Sunday, 16 July 2017 00:00

ወጋገን ባንክ አርማውን ቀየረ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ወጋገን ባንክ ባለፉት 20 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ዓርማ በአዲስ ቀየረ፡፡ ዓርማው የባንኩን ዋነኛ እሴቶችና በ2025 በአፍሪካ ከሚገኙ 10 ስመ ጥርና ተፎካካሪ ባንኮች አንዱ ለመሆን የነደፈውን ራዕይ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ባንኩ፤ ከትናንት በስቲያ በሸራተን ሆቴል አዲሱን ዓርማ ባስተዋወቀበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ዘውዱ፣ አዲሱ የንግድ ምልክትና ዓርማ፣ ያለፉትን ዓመታት ስኬት የወደፊቱን ብሩህ ተስፋና የደረስንበትን ጥሩ መሠረት እንዲያንፀባርቅ እንዲሁም የመጪውን ትውልድ ስሜትና ዝንባሌ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር የተቀረጸ ነው ብለዋል፡፡
አዲሱ አርማ ወጋገን ባንክ በ20 ዓመታት ቆይታው ለደንበኞቹ ከሰጠው አገልግሎት ያበረከታቸውን መልካም እሴቶችና ልምዶን ጠብቆ ለማቆየት፣ የባንኩን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፍላጎት ለማርካት የተዘጋጀ ብራንድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዓርማው ላለፉት 12 ወራት ሲዘጋጅ ቆይቶ መቆየቱንና ከቀረቡት አማራጮች ተመርጦ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አርአያ ገ/እግዚአብሔር አዲሱ የባንኩ መገለጫ ዓርማ ለደንበኞችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የባንኩን ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዕሴቶች፣ ያለፈውን ስኬትና የወደፊት ግቡን በመወከል ከሌሎች ተወዳዳሪ ባንኮች በቀላሉ ለይተው እንዲያውቁትና እንዲያሳተዋውቁት ያደርጋል፤ የባንኩ ገጽታ በወጥነትና በትኩረት ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል፡፡  ውስብስብነት የሌለው፤ ሰዎች ያለምንም ችግር በቀላሉ እንዲለዩት ተደርጎ የተሰራው አዲሱ ዓርማ፣ ወጋገን ከሚለው የአማርኛ አጠራር ‹‹ወ›› እና ከእንግሊዝኛው ‹‹W›› ፊደላት የመጀመሪያዎቹን ቃላት በመውሰድ የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወጋገን ባንክ አርማ ዋነኛ ቀለም ብርቱካናማ ሲሆን ጎህ ሲቀድ በሰማይ አድማስ ላይ ከሚታየው የጠዋት ፀሐይ ደማቅ ብርሃን የተቀዳ፤ በተስፋና በመልካም ምኞት የተሞላ ብሩህ ጊዜን እንደሚያመለክት ተገልጿል፡፡

Read 3070 times