Sunday, 16 July 2017 00:00

አቶ አማረ አረጋዊ እና አቶ ክፍሌ ወዳጆ የክብር እውቅና ተሰጣቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

· “የአገሪቱ የፕሬስ እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ያህል አልተጠናከረም” - ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ
· “የኢትየጵያ ሚዲያ ችግር ቢኖርበትም ጠንካራ ጋዜጠኞች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም” - አቶ አማረ አረጋዊ
የ”ሪፖርተር” ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ እና ህገ መንግስቱን በማርቀቅ ሂደት ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው አቶ ክፍሌ ወዳጆ፤ “ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት” ላበረከቱት አስተዋፅኦ ከትናንት በስቲያ በሒልተን ሆቴል በተከናወነ ሥነ ስርአት ላይ ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እጅ የክብር እውቅና ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
አቶ አማረ አረጋዊና በህይወት የሌሉት አቶ ክፍሌ ወዳጆ፣ ሩብ ክ/ዘመን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት መሰረት በመጣላቸውና ነጻነቱ በተግባር እንዲፈተሽ በመጣራቸው ዕውቅናው ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡
የደርግ መንግስት ውድቀትን ተከትሎ ሲደረጉ በነበሩ ፖለቲካዊ ውይይቶች፣ አብዛኛው የፖለቲካ ሃይል የቡድን መብት ላይ በሚያተኩርበት ወቅት አቶ ክፍሌ ወዳጆ የግለሰብ መብት፣ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የማምለክ፣ የመደራጀት … መብቶችን ለማስከበር በእጅጉ በመሟገታቸው እንዲሁም በህገ መንግስቱ የማርቀቅ ሂደትም እነዚህ መብቶች እንዲካተቱ ለማድረግ በእጅጉ የደከሙ በመሆኑ ለእውቅናው እንዳስመረጣቸው ታውቋል፡፡ የአቶ ክፍሌ ወዳጆ ቤተሰቦችም ከፕሬዚዳንቱ የእውቅና ሽልማቱን ተረክበዋል፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት እነዚህ መብቶች ስለመረጋገጣቸው በተግባር በመፈተሽና በመሞገት አስተዋፅኦ አድርገዋል የተባሉት የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው፤ በየጊዜው የነበሩ ፈተናዎችንና ጫናዎችን ተቋቁመው፣ ሪፖርተር ጋዜጣን ለ20 ዓመታት ያለማቋረጥ እንዲራመድ በማድረጋቸው፣ ከዚያም በፊት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅትን በኃላፊነት ሲመሩ ተቋማቱን ለማዘመን ባደረጉት ጥረት የክብር ዕውቅናው እንደተሰጣቸው ታውቋል።   
ባለፉት 25 ዓመታት  የግል ሚዲያው እንዳይቋረጥ በፅናት መታገላቸውና በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችን  ማፍራታቸውም ተጠቅሷል፡፡ አቶ አማረ አረጋዊ በሳምንት ሁለቴ የሚታተመው “ሪፖርተር” የአማርኛ ጋዜጣና በሳምንቴ አንዴ የሚወጣው “The Reporter” የእንግሊዝኛ ጋዜጣ መስራችና ባለቤት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በግሉ ፕሬስ ለረዥም ዓመታት በህትመት በመዝለቅ የሚታወቀው ሪፖርተር ጋዜጣ፤በማስታወቂያ ከፍተኛውን ገቢ በማስገባትም በህትመቱ ዘርፍ ግንባር ቀደም ነው፡፡
አቶ አማረ በጋዜጣ ሳይወሰኑ አሁን ደግሞ African Renaissance የሚል የቴሌቪዥን ጣቢያ በማቋቋም ላይ እንደሚገኙ በስነ ስርአቱ ላይ ተገልጿል፡፡  አቶ አማረ አረጋዊ ወልደኪዳን እ.አ.አ ጃንዋሪ 7, 1948 በትግራይ ተወለዱ፤ በልጅነታቸው በመጀመሪያና በመካከለኛ የትምህርት ክፍሎች ያስመዘገቡትን ውጤት ተከትሎ ጀነራል ዊንጌት ት/ቤትን የተቀላቀሉት አቶ አማረ፤ ወደ እንግሊዝ ሀገር በማምራት የሁለተኛ ደረጃና የኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ፣ የህውሓትን የትጥቅ ትግል ተቀላቅለው፣ በትጥቅ ትግሉ በተለያዩ ኃላፊነቶች መስራታቸው ተገልጿል፡፡
የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ መስራችና ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ፤ በኘሮግራሙ መክፈቻ ላይ ባደረገችዋ ንግግር “በአገራችን ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በተለይ በግል የሚዲያ እንቅስቃሴ ረገድ ትልቅ ለውጥ የታየባቸው መሆኑን በበጎ ጎኑ ብናነሳም፤ በሌላ በኩል በእነዚሁ ዓመታት ውስጥም ወጣት ጋዜጠኞች ለዕስርና ስደት መዳረጋቸው፤ ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው የሕትመት ውጤቶች ገና በለጋነታቸው መጨናገፋቸውን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል”  ብላለች፡፡
ጋዜጠኛ መዓዛ በመቀጠልም፤ “የዛሬ ሙከራችን የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ሊሆን የሚችለውን የሚመኘውንና የሚፈልገውን ትንሽን ሚና በተግባር ሲተረጐም ማየት ነው፡፡ ዛሬ እዚህ መገኘታችን ምክር ቤቱ እፈጽማቸዋለሁ ከሚላቸው ተግባራት መካከል አንዱን በሚዲያ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎችን እውቅና ለመስጠት የሞከረ የጀማሪ መጠነኛ ጥረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ በሙያቸው፤ በሥራቸው ያውም እጅግ ከልካይ በሆነው የቀድሞ ስርዓት ውስጥ ሕዝብን ያገለገሉ ጋዜጠኞች እንደነበር በዚህ አጋጣሚ ማንሣት ተገቢ ሆኖ፤ የዚህ ዝግጅት ኮሚቴ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁለት ሰዎችን መርጧል” አቶ አማረ አረጋዊ እና አቶ ክፍሌ ወዳጆን ማለቷ ነው፡፡
በስነ ስርአቱ ላይ በክቡር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ በህይወት የሌሉት አቶ ክፍሌ ወዳጆ እና አቶ አማረ አረጋዊ በእርግጥም በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት 25 ዓመታት የፕሬስ ነፃነትን መሰረት ለማስያዝና ለማጠናከር የሚያግዙ አዋችና ድንጋጌዎች ተግባራዊ ቢደረጉም የአገሪቱ የፕሬስ እንቅስቃሴ ግን የሚፈለገውን ያህል አልተጠናከረም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድትገሰግስ ከተፈለገም ኃላፊነቱን የሚወጣ መገናኛ ብዙኃን መገንባት ተገቢ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። አንዳንድ አካላት በሚዲያዎች ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት የሚዲያዎችን የአሰራር ነፃነት እየተጋፋ እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች መነገሩን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች በመንግስት በኩል ፍፁም ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡
ከፕሬዚዳንቱ የክብር እውቅና ሽልማታቸውን የተቀበሉት አቶ አማረ አረጋዊ ለተሰጣቸው እውቅና ምስጋናቸውን አቅርበው፤ “የኢትዮጵያ ሚዲያ ችግር ቢኖርበትም በየዘርፉ ጠንካራ ጋዜጠኞች መኖራቸውን መዘንጋት የለበትም፤ ሽልማቱ የእነሱም ነው” ብለዋል፡፡ ሰራተኞቻቸውና የጋዜጣው አንባቢዎችም ለጥንካሬያቸው ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡  የኢትዮጵያ ፕሬስ ነጻነት የታወጀበትን 25ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የክብር ዕውቅና ፕሮግራሙን መዘጋጀቱ የታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ም/ቤት እና ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር በጋራ ነው ያዘጋጁት ተብሏል።

Read 5854 times