Print this page
Sunday, 16 July 2017 00:00

በአማራና በአፋር ክልል አዋሳኞች በተፈጠረ ግጭት የበርካቶች ህይወት አለፈ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

   በአማራና በአፋር ክልል አጎራባች ወረዳ በተነሣ ግጭት የበርካቶች ህይወት ማለፉን ምንጮች ለአዲስ አድማስ የጠቆሙ ሲሆን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን በበኩሉ፤ ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳና በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ለ4 ቀናት የዘለቀ በመሣሪያ የታገዘ ግጭት መፈጠሩን የጠቆሙት ምንጮች፤በግጭቱ የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ንጉሡ፤ሰኔ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ግጭቱ መቀስቀሱን ጠቅሰው፤በእለቱ 8 ሰዎች ከሁለቱም ወገን ህይወታቸው እንዳለፈና 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል እንደገቡ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በሰሞኑ  ግጭት ከሞቱትና ሆስፒታል ከገቡት በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ አባወራዎች ቀዬአቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።  
በሁለቱ ክልሎች ተዋሳኝ በተለይም በሀብሩና በጭፍራ ወረዳዎች መካከል ከዚህ ቀደምም ተደጋጋሚ ህይወት የቀጠፉ ግጭቶች እየተፈጠሩ በተደጋጋሚ እርቀ ሰላም ቢደረግም ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አለመቻሉን ምንጮች ገልፀዋል።
የአሁኑም ሆነ ከዚህ በፊት የነበሩት ግጭቶች መንስኤ የግጦሽ፣ የውሃ እና የእንስሳት መዘራረፍ ችግር መሆኑን ያስረዱት የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ፤ግጭቶቹን በዘላቂነት ለማስቆም የሁለቱን ክልሎች ተዋሳኝ ህዝቦች በልማት የማስተሳሰር እቅድ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል። የሰሞኑን ግጭት ለማስቆም የሽምግልና ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት በመካሄድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ መንግስት ግጭቱን የፈጠሩ አካላትን  በቁጥጥር ስር አውሎ፣ለህግ እንደሚያቀርብም  ጠቁመዋል፡፡  
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት፤ የሁለቱ አጎራባች ህዝቦች ትስስርን ለማሳደግ፣ የአፋርኛ ቋንቋ ፕሮግራም መጀመሩን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡  

Read 5873 times