Print this page
Sunday, 16 July 2017 00:00

አሐዱ ኤፍኤም 94.3 ሬዲዮ ጣቢያ ስርጭቱን ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አሐዱ ኤፍኤም 94.3 ሬዲዮ ጣቢያ የሙከራ ስርጭቱን የጀመረ ሲሆን ከሐምሌ 15 ቀን 2009 በኋላ መደበኛ ፕሮግራሞቹን እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ጣቢያው በይፋ ስርጭት መጀመሩን አስመልክቶ የሬዲዮ ጣቢያው የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን  ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫና የጉብኝት ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፤ከስምንት ዓመታት አድካሚና እልህ አስጨራሽ ሥራ በኋላ ጣቢያው የብሮድካስቲንግ ፈቃድ አግኝቶ ተቋቁሟል፡፡  
የኤዲስቴይለር ትሬዲንግ እህት ኩባንያ በሆነው ኤዲስቴይለር ሚዲያ ሴንተር ውስጥ የተቋቋመው ይኸው የሬዲዮ ጣቢያ፤የኢትዮጵያውያን ድምፅ በመሆን ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለማስታወስና ለማስተዋወቅ እንዲሁም ማህበራዊና ባህላዊ ህይወትን ለማጠናከር እንደሚሰራም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡  
የኤዲስቴይለር ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እሸቱ በላይ በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት፤ ጣቢያው እንደ ስሙ በመረጃ፣ በቴክኖሎጂና በአቀራረቡ ቀዳሚ ሆኖ አድማጮቹን ቀዳሚ ለማድረግ ይተጋል፡፡ በአዳዲስ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች በማደራጀትም የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይሰራል፡፡ ጣቢያው በሚዲያው ዘርፍ የልዕቀት ማዕከል (Center of Excellence) የመሆን ራዕይ እንዳለውም ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የሬዲዮ ጣቢያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፤የሬዲዮ ጣቢያው በአገሪቱ የሚገኙትን የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ቁጥር በአንድ ከፍ ከማድረግ በዘለለ የራሱን ቀለምና መልክ ይዞ በማህበረሰቡ አኗኗርና አስተሳሰብ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ብለዋል፡፡
የአሐዱ ሬዲዮ ዋና አዘጋጅ አቶ ካሣ አያሌው ካሳ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ጣቢያው በረቀቁ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችና በዘመናዊ ስቱዲዮ የተደራጀ ከመሆንም ባለፈ በሙያው ልምድ ባካበቱና ለሙያቸውና ለሚያገለግሉት ህዝብ ክብር ባላቸው ሙያተኞች የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፤ ጋዜጠኛው ራሱ የቴክኒኩንም ሥራ እየተቆጣጠረ ፕሮግራሞችን የሚሰራበት አዲስ አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡
ጣቢያው ከሬዲዮ ስርጭቱ በተጨማሪ የድረ ገፅ መገናኛ ብዙኃን እያደራጀ እንደሚገኝና ድረ ገፁ የአሐዱ ሬዲዮንን መሰረታዊ ባህርያት ተከትሎ፣ ከድምፅ ባሻገር መረጃዎችን በፅሁፍ፣ በፎቶና በቪዲዮ አስደግፎ እንደሚያቀርብና የሬዲዮ ስርጭቱንም በኢንተርኔት በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሙከራ ስርጭት ላይ የሚገኘው የሬዲዮ ጣቢያ፤ከመጪው ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ስርጭቱን እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡



Read 3079 times
Administrator

Latest from Administrator