Sunday, 09 July 2017 00:00

“ድሃ ይበላው እንጂ ይገብረው አያጣም”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

“መንግስት፤ አዳዲስ መጫወቻ እንደሚያምረው ሕጻን አዲስ ተ ሽከርካሪ በተመረተ
ቁጥር ለመግዛት ከቋመጡ፤ በየዓመቱ መጀመርያ ላይ አዳዲስ ሞባይል፣ ኮምፒዩተርና
የቢሮ ቁሳቁስ ከሚያግበሰብሱ እንዲሁም አዲስ ሕንጻ ባለቀ ቁጥር ለመከራየት


ዜጎች በሃገራቸው ላይ ሰርቶ የመኖር መብታቸው ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግለት ለይስሙላ አይደለም፡፡ መሰረታዊ ግቡ የመንግስት ድጎማን ጨምሮ ከውስጣዊም ሆነ ከውጫዊ ሃይሎች ጥገኛነትና ተመጽዋችነት ተላቀው፣ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በስርዓቱ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡ ነግደውም ሆነ ጉልበታቸውን ሸጠው የሚያድሩ  ዜጎች፤ ከግብር ከፋዮች ተርታ ተሰልፈው ማህበራዊ ግዴታቸውን መወጣትና ሌሎችን መርዳት የሚገባቸው የሙሰኞችንና ጊዜ የወለዳቸውን ዘመናዊ ፊውዳሎች ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ሲባል፤ በግምትና በይሁንታ ላይ ተመስርቶ መሆን የለበትም፡፡ ግብር መክፍል የዜግነት ግዴታ የመሆኑን ያህል ሕጋዊነትንና ወጥነትን በተከተለ የግብር አከፋፈል ስርዓት እየተመሩ መሆን አለበት፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ መሰረታዊ የሆነውን የግለሰቦች መብት በቅድሚያ ለማስቀመጥ የፈለግኩት፤ በችርቻሮ ንግድ ላይ  የተሰማሩ የመለስተኛና አነስተኛ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ሰሞኑን ከገቢ ግምትና ከግብር ክፍያ ስርዓት ጋር ተያይዞ እያሰሙ ያለው እሮሮ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡
በነጋዴው ማህበረሰብና በመንግስት መካከል ይህን ያህል ሰፊ ልዩነትና አለመግባባት መከሰቱ እውን በአንድ ሃገር ውስጥ የሚገኙና ስለ አንድ ዓይነት ጉዳይ የሚወያዩ አይመስልም፡፡ ነጋዴዎች፤ “የማንንም እጅ ሳናይ ከማንም ምንም ሳንጠብቅ ቀኑን ሙሉ እግራችን እስኪንቀጠቀጥ ድረስ ሱቅ በር ላይ ቆመን  ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ የእለት ጉርሳችንን አሸንፈን ቤተሰብ በደጎምን፤ ሰምተንና አይተን የማናውቀውን የሚሊዮን ብር ባለዕዳ የሚያደርገን መንግስት ምን ያህል ቢጠላን ነው? “  የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
ቀሪዎቹ ደግሞ “ከኛ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩ ሹመኞች በየሚዲያው እየቀረቡ ትንታኔ ሲሰጡ፣ ነጋዴውን ማህበረሰብ እንደ አጭበርባሪ፣ ግብር የሚሰውሩ ሕገ ወጦችና በጥቅሉ  እንደ ተጠርጣሪ ዜጋ የሚፈርጁን ምን ሕጋዊ መሰረት ይዘው ነው? በዚህም ምክንያት አሁን አሁን ነጋዴ መባል ሌባ ከመባል ያልተናነሰ ገጽታ እንዲኖረንና እንድናፍር አድርገውናል” የሚል ቅሬታ ይሰነዝራሉ።
ዞር ዞር ብዬ ለመታዘብ እንደሞከርኩት፤ አብዛኞቹ  አነስተኛ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በመቶ ሺህ ብር የሚቆጠር ወረት ይዘው የሚቸረችሩ ናቸው። ይህንን ወረት ስንት ጊዜ ደጋግመው ቢሸጡት አመታዊ ገቢያቸው ሁለት ሚሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል የሚያስረዳኝ ማግኘት አልቻልኩም! የሂሳብ ሙያ ትምህርቴ  ቢሆንም አዕምሮዬ አውጥቶ አውርዶ ስሌት መፍጠር አልቻለም፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ደግሞ በተሰጣቸው የገቢ ግምት ማሳወቂያ ደብዳቤ ላይ፤ ‹‹የንግድ ድርጅትህ/ሽ ገቢ ተገምቶ በዓመት ይህንን ያህል ገቢ እንዳለህ/ሽ ተረጋግጦብሃል›› በማለት ግምትና ማረጋገጥን መሳ ለመሳ በመፋረጃነት ማቅረባቸው ነው፡፡
አንጀታቸው የቆሰለ በርካታ ዜጎች እንደተበራከቱ ከየመገናኛ ብዙኃኑ ላይ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ መነሻቸው ደግሞ ሌላ አይደለም፤ ወጥነትና ስርዓት ባልተከተለ መንገድ አምስት ደቂቃ በማይሞላ ጉብኝት፤ አንዳችም ሙያዊ ትንታኔና እውቀት ሳይታከልበት፣ የዓመት ሽያጭህ/ሽ አንድ ሚሊዮን ወይም ሁለት ሚሊዮን ነው መባሉ ነው፡፡ ይሄ በእርግጥም ግራ ከማጋባቱም በላይ አንጀት እርር ድብን ያደርጋል፡፡ ገፋ ሲልም ከድንጋጤ የተነሳ ለተለያየ  በሽታ የተዳረገውን  ቤቱ ይቁጠረው ከማለት ውጭ መልስ ሊገኝለት አይችልም፡፡
‹‹ተጠርጣሪ ዜጎች››
 ኢህአዴጋውያንን ለጫካ አመጽ ከዳረጋቸው የደርግ ስርዓት ኢ-ዴሞክራሲያዊ መገለጫዎች መካከል፤ ዜጎችን በጅምላ የመጠርጠርና የመፈረጅ አባዜ አንዱ ነበር፡፡ ዜጎችን በጅምላ የመጠርጠርና የመፈረጅ አባዜ ለደርግ ሹመኞች በሕግ የተፈቀደ መብት ነበር፡፡  ደርጎች፤ ከአብዮት ጥበቃ ጀምሮ እስከ ሚኒስትሮቹ ድረስ ጸጉሩን ያጎፈረን ሁላ ፀረ-አብዮተኛ ነው በማለት በጅምላ ፈርጀው፣  ያለ በቂ ማስረጃና ማጣራት  ማሰር፤ በድብደባ አካለ ጎዶሎ ማድረግና መግደል… ጥያቄ የሚነሳበትና ሕግ ፊት የሚያቀርብ ጉዳይ አልነበረም፡፡ በዚህ መንገድ ቁጥራቸውን ለመገመት የሚያዳግቱ  ዜጎች ጥሩ በመልበሳቸው፤ የተደላደለ ቁመናና ያልተጎሳቆለ ገጽታ ስለነበራቸው ብቻ ‹‹በዝባዥና ፊውዳል›› በሚል ጥቅል ፍረጃ በህዝብ ፊት ተዋርደው ከማህበረሰቡ እንዲገለሉ ተደርገዋል፡፡ ሰብእናቸው ተዋርዶ የበረታባቸውም እጅግ ለሚዘገንን ኢ-ሰብአዊ  እስርና እንግልት፣ አልፎ ተርፎ ሞት ተዳርገዋል፡፡
ይህ ዘመን ፈጽሞ እንዳይደገም አገር ተማምሎ ሕገ መንግስት ባጸደቅን 25 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይሆን ሰርቶ ለመብላትና ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች በጅምላ ሲፈረጁ፤ ሲጠረጠሩ ከማየት አልፈን ተርፈን፤ ይሄው  የተዛባና ጤናማ ያልሆነ አመለካከት እንደ መብት ተቆጥሮ፣ ያለአንዳች ይሉኝታና መታቀብ በየአደባባዩና በሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በስፋት ሲነገር ለማዳመጥ በቅተናል፡፡ ሰሞኑን ከገቢ ግምት ጋር ተያይዞ፣ ነጋዴዎች በሕገ መንግስቱ ላይ የሰፈረ መብታቸውን ተጠቅመው ተቃውሟቸውን እንዳያሰሙ ለማድረግና ቀድሞ አፍ ለማዘጋት  ሲባል፣ ግብር በመሰወርና ገቢ በማሳነስ ጅምላ ተጠርጣሪነት ሲፈረጁ በስፋት አድምጠናል፡፡
ሕገ መንግስቱ ዜጎች ኢ-ሰብአዊ ለሆነና ሰብእናቸውን ለሚነካ ድርጊት አይጋለጡም ቢልም፣ ነጋዴውን ማህበረሰብ በጅምላ መጠርጠርና ከጥርጣሬ ተነስቶ ሰብእናውን የሚነካ ሃሳብ መሰንዘር ወይም ከጥርጣሬ ተነስቶ ሰርቶ የመኖር መብቱን የሚፈታተኑ ሕጎችና ድንጋጌዎችን ማውጣት ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ነጋዴዎች በተለይ ደግሞ በመለስተኛና አነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎች፣ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ለበርካታ ጊዜ ገቢ በመሰወርና ግብር በማሳነስ እየተጠረጠሩ ዓመታዊ ገቢያቸውና የሚከፍሉት ግብር በተደጋጋሚ ተከልሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ተረጋግተው ስራቸውን ለማከናወንና የንግድ ሥራቸውን ለማስፋፋትም ሆነ የሚጠበቅባቸውን የግብር ግዴታ ለመወጣት አልታደሉም፡፡ ህይወታቸውም እንደ ቆቅ የስጋት ነው፡፡ ዘንድሮ የማይጠበቅ  ግብር ይጣልብኛል በሚል ስጋትና በድብብቆሽ ተጠምደው ጊዜያቸውን እየገፉ እንደከረሙ ግልጽ ነው፡፡  የዘንድሮው ፈተና ደግሞ ከፈተናም የከበደ ፈተና!
‹‹ሁለተኛ ዜግነት››
በበርካታ አገራት እጃቸውን አጣምረው ከመንግስት የስራ ዕድል የማይጠብቁ፣ በራሳቸው ጥቂት ጥሪት፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ተጠቅመው፣ ኑሮአቸውን የሚያሸንፉ ዜጎች ከተደራራቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ ይደረጋሉ። በተቃራኒው ለመሰረተ ልማት፣ ለሃገር ደህንነት የሚውል የግብር ከፋዩን ገንዘብ እጃቸውን አጣምረው የሚጠብቁ ዜጎች ደግሞ ድርጊታቸው የሚበረታታ ሳይሆን የሚነወር ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ ሃገራት የመንግስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ዜጎች፤ በልዩ ድጋፍ ውስጥ የሚታቀፉ  በተለይ መስራት የማይችሉ፣ ቤተሰብ አልባ የሆኑ ሕጻናት ወይም ሀገራቸውን አገልግለው ጧሪ በማጣታቸው የተቸገሩ አረጋውያንና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የሚሰራው በተቃራኒው ነው፡፡ ሃገር መለወጥ የሚጠበቅባቸውና መስራት የሚችሉ ዜጎች፤ መሬትና ገበያ በነጻ ተመቻችቶላቸው፣ መንገድ ተለቆ ግብር ሳይከፍሉ ይነግዳሉ፡፡ በራሳቸው ጥሪት ድርጅት ከፍተው፣ ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የሚታገሉ ዜጎች ግን ከመጠርጠር ጀምሮ የሌሎችን ሕይወት ለመለወጥና “ሚሊዬነር” ለማድረግ  የማይሞላ ኮሮጆ እንዲሞሉ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ስለ ዜጎች እኩልነት በሰፊው ይዘረዝራል፡፡ በአጠቃላይ ግንዛቤ ደረጃ ዜጎች በተፈጥሮም ሆነ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ማንኛውም ዜጋ ከፍላጎቱ ውጭ የሌሎችን ሕይወት ለመለወጥም ሆነ ለመደጎም  ሲባል በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በጉልበቱና በላቡ ያፈራውን ሃብትና ጥሪት እንዲያጋራና እንዲያካፍል ሊገደድ አይገባውም፡፡ በግብር መልክ የሚሰበሰብ ገንዘብም ቢሆን ለዜጎች የጋራ ጥቅም የሚውሉ መሰረተ ልማቶችን ለማሳካትና  የሁሉንም ዜጎች ደሕንነት ለማስጠበቅ፣ የሃገርን ሉአላዊነት ለማስከበር ከመዋል ውጭ የማንንም ሕይወት ለመደጎም መዋል የለበትም፡፡ በዚህ መንገድ የሚደረግ ጉዞ ደግሞ ተያይዞ የመውደቅና የዜሮ ድምር ውጤት ከመሆን አያልፍም፡፡
የዜጎች እኩልነት የሚረጋገጠው በተፈጥሮና በሕግ ፊት እንጂ ክህሎቱን፣ ጥሪቱን፣ ጊዜና ጉልበቱን አፍስሶ ከሚሰራው ዜጋ ላይ በግብር ስም ሀብት እየቀነሱ፣ ስራ የለም በሚል እጃቸውን አጣምረው ለተቀመጡና በግብር ከፋዩ ሀብት ተሽከርካሪ፣ ሕንጻና የቢሮ ቁሳቁስ ለሚያማርጡ ሙሰኞችና አባካኞች ካዝናውን ምቹ በማድረግ ሊሆን አይገባም፡፡  ይህ ከሆነ ደግሞ ስርዓቱ ዛሬም እንደ ቀደምት ስርዓቶች ሁላ አንዱ ሳይሰራ ሕይወቱን የሚያደላድልበትና ቀሪው ደግሞ እንደ ሁለተኛ ዜጋ  ተቆጥሮ፣ በዘመናዊ አገልጋይነት የላብና የድካሙን ዋጋ ከሚገፈግፍበት ከፊውዳሎች ስርዓት የሚሻል አይሆንም፡፡
ለብልጽግና እና ለእድገት የበቃ ስርዓት ያላቸው ሀገራት፤ ዜጎቻቸው በእውቀታቸውና በላባቸው ያፈሩትን ሃብት በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሌሎች እንዲያካፍሉ በተገደዱባቸው ሀገራት ሳይሆን የሰዎች ላብና ድካም ተገቢውን ዋጋና ክብር ባገኘባቸው ሃገራት እንደሆነ ታሪክን መለስ ብሎ ማጤን ያሻል፡፡ መንግስት ሀገራዊ ሃብቱን አቀራምቶና ተቀራምቶ፣ ሁሉንም ዜሮ በማስገባት ተያይዞ ላለመውደቅ፣ ዜጎች ሁላ እኩል በጉልበታቸው፣ በእውቀታቸውና በላባቸው ማደርን የሚያስገድዳቸው የግብር ስርዓት መዘርጋት አለበት።
የማይሞላ ኮሮጆ ሌላ ገጽታ
ዜጎች የሚከፍሉት ግብር ተገቢው ጥበቃ እየተደረገለት እንደሆነ፣ አላግባብ እንደማይባክን፣ ለሙስና እንዳልተጋለጠ አልፎ ተርፎም ለምን ተግባር እንደዋለ የማወቅ ሕገ-መንግስታዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በተከበረበት ሃገር፤ ግብር የዜግነት፣ የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት ለዘረፋ፣ ለብክነት፣ ለሙስና እየተጋለጠ ባለበት ሁኔታ ከአንድ ወገን የሚነሳ ፍላጎትን ለማሟላት ሲባል ብቻ በግብር ስም የአንዱን ሃብት በተጽእኖ ለሌላው ማጋራት ፍትሃዊነት የጎደለው ተግባር ነው።
መንግስት በየዓመቱ በኦዲት ተቋሙ አማካኝነት ለተወካዮች ምክር ቤት በሚያቀርበው ሪፖርት ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ሃብት ለከፍተኛ ብክነት፣ ሙስና እና ዘረፋ የተጋለጠ መሆኑን ሳያስደምጥ አልፎ አያውቅም፡፡ መንግስት በተለያየ ጊዜ ፓርላማ ላይ እየቀረበ “የመንግስት ሌቦች” የሚላቸውን አንዳንድ ባለሟሎች፤ ምን ያህል የመንግስት ካዝና እንደሚቦጠቡጡ በምሬት ሳይገልጽ ውሎ አድሮ አያውቅም፡፡ መንግስት ፍጆታውን በመቆጠብ ዘረፋን፣ ሙስናንና ብክነትን በመከላከል ካዝናውን መጠበቅ አቅቶት እያለ፣ ዘረፋና ሙስና የቦጠቦጠውን ካዝና ለመሙላት ሲባል፣ ዜጎች ከፍትሐዊነት በራቀ መልኩ በየዓመቱ በግምት ላይ ተመስርቶ የሚጣልን የተጋነነ ግብር መገፍገፍ የለባቸውም የሚል እምነት አለኝ፡፡
ዜጎች፤ ሕይወታቸውን ከማሸነፍ ባሻገር ጥሪት የመያዝ፣ ሃብት የማፍራት፣ ሕይወታቸውን ወደ ላቀ የአኗኗር ደረጃ የማሳደግ መብት አላቸው። ትርፋቸውን መጠነ ሰፊ የሆነ ግብርና የማያበቃ መዋጮ ሳይቀራመትባቸው፣ ጥሪታቸውን አጎልብተው በመቆጠብ፣ የቤተሰባቸውን ሕይወት የማሻሻል መብት አላቸው፡፡ ቁጠባቸውና ያፈሩት ጥሪት ለሌላ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ሊሆንና በሚገኘው ተጨማሪ ወረት ሕይወታቸውን ሊያሻሽሉበት ይገባል፡፡ ኢንቨስትመንትም የሚያድገው በብድርና በባለቤቶች ሃብት ብቻ ሳይሆን ዜጎች ከቁጠባቸው ላይ ሼር በመግዛት በሚያደርጉት መዋጮ ጭምር መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ዜጎች በሙስና ብክነትና ዝርክርክነት በሚሸረሽረው የማያልቅ የመንግስት የገንዘብ ፍላጎት ውስጥ ተጠምደው በመዳከር ሕይወታቸውን ማሻሻል እንዳያዳግታቸው መንግስት ጥንቃቄ  ማድረግ ይገባዋል፡፡ መንግስት አዲስ የመጣ ተሽከርካሪ፣ የቢሮ ቁሳቁስና ሞባይል ለሚያምራቸው ሹመኞቹ የፍላጎት ገደብ ማበጀት አለበት፡፡ ቤታቸው ውስጥ የማይደፍሩትን ድግስ፤ በሕዝብ ሃብት አዘውትረው በመደገስ፣ በግብር ከፋዩ ሃብት ቸር ለሚሆኑ ሹመኞቹ ሲባል ግብር  በየዓመቱ መጨመር ምክንያታዊነትና ፍትሐዊነት የሚጎደለው አካሄድ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔው ደግሞ መንግስት አስተዳደራዊ ወጭን በአግባቡና በቁጠባ መጠቀምን መርህ በማድረግ፣ ለየሹመኞቹ ምክንያታዊነትና ፍትሐዊነትን ማስተማር ብቻ ነው። የሕዝብን ሀብት ከዘረፋ በመታደግ ግብር ከፋይ ዜጎች ከከፍተኛ የግብር ጫና እና ከእለት ተእለት ስጋት እፎይ የሚሉበት ጊዜ  እውን  መሆን አለበት፡፡ ለዘረፋና ለሙስናና ለብክነት የተጋለጠና የማይሞላ ካዝና ይዞ ሕዝብ ፊት ከመቅረብ፣ ካዝናውን ጠግኖና ቀልፍ አበጅቶ፣ ዜጎችን ተስፍ ከመቁረጥና ከተመጽዋችነት አልፎ ተርፎም የሀገርና የባዕድ ጥገኛ ከመሆን መታደግ ያሻል፡፡
ግምትና ማረጋገጥ
መሳ ለመሳ እንደ መፋረጃ
አዲሱ የገቢ ግምት አሰራር ሌላው አወዛጋቢ ገጽታው ግምቱን ለመከወን የተሰማሩት ግለሰቦች ሙያዊ ብቃት ጥያቄ ላይ የወደቀ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር በባህላዊ መንገድ መሰብሰብ ከጀመረ በርካታ ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል። የግብር አሰባሰብ ስርዓቱም በሙያ እንዲታገዝ ጥረት መደረግ ከጀመረ  ቢያንስ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ዛሬ ላይ ግን ለግምት ስራ መስክ ከወጡት ሰራተኞች አብዛኛዎቹ ስለ ንግድና ግብይት ተመክሮም ሆነ ልምድ የሌላቸው ናቸው፡፡ ገማቾቹ ቢያንስ ቢያንስ ነጋዴው ለሽያጭ ያቀረበውን ቀሳቁስ በዋጋ፣ በጥራት ደረጃ፣ በብዛት፣ በዓይነት የሚለዩ እንዲሁም የትርፍ ሕዳጉን በየስራ ዘርፉ ተንትኖ ለመረዳት የሚያስችል እውቀትና ልምድ የቀሰሙ መሆን ነበረባቸው፡፡  
በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን፣ መንግስት የግብር አሰባሰብ ስርዓታችንን በባለሙያ፣ በዘመናዊ የኮምፒዩተርና የሶፍትዌር አመዘጋገብ ስርዓት እንዲታገዝ በማድረግ  ወጥነትና ቀጣይነት ያለው የግብር አሰባሰብ ዘይቤ ተግባራዊ መድረግ ሲገባው፤ ዛሬም ላይ ሆነን ነጋዴውን ከቀቢጸ ተስፋ ለመታደግ የሚያስችል በደመ-ነብስ ከሚደረግ የግምት አሰራር መውጣት አልተቻለም፡፡ የመንግስት የገንዘብ ፍላጎትና ወጭ ባደገ ቁጥር አስቀድሞ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ነጋዴዎችን በተጠርጣሪነት በመፈረጅና በማሸማቀቅ፣ እንደ ቁም ከብት ንግድ  የአቦሰጡኝ ግብር መጣል በምንገኝበት ዘመን አስተዛዛቢ ድርጊት ነው፡፡  
እጅግ የሚያስደንቀው ጉዳይ ደግሞ በአንድ ህንጻ ላይ ያሉ የሕጻንም ሆነ የሴት ወይም ወንድ ልብስ አሊያም አንደኛና ወይም ሁለተኛ አሊያም ሶስተኛ ይገኙ አሊያም ሕንጻው አስፋልት ዳር ይገኝ መንደር ውስጥ ገማቾቹ  ዓመታዊ የሽያጭ ገቢ የሚገምቱት በአብዛኛው እኩል ነው፡፡ ነገሩን እጀግ አስቂኝ የሚያደርገው ደግሞ በየስማቸው የሚሰጣቸው ደብዳቤ ይህንኑ ሲያትት በዚህ ቀን በተደረገው ግምት፣ ‹‹የቀን ገቢህ ይህንን ያህል ብር መሆኑ ተረጋግጧል” የሚል መሆኑ ነው፡፡ መገመትና ማረጋገጥ መሳ ለመሳ እየቀረቡ፣ የፈለጉትን ለመወሰን መፋረጃ ሆነው መቅረባቸው ከግዴለሽነት ውጭ ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡
ግምት ግምት ነው፡፡ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስሜት ነው፡፡ ማረጋገጥ ግን ከጥናትና ከምርምር የሚገኝ ውጤት ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከግምት በኋላ ገለልተኛ ከሆነ አካል ጋር በይፋ ቢያንስ እንኳን ዘርፍ በዘርፍ ድርድር  ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ማረጋገጥም ሆነ ስምምነትን ማግኝት በተቻለ ነበር። ይህ ግን አልሆነም፡፡
ኃላፊነትን ሳይወጡ ኃላፊነትን እንዲወጡ መጠበቅ
እንደ አፍሪካ ባሉ ሃገራት ዜጎች በስልጣንና በፖለቲካ ጉዳይ መጠርጠራቸው ነውር የሌለው ድርጊት ነው፡፡ የአፍሪካ መንግስታት መቶ በመቶ መረጠን የሚሉትን ሕዝብ በስጋት መከታተል፤ ፈጽም የተባለውን አይፈጽምም ከሚል ጥርጣሬ በመነሳት መሰለል፣ ኢ-ፍትሐዊነትን እንዳይቃወም አስቀድሞ አጀንዳ በማስጣል ማሸማቀቅና እጁንና አፉን እንዲሰበሰብ ማድረግ የተለመደ በስልጣን ላይ የመቆያ ዘዴ ነው፡፡
ወደ ሃገራች ገቢና የግብር ስርዓት ስንመጣ፣ ይኸው የተለመደው የአፍሪካውያን መሪዎች ዘዴ ተግባር ላይ ሲውል በገሀድ እንመለከታለን፡፡ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያለው ነጋዴ ማህበረሰብ የሚገኘው ትርፍ ከእጅ ወደ አፍ ከመሆንም በላይ የትርፉም አመጣጡ እንዲያው በዋዛ አይደለም፡፡ትርፉ የሚገኘው እለት ከእለት በሚደገር ከጦር ሜዳ ያልተናነሰ ትንቅንቅና ግብግብ ውስጥ ታልፎ ነው፡፡ ብዙ ሕገ ወጥ ድርጊት ማሸነፍ ይጠይቃል ፤ በሕግ ስም ከተሰማሩ ሕግ ከሚጥሱ ሕግ አስከባሪዎች ጀምሮ ከኮንትሮባንዲስቶች፣ ንግድ ሚኒስቴር ከማያውቃቸው የኮንትሮባንድ ልባሽና እቃ አዟሪዎች፣ የሃገሪቱ የንግድ ስርዓት ከማይገዛቸው ልዩ ድጋፍ ከሚደረግላቸውና መንገድ ተዘግቶላቸው የአካባቢን ንጽህናና ድምጽ በመበከል ከሚነግዱ ጋር ከፍተኛ ውድድር ተካሂዶ ነው፡፡
ከፍተኛ ነጋዴ የሚባሉትና የጅምላ አስመጭዎችና አከፋፋዮችም እጃቸው ረጅም ስለሆነ ተጸእኖአቸው ቀላል የሚባል አይደልም፡፡ ምሳሌ ልስጥ፡፡ ጅምላ አከፋፋዮች የሚያስገቡትን እቃ ለቸርቻሪዎች ሲሸጡ የሚቆርጡት የቫት ደረሰኝ አንደር ኢንቮይስ የሆነ ነው፡፡ በአምስት መቶ ብር የገዙትን እቃ ወደ ሃገር ውስጥ ሲያስገቡ ከጉምሩክ ሰዎች ጋር በመመሳጠር፣ ሁለት መቶ ብር እንደተገዛ አድርገው ተጨማሪ እሴት ታክሰ  ይከፍሉበታል። ቸርቻሪው ሲገዛ የሚጠየቀው የእቃው ዋጋ ግን የተገዛበት እውነተኛ ዋጋ ማለትም አምስት መቶ ሲደመር የጅምላ ነጋዴው ትርፍ ተጨምሮበት ነው። የጅምላ ነጋዴው ትርፍ እንበል ሁለት መቶ ብር ቢሆን የእቃው አጠቃላይ ዋጋ ሰባት መቶ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ቸርቻሪው የሚከፍለው ይህንን ዋጋ ነው፡፡ ደረሰኝ የሚሰጠው ግን ተጨማሪ እሴት ታክስ በተከፈለበት ዋጋ ብር ሁለት መቶ እና የአከፋፋዩ ትርፍ ሁለት መቶ ብር ተደምሮ አራት መቶ ብር ብቻ ነው፡፡ የጅምላ ነጋዴዎቹ በጣት የሚቆጠሩና ምትክ የሌላቸው ስለሆኑ ለቸርቻሪው የሚሰጠው አማራጭ ከፈለክ ውሰድ አሊያም ተወው ነው፡፡ ሲያሻቸውም ደረሰኝ ይነፍጉታል፡፡ በዚህም ምክንያት ቸርቻሪው ተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ መግባት አያዋጣውም፡፡ ለምን ? በሕገ ወጥ ደረሰኙና ቸርቻሪው በሚሸጥበት ዋጋ መካከል ያለው ያልተመዘገበ የጅምላ አከፋፋዩ ትርፍ የግብር እዳ ከፋዩ ቸርቻሪው ስለሚሆን ነው፡፡  
መንግስት በየተቋሙ ውስጥ ያሉ ሕገ ወጦችን መከላከል ያለበት ለነጋዴው ማህበረሰብ ብሎ ሳይሆን ሕጋዊ ግዴታ ስላለበት ነው፡፡ ነጋዴዎች ደግሞ አግባብ ላለው ትርፍ፣ ተገቢውን ግብር የመክፈል የሞራልና ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡  በመንግስትም ሆነ በነጋዴዎች  ላይ ሕግ የሚጥለው ግዴታ እኩል ነው፡፡ ነጋዴው ማህበረሰብ ግብር የመክፍል ግዴታ ያለበትን ያህል ለከፈለው ግብር ተመጣጣኝ የሕግ ጥበቃና ከለላ የማግኘት መብት አለው፡፡
መንግስት ከሀገራዊ አጠቃላይ ምርት እድገት ጋር ተመጣጣኝ ገቢ ከግብሩ ለማግኘት በግምት ግብር መጨመር መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ትክክለኛው መንገድ ለግብሩ መቀነስ  ምክንያት የሆኑ አካላት ወደ ሕጋዊ ስርዓቱ  እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡  የነገደና ያተረፈ ሁሉ ተገቢውን አገልግሎትና ግብር መክፍል አለበት፡፡ ከግብር ነጻ የሆነ አገልግሎት ማንም ዜጋ ማግኘት የለበትም፡፡ በሌላው ላብ፣ ጊዜና ጉልበት እራስን በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥተኛ መንገድ ማበልጸግ የሚሹም ከዚህ ድርጊት መታቀብ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ድጋፉ ለሁሉም  ዜጋ በእኩል መስፈርት መሆን አለበት፡፡
ከላይ በዝርዝር ያቀረብኳቸው ከኮንትሮባንድ ንግድ ጀምሮ የመንገድ ላይ ግብይትና የኮንትሮባንድ አዟሪዎችን ጨምሮ የመንግስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ነጋዴዎች፤ በግብር ስርዓቱ ውስጥ የሚካተቱበትን መንገድ መፍትሔ የመሻት ሕጋዊ ግዴታ መንግስት አለበት፡፡ በመጨረሻም የግብር መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ሕጋዊ የሆነውን መካከለኛና አነስተኛ ነጋዴው በሕግ እይታ ውስጥ ስለሆነ ብቻ  ክፍተት እንዲሞላ የማድረግ ተጽእኖ እንዲቆም ከተፈለገ፣ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ነጋዴዎች፤ በሙስናና  በጥቅም በመተሳሰር የሚያሸሹትን ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ፤ በሕግ ጥላ ስር የማይነግዱ ኮትሮባንዲስቶች ወደ ግብር ስርዓት እንዲገቡ መታገል ከመንግስት  ይጠበቅበታል፡፡
በመጨረሻም ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ መንግስት አዳዲስ መጫወቻ እንደሚያምረው ሕጻን አዲስ ተሽከርካሪ በተመረተ ቁጥር ለመግዛት ከቋመጡ፤ በየዓመቱ መጀመርያ ላይ አዳዲስ ሞባይል፣ ኮምፒዩተርና የቢሮ ቁሳቁስ ከሚያግበሰብሱ እንዲሁም አዲስ ሕንጻ ባለቀ ቁጥር ለመከራየት ከሚተጉ ሹመኞች፤ የግብር ከፋዩን ገንዘብ መታደግ አለበት፡፡ ብክነት የእድገት ጠር ስለሆነ በግብር ከፋዩ ድሃ ሕዝብ አቅም ልክ በቁጠባ መኖር የመንግስት ባህል መሆን አለበት፡፡ ሙስና  የመንግስትን ገቢ በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያዳክም ቀበኛ ነው። ድሃው ሕዝባችን ላቡን፣ ጊዜውን፣ ጉልበቱን አፍስሶ የሚያፈራው ሃብት፤ የሙሰኞች አስረሽ ምችውና ዳንኪራ ማድመቂያ መሆን የለበትም፡፡ ገቢ ሲያንስ ድሃ ይበላው  እንጂ ይገብረው አያጣም የሚለው አመለካከት ከፊውዳሊዝም ስርዓት ጋር አብሮ የተቀበረ አስተሳሰብ መሆን አለበት። ዜጎች ተመጣጣኝ ግብር የመክፈል ግዴታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጥሪታቸውን ለዘመናዊ ፊውዳሎች መገበራቸው መቆም አለበት፡፡   Read 2282 times