Print this page
Wednesday, 12 July 2017 14:15

ጥቁር እንልበስ - ለምርቃታችን!!

Written by 
Rate this item
(10 votes)

የመመረቂያ ቀናችን እየቀረበ ነው ….አንዱ ቀን አልፎ ሌላው በተተካ ቁጥር ጥቁር የምንለብስበት ቀን ወደ እኛ እየቀረበ ነው፡፡ ኃላፊነት …. ቤተሰብ …. ትዳር …. ሥራ…. ወዘተ የሚባሉ ነገሮች እኛነታችንን እየጠበቁን ይገኛሉ፡፡
ተኝተን በተነሳን ቁጥር መቶ ሃያ ቀን ቀረን …. መቶ ቀን ቀረን …. ስልሳ ቀን ቀረን …. እያልን ነው፡፡ ጊዜ እየተፍገመገመ ወደ እኛ እየቀረበ ነው …. ሰቀቀን ሊገድለን ነው …. ሙሾ ሊከበን ነው …. በጥቁር ልብስ ውስጥ ልንሞሸር ነው…. መመረቃችን ለኛ ሞት ነው…. ለዛም ነው የምናለቅሰው፤ ለዛም ነው ሆዳችንን ባር ባር የሚለው፤ ለዛም ነው ጥቁር የምንለብሰው….
እንዴት ባር ባር አይለንም ….እንዴትስ ውስጣችን አይጠቁር …. እንዴትስ የእንባዎች ጅረት በጉንጫችን አይውረድ…. አዎን ያቺ የመመረቂያ ቀናችን የምትቀማን በወጣትነት ዘመናችን ያፈራናቸውን…. ጓደኞቻችንን  ነው፡፡ የዋሆቹን …. ፖለቲከኞቹን …. ቸካዮቹን …. ዘረኞቹን ….ነጭናጫዎቹን …. አፍቃሪዎቹን …. ስፖርት ወዳጆቹን ….ዘናጮቹን…….ወዘተ ነው የምትቀማን፡፡ ያቺ ቀን በደግም በክፉም ከምናውቃቸው መምህራኖችና የአስተዳደር አካላት ጋር የምትለየን ቀን ነች፡፡
ጥቁር ለመልበሳችን ብዙ አመክንዮ አለን። አዎን ከፍቶን ተምረናል …. ለቤተሰቦቻችን ብቻ ስንል ውስጣችን የማይቀበለውን የሽንፈት ታሪክ እያስተናገድንም ቢሆን ተምረናል …. ዕሳቤያችን ሁሉ ተዛብቷል …. የት ይደርሳል የተባለ ዛፍ ሆኖብናል ነገሩ …. ዓለሙ… መንደሩ…. ሁሉ ነገር ተምታቶብን ተምረናል …. ሀዘን ክንዳችንን አዝሎታል …. ሞትን ወደ ቤታችን ግባ ብለን ጋብዘነዋል …. የሚረዱንን ደጋፊዎቻችንን….. ወላጆቻችንን ሳንደርስላቸው ….  ቀና ሳናደርጋቸው በጊዜ ርዝማኔ ተነጥቀናል …. ትምህርት ዋጋ አስከፍሎናል …. የመኖር እንቆቅልሽ አልገባ ብሎናል፤ ስንትና ስንት ቀናትን ዶርማችን ውስጥ ተሸሸገን አልቅሰናል …. የምንገባበት ቢጠፋን ጊዜ ተጨንቀናል ….የተጫሩት ወንድሞቻችን ዩኒቨርስቲያችን በሚገኝበት ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሆቴሎች በራፍ ላይ ሲባዝኑ ስናይ ውስጣችን ደምቷል …. ፈተና ቢከብደን ጊዜ በረኪና ጠጥተናል …. ኽረ እኛ ያላሳለፍነው ከቶ ምን አለ?
ታዲያ  ያለፈው ማንነታችንን የሚገልፀው ነጭ ሳይሆን ጥቁር ነው …. አዎን ጥቁር ነው መልበስ ያለብን …. በጥቁር ነው መሸፈን ያለብን …. ጥቁርማ የውስጣችን ገላጭ ነው ….ቆመን መሄዳችን …. መሳቅ መጫወታችን ….ተኝተን መነሳታችን …. እኛነታችንን አይገልጹትም …. እኛነታችንን የሚገልጸው ያ ጥቁር ልብስ ነው፡፡
ይገርማል ዩኒቨርስቲዉ ውስጥ በቆየንባቸው ዓመታት የተፈራረቁት ብርሃንና ጨለማ ስለ እኛ ምን ይናገራሉ…. ስለ እኛ ምን ያወራሉ …. ሺ ጊዜ ወድቀናል …. ሺ ጊዜ ተነስተናል …. መውደቃችን …. መሸነፋችን …. ከተራራ በላይ ገዝፎ ተነግሯል …. የተስፋ ታንኳችን በወጀብ ተመታ …. በማዕበል ተገፍታ …. ተንቃቅታ …. ተንቃቅታ….በግማሽ ጎኗ ሰምጣለች …. ሕይወታችን እዛው ከታንኳ ጋር  አብሮ ሰምጧል…. ክረምት ወደ ቤታችን ለመሄድ አስበን የትራንስፖርት ቸግሮን፣ ከቤተሰቦቻችን ጋር ሳንተያይ አንዱ በጋ አልፎ በአንዱ ላይ ተተክቶ አምስት አመት ተቆጥሯል ….የልጅነታችን ወዝ ተንጠፍጥፎ ደርቆብናል …. ገላችን  ከስሟል … ውበታችን ረግፏል …. የምንሆነውን ሳይሆን የማንሆነውን  ሆነናል …. ለተደራቢው ጥቁር ልብስ ቀሚሳችንን ጥለን …. ሱሪ ታጥቀናል …. ሱሪ መታጠቃችንን የተመለከተ ወንድ ሥጋ ቸርቻሪ መስለነው ስጋችንን እንድንሸጥለት ጠይቆናል …. የእኛ ማንነት ግን መሸጥ መለወጥ አልነበረም …. ማንነታችን ግን መባከን አልነበረም…. ሱሪውን አውልቀን ቀሚስ ብናጠልቅ ጊዜ ያው የሥጋ ደንበኛ ሥጋ እንድንሸጥለት ብሮችን ዘርዝሯል …. የኛ ዓላማ ግን ሥጋ መሸጥ አልነበረም…. ቀዳዳውን መድፈን  እንጂ …. የሃንድ አውት ስንባል እንዳንሳቀቅ …. ለዝግጅት ስንባል እንዳናፍር ነበር …. እውነቴን ነው የምለው የምንሆነውን ሳይሆን የማንሆነውን ነው የሆነው …. ታዲያ ለአንዳንዶቻችን ተገላቢጦሽ ለሆነብን ሕይወት---- ከጥቁር ወዲያ የሚገልፀው ምን አለ?
የሞዴስ መግዣ  ቸግሮን …. ከዶርም መውጣት አሳፍሮን፣ ተሸሽገን ቀናቶችን አሳልፈናል …. ሃንድ አውት ኮፒ የምናደርግበት ሳንቲም አጥተን ተውሰን አንብበናል …. አሊያም ምንም ሳናነብ ወደ ፈተና ገብተናል …. አዳሜ በምላሱ ተማምኖ  ግሬድ  ሲያስጨምር፣ የእኛ ምላስ ደርቆ ውሃ ሳያነሳ ሲቀር ፅልመት ወርሶናል …. አልጋ ላይ ሲወጡ ኤ፣ ከአልጋ  ላይ ሲወርዱ ኤፍ ከሚሉት መምህራን ጋር አንዳንዶች አንሶላ ሲጋፈፉ …. እኛ ግን ለሚያልፍ ቀን ብለን …. ለክብራችን ብለን …. የአልጋ ላዩን ጨዋታ…. የአልጋ ላዩን  ዕቃቃ …. አንቀበልም ብንል ጊዜ የሚተማመኑበትን በትር ሰንዝረውብናል …. ለዜሮ ነጥብ አምስት A ማግኘት እያለብን ሳናገኝ …. B ማግኘት እያለብን ሳናገኝ፣ ሴሚስተሩን በሙሉ ጨጓራችን እየበገነም ቢሆን ሁሉን አልፈነዋል …. ማለፊያ ነጥብ ሞላልኝ አልሞላልኝ እያልን ለተሳቀቅንባቸው …. ለእነዛ ሴሚስተሮች መልበስ  የሚገባን ጥቁር ልብስ ነው …. አንድ ከአርባ (1/40) …. ሁለት ከአርባ (2/40) ….ሦስት ከአርባ (3/40)  ለሰጡን መምሕራን …. በቦክስ ለመቱን መምህራን …. ዓለም ያልደረሰበት ሚስጢር በእጃቸው ያለ ይመስል ከመጠን በላይ ለተኮፈሱብን ለእነዛ መምህራን --- መልበስ ያለብን ልብስ ቢኖር ጥቁር ነው….
የተናገርነውን ንግግር ትርጉሙን ለጠመዘዙብን ኃላፊዎች…. ለማየት ከምንጓጓለት ቦታ ላስቀሩን …. የአስተዳደር አካላት….የተሻለ አስተሳሰብ ሲቀርብ ለሚደነግጡት…. ቆይ እንወያይ…..ወዘተ እያሉ ጊዜ ለገደሉብን ለእነርሱ መልበስ የሚገባን ጥቁር ልብስ ነው …. አዎን ጥቁር የምንለብስባት ያቺ የምርቃት ቀናችን በሕይወታችን ብዙ ነገር መከናወኑን የምትነግረን ነች ….. ነጭ የለበስንበት የቀለም ቀናችንን (colour day) የምትቀማን ናት…..
አዎን በቀለም ቀናችን …. ነጭ ለብሰን በደመቅንበት ቀን …. ፊታችን በሕብረ ቀለም አሸብርቋል …. ቲ-ሸርታችን በአባባል ደምቆ …. ወንድምነታችን እህትነታችን አይሎ የወጣንበትን የቀለም ቀን የምትቀማን ቀን ነች…. አዎን በዛች ቀን ያሻነውን ፅፈናል፤በፈለግነው ሙዚቃ ዘፍነናል …. ይሄ አንገት ነው …. ምን ታፈጣለህ…. ምን ታፈጫለሽ ….ታስጨርሰኛለህ…. እንወድሀለን …. እንወድሻለን…. ሴት ልጅ ደሀ የምትወደው ፊልም ላይ ብቻ ነው …. ብልጭ እና ቁልጭ…. U R Z Best …. እንዳትረሱኝ …. ሲጋራውን አፕላይ…. የተባባልንበት የቀለም ቀናችንን የምትቀማን ቀን ነችና እባካችሁ በምርቃት ቀናችን ጥቁር እንልበስ …. ነጭ  እንደሆነ ብርሀን ነው፡፡ ነጭማ ከዋሻው ጫፍ ለመድረሳችን ምልክት ይሆነን ዘንድ የተሰጠንን ማህተም ነው፡፡ ነጭማ ትንሣኤ ነው፤ የትዝታ ድንጋዮችን የሚፈነቅል የትዝታ መቃብሮችን በደስታ የሚያሸንፍ፤ ወንድምነታችንን የሚያድስ፣ እህትነትን የሚዘክር፤ መዋደዳችንን የሚሰብክ ነው፡፡ ነጭማ ንፁህ ባህሪ ነው፡፡ ነጭማ እንበለ ሙስና ነው። እንበለ ድካም ነው፡፡ እንበለ ህማም ነው፡፡ እንበለ ፃማ  ነጭማ  አሐዱ ውእቱ ነው፤ በቃ ማፍቀር ብቻ፤ መደሰት ብቻ፤ ተዋዶ ተሳስቦ መኖር ብቻ ነው። አሸብሽቦ መዝሙር  ነው፡፡ ለነገ ትውስታ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ አንገት ለአንገት ተቃቅፎ  ፎቶ  መነሳት ነው፡፡ ቲ-ሸርት በዲፓርትመንት ማሰፋት ነው፡፡
ነጭማ ሕመም የለውም፤ አይጎረብጥም አይሻክርም፤ እንቅፋት የሌለበት የሜዳ ላይ ጉዞ ነው። ጥቁር  ግን ብዙሃን ባህሪ  ነው፡፡ ጥቁር መለየት ነው፤ ጥቁር መሰደድ ነው፤ ጥቁር እንደ ቀራንዮ ጉዞ በመውደቅና በመነሳት የታጀበ ነው፤ ህመማችን የተፃፈበት የደም ልብሳችን  ቢኖር ጥቁር ልብስ ነውና እባካችሁን ጥቁር እንልበስ፡፡
አፍሮ  ጸጉር ሆነን ገብተን ራስ በራ ሆነን የምንመረቀው እኛ ጥቁር እንልበስ፡፡ ሃይማኖተኛ ሆነን ገብተን ጀነግ /ጀዝብ ነፃነት ግንባር/ ሆነን ለወጣን እኛ መልበስ የሚገባን ልብስ ጥቁር ነው። ቁጭት ሆድ አስብሶን እግራችን ፈርከክ አድርገን የአረቄ ብትሌ እያነሳን ለለጋንባቸው ቀናቶች፣ ጠጅ ለጠጣንበቸው ለእነዛ ቀናቶች መልበስ ያለብን ጥቁር ልብስ ነው፡፡
በምርቃት ቀን የምንለብስው ልብስ የሚናገርልን ነገር ቢኖር ያለፈ ታሪካችንን ነው፡፡
አንድ ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን /Readmission student/  የተማርንበትን የጊዜ ወሰን የሚገልፅ ነው፡፡ ያ ልብስ የሚነግረን በተጫርን ጊዜ፤ አንድ ሴሚስተር ወደ ኋላ በተባረርን ጊዜ ፤ወደ ቤት መሄድ አፍረን ጎንበስ ቀና እያልን ያስተናገድንባቸው ካፌዎችን ነው። ወደ ቤት ላለመመለስ ስንል ብቻ አስተናጋጅ ሆነን የተሸሸግንባቸውን  ሆቴሎች የሚዘክር ነው፡፡ ጥቁርማ ከእኝ እኩል በምርቃት ቀን በሱፍ፣ በከረባት፣ በፎቶ ሊደምቁ ያልችሉትን፣ ሞት የቀደማቸውን ተፈጥሮ ክንዷን ያበረታችባቸውን፣ አፈር ያንተረሰችባቸውን፣ በሞት የተለዩን ወንድሞቻችን እህቶቻችን የሚዘክርልን ልብስ ነው። በዩኒቨርስቲ ቆይታችን አብረን ታድመን፤ ክላስ ላይ ተምረን፣ ካፌ ተመግበን፣ አብረን አጥንተን፣ ያንን ሁሉ  ዓመት የማዕበሉ ጊዜ አሳልፈን፤ ነገር ግን ዛሬ ላይ ጥቁሩን ልብስ ለመልበስ ላልታደሉት ወንድሞቻችን  እኛ መልበስ የሚገባን የእነርሱን ጥቁር ልብስ ነው፡፡ በጥቁር የሚጻፍ እውነታ ምንግዜም ቢሆን አይሻርም፤ እኛም  እነሱም ጥቁር እንልበስ እስኪ፤ ማን ነው በየዓመቱ  የሞትን መርዶ ሳይሰማ እዚህ የደረሰ? እስኪ የቱ ነው በቆየንባቸው አምስት ዓመታት ለሞቱት ወገኖቻችን አንፊ ላይ ቁጭ ብሎ በሕሊና ጸሎት ያልተከዘ፣ ሻማ ያላበራ፣ ጧፍ ያለኮስ፣ እስኪ ማን ነው?
ያቺ የምርቃት ቀን እጅግ አብዝተን የምወዳቸውን ፍቅረኞቻችን የምትነጥቀን ቀን ነች። ስትስቅ  የምወደውን እርጋታዋን፣  አስተሳሰቧ የሚማርኩኝ ያቺን የከንፈር ወዳጄን የምትቀማኝ ቀን ነች፡፡ ጥቁር ከምለብስበት የምርቃት ቀን በኋላ የከንፈር ወዳጄ ምክር የለም፤ እሷ ከአድማሳት ወዲያ እኔ ከአድማሳት ወዲህ መለያየት  ዕጣ ፈንታ ውስጥ እንወድቃለን፤ ከዛች ቀን በኋላ ትዝታን ብቻ  በጥቁር ልብስ ውስጥ እየወዘወዙ እንደ ክራር እየጠዘጠዙ፤ እንደ በገና እየደረደሩ፤ በምልክት ጥይት ውስጥ ትዝታን ከተው በሰመመን ሩጫ መጋለብ ብቻ። ሌላ  አንዳች የሚፈጥሩት ነገር ላይኖር ብቻ ዝም ብለው ሊሸረክቱ  ብቻ፣ ዝም ብለው ሊያለቅሱ ፣ ብቻ  ዝም  ብለው ዝም ለሚሉባት  ለዛች መናጢ ቀን መልበስ ያለብን ልብስ ቢኖር  ጥቁር ነው፡፡ እናም  ጥቁር እንልበስ፡፡
አንተስ ብትሆን፤ አንቺስ ብትሆኚ ሰላሳለፍከው፣ ስላሳለፍሽው  የፍቅር ዘመናት መልበስ የሚገባሕ/ሽ ጥቁር ልብስ ነው፡፡ እሷን ለመናገር  ላፈርክባቸው ቀናት፣ እሷን ስታስባት ደረት ለደለቀው ልብህ ለመታው ለዛች ቀን ምን ይሆን የምትለብሰው? ፍቅረኛህን እንደምትለያት የተማርክበት ጊቢ ሲነግርህ  የሕይወት  ዑደት መለያያት መሆኑን ስታውቅ ምን ትለብስ? መለያየት በአንተ ዘንድ ዋጋ ከሌለው ነጭ ልበስ፣ መለያየት ለአንተ ለአንቺ ዋጋው ብላሽ ከሆነ፣ ትርጉም ከሌለው፣ ውሃ የሚያነሳ  ከሆነ ነጭ ልበስ፡፡  መለያየት ግን ትርጉም ካለው፣ መነፋፈቅ ተገናኝቶ መበታተን፣ ባህሪን ተላምዶ ማን ምን እንደሚያስደስተው፣ ምንስ  እንደሚያስቀይመው አውቆ፣ ዳግም ላይገናኙ መበታተንን ከተረዱ፣ አንተም አንቺም፣ እኛ ሁላችን የመለየትን መጥፎነት ከተረዳን እባካችሁ ጥቁር እንልበስ፡፡ የፍቅረኛሞችን መንገድ ልንረሳው ነው…. ቁጭ ብለን እያወጋንባቸው በዛፍ የተከበቡ ጨለማ የዋጣቸው እነዛ  የፍቅረኛሞች መቀመጫን ልንረሳቸው ነው፡፡ እስኪ እና ሁላችን በምርቃት ቀናችን ጥቁር አንልበስ፡፡
ያቺ ቀን የማትቀማን ሁልጊዜ ዕሮብ ዕሮብ እየተሰባሰብን የስነጽሁፍ አምሮታችንን የምናስታግስባትን ምሽትን ነው፡፡ በተለይ ለእኔ የምታስቀርብኝ ነገር  ቢኖር ብዙ ነው፡፡  ፍቅር ባጣ ዪኒቨርስቲ ውስጥ ስነጽሑፍ በፍቅር አንድ ያደረገችን፣ በግጥም በወግ በድራማ  የተሳሰርን አንድ የሆነ እኛ ---- ፍቅር እርሷ ፈትላ እርሷ ባዝታ፣ የደደረውን ማንነታችን  ነቅሳ፣  ጥፍጥሬውን ጥላ የገመደችን የሻሸመኔ መደወሪያ በሚመስለው የፍቅር መርከቧ ከአንዱ ጥግ ወደ አንዱ በሃሳቦች፣ በጽሑፎቻችን አስጉዛ ለብርድ ብላ ያዘጋጀችን ኩታ ነን፡፡ እናም ከዚህ ውህደት ውስጥ ተለይቶ መኖር ይከብዳል፡፡ እናም እናንተን የስነጽሑፍ ወዳጆቼን ሳስብ ውስጤ ጥቁር ልበስ ልበስ ይለኛል፡፡ በጥቁር ተሞሸር ይለኛል፡፡ ቢጫ አለብስ ነገር ጨነቀኝ፤ ቢጫ ፍካት ነው፤ እንደፈካን  ደግሞ መች እንኖርና! አረንጓዴ አለብስ  ነገር  ልምላሜ ነው፡፡ ጓደኝነታችን መለያየት ሲገባን፣ ልምላሜው ይከስማል፡፡ ነጭ እንዳልለብስ ነጭ ደስታ ነው፡፡ ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ጥቁር መልበስ ነው፡፡ እናም በዛች የምርቃት ቀን ጥቁር እለብሳለሁ፤ እናንተስ ምን ትለብሱ ይሆን? እባካችሁ ጥቁር እንልበስ፡፡
ከዓመታት በኋላ ስንገናኝ በተስፋ እንታደሳለን፤ ብርሃን የሆነውን ነጭ ልብስ እንለብሳለን፡፡ ያኔ ተገናኝተን “አንተ አለህ  አንቺ አለሽ ወይጉድ” አስክንባባል ድረስ ጥቁር እንልበስ፡፡ አዎን እስከዛ ድረስ  በጠቆረ  ልብስ፣  የጠቆረ ማንነታችንን እንግለፀው። ጊዜ አገናኝቶን ለሚለየን፣ ለለያየንም ለእኛ ለዚህ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎች ጥቁር እንልበስ፡፡ ጥቁር ይሁን ቃልኪዳናችን፤ ጥቁር ይሁን ውላችን፡፡ ጥቁር ለመገናኘታችን ዋስትና ይሁን፡፡ ጥቁር፤ ስንገናኝ ነጭ ለመልበሳችን ዋስትና ይሁነን፡፡
እውነት ነው፤ ጊዜ እየተፍገመገመ ወደ እኛ እየቀረበ ነው፤ ሰቀቀን ሊገለን ነው፡፡  ሙሾ  ሊከበን  ነው፤ አበባ  ታቅፈን ልናነባ ነው፤ በጥቁር ልብስ  ልንሞሸር ነው፤ መመረቃችን ለእኛ ሞት ነው፡፡ ለዛም ነው የምናለቅሰው፤ ለዛም ነው ሆዳችንን ባር ባር የሚለው፤ ለዛም ነው ጥቁር የምንለብሰው። ለሁሉም የቸርነት አምላክ እርሱ አይለያየን፤ የአንድነት አምላክ ፍቅርን ይስጠን፡፡ ኪሎ ሜትሮችን ሳይገድቡን፣ አድማሳት ጋራዎች ሳይከልሉን እንደንጠያየቅ ያድርገን፡፡ መለያየት  ያለበሰንን ጥቁር ልብስ፤ ትዝታውን የምንችልበት ትከሻ ይስጠን፡፡
የፍቅር አምላክ የጨከኑባችሁን  የፍቅረኞቻችሁን ልብ አራርቶ፣ በአንድነት ጥላ ውስጥ ያስጠልላችሁ። አንድ ሆናችሁ መለያየት ላይ ፎክሩበት፤ አቦ ይመቻችሁ፡፡ የእናታችሁ ምርቃት አይለያችሁ፡፡  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
እኛም ለዘላለም እንኑር!!                               

Read 6345 times
Administrator

Latest from Administrator