Sunday, 09 July 2017 00:00

ከአሊ ቢራ እስከ አቢ ላቀው የሚያቀነቅኑበት ኮንሰርት - በሚሊኒየም አዳራሽ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ድምጻውያኑ ለአዘጋጆቹ አድናቆትና ምስጋና ቸረዋል

        ጆርካ ኤቨንትና ዳኒ ዴቪስ በጋራ ያዘጋጁት “አዲስ ኮንሰርት ሁለት” የተሰኘ የሙዚቃ ድግስ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ አንጋፋዎቹ ድምጻዊያን አሊ ቢራ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ኤፍሬም ታምሩ እንዲሁም ሚካኤል በላይነህ፣ አቢ ላቀውና መስፍን ብርሃኔ በአንድ መድረክ ያቀነቅናሉ ተብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከተወዳጁ ድምፃዊ አሊ ቢራ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ አቢ ላቀውና መስፍን ብርሃኔ ጋር በኮንሰርቱ ዝግጅታቸውና በመጪ ሥራዎቻቸው ዙሪያ አጫጭር ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡

              “ላለፉት 52 ዓመታት በትጋት ሰርቻለሁ”
                 አሊ ቢራ

      በጥሩ ደህንነት ላይ እንዳለህ ያስታውቃል፤ ደግሞ ገና ጎረምሳ ነህ፡፡ ለመሆኑ እድሜህ ስንት ሆነ?
እንዴ ገና አፍላ ጎረምሳ እኮ ነኝ፤ እድሜዬም 69 ዓመት ብቻ ነው፡፡
አሁን የት ነው የምትኖረው?
በፊት እዚህ አዲስ አበባ ነበር የምኖረው፤ አሁን ወደ ቢሾፍቱ ተዛውሬ እየኖርኩ ነው፡፡
ቢሾፍቱ የምትኖረው በተሸለምከው ቤት ነው? ኑሮ በቢሾፍቱ ምን ይመስላል?
ኑሮ በጣም ጥሩ ነው፤ ደስ ብሎኝ እየኖርኩ ነው፤ ባለቤቴ በጣም ንፅህና ስለምትወድ ቤታችንና ግቢያችን ሁሌም ንፁህና ለመኖር ምቹ ነው፡፡ ብዙ ጎብኚዎች ሊጠይቁን ሲመጡ ስለ ንፅህናው፣ ስለ ግቢው ውበት መልካም አስተያየቶችን ይሰጡናል። እንዳልሺው በተሸለምኩት ቆንጆ ቤት፣ ከቆንጆዋ ባለቤቴ ጋር እየኖርኩኝ ነው፡፡
አሁን ጊዜህን የምታሳልፈው ምን እየሰራህ ነው? ገቢህስ ምንድን ነው?
እየኖርኩ ያለሁት በጡረታ ገቢ ነው፡፡
ከጡረታ ምን ያህል ታገኛለህ?
እሱ አይነገርም፤ እንደ ሴቶች እድሜ ነው፡፡
ብዙ ነው ለማለት ነው?
ለዚህ መመለስ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ብዙ ነው ካልኩ ሴቶች ሊቀየሙኝ ነው፡፡ ትንሽ ነው ካልኩም ውሸት ይመስላል፤ ስለዚህ አለመግለፁ ይሻላል፡፡
ታዲያ መጀመሪያ እንደ ሴቶች እድሜ ነው ለምን አልክ?
በቃ አይነገርም ለማለት ነው፤ ደግሞም አንዴ ወጣኝ ምን ይደረግ (ሳ….ቅ) በምንድን ነው ጊዜህን የምታሳልፈው ላልሺኝ ቴሌቪዥን አያለሁ፣ አንዳንድ ነገሮችን አነባለሁ፡፡ ብዙ ጊዜዬን ሪላክስ በማድረግ ነው የማሳልፈው፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የኔ ሥራ ጡረታ ነው፡፡
የፊሊፒኖ ዜግነት ካላት ባለቤትህ ከወ/ሮ ሊሊ ማርኮስ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ በትዳር መኖራችሁ ይታወቃል፡፡ ልጆች አፍርታችኋል?
ልጆች አልወለድንም፤ ነገር ግን እኔ እሷን ወለድኩ፤ እሷ ደግሞ እኔን ወለደች፤ አንዳችን ለአንዳችን ልጅ ነን፡፡ ስለዚህ አንዳችን አንዳችንን እንከባከባለን፡፡ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ቢሾፍቱ ከተማ አየሩ፣ ነዋሪው፣ ሁሉም ነገር ደስ ይላል። ለኑሮ ምቹ ነው፡፡ በቤቴም ምቾት ስላለኝ በዚህ መልኩ በጥሩ ሁኔታ እያሳለፍኩ ነው፡፡ ለምን? ላለፉት 52 ዓመታት በትጋት ሰርቻለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብዙ መድከም እንደሌለብኝ ለራሴ ነግሬው፣ እሱን እየተገበርኩኝ ነው፡፡ በትርፍ ጊዜ ላልሺው አሁን ለእኔ ሁሉም ትርፍ ጊዜ ነው፤ አሁንም ደግሜ የምነግርሽ የኔ ስራ ጡረታ ነው፡፡
አዳዲስ ግጥሞች መፃፍስ …?
ላለፉት 52 ዓመታት የሰራኋቸውን ስራዎች አናላይዝ አደርጋለሁ፤ መቼም ጭንቅላታችን መስራቱን እስካላቆመ ድረስ ማሰላሰል ስለማይቀር አሰላስላለሁ፡፡ ምን ነበር የሰራሁት? እንዴት ነበር ያደረግኩት እያልኩ ነው ስራዎችን የምተነትነው፡፡ አሁን ጡረታ ላይ እያለሁ አዲስ ግጥም ለመስራት፣ ሌላ ዘፈን ለማውጣት አላስብም፡፡
ስለዚህ ከታላቁ አርቲስት አዲስ አልበም እንዳንጠብቅ ቁርጣችንን እየነገርከን ነው?
ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ አሁን አልበም ለማውጣት ትኩስ ሀይሎች አሉ፤ ለእነሱ ቦታውን ፈግፈግ ብሎ መልቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሳንዘረር በፊት መልቀቅ ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
የእናንተ ዘፈኖች ሳይሰለቹ ሳይጠገቡ ዘመን ተሻግረዋል፤ አሁንም መደመጣቸውን ቀጥለዋል፡፡ እንዲህ አይነት ተተኪ ትውልድ አፍርቻለሁ ብለህ ታስባለህ? ተተኪ አለ ካልክ እነ ማንን በምሳሌነት ትጠቅሳለህ?
በስም እከሌ እከሌ ማለት አፈልግም፤ ነገር ግን በጣም ብዙ ተተኪ ጎበዝ ወጣት አርቲስቶች አሉ። እንደምሰማው ስራቸው በጣም አርኪ ነው። በኦሮምኛም በአማርኛም በትግርኛም ጥሩ ጥሩ ዘፈኖች፣ ጥሩ ጥሩ ገጣሚዎች አሉ፡፡ በሙዚቃ ብቻም አይደለም፣ በፊልምም በድራማም ጥሩ ጥሩ ስራዎች እየሰሩ ያሉ በርካታ አቅም ያላቸው ወጣቶች እያየሁ ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም ዘርፍ ያለው ኪነ-ጥበብ በተተኪዎች እየቀጠለ ነው፡፡ ይሄ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቴሌቪዥን በጣም የምመለከተው፡፡ ፊልሙን ድራማውንም ሆነ ሙዚቃውን ለመገምገም ያስችላል፡፡
ከዚህ ቀደም ከጋሽ ማህሙድና ከኤፍሬም ጋር በአንድ መድረክ ተጫውታችሁ ታውቃላችሁ?
ከማህሙድ ጋር በጣም ብዙ ጊዜ አብረን ተጫውተናል፡፡ ለምሳሌ ከአንድ ወር በፊት አውስትራሊያ አብረን ነበር፡፡ ‹‹ሜልቦርን አርት ሴንተር›› ላይ አብረን ሰርተን ነው የተለያየነው፡፡ ከዚያ በፊት እኔም እሱም ለሙያው አዲስ ሆነን፣ ክቡር ዘበኛ ውስጥ ከእኔ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነው የገባው፡፡
በዚሁ በክቡር ዘበኛ ለዓመታት አብረን ሰርተናል። በምሽት ክበብ ደረጃ ራስ ሆቴል፣ በኮንሰርት ደረጃ ከኤፍሬም ጋር አብረን መስራታችንን ባላስታውስም፣ ከማህሙድ ጋር ግን ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ስንሰራ ኖረናል፡፡
ለኮንሰርቱ ምን ያህል እየተዘጋጀህ ነው? ምን ያህል ዘፈኖችን ታቀርባለህ? የሚያጅብህስ የትኛው ባንድ ነው?
በጣም ጥሩ! እኔ በጣም እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ ሁሌም ለኮንሰርት ስዘጋጅ ይሄኛው ኮንሰርት ትልቅ ነው፣ ያኛው ትንሽ ነው በሚል የምከፋፍለው ነገር የለም፡፡ ሁሌም ዝግጁና ራሴን አሊን ሆኜ መቅረብ ነው የምፈልገው፤ ስለዚህ እየተዘጋጀሁ ነው፤ ባለኝ ችሎና አቅም እጫወታለሁ፡፡ እርግጥ ነው ይሄኛው ኮንሰርት ወደ መጨረሻዎቹ የእኔ የኮንሰርት ስራዎች የተጠጋ በመሆኑ የተሻለ ሆኜ ለመቅረብ እሞክራለሁ። የሚቀርበው የዘፈን መጠን እንደ ሰዓቱ ይወሰናል፤ ብቻ ሰው በጣም በሚወዳቸው ዘፈኖቼ ላይ በጣም እየተዘጋጀሁ ነው፤ የሚያጅበኝ ሮሃ ባንድ ነው፡፡
በውጭ አገራትም በብዛት ኮንሰርት እየሰራህ ነው ልበል?
በብዛት አይደለም፤ አልፎ አልፎ የተመረጡ ኮንሰርቶች ላይ እሰራለሁ፡፡ የተጠራሁበት ሁሉ አልሄድም፡፡ መርጬና አይቼ አልፎ አልፎ በውጭም በአገር ውስጥም እሰራለሁ፡፡ አሁን ወደ መጨረሻው ዘመን እየተቃረብኩ ነው፡፡
ይህን ስትል አድናቂዎችህ የሚከፉ ይመስለኛል። ለመሆኑ ስለ አድናቂዎችህ ምን ታስባለህ?
እንዴ! ምን ማለትሽ ነው፡፡ ዓመታቶቹ ይመሰክራሉ፡፡ እኔ ሙዚቃ ስጀምር ይህንን ያህል እዘልቅበታለሁ ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን የህዝቡ ፍቅር፣ አድናቆትና ክብር ነው፣ ተሸክሞ ይህን ሁሉ ዓመት በሙያው እዚህ እንድደርስ ያደረገኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዘመኔ ተደንቄ ተወድጄ መኖሬን ልብ እለዋለሁ፤ እገነዘበዋለሁ፡፡ በተረፈ ሀምሌ 8 ቀን በሚሊኒየም አዳራሽ እንገናኝ፤ ጥሩ ጊዜ እናሳልፍ እላለሁ፤ አዘጋጆቹ ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘርንና ዳኒ ዴቪስን አመሰግናለሁ፡፡ ላሰቡት ቀና ነገር ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

-----------

               “ከአድናቂዎቼ ጋር ናፍቆቴን እወጣለሁ”
                    ድምፃዊት አበባ ላቀው (አቢ)

      ለኮንሰርቱ ብቻ ነው ወይስ ለአዲሱ አልበምሽም ሥራ ነው የመጣሽው?
በመጀመሪያና በዋናነት የመጣሁት ለኮንሰርቱ ነው፡፡ ከዚያው ጎን ለጎን ደግሞ አልበሙን በተመለከተ የጀመርኳቸው አንዳንድ ነገሮች ስላሉ ለሁለቱም ጉዳይ ነው የመጣሁት፡፡
እዚህ የተሰሩ ግጥምና ዜማዎች አሉሽ ማለት ነው?
አልበሙ የተሰራው የተለያየ ቦታ ነው፡፡ እኔም የሞከርኳቸው ግጥምና ዜማዎችም አሉ፡፡ ብዙ ሰው ተሳትፎበታል፡፡
ከእነዚህ አንጋፋ አርቲስቶች ጋር ኮንሰርት እንድትሰሪ አዘጋጆቹ ሲመርጡሽ ምን ተሰማሽ?
በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ በፊትም የእነሱን ዘፈኖች እየሰማሁ ነው ያደግኩት፡፡ አጋጣሚውን አግኝቼ ያውም አገሬንና ወገኔ ባለበት ቦታ ላይ ከእነርሱ ጋር ኮንሰርት ለማቅረብ በመመረጤ እድለኛ ነኝ ነው የምለው፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
እዚህ አገር በጣም ብዙ አድናቂዎች እንዳሉሽ ታውቂያለሽ?
በጣም ብዙ አድናቂ አለሽ? አንዳንዴ እንዲህ አይነት ጥያቄ ስትጠየቂ ምን እንደምትመልሺ ይጨንቅሻል፡፡ እውነቴን ነው የምነግርሽ፤ ከሰው የማገኘው ምላሽ በጣም ነው የሚከብደው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአድናቂዎቼን ውለታ ለመክፈል ለሀምሌ 8ቱ ኮንሰርት በጣም እየተዘጋጀሁ ነው ያለሁት፡፡ ያኔ አስደስታቸዋለሁ፤ እንዳይቀሩም እጠይቃለሁ፡፡
ምን ያህል ዘፈኖችን ለማቅረብ እየተዘጋጀሽ ነው? የሚያጅብሽስ ባንድ ማን ነው?
በተቻለ መጠን በርከት ባሉት ሥራዎቼ ላይ ልምምድ እያደረግኩ ነው፤ የማቀርባቸው ዘፈኖች ብዛት የሚወሰነው በሰዓቱ ነው፤ የሰውን ፍላጎት እያየን እናቀርባለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የሚያጅበኝ ባንድ የተውጣጣው ከተለያዩ ባንዶች ነው፡፡ ከየባንዶቹ ጎበዝ ጎበዝ የተባሉትን የተለያዩ ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች መርጠን ነው ያሰባሰብነው፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ባንዱ ስም የለውም፡፡
አዲስ አልበምሽን ለአዲስ አመት ለመልቀቅ መዘጋጀትሽን ሰማሁ … ?
እውነት ነው፤ 14 ዘፈኖች ያሉት አልበም ሰርቻለሁ። ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ከኮንሰርቱ ቀጥሎ በአልበሙ ዙሪያ የምሰራቸው ስራዎች አሉኝ፤ ለአዲስ አመት ይደርሳል፡፡ ስያሜው “ሰርፕራይዝ” ቢሆን ይሻላል፡፡
ከዚህ በፊት ‹‹ኢየሩስ›› በተሰኘ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት ከድምፃዊ ሳሚ በየነ ጋር ሰርተሻል፡፡ በፊልሙ ላይ  ጥሩ የትወና ብቃት አሳይተሻል ይባላል፡፡ በፊልሙ የመግፋት ሀሳብ የለሽም?
ልክ ነሽ ፊልሙ ላይ በተወንኩ ጊዜ ጥሩ አስተያየቶችን ከተመልካች አግኝቼ ነበር፡፡ አሜሪካ አገር እየኖርኩ ፊልም ለመስራት ብዙ አይመችም፤ ምክንያቱም ወደ ኢትዮጵያ የምመጣው አልፎ አልፎ ነው፡፡ ለወደፊቱ ጊዜውና እድሉ ከተመቻቸ ብሰራ ደስ ይለኛል፡፡
እዚህ አገር በግልሽ ኮንሰርት የማዘጋጀት ሀሳብ የለሽም?
ሀሳብ አለኝ፡፡ መቼ ነው ካልሽኝ፣ አልበሜ ወጥቶ በደንብ ህዝብ ጆሮ ገብቶ ከተደመጠ በኋላ ወደ አገሬ ተመልሼ፣ ትልቅ ሾው የማዘጋጀት ሀሳብ አለኝ፡፡
ከልጅሽ ጋር ብቻ ነው ወይስ ባለቤትሽም አብሮሽ መጥቷል?
ሁላችንም አብረን ነው የመጣነው፡፡
ከኮንሰርቱ ምን ትጠብቂያለሽ?
በእለቱ ከአድናቂዎቼ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቼ ናፍቆቴን እንደምወጣ ነው የምጠብቀው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እዚህ ትልቅ የሙዚቃ ድግስ ላይ ከትልልቅ ባለሙያዎች ጎን እንድሰለፍ እድል የሰጡኝን ጆርካዎችንና ዳኒ ዴቪስን አመሰግናለሁ፡፡

--------------

                         ‹‹ሙሉ አልበም ሳልሰራ በዚህ ኮንሰርት በመሳተፌ በጣም ደስተኛ ነኝ››
                        መስፍን ብርሀኔ

       በጣም የምታወቀው ‹‹ገና ገና›› በተሰኘው የትግርኛ ነጠላ ዜማህ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ያህል ዘፈኖችን ሰርተሀል?
እንዳልሽው ነው፤ እኔ ወደ ጥበብ ስራ የገባሁት ከሰርከስ ጀምሬ ነው፤ ትግራይ ሰርከስ ውስጥ እየሰራሁ ነው ወደ ዘፈን የገባሁት፡፡ ከዚያም ድራማ እጫወት ነበር፡፡
ወደ እውቅና የመጣሁት ‹‹ገና ገና›› በተሰኘው ነጠላ ዜማዬ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹ቶሎ ቶሎ›› ቀጥሎም ‹‹መህንኔት›› የተሰኘ ነጠላ ዜማ በቅርቡ አውጥቻለሁ፡፡
ከእንደዚህ ያሉ አንጋፋዎች ጋር ኮንሰርት እንድትሰራ ስትጋበዝ ምን ተሰማህ?
ስሜቱን መግለፅ አልችልም፡፡ ምንም እንኳን በሙዚቃው ውስጥ ብቆይምና ብታወቅም ገና ሙሉ አልበም አልሰራሁም፡፡ አገሪቱ ላይ በሙዚቃ በአርአያነት ከሚጠቀሱ አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር መስራት ትልቅ ነገር ነው፤ እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ አዘጋጆቹ ለዚህ ትልቅ ሥራ ስለመረጡኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
በኮንሰርቱ ላይ ምን ያህል ዘፈኖች ትጫወታለህ? አዳዲስ ዘፈኖች ታቀርባለህ?
በእርግጥ በቅርቡ የሚወጣ አዲስ ነጠላ ዜማ አለኝ፤ ሆኖም የምታወቅባቸውን ነው ለአድማጭ የማቀርበው፡፡ “ገና ገና” ከተባለው የራሴ ባንድ ጋር ነው የምጫወተው፡፡ አራት ያህል ዘፈኖችን ለመጫወት ከባንዴ ጋር ከፍተኛ ልምምድ እያደርግሁ እገኛለሁ፡፡
ሙሉ አልበም የመስራት ሀሳብ አለህ ወይስ በነጠላ ዜማ ስራ ነው የምትቀጥለው?
ሙሉ አልበም እየሰራሁ ነው፤ 50 በመቶው ተጠናቅቋል፤ ቀሪውን ለመጨረስ እየሰራሁ ነው። የአልበም ስራ ከባድ እንደሆነ እያየሁ ነው። ትክክለኛውን ቀን አውቄ በዚህ ቀን ባልልም አልበሜ ይወጣል፡፡
በአዲስ አልበም እንገናኛለን፡፡ በመጨረሻም አድናቂዎቼ ሀምሌ 8 እንገናኝ አሪፍ ጊዜ እናሳልፋለን እላለሁ፡፡ አዘጋጆቹ ስለሰጡኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

-------------

                     ‹‹ከአንጋፋዎቹ ጋር እንድሰራ ስመረጥ የእስከዛሬው ስራዬ ትክክል ነበር ብዬ አምኛለሁ››
                      ሚካኤል በላይነህ

      ከእነ ጋሽ አሊ ቢራ፣ ጋሽ ማህሙድና ከእነ ኤፍሬም ጋር ኮንሰርት ትሰራለህ ስትባል የተሰማህን ስሜት እስኪ ንገረኝ?
እውነት ለመናገር ደስ ብሎኛል ብሎ መናገር የተሰማኝን አይገልፅም፡፡ መጀመሪያ ግን ከአዘጋጆቹ ልጀምር፡፡ ጆርካዎች ሁሌም ጥሩ ስራ ለመስራት በጣም የሚተጉ ናቸው፡፡ በቅርብ ጊዜ ማለትም ከአንድ ሶስት ዓመት ወዲህ ነው ያየናቸው፡፡ ለእኔ ከእነሱ ጋር ስሰራ የአሁኑ አራተኛዬ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም “የፍቅረኞች ቀንን”፣ ከዚያ ‹‹አዲስ ኮንሰርት አንድን›› በፋና ፓርክ፣ ከዚያም ‹‹ሄሎ መቀሌን›› በመቀሌ በተሳካ ሁኔታ አብረን ሰርተናል፡፡ ይሄኛው አራተኛዬ ነው፡፡ በጥሩ ፕሮሞሽንና በጥሩ ትጋት የሚሰሩ ናቸውና አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ወደዚህኛው ኮንሰርት ስንመጣ፣ በጣም ግዝፍ ያለ፣ ጥሩ ስብጥር ያለው፣ አንጋፋና ወጣቶችን ያሰለፈ ነው፤ ጥሩ ሆኖ ያልፋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከአሊ ቢራ፣ ከማህሙድ እና ከኤፍሬም ጎን ቆሜ መዝፈኔ ለእኔ እውቅና ነው፡፡ እውቅና ነው ስልሽ እስከዛሬ የሰራሁት ስራ፣ የሄድኩበት መንገድ ትክክል ነው ብዬ እንዳምን አድርጎኛል፡፡
ዝግጅት ምን ይመስላል? ከየትኛው ባንድ ጋር ነው ስራህን የምታቀርበው?
ስራዎቼን የማቀርበው ከዘመን ባንድ ጋር ነው። ከዘመን ባንድ ጋር ለረጀም ጊዜ ነው አብረን የሰራነው፡፡ ‹‹ናፍቆትና ፍቅር›› የተሰኘው አልበሜ ከወጣ አምስት ዓመት ሊሆነው ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አብረን እየሰራን ነው፡፡ ዝግጅትን በተመለከተ ለ200፣ ለ500 ሆነ ሌላ በርካታ ሰው ለሚገኝበት ኮንሰርት እኩል ነው የምዘጋጀው፡፡ በየትኛውም ሁኔታና ቦታ ሙዚቃው እንዲጎዳና እንዲቀንስ ስለማልፈልግ፣ ሁሌም በጥሩ ሁኔታ እዘጋጃለሁ፡፡ አሁንም በዚያው መጠን እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
በኮንሰርቱ ላይ አዳዲስ ዘፈኖችን የማቅረብ ሀሳብ የለህም?
እውነት ለመናገር በኮንሰርቱ ላይ አዳዲስ ዘፈኖች አይኖሩም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ሰብሰብ ብለን ሥራችንን የምናቀርብበት በመሆኑ አዲስ ዘፈን ማስተዋወቅ ይከብዳል፡፡ የበለጠ አድማጭ የሚያውቃቸው ዘፈኖች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ከልባቸው ከህይወታቸው ጋር የሚገናኙትን ዘፈኖች ለማቅረብ ነው እየተዘጋጀሁ ያለሁት፡፡ ሊዝናና የመጣን ሰው ከአዲስ ዘፈን ጋር ማታገሉም አግባብ መስሎ አልታየኝም እንጂ አዲስ ዘፈን ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፡፡
ጠፋ ብለህ ነው የከረምከው፡፡ አድፍጠህ ምን እየሰራህ ነው? አዲስ አልበምስ የማውጣት ሀሳብ የለህም?
የህይወት እንቅስቃሴ ትንሽ ያዝ አድርጎኝ ነበር የጠፋሁት፡፡
የህይወት እንቅስቃሴ ማለት?
ለምሳሌ አዲስ ልጅ፣ አዲስ ቤት እና ተያያዥ ነገሮች ይዘውኝ ነበር፡፡ በቅርቡ ሁለተኛ ልጄን ወልጃለሁ፡፡
ሴት ልጅ አግኝቻለሁ፡፡ ከዚያም በፊት ሌሎች ጉዳዮች ስለነበሩኝ ነበር የጠፋሁት፡፡ አሁን በመጠኑ እነሱን አስተካክዬ ጨርሻለሁ አልጠፋም። በሚቀጥለው 6 ወር ውስጥ አዲስ አልበሜን ለአድማጭ ለማድረስ ተፍተፍ እያልኩ ነው፡፡
ስለ አዲሷ ልጅህ፣ ስለ አዲሱ ቤትህ፣ እየሰራህ ስላለውም አዲስ አልበም እንኳን ደስ አለህ፡፡
አመሰግናለሁ በጣም!
ከኮንሰርቱ ምን ትጠብቃለህ?
ብዙ አስደሳች ነገሮች እጠብቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ተቀራራቢ ስሜትና የዘፈን ምርጫ ያላቸው ወይም ሁሉም የሚስማማባቸው ታዳሚዎች ይገኛሉ ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ለምሳሌ ማህሙድን የሚወድ አሊ ቢራንም ይወዳል፡፡ ኤፍሬምን የሚወድ የእኔም አድናቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የዘፈኖቹ ስብጥር አስደሳች በመሆኑ ብዙ የሚያስደስቱና ታሪካዊ የሚሆኑ ጊዜያትን እናሳልፋለን የሚል ትልቅ ጉጉት አለኝ፡፡
ከእነ ጋሽ አሊና ከኤፍሬም ጋር ከዚህ በፊት ኮንሰርት የመስራት አጋጣሚ ነበረህ?  በፍፁም አልነበረኝም፡፡ በእርግጥ ከጋሽ ማህሙድ ጋር ገና ሙዚቀኛ ነን ብዬ ሳላስብ ድሮ ከመዲና ባንድ ጋር ስጫወት የሸራተን መክፈቻዎች ላይ አብረን ሰርተናል፡፡ ያን ጊዜ እኔ ሙዚቃን በትርፍ ጊዜ እንደ መዝናኛ እንጂ እንደ ሙያ አልነበረም የምሰራው፡፡ በወቅቱ ጥላሁን ገሰሰ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ምንሊክ ወስናቸው፣ ሀመልማል አባተና እኔ ነበርን የተጫወትነው፡፡ ያንን ጊዜ በደንብ አስታውሰዋለሁ፡፡ ከአሊ ቢራና ከኤፍሬም ጋር በፍፁም ሰርቼ አላውቅም፡፡
በኮንሰርቱ ምን ያህል ዘፈኖችህን ታቀርባለህ?
የተሰጠኝ አንድ ሰዓት ነው፡፡ በዚህ አንድ ሰዓት ውስጥ 10 ዘፈኖቼን ለማቅረብ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
መልካም ጊዜ እመኛለሁ …
እኔም አመሰግናለሁ፡፡ እግዜር ይሰጥልኝ። አድናቂዎቼን ሀምሌ ስምንት ቀን በጉጉት እንደምጠብቃቸው ንገሪልኝ፡፡


Read 2083 times