Sunday, 16 July 2017 00:00

ፓርቲዎች ድርድራቸውን በ90 የስብሰባ ጊዜያት ለማጠናቀቅ ተስማሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    ከኢህአዴግ ጋር 12 አጀንዳዎችን መርጠው ለድርድር የተቀመጡት 17 ተደራዳሪ ፓርቲዎች  አጠቃላይ ድርድሩን በዘጠና የድርድር ጊዜያት (ቀናት) ለማጠናቀቅ ተስማሙ፡፡ ፓርቲዎቹ ትናንት የተመረጡ 12 አጀንዳዎች ላይ ተወያይተው ቅደም ተከተል በማስያዝ ለመደራደር የተስማሙ ሲሆን በቅድሚያ በምርጫና በፓርቲዎች ስነ ምግባር ጉዳይ እንደራደራለን ብለዋል፡፡
ድርድሩ ምን ያህል ጊዜ ይፍጅ የሚለው ፓርቲዎቹ ከተወያዩበት አንዱ ሲሆን አደራዳሪ አካሉ ያቀረበው የጊዜ ሰሌዳ ከ200 በላይ የድርድር ስብሰባ ቀናትን ቢሆንም ፓርቲዎቹ 90 የድርድር ቀናት ይበቃናል ሲሉ ተስማምተዋል፡፡
የመጀመሪያ ድርድር አጀንዳ ሆኖ ለተመረጠው የምርጫ ጉዳይ ፓርቲዎች የመደራደሪያ ነጥባቸውን በ5 ቀናት ውስጥ በፅሁፍ ለማስገባትም ተስማምተዋል፡፡
በዚህ መሰረት በመጀመሪያ ለመደራደሪያነት ለተመረጠው የምርጫ ህግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ እስከ ሰባት ቀን የሚደርስ የመደራደርያ የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጧል፡፡  በ2ኛ ነት ለተመረጠው የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ ለበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ፣ ለሰብአዊና ዲሞክራሲ ተቋማት አደረጃጀት መደራደሪያነት በድምሩ 20 የመደራደሪያ የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጧል፡፡
ቀጥሎ ለተመረጠው የፍትህ አካላት አደረጃጀት አስር የድርድር ጊዜያት እንዲሁም የዜጎች በማንኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዟዙሮ የመስራት መብት እና የታክስ ህግ ጉዳይ በድምሩ 16 የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጧል፡፡
በመጨረሻ አጀንዳነት ለተመረጠው የብሄራዊ መግባባት ጉዳይ፣ አስር የመደራደሪያ የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጧል፡፡  

Read 2538 times