Saturday, 08 July 2017 13:46

“…የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በ2020 …55%...”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  የቤተሰብ ምጣኔ ወይንም እቅድ ማለት ትርጉሙ አንድ ቤተሰብ የሚፈልጉትን ያህል ልጅ በሚፈልጉበት ጊዜ መውለድ እንዲችል የሚያግዝ የህክምና አገልግሎት ማለት ነው። ይህን የተናገሩት ዶ/ር ደመቀ ደሰታ በአይፓስ ኢትዮጵያ የፕሮግራም ማናጀር ናቸው።
ባልና ሚስት የተለያዩ እቅዳቸውን እስኪያከናውኑ ድረስ መውለድ ካልፈለጉ የሚቆዩበት ወይንም የተወሰኑ ልጆችን ከወለዱ በሁዋላ በቃን ከዚህ በሁዋላ ልጅ መውለድ አንፈልግም ሲሉ እንዳይወልዱ ማገዝ ማለት ነው። ይህ እንግዲህ በቤተሰብ ደረጃ ከተጣመሩ ወይንም ከተጋቡ በሁዋላ ያለው ሲሆን ሌላው ደግሞ ሰዎች በግላቸውም የሚኖሩበት ሁኔታ ስላለ ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያ መጠቀም እንዲችሉ ይደረጋል። ለብቻ የሚኖሩ ሰዎች የሚጠቀሙበት መንገድ መጸነስ እንዳይችሉ ወደሚለው ትርጉዋሜም ይሄዳል። ይህንን መወሰን የሚጠቅመው ለምንድነው ወደሚለው ጥያቄ ስንሄድ አንድ ቤተሰብ መውለድ ያለበት ማብላት ማጠጣት ማልበስ ማስተማር የሚችለውን ልጅ ያህል መጥኖ እንዲወልድ ለማድረግ እና ሙሉ ዜጋ አድርጎ ማሳደግ እንዲችል ነው። ቤተሰቡ አቅሙ ትንሽ ሆኖ ሊያሳድገው ከሚችለው በላይ ልጅ ከወለደ በበቂ ሁኔታ መግቦ እና አልብሶ አስተምሮ ማሳደግ ስለሚሳነው የተወለደው ልጅ በትምህርቱ ውጤታማ እንዳይሆንና ወደተሸለ ሕይወት እንዳያመራ እንቅፋት ይሆንበታል። ያ ቤተሰብም ወደባሰ ድህነት ይወርዳል። ይህ በሀገር ደረጃም ሲታይ መንግስት ማሟላት የሚባቸው እንደትህርትቤት የጤና አገልግሎት መንገድ የመሳሰሉት ሁሉ የሚጠበቅበት ከሆነ መጠነኛ ገቢ ያለው እና ብዙ ሰው የሚያስተናግድ መንግስት ከሆነ አገልግሎቱንም ማዳረስ ስለሚሳነው እራሱ መንግስትም የድህነቱ ተቋዳሽ ይሆናል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር July 2012 ነበር በለንደን ስለቤተሰብ እቅድ ሀገራት በአዲስ መልክ የሚያስፈጽሙትን በተመለከተ ቃል የሚገቡበት አለም አቀፍ እቅድ የተነደፈው:: በዚህ ረገድም ሀገራት ውጤታማ በሆነ መንገድ ብዙም አቅምን በማይፈታተን መንገድ እርምጃ ለመውሰድ የየራሳቸውን ትልም ተልመዋል። ኢትዮጵያም በ2014 አጋማሽ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር በሚገኘው የእናቶችና የሕጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት አማካኝነት ከ2015-2020 ድረስ የሚፈለገውን ስኬት ለማስመዝገብ እየሰራች ትገኛለች። በፈረንጆቹ አቆጣጠር May 2015 የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቴክኒክ ድጋፍ ከሚያደርገው ቡድን ጋር በመሆን በተቀናጀ መልክ ሁኔታው እንዲታይ አድርጎአል።
ስለዚህ የጤናና የልማት ተሳታፊዎች ተባባሪዎች እና የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ባለሙያዎች እንዲሁም አማካሪዎች ጁን 2016 ከብሔራዊው የስነተዋልዶ ጤና እቅድ ጋር በሚጣጣም መልኩ ስራው እንዲሰራ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገዋል። የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርገው አካል ከ30 በላይ የሚሆኑ በስራው የሚሳተፉ አካላትን በማጋገርና ከ20 በላይ የሚሆኑ አማካሪዎችን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች እና አብረዋቸው ከሚሰሩ በ9 የክልል መስተዳድሮች እና ከአዲስአበባና ድሬደዋ ጋር እንዲገናኙ በማድረግ በአንዳንድ አስፈላጊ ነጥቦች ላይ አትኩረዋል።
የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በግል ደረጃ ምን ያህል አስፈላጊ ነው ስንል ላነሳነው ጥያቄ ዶ/ር ደመቀ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል። “…በግል ደረጃ ድሮ እንደሚታወቀው በሀይማኖትም ይሁን በባህል ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከጋብቻ በፊት ወሲብ እንዲፈጽሙ አይደገፍም ነበር። አሁን ግን በፈቀዱ ጊዜ ወሲብ መፈጸም እንደነውር ከማይቆጠርበት ዘመን ላይ ደርሰናል።ነገር ግን ማንኛውም ሰው እራሱን ለመቻል እንደድሮው ከቤተሰብ የሚወረስ ወይንም የሚገኝ ሀብት ብዙም ባለመኖሩ ሁሉም ሰርቶ ጥሮ ግሮ እንዲያገኝ ከሚገደድበት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ለዚህም አስቀድሞ መማር አንድ መመዘኛ ሲሆን ነገር ግን አንዲት ሴት ልጅ ለምሳሌ ወደሁለተኛ ደረጃ ስትደርስ ወይንም ዩኒቨርሲቲ ስትደርስ እርግዝና ቢከሰትባት ትምህርቱዋንም ታቋርጣለች…ስራ ሰሰርቶ ለማደርም የተሸለ እውቀት ሰለሌላት ከዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንድትሆን ትገደዳለች።በዚህም ምክንያት የወደፊት ሕይወትዋ ይጨናገፋል። ይህች ልጅ በቤተሰብ ተቀባይነትን ማጣት ልጅዋን ለማሳደግ አቅም ማጥት የፍቅር ጉዋደኛዋ የነበረ ሰው ትኩረትን ማጣት በመሳሰሉት ምክንያቶች ሕይወትዋን እንድትጠላ ትገደዳለች። አንዳንዶች ይህንን በመፍራት አስቀድሞውኑ ጽንሱን ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ወደማቋረጥ ስለሚሄዱ ሕይወትን እስከማጣት የሚደርሱበት ሁኔታ ይከሰታል። ወንዶቹ ግን ምንም እንኩዋን የጉዳዩ ባለቤቶች ቢሆኑም አርግዘው አይታዩም ትምህርታቸውንም አያቋርጡም በቤተሰብ ዘንድ ውግዘት አይደርስባቸውም ። ነገር ግን ድርጊቱን የፈጸሙ በመሆናቸው ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባቸዋል። ስለዚህ እንደዚህ ካለው ችግር ከመውደቅ በፊት ፍቅረኛሞች ተመካክረው ወሲብ ከመፈጸማቸው በፊት ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችል አገልግሎት ማግኘት ይገባቸዋል። ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት 2015-2020 የአምስት አመት እቅድ የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት ለማሻሻል ራእይ አለው። የዚህም እቅድ አንዱ ማስፈጸሚያ ተደርጎ የተወሰደው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በተገቢው ለህብረተሰቡ መስጠት ነው። በዚህም የተነሳ ኢትጵያ በውጭው አቆጣጠር እስከ 2020 ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቱን መጠን ወደ 55% ማሳደግ ትሻለች። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በትክክል መገኘት መቻልø ወደትግበራው ሲገባ አስፈላጊው የሰው ኃይል እንዲኖር፣ የጤና አጠባበቅ መመሪያ መኖር፣ ፖሊሲ፣ ምጣኔ ኃብት እና ምቹ ሁኔታን ስለመፍጠር አስፈላጊውን መመሪያ ማግኘት በህብረተሰቡ ዘንድ ማህበራዊና ባህሪያዊ ለውጥን ለማምጣት የሚያስችል ግንኙነት መፍጠር፣ ለወጣቶች ግልጽ እና ቅርብ የሆነ ቀለል ባለ መንገድ የስነተዋልዶ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ድጋፍ ማድረግ …ወዘተ የመሳሰሉትን በሚመለከት ቅድመ ዝግጅት ተደርጎአል።
ፍላጎትን መፍጠር፡-
ሰዎች የቤተሰብ እቅድ ዘዴን በተለይም ለረጅም ጊዜ ዪያገለግለውን ፈልገው እንዲጠቀሙ በማድረግ አገልግሎቱንም በቀላሉ ሊደረስበት በሚችል መልኩ ማመቻቸት እንዲሁም ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
አቅርቦትና አገልግሎት፡-
በሙያው የተሰማሩ ጥራት ያለው ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያ ማቅረብ እንዲችሉ፣ እንዲሁም ሁሉም ተጠቃሚዎች መድሀኒቶቹን የማግኘት እድል እንዲኖራቸው በተለይም ወጣቱ እና አርብቶአደሮች ተገቢውን ደረጃ በጠበቀ መንገድ እንዲሁም በሪፈራል እና ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች አማካኝነት እንዲሁም ለአዋቂዎችም ሆነ ለወጣቶች ተስማሚ የሆነ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን እውን ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በ1960 ዓ/ም 22.2 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2015 ወደ 90 ሚሊዮን አድጎአል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥርም በየአመቱ 2.6% ሲሆን በዚህ ከቀጠለ በ2020 የህዝቡ ቁጥር ወደ 112 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። የመዋለድ ቁጥር ግን በ200 ዓ/ም 5.9 የነበረ ሲሆን በ2014 ግን 4.1 ተመዝግቦአል። ይህም የመዋለድ ደረጃው ቀስ በቀስ እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያል። ምናልባትም በየቤተሰቡ የልጆች ቁጥር መጨመር ከተለመደው የጋብቻ አይነት ማለትም በብዙው ቦታ ሴቶቹ በወጣትነታቸው ስለሚያገቡ ብዙ ልጅ ይወልዳሉ የሚል እምነት አለ። በትዳር ከመጣመር ውጪም በርካታ ልጃገረዶች ትምህርታቸውን እያቋረጡ ልጅ የሚወልዱ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎች ደግሞ ካለው የመከላከያ አቅርቦት ችግር ያልታቀደ እርግዝና እንደሚገጥማቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዶ/ር ደመቀ እንደሚገልጹት የጤና ኤክስቴንሽን ስራ ዋና አላማ ከማከም ይልቅ በመከላከል በሽታዎችን ማስቀረት እንችላለን የሚል ስለሆነ በህብረተሰብ ውስጥ ገብተው ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። ያ ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ ብዙ ለውጥ ወይንም እድገት ታይቶአል። በእርግጥ ይህ ተፈላጊው ደረጃ ላይ ደርሶአል የሚያሰኝ አይደለም። በ2016 ባገቡ ሴቶች ላይ የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው የቤተሰብ እቅድን መጠቀም እንፈልጋለን ብለው አገልግሎቱን ያገኙት 36 ከመቶ ናቸው። ይህ ቀድሞ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ጥሩ ቢሆንም አሁንም ግን ዝቅተኛ ነው። በሌላም በኩል በዚሁ ጥናት የተገኘው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን መጠቀም ፈልገው ማግኘት ያልቻሉት አሁንም ቁጥራቸው ወደ 23 ከመቶ ስለሆነ ብዙ ነው። ወደ 9 ከመቶ የሚሆኑት ከዚህ በሁዋላ ልጅ ማርገዝ የማይፈልጉ ወይንም ደግሞ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ መጠቀም የሚፈልጉ ሲሆኑ አገልግሎቱ ግን አልደረሰላቸ ውም።በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤው ግን በጥሩ ደረጃ ነው ማለት ይቻላል።

Read 1181 times