Sunday, 09 July 2017 00:00

አነጋጋሪው “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጅ”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“የልዩ ጥቅም አዋጅ በእውነት ጥያቄውን ይመልሳል?”

በአዲስ አበባ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ም/ቤት ከጸደቀ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት
መቅረቡ ተነግሯል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ ዜጎች እንደሚወያዩበትም ተገልጧል፡፡ ለመሆኑ ረቂቅ አዋጁ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ግንኙነት ላይ
ምን አንደምታ አለው? ከህገ መንግስቱ አንጻርስ እንዴት ይታያል? በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የወደፊት ስጋቶችና አደጋዎች ይኖሩት ይሆን? ለምንስ
አነጋጋሪ ሊሆን ቻለ? ምሁራንና ፖለቲከኞች ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤የተለያዩ አስተያየቶችን አሰባስቦ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ (ለፖለቲካዊ ችግሮች ሁሌም መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው) ከሚተጉ ሹመኞች፤ የግብር ከፋዩን ገንዘብ መታደግ አለበት፡፡ “

አቶ አሊ አብዱ ሂጅራ (የህግ ባለሙያ)

በሽግግሩ መንግስት ጊዜ የተዘጋጀው የክልሎች አወቃቀር አስራ አራት ክልሎች እንዳሉ የሚያሳይ ነው፡፡ አዲስ አበባም አንዱ ክልል ሆኖ ክልል 14 ይባል ነበር፡፡ በመሰረቱ ኋላ ላይ ዛሬ የምናያቸው 9 ክልሎች የተፈጠሩት ከክልል 7 እስከ 11 የነበሩት በአንድ ተጠቃለው “ደቡብ ክልል” በመባላቸው ነው፡፡ ሁሉም ክልላዊ መስተዳድሮች በመልክአ ምድራዊ ክልላቸው ውስጥ ባሉ ጉዳዮች ሁሉ የህግ አውጪነት፤ የህግ አስፈፃሚነትና የዳኝነት ሥልጣን እንዲኖራቸው ተደርጎ፣ ዋና የበላይ የሥልጣን ባለቤት ግን ማዕከላዊ መንግስቱ ሆኖ ተቋቋመ፡፡
በወቅቱ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በሀረር ክልል የኦሮሚያ ልዩ ብሄራዊ ጥቅምና የፖለቲካ መብት የተጠበቀ ይሆናል የሚል ህግ ወጣ፡፡ የእነዚህ ክልሎች ተጠሪነት ለማዕከላዊ የሽግግር መንግስት ሆኖ የመስተዳድሮቹ ግንኙነት በዝርዝር በህግ ይወሰናል ተባለ፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን የተደነገገው በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን ሃረር ላይም ነው፡፡ እዚህ ህግ ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋና በአማርኛ ቋንቋ የቀረበው ላይ የትርጉም ልዩነት አለው፡፡ በአማርኛው ላይ በኦሮሚያ ክልል እና በሁለቱ አስተዳደሮች መካከል ያለው ግንኙነት በሌላ ህግ በዝርዝር ይወሰናል ይላል፡፡ እንግሊዝኛው ደግሞ በማዕከላዊ መንግስት እና በሁለቱ አስተዳደሮች መካከል ነው የሚለው፡፡ በወቅቱ የተነሳው ስለ “ልዩ ጥቅም” ብቻ ሳይሆን ስለ ልዩ ብሄራዊ ጥቅምና የፖለቲካ መብት ነበር፡፡ ይሄ የሆነው በጥር 1984 ዓ.ም በወጣ፣ አዋጅ ቁጥር 7/84 ህግ ነው፡፡
በ1987 ህገ መንግስቱ ሲወጣ ደግሞ በአንቀፅ 49 የተቀመጠው ጉዳይ አለ፡፡ አንቀፁ ላይ የተቀመጠው ጉዳይ ስለ ክልል የሚደነግግ አይደለም፡፡ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ርዕሰ ከተማ መሆኑ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን እንዳለው፣ አዲስ አበባ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስቱ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ራሳቸውን ችለው በፓርላማው እንደሚወከሉ ይገልጽና በመጨረሻ ላይ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፤ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ እንደመሆኑ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ጥቅም ይጠበቅለታል፤ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል ነው የሚለው፡፡
እንግዲህ ከአዋጅ 7/84 በኋላ እስከ 1987 ዓ.ም ልክ እንደ ሌላው ራሱን ችሎ ክልል የነበረው አዲስ አበባ፤ ህገ መንግስቱ ሲወጣ፣ ክልል አይደለም የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ግዛት ነው፤ ተጠሪነቱም ለፌደራል መንግስት ነው፤ አዲስ አበባ ራሱን የቻለ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ማለት አዲስ አበባ የማንም ክልል መሬት ሳይሆን የፌደራል መንግስቱ ግዛት ነው፡፡ እንደ ናይጄሪያዋ ዋና ከተማ አቡጃ፣ እንደ ዋሽንግተን ዲሲ ማለት ነው፡፡ ማንም የኔ ነው ሊል አይችልም፡፡
ወደ ልዩ ጥቅም ጉዳይ ስንመጣ፤ ቀደም ሲል በሽግግሩ ጊዜ “ልዩ ብሔራዊ ጥቅም” ነበር የሚለው፤ እዚህኛው ላይ ደግሞ “ልዩ ጥቅም” በሚል ነው የተገለፀው፡፡ ሀረር ላይ በሽግግሩ ጊዜ የነበረው አዋጅ ያስቀመጠው በህገ መንግስቱ አልተካተተም፡፡
በህገ መንግስቱ “አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሃል የምትገኝ” በሚል ነው የተቀመጠው፡፡ ይሄ ማለት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች ማለት ነው? በህገ መንግስቱ በግልፅ የተቀመጠውን ጥሠን አንድ ክልል በሌላው ክልል ውስጥ ስልጣን እንዲኖረው ማድረግ እንችላለን? በኔ ትሁት አረዳድ ትግራይ በኦሮሚያ፣ ኦሮሚያ በትግራይ ወይም አንድ ክልል በሌላው ክልል ላይ ስልጣን እንዲኖረው ህገ መንግስቱ አይፈቅድም፡፡ ወንጀለኛ እንኳ ጠፍቶ ሲሄድ የዚያን ክልል ፍቃድ መጠየቅ ወይም ጉዳዩ የፌደራል ስልጣን ነው የሚሆነው፡፡ ግን ይህ ተጥሶ የተደረገበት አጋጣሚ በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የጎንደር ፖሊስ ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊን አዲስ አበባ መጥቶ ነው የወሠደው፣ በፍቃዱ ሞረዳን አዲስ አበባ ላይ ተሠራ በተባለ ወንጀል የአሶሳ ፖሊስ ነው አዲስ አበባ መጥቶ የወሰደው፡፡ ግን የአሶሳም ሆነ የጎንደር ፖሊስ አዲስ አበባ ላይ ስልጣን አልነበረውም፡፡ ስልጣን ያለው የፌደራል ፖሊስ ነው፡፡
በ1989 የወጣው የአዲስ አበባ አዋጅ ማለትም አዋጅ ቁጥር 87 የሚባለው ምን ይላል? የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዲኖረውና ዝርዝሩ በህግ እንደሚወሰን፣ አስተዳደሩ በፌደራል መንግስት የሚወከልበትን የሚገልፅ ህግ ወጣ። ይሄው ህግ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር ስለሚኖራት ግንኙነት ድንጋጌ አውጥቷል፡፡ በዚህ ቻርተር አንቀፅ 2(1) መሠረት፤ የሚከለለው የአዲስ አበባ ወሠን በከተማው መስተዳደርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በጋራ ተለይቶ ምልክት ይደረግበታል፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መቀመጫውን በአዲስ አበባ የማድረግ መብት ይኖረዋል፤ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ለአዲስ አበባ ህዝብ የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች በመስተዳድሩ አዋሣኝ ለሚኖረው የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ሊዳረሱ የሚችሉ ሲሆን ነዋሪዎቹ በተመሣሣይ ሁኔታ የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይደረጋል የሚሉ ድንጋጌዎችን በማስቀመጥ የህገ መንግስቱን ነገር የበለጠ አብራርቶታል፡፡
በዚህ ቻርተር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ለአዲስ አበባ ህዝብ ከሚያቀርባቸው አገልግሎች ጋር የተያያዙ የልማት ስራዎችን በኦሮሚያ ክልል መስራት የሚችለው በቅድሚያ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በመመካከርና በመስማማት ይሆናል ይላል፡፡ ይሄ የጉርብትና ግንኙነቱን ይመለከታል ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ እያለ በድጋሚ የአዲስ አበባ ከተማ ህግ በጥር 1995 ዓ.ም ተሻሻለ፡፡ በዚህ የተሻሻለ ቻርተር ላይ የከተማዋ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር ፍሬያማ ትብብርን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ይኖረዋል፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት፤ የኦሮሚያ ጥቅም የተጠበቀ ነው ብሎ አሁንም ዝርዝሩ በከተማዋ አስተዳደር እና በክልሉ መካከል በሚደረግ ስምምነት ወይም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሚወጣ ህግ ይወሰናል አለ፡፡ በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ በድጋሚ ሌላ አዋጅ ቁጥር 362/95 የሚባል ቻርተር ወጣ፡፡ 6 ወር ሳይሞላ ቻርተር ተቀየረ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የይዘት ችግር አለበት የሚል ነበር። በዚህ ቻርተር ላይም የሁለቱን አካላት ግንኙነት በተመለከተ የተቀመጠው ተመሳሳይ ነበር፡፡ እንግዲህ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአንቀፁ እንደተቀመጠው ነው ያለው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት በ1984 በወጣው አዋጅ፤ ኦሮሚያ ዋና ከተማው “ፊኒፊኔ” ይሆናል የሚል ተቀመጠ፣ እንደገና በ1987 የወጣው አዋጅ፣ ርዕሰ ከተማውን “ፊኒፊኔ” አደረገ፡፡ ከዚያ በ1994 በወጣ አዋጅ አዋጅ ርዕሰ ከተማው “አዳማ” መሆኗን ገለፀ፡፡ በኋላ አዲስ አበባ ሆነ፡፡  
በአዲስ አበባ ውስጥ ስልጣን የሌለው ክልል ለምንድን ነው አዲስ አበባ ውስጥ ርዕሰ ከተማውን የሚያደርገው? የሚያዝበት ነገር‘ኮ የለውም። የፌደራል መንግስት መቀመጫ የማንም ክልል አይደለችም። አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ከሆነች በኋላ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መሆኗ ለምን አስፈለገ? የፌደራል መንግስት መቀመጫ የሁሉም ነው መሆን ያለባት፡፡ በኦሮሚያ መሀል መሆኗ ብቻ የኦሮሚያ ነች አያስብላትም። ሌላው ችግር የሁለቱ ክልል ድንበር እስከ ዛሬ በግልፅ አለመካለሉ ነው፡፡
ወደ ልዩ ጥቅም ጉዳይ ስንመጣ የነባር እና የመጤ ህዝብ ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ፣ የዚህ ሀገር ባለቤት የአገው ህዝብ መሆን ነበረበት፡፡ እቺ ሀገር የሁሉም ናት፤ የችግራችን መንስኤ ህብረ ብሄራዊነትን መዘንጋትና በብሔረሰባዊ ግቢ ውስጥ የታሰረ “የኔ ብቻ ነው” ባይነት ነው፡፡ ይሄ የልዩ ጥቅም አዋጅ በእውነት ጥያቄውን ይመልሳል? ህዝቡ፣ የፌደራሊዝም ባለሙያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር አለባቸው፡፡
ሌሎች ነባር ህጎች የማይፈቱት የአካባቢ አየር ብክለት ጉዳይ፣ የስራ አጥነት፣ የካሣ ጥያቄ ችግር አለብን ወይ? ይሄ የውሸት ቁስል ማከሚያ ነው፡፡ ይልቅ ቁስሉ ምንድን ነው የሚለውን እንመርምረው። የቋንቋ ጉዳይ ከተነሳ ኦሮሚኛ የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለምን በመላ ሀገሪቱ በትምህርት ተሰጥቶ የስራ ቋንቋ አይሆንም፡፡ አማርኛም በታሪክ አጋጣሚ የመጣ ቋንቋ ነው፡፡ በግድ እና በልዩ ጥቅም ሳይሆን ለምን በትምህርት አናስፋፋውም፡፡

==============================

“አዲስ አበባ ላይ የመወሰን መብቱ የአዲስ አበባ ህዝብ ነው”

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

በመሰረቱ የእኛ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ የስልጣን ባለቤት የሚላቸው ዜጎችን ሳይሆን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ነው፡፡ አንድ ዜጋ በራሱ ስልጣን የለውም ማለት ነው፡፡ በአንድነት ከሚያስተሳስሩን ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮረ ነው፤ ህገ መንግስቱ ራሱ፡፡ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ ልዩ ጥቅም ማለት የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ ከባዕድነት የሚመነጭ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ባድመ ላይ ሄደው ሲሰዉ ሀገራችን ለሁላችንም እኩል ናት፤ አባቶቻችን ጠብቀው ያዩዋት፣ ሀዘንም መከራንም እኩል የምንካፈልባት ናት ብለው ነው። ይሄ ልዩ ጥቅም ደግሞ ከዚህ አስተሳሰብ የራቀ፣ ከባዕድነት የሚመነጭ ነው፡፡ በዚህ ልኬት ከሄድን ደግሞ የአባይ ምንጭ ጎጃም ነው፣ የህዳሴው ግድብ ደግሞ ቤኒሻንጉል ነው፡፡ ስለዚህ የጎጃም ህዝብ፤ የአባይ ምንጭ ባለቤት በመሆኔ ልዩ ጥቅም ይገባኛል፣ ቤኒሻንጉል፤ ግድቡ የኔ መሬት ላይ ስላረፈ ልዩ ጥቅም ይገባኛል ሊባል ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ አስተሳሰብ ራሱ ከመሰረቱ የተሳሳተ ነው፡፡ ዜጎችን በአንድነት በማስተሳሰር፤ ልዩነትን በማክበር፣ የጋራ የሚያደርጉንን ነገር ማዳበር ሲገባ፣ ይሄ ግን በትኖ እንደገና መሰብሰብ አይነት አስተሳሰብ ስላለው በኔ እይታ መሰረታዊ ስህተት ያለው ነው፡፡
ተረቀቀ የተባለው አዋጅም ከህገ መንግስቱ አንፃርም ቢሆን መሰረት የሌለው ነው፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ለሚፈናቀሉ የኦሮሞ” አርሶ አደሮች ካሳ ይከፈላል ይላል፡፡ ይሄን ማለት ለምን አስፈለገ። በኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ያልሆኑም ይኖራሉ፡፡ በክልሉ በሚወጣው ህግ በጋራ ይጠቀማሉ፤ የሚጎዱም ከሆነ በጋራ ይጎዳሉ፡፡ ታዲያ እንዲህ አይነት ከፋፋይ ነገር ለምን ያስፈልጋል፡፡ ቢያንስ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በሙሉ ማለት ምን ይከብዳል? የኦሮሞ አርሶ አደሮች ብሎ መለየቱ ለምን አስፈለገ? የሌላ ብሄር ተወላጅ በአካባቢው ቢኖር ይሄ አዋጅ አይመለከተውም ማለት ነው፡፡ ይሄ በዚህ ረቂቅ ውስጥ ያየሁት አንደኛው ችግር ነው፡፡
ሁለተኛ አዲስ አበባ በሽግግር መንግስቱ ጊዜ ራሱን የቻለ ክልል ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ በቻርተሩ መሰረት ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ሆነ። ይሄ ከሆነ ደግሞ በህገ መንግስቱ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው፤ የራሳቸውን የሥራ ቋንቋ የሚወስኑት የሉአላዊ ስልጣን ባለቤቶቹ ክልሎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ አሁን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ደግሞ የአዲስ አበባ የሥራ ቋንቋ ከአማርኛ ጎን ለጎን ኦሮሚኛ ይሆናል ይላል። በህገ መንግስቱ መሰረት፣ ይሄን መምረጥ ያለበት ማን ነው?
አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ሰው ደግሞ መግባቢያው አማርኛ ነው፡፡ ኦሮሚኛ መናገር ስለማይችሉ ከስራ ይገለላሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ የዜጎችን መስተጋብር የሚንድና የከፋፋይነት ባህሪ ያለው አዋጅ ነው፡፡ ህገ መንግስቱም ይሄን ነገር አይደግፈውም፤ ምክንያቱም አዲስ አበባ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር፣ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት መሆኑ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ሃውልትን ለመሳሰሉት ቦታ መርጦ ማስቀመጥ ያለበት የግዛቲቱ አስተዳዳሪ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ነው፡፡ ሌላው እንዴት ነው ስልጣን የሚኖረው? ከህግም ከሞራልም አንፃር አዋጁ፤ ከፋፋይና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚጎዳ፣ የሀገርንም እድገት የሚፈታተን ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የመወሰን መብቱ የአዲስ አበባ ህዝብ ነው፡፡   

===================================


“በቻርተር በተቋቋመ ከተማ ውስጥ አንዱን ለይቶ ተጠቃሚ ማድረግ ተገቢ አይደለም”

አቶ ክቡር ገና (በቢዝን መሪ)
የኦሮሚያ ዋና ከተማ ቀደም ሲል አዳማ ነበር፤ በኋላ በ1997 ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ይሄ ማለት አንድ ከተማ ለሁለት አካላት ዋና ከተማነት ያገለግላል ማለት ነው፡፡ አስተናጋጁ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ሆነ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የአዲስ አበባ አስተዳደር እንደ ጭሰኛ ነው የሆነው፡፡ አስተዳደሩ መሬት ይኖረዋል፣ ህንፃዎች ይኖሩታል፤ በሌላ በኩል ግን ግዛቱ የኦሮሚያ ነው፡፡ ይሄ ነው ዋናው ነጥብ። የልዩ ጥቅም ጉዳይን ስናነሳም፣ ከእንዲህ ያለው ትስስሮሽ ምን ልዩ ጥቅም ይጠየቃል? እንድንል ያስገድደናል። ልዩ ጥቅም ሊገባ ይችል የነበረው አዲስ አበባ ራሱን የቻለ ነፃ ከተማ ቢሆን ኖሮ ነው፡፡ ማለትም ሌላ ከተማ ባይደረብበት ነበር፡፡ ይሄን ስል ከተማዋ ለሁለት መንግስታት መቀመጫ መሆኗን ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡ አዲስ አበባ ራሱን የቻለ ነፃ ከተማ ቢሆን ኖሮ ልዩ ጥቅም መነሳቱ ላይደንቅ ይችላል፡፡
ህገ መንግስቱ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ነው ሲል እና ኦሮሚያ ደግሞ መቀመጫውን አዲስ አበባ ሳይሆን አዳማ እንዳደረገ ቢቀጥል ነበር የልዩ ጥቅም ጉዳይ ሊነሳ የሚገባው። አሁን ግን አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ በሆነችበት ልዩ ጥቅም እንዴት ሊታሰብ ይችላል? የቋንቋ ጉዳይም ኦሮሚያ በግዛቴ ውስጥ የሥራ ቋንቋዬ ኦሮሚያ ነው ካለ አዲስ አበባንም ይጨምር ነበር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ዋና ከተማውን ወይም መቀመጫውን አዲስ አበባ ስላደረገና ግዛቴ ነች ስላለ፡፡ በከተማው ቋንቋው ስራ ላይ ሳይውል ይቆይ እንጂ ይሄ አዋጁ ሳይወጣ በፊትም ኦሮሚያ ቋንቋውን በስራ ቋንቋነት እንዲጠቀምበት ተፈቅዶለት ነበር፡፡ ኦሮሚያ ቋንቋውን በአስተዳደሩ ውስጥ መጠቀም ይችል ነበር፡፡ እንግዲህ የልዩ ጥቅም ጉዳይ የኦሮሚያ ክልል ዋና መቀመጫውን ከአዳማ ቀይሮ አዲስ አበባ ሲያደርግ ያለቀ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
አዲስ አበባ በቻርተር የተቋቋመች ከተማ ነች። የሀገሪቱ ዋና ከተማ ነች፡፡ ዋና ከተማ ስትሆን ደግሞ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጣ ሁሉ የሚስተናገድባት ነች፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ በዚያ ከተማ ውስጥ የተለየ ጥቅም ሊያገኝ የሚችል አካል ሊኖር አይገባም፡፡ ይሄ ህዝብን መለያየት ነው፡፡ በቻርተር በተቋቋመ ከተማ ውስጥ አንዱን ለይቶ ተጠቃሚ ማድረግ ለሙስና በር ይከፍታል፣ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን ያመጣል፡፡
እኛ ሀገር የፌደራል ጉዳይ ሚኒስቴር የሚባል አለ፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በምን ላይ እንደሚሰራ አይታወቅም፡፡ ህዝብን በማቀራረብ ላይ ነው? በመሬት ጉዳይ ላይ እየሰራ ነው ወይስ ትምህርት በመስጠት ላይ ነው? ይሄ ለኔ ግልፅ አይደለም፡፡ የፌደራል ስርአት ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ በአንድ በኩል ማዕከላዊ መንግስቱ ስልጣኑን ማጠናከር ይፈልጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ክልሎቹ በራሳቸው መንገድ የራሳቸውን ስልጣን ማጠናከር ይፈልጋሉ፡፡ እንግዲህ ዋናው ቁምነገር በዚህ መሃል ያለውን ሚዛን መፈለግ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ከሀገሪቱ ሰፊው ግዛት ነው፤በርካታ ክልሎች ያዋስኑታል፡፡ ስለዚህ ክልሉ ከሌሎች ክልሎች የተለዩ ጥያቄዎች ቢኖሩት ፌደራል መንግስቱ ያንን የመንከባከብ ግዴታም ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡
በእኛ ሀገር ተሞክሮ አሁንም ድረስ የሚታየን የማዕከላዊ መንግስት ጥንካሬ ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን የክልል መንግስታት ጥንካሬ ሊኖር እንደሚችል ማሰብ መቻል አለብን፡፡ ይሄ ጥንካሬ ሲመጣ የሚጠይቁት ጥያቄ ለፌደራል መንግስቱ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ጉዳይ፣ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ህዝብ ነው ሊወስንባቸው የሚገባው። የህዝብ ውይይት ተካሂዶ ሊረቀቅ የሚገባው እንጂ ዝም ብሎ ተፅፎ ወደ ህዝቡ ማውረድ ተገቢ አይደለም፡፡

================================

“ያለውን ግፊት እንዳለ ከተቀበልነው የወደፊታችን አስጊ ይሆናል”
አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ (የቢዝነስ መሪ)

እኔ በውይይት በጣም አምናለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የፌደራል ስርአትን ተቀብለን እየሄድን ነው ያለነው። ይሄን ተቀብለን ስንሄድ አንድ ላይ ሆነን አንድ ህገ መንግስት እንዳፀናን፣ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እንገነባለን ብለን እየሄድን እንደሆነ ሁሉ፣ ፌደራል ስርአታችን አንድ መቀመጫ ያስፈልገዋል፤ሰማይ ላይ ተቀምጦ መስራት አይችልም፡፡ አሁን ያለው ግፊት ወደ ኋላ ተመልሰን እንደ መሄድ ይመስላል። በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልልም እስከ 8ኛ ክፍል ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ በአማርኛ ብቻ ይማሩ የሚል ነው የምሰማው፡፡ ይሄ ሁሉ ለዘለቄታው ልንገነባው ለምናስበው፣አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግባችን አይወስደንም፡፡
 ፌደራል መንግስት ካቋቋምን፤ አንድ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ የሆነ፣ ማንም ሌላ ክልል የማያዝበት፣ ፌደራል መንግስቱ ብቻ የሚያዝበት መኖር አለበት፡፡ የዚህ ስርአት መቀመጫ ደግሞ በህገ መንግስት እንደተቀመጠው አዲስ አበባ ናት። ይሄ ማለት አንድ ክልል ብቻውን የሚቆጣጠራት አዲስ አበባ ሳትሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች፡፡ ይህቺ ሀገር ደግሞ አብረን ሆነን እንጂ ብቻ ለብቻ ሆነን አይደለም ወደፊት ልናራምዳት የምንችለው። ለዚህ ደግሞ በፌደራል ስርአት እንተዳደራለን ግን አንድ ኢትዮጵያ ሆነን እንቀጥላለን ብለን ነው የተስማማነው፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ አንድ የፌደራል መቀመጫ፣ የሁሉም የሆነች፣ አንዱ ለብቻው የማያዝባት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
አንድ አጋጣሚ እዚህ ላይ ልጥቀስ፡፡ ናይጄሪያ ከሌጎስ ወደ አቡጃ ዋና ስማቸውን ሲቀይሩ እዚያ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ ከበርካታ ክልሎች መሬት አዋጥተው ነው አንድ አቡጃ የምትባል ግዛት የፈጠሩት፡፡ የማንም ብሄር መኖርያ ይሁን ብቻ አንድ የተወሰነ ቦታ ተቆርሶ ነው ከተማው የተመሰረተው። የአዲስ አበባም እንዲሁ ነው መታሰብ ያለበት፡፡ የፌደራል መቀመጫ ነች ብለን መቀበል አለብን፡፡ አንዱ ከሌላው የበለጠ ወይም የተሻለ ኢትዮጵያዊ መሆን አይችልም፡፡
ልዩ ጥቅም ሲባል ምን ማለት ነው? መቼም አንደኛችን ከሌላችን የበለጥን ወይም የተሻልን ኢትዮጵያዊ አይደለንም፡፡ ለዚህች ሀገር እኩል ነን። ጥሩ ነገር ለመስጠትም ቢሆን አድሎአዊ እስከሆነ ድረስ ጥሩ አይደለም፡፡ ህገ መንግስታችን ተረቅቆ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ለመነጋገር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ የተካተቱበት 5 ልዑካን ሌጎስ መጥተው አነጋግረውኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ስለ ሀገራችን ሁኔታ ስንነጋገር ብዙ ነገሮች ነገሩኝ፡፡ አንዳንድ ብሄሮች የራሳችንን ፋንታ ከኢትዮጵያ ቆርጠን እንወስዳለን ብለው የተነሱ አሉ፤ ይሄ እንዳይሆን እየሞከርን ነው ብለው አስረዱኝ፡፡
በወቅቱ ክልሎችን ፈጠራችሁ፤ ድንበር ወሰናችሁ፤ ይሄን እንዴት አደረጋችሁ? ይሄ ሊደረግ የሚገባው በሽግግር መንግስት ሳይሆን በህዝበ ውሳኔ ነበር፤ ይሄን ማድረጋችሁ የሽግግር መንግስት ላይ ሆናችሁ ስር ነቀል ለውጥ ነው፤ ይሄ ትክክል አይደለም ብያቸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል የብሄር ፌደራሊዝም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። እንደው የግድ ከሆነ የሚያቀራርቡንና የሚያገናኙን እሴቶች እንዳይዘነጉ እባካችሁን ተጠንቀቁ፡፡ ብሄር ላይ ብቻ ካተኮርን የተዳፈነ እሳት ሆኖ ነገ ያቃጥለናል ብያቸው ነበር፡፡ አሁን አንዳንድ የማየው ነገር ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ልትቆራረጥ ነው በሚል ፍራቻ አንዳንድ ሊደረጉ የማይገባቸው ጉዳዮች ለጊዜው በሚል በመደረጋቸው የመጣ ነው። ይሄ የልዩ ጥቅም ጉዳይም አንዱ ይመስለኛል፡፡
እኔ አስብ የነበረው አብረን በቆየን ቁጥር ተነጋግረን፣ ትክክለኛው ይሄ ነው፤ ያኔ በነበረው ሁኔታ ያስፈልግ ነበር፤ አሁን ግን ያስፈልገናል ወይ ብለን የበሰለ ውይይት አድርገን የበለጠ መቀራረብ ይመጣል የሚል ነበር፡፡ አሁን ግን ሳየው ሁኔታው አስፈሪ ነው። አሁን ያለውን ግፊት እንዳለ እንቀበለው ብንል በእርግጥም የወደፊት ሁኔታችን አስፈሪ ይሆናል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
አዲስ አበባ የግድ ራሷን የቻለች የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ መሆን አለባት፡፡ የኢትዮጵያ የወደፊት ስዕልን ማየት ከተፈለገ፣ የአንድ ወገንን ጥቅም በዚህች ከተማ ላይ ማድረጉ አስፈላጊ አይመስለኝም። እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ያለፉትን 26 ዓመታት ለመቀራረብ ምንም አልሰራንም እንደ ማለት ነው፡፡ ፖለቲካችንም እንዲሁ ጥሬውን ቆይቷል እንደ ማለት ነው፡፡
የአዋጁ አፀዳደቅ አካሄዱ በራሱ ትክክል አይደለም። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የማፅደቅ ስልጣን የለውም፡፡ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው መምራት ያለበት፡፡ እኔ ሳስበው የፖለቲካ ክፍፍል በአመራሩ ላይ ያለ ያስመስላል፡፡ እንዲህ አይነቱ አለመግባባት ደግሞ ለተደራጀ ኃይል ስልጣን ማስወሰድን ነው የሚያስከትለው፡፡ በተማሪ ንቅናቄ ጊዜ የተማሪዎች መሪዎች ተሰብስበን፣ ጃንሆይ ይህቺን ሀገር ዲሞክራሲያዊ ቢያደርጉ ጥሩ ነበር፤ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ የተደራጀ ቡድን ላይ ነው የምትወድቀው ብለን ነበር፡፡ በወቅቱም ወታደሩ ሥልጣኑን ሊነጥቅ ይችላል ብለን ነበር፤ እንዳልነውም ስልጣኑን ወታደሩ ወሰደ፡፡  የዛሬው ወታደር ህዝባዊ ነውና ከእንዲህ አይነቱ ድርጊት ይቆጠብ ይሆናል። ነገር ግን ይሄ እንዳይሆን መመኘትና አምላክንም መማፀን ያስፈልጋል፡፡ በእውነቱ በአሁኑ ሰዓት በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡     

Read 7845 times