገር ከሚገመተው በላይ በመለጠጥ በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልበት ሁኔታ ቢፈጠር ወይም የአዲስ አበባ አስተዳደር በዙሪያው ያሉትን ነዋሪዎች ግምት ውስጥ የማያስገባ የቆሻሻና የተረፈ ምርት አወጋገድ ሁኔታን ቢከተል ጭቅጭቅ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ባለው የገዥው ፓርቲ ጥብቅ ቁጥጥርና የተማከለ አሠራር ችግሩን በጡንቻ ለመቆጣጠር ተችሎ ሊሆን ይችላል፤ ነገሮች አሁን ካለው ሁኔታ በተቀየሩ ጊዜ ግን የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ጉዳይ እጅግ አጨቃጫቂ ከሚሆኑት ጉዳዮች  አንዱ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
ሌላው ቢቀር፣ አዲስ አበባ የያዘው መሬት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚጠቃለል ነው ወይስ ራሱን የቻለ ነው? የሚለው ጉዳይ ራሱ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ያላገኘ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት፤“አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ” ይላል፡፡ ይሄ በራሱ ምን ማለት ነው?! በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ ሕገ መንግሥት፤ “ኦሮሚያ ያላት መሬት ያልተቆራረጠ ነው” የሚል በመሆኑ፣ አዲስ አበባንም በዚህ ውስጥ የሚያጠቃልል አንድምታ ያለው ነው የሚሉ ምሁራን አሉ፡፡ እንደዚያ ከሆነ፣ በክልሉና በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት መሀል እርስ በርስ የሚጋጭ ሐሳብ እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡
በእርግጥ፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት፤ የሁሉም ሕጎች የበላይ ሕግ በመሆኑ፣ በማንኛውም መልኩ፤ በክልል ደረጃም ቢሆን የሚወጡ ሕጎች ከዚሁ ሕገ መንግሥት ጋር መስማማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ችግር የሚሆነው፣ በዋናው ሕገ መንግሥት አተረጓጎም ወይም ይወጣል በሚባለው ይህን ጉዳይ የሚመለከት ዝርዝር ሕግ ላይ ስምምነት የጠፋ እንደሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ፣ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ከያዘው ፓርቲ የተለየ ኃይል በኦሮሚያ ክልል ቢያሸንፍ አሁን እንደሚያደርገው፣ የፌዴራሉ መንግሥት ክልሎችን እንደ ፈለገ መኮርከርም የሚችልበት ዕድል ላይኖር ይችላል። በዚሁ ሁኔታ፣ እንደዚህ ዓይነት አጨቃጫቂ ጉዳዮች ቢነሱ፣ አስቀድሞ በሕገ መንግሥት ደረጃ የተወላገደን ነገር ማቃናት የሚያስቸግር ነው የሚሆነው፡፡
“አዲስ አበባ የማናት?” ከሚለው ፖለቲካዊ እሰጣ ገባ በላይ መታሰብ ያለበት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉት ነዋሪዎች ቋሚና ዘላቂ ጥቅሞች ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አዲስ አበባ በብዙ መንገድ፣ በመሰረታዊ ልማት፣ በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በፀጥታ፣ በመንገድና በውሃ ልማት ወዘተ. ከኦሮሚያ ጋር የሚያገናኛት በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው ይህን የሚመለከት ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት ተገቢ ነው፡፡
በተለይ ከተማዋ ስትስፋፋ በአካባቢው ያሉት አርሶ አደሮች እንዳይጎዱና እንዳይፈናቀሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ አንዱን ዜጋ ጎድቶ ሌላው ዜጋ እንዲጠቀም ማድረግ ኢ-ፍትሀዊ አካሄድ ነው። በዙሪያዋ ያሉት ገበሬዎች የከተማዋ መስፋፋት ከሚፈጥረው ጸጋ ተካፋይ መሆን መቻል አለባቸው እንጂ በማነኛቸውም መልኩ ተጎጂ የሚሆኑበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡ እስካሁን ይደረግ እንደነበረው ገበሬውን ብጣሽ መሬትና የዓመት ቀለብ እንኳን የማይሸፍን ገንዘብ እየሰጡ ከቀዬው እንዲፈናቀል ማድረግ በሕግም በሞራልም አግባብ አይደለም፡፡ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በዚህ መልኩ ሲፈናቀሉ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ከጎናቸው መቆም ያለበት፣ ይኼ ጉዳይ ለኦሮሞ ልጆች ብቻ የሚተው መሆን የለበትም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከተማዋ ጤናማ የሆነ መስፋፋት እንዳይኖራት፣ በዙሪያዋ ከሚገኙት ከተሞች በኢኮኖሚና በመሠረታዊ ልማት እንዳትተሳሰር እንቅፋት የሚሆን ነገር መኖር የለበትም፡፡ እርግጥ ነው ከተማዋ ስትፋፋ በአካባቢው የሚኖረው የብሔር ስብጥር፣ ለውጥ እንደሚያመጣ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ሕዝብ ዕጣ ፈንታው ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለዚህ አብሮ እየኖረ ነው፣ አብሮ የሚያድገው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነገር ነው መታሰብ ያለበት፡፡ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አስተሳሰብ ሁሉ ጥፋት እንጂ ጥቅም ይዞ አይመጣም፡፡ የብሔር፣ ብሔረሰቦችን መብት ያለ ልክ በመለጠጥ የሚተቸው፣ የአሁኑ ሕገ መንግሥትም አንድን መሬት ለይቶ ለሆነ ብሔር አይሰጥም፡፡ መሬት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ ነው የሚገልጸው፡፡ አዲስ አበባ የቆመችበትና በዙሪያዋ ያለው መሬትም ከዚህ የተለየ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
ምንጭ፡- (“የህገ መንግሥቱ ፈረሰኞች”፤ ከገጽ 123-129)

Read 2826 times