Print this page
Sunday, 16 July 2017 00:00

ኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥሯን ካልመጠነች የመካከለኛ ገቢ ዕቅዷ አይሳካም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

· ከ35 ዓመት በኋላ የህዝቡ ቁጥር ከ204 ሚ. በላይ እንደሚሆን ተገምቷል
· እንግሊዝ ለቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት 90 ሚሊዮን ዩሮ እሰጣለሁ ብላለች
· “በ2017 ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እድገት ከዓለም ቀዳሚዋ ነች” - የዓለም ባንክ
· ኡዝቤክስታን፣ ኔፓል፣ ህንድ በዕድገት ኢትዮጵያን ይከተላሉ

ኢትዮጵያ ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገቷን ካልመጠነች በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ እንደማትችል ሰሞኑን ለንደን ላይ በተደረገ ጉባኤ የተገለፀ ሲሆን እንግሊዝ በበኩሏ፤ በፍቃደኝነት ላይ ለሚመሰረት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት 90 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደርጋለሁ ብላለች፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያ በቤተሰብ ምጣኔ የተሻለ ለውጥ ብታመጣም የህዝቧ ቁጥር በእጥፍ ከመጨመር አልታደገውም ተብሏል፡፡ ከዛሬ 25 ዓመት በፊት 50 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር፤ በአሁን ወቅት ወደ 102 ሚሊዮን ማደጉ ተጠቁሟል፡፡
ከሦስት እናቶች አንዷ የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚ በሆነችበት ኢትዮጵያ፤ አሁንም እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙ ካልተደረገ ከ35 ዓመት በኋላ የሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር በእጥፍ አድጎ፣ ከ204 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ተገምቷል። ይህም ሀገሪቱ ከ8 ዓመት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ለመሠለፍ በያዘችው እቅድ ላይ እንቅፋት ይፈጥራል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የቤተሰብ እቅድ እንግሊዝ 90 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደምታደርግ ያስታወቀች ሲሆን ድጋፉም በሚቀጥሉት አራት አመታት ውስጥ ከ3 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ እናቶችን የቤተሰብ ምጣኔ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ በተጨማሪም ቀድሞ መቆጣጠሪያ የማይጠቀሙ ለነበሩ 6 ሚሊዮን እናቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ይውላል ተብሏል፡፡ 13 ሚሊዮን እናቶችም በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የቤተሰብ ምጣኔ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡
ሰሞኑን በለንደን በቤተሰብ ምጣኔ ላይ የመከረው ጉባዔ የተዘጋጀው በእንግሊዝ አለማቀፍ ልማት ፅ/ቤት፣ በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ ትብብር መሆኑ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የዓለም ባንክ ሰሞኑን ባወጣው የ2017 ዓለም ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ፤ ኢትዮጵያ በአማካይ 8.3 በመቶ አገራዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) ምጣኔ በማስመዝገብ ከዓለም ቀዳሚዋ ሆናለች ብሏል፡፡
ኡዝቤክስታን በአማካይ 7.6 በመቶ በማስመዝገብ፣ ኔፓል 7.5 በመቶ እንዲሁም ህንድ 7.2 በመቶ በማስመዝገብ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይይዛሉ ተብሏል፡፡
በ2017 ፈጣን አዳጊ ይሆናሉ ከተባሉት 10 የዓለም ሀገራት መካከል ጅቡቲ፣ ላኦስ፣ ካምቦዲያ፣ ፊሊፒንስ እና ማይናማር ይገኙበታል፡፡ ቻይና 8.5 በመቶ በማስመዝገብ በ16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያዎች በአገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያከራክሩ ቆይተዋል፡፡ የኖቤል ተሸላሚው ኢኮኖሚስት ጀሴፍ ስቲግሌዝ፣ የአይኤምኤፍ ዳይሬክተር ክርስቲና ላጋርድን ጨምሮ አለማቀፍ ምሁራን፤ አገራዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) ሁነኛ የዕድገት መለኪያ አለመሆኑን የሚሞግቱ ሲሆን የዕድገት መለኪያዎች መሆን ያለባቸው፡- የዜጎች የስራ ዕድል፣ የጤና ዋስትና፣ ናቸው ይላሉ፡፡ GDP የአየር ጠባይ ለውጥን እንኳን የማያገናዝብ መለኪያ በመሆኑ ትክክለኛ መለኪያ ወይም ተጨባጩን እውነታ የሚያሳይ አይደለም ብለዋል፡፡



Read 6463 times