Sunday, 16 July 2017 00:00

ለመተራመስ መቸኮል ምንድነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(9 votes)

1. የዞረበት ዘመን...
• ተመራቂ ወጣቶች ሲበራከቱ፣ መፍራትና መጨነቅ ሳይሆን፣ ‘ብሩህ ዘመን እየመጣ ነው’ የሚል ስሜት
ሊፈጠርብን ይገባ ነበር። ግን፣ በዓመት ለ1 ሚሊዮን ወጣቶች፣ በየት በኩል ተጨማሪ የስራ እድል ይከፈት ይሆን?
2. የዞረበት አገር...
• ለተመራቂ ወጣቶች ብዙ ሺ የስራ እድል የሚፈጥሩ፣በዚህም ከአደጋ የሚያድኑን ኢንቨስትመንቶች
እንዲበራከቱና እንቅፋት እንዳይገጥማቸው ከመጣርና ከመዝመት ይልቅ፤ በኢንቨስትመንቶች ላይ እንዘምታለን።

በ1 ዓመት......
====================================
በዲግሪ ተመርቀው ስራ የሚፈልጉ ወጣቶች              120 ሺ
====================================
ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው ስራ የሚፈልጉ ወጣቶች     400 ሺ
====================================
10ኛ ክፍል አጠናቅቀው ስራ የሚፈልጉ ወጣቶች          500 ሺ
====================================
የተማሩ-የተመረቁ ስራ ፈላጊ ወጣቶች - የ1 ዓመት     ከ1 ሚሊዮን በላይ
===================================

ይሄ በየዓመቱ ነው። ከ10ኛ ክፍል እስከ ዲግሪ ድረስ የተማሩ 1 ሚሊዮን ወጣቶች፣ በየዓመቱ ስራ ይፈልጋሉ።
ስለ ትምህርትና ስለ ተመራቂዎች ስናወራ፣ የእውቀትን ሃያልነትና የወጣትነትን የስራ ብርታት እያሰብን ስሜታችን በብሩህ ተስፋና በጉጉት የተሞላ መሆን ነበረበት። እንዲሆን ማድረግም ይቻላል። ሕይወትን የሚያሻሽል፣ ድንቅ የብልፅግናና የስልጣኔ ለውጥ የምናመጣበት የስኬት ጎዳና ሊሆንልን ይችላል - ትክክለኛውን የመፍትሄ ሃሳብ ከጨበጥን።
አሁን ግን፣ የዞረበት ዘመን ሆነና፤... የተመራቂ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ የመምጣቱን ያህል፣... ሃሳባችንም ጭንቀትና ፍርሃት ያጠላበት ሆኗል (ለማሰብ ፈቃደኛ ከሆንን ማለቴ ነው)። በአንድ በኩል፣ የስራ እድልና ተስፋ ብዙም የለም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተማሩና የተመረቁ 1 ሚሊዮን ተጨማሪ ወጣቶች፣ በየዓመቱ!
መዘዞቹ፤... የስራ እጦትና የኑሮ ችግር፣ ቅሬታና ስደት፣ ቀውስና ትርምስ... ያስጨንቃሉ! ያስፈራሉ።
አዎ፤ “ምንም የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም” ብለን ራሳችንን ለማታለል እንሞክር ይሆናል። በእርግጥም፣ የስራ እጦትና የኑሮ ችግር፣ ለዓመታት አብረውን ኖረዋል። በዓመት 100ሺ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ በጂቡቲና በሶማሊያ አቅጣጫ ሲሰደዱ አይተናል - ለዚያውም በጦርነት በምትታመሰው በየመን በኩል። ቅሬታና ቀውስም ከዓመት ዓመት ሲከማች፣ ዓመፅና ትርምስም... በየጊዜው ሲፈነዳ ተመልክተናል (የአምናው አስፈሪ ቀውስ ጭምር)። ነገር ግን፣ የእስከዛሬዎቹ ቀውሶችና ትርምሶች፣ ከወደፊቱ አደጋዎች ጋር ሲነፃፀሩ፣... ኢምንት ናቸው፤ ወይም የሕፃናት ጨዋታ ቀልለው የሚታዩ ይሆናሉ።
አዲስ የተፈጠረ ነገር አለ?
እስቲ ጥቂት መረጃዎችን ልጥቀስላችሁ።
1. የቴክኒክና ሙያ
ከ10 ዓመት በፊት፣ የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች ቁጥር፣ 80ሺ ገደማ ነበር።
ዛሬ፣ 400ሺ ደርሷል - በየዓመቱ።
2. የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች
ከ20 ዓመት በፊት፣ እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ፣... የየዓመቱ የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ቁጥር፣ ከ2500 ገደማ አይበልጥም ነበር። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ማለትም ከዛሬ 10 ዓመት በፊት እንኳ፣ የዲግሪ ተመራቂዎች ቁጥር 7ሺ አይሞላም ነበር። በአስር ዓመት ውስጥ፣ በዲግሪ የሚመረቁት ወጣቶች ከ50 ሺ አይበልጡም ነበር።
በአማካይ በዓመት 5ሺ ያህል ማለት ነው!
ዛሬስ? በዓመት 120ሺ ወጣቶች ይመረቃሉ። ከ20 እጥፍ በላይ እንደሆነ ልብ በሉ።
3. የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች
የዛሬ 20 ዓመት ጠቅላላ የዩኒቨርስቲ የዲግሪ ተማሪዎች ቁጥር፣ 20ሺ ነበር።
ዛሬ፣ ከ1 ሚሊዮን በላይ ነው። 50 እጥፍ ማለት ነው። ታዲያ፣ ምንም አዲስ ነገር አልተፈጠረም? ተፈጥሯል እንጂ። አዎ! የትምህርቱ ጥራት ራሱ፣ በጣም አሳሳቢ መሆኑ ባንዘነጋም፣ የተማሪዎችና የተመራቂዎች ቁጥር በሃምሳ እና በሃያ እጥፍ መጨመሩን፣... እንደ ስኬት ልናየው ይችላል። ያው፤ የመማርና የማወቅ እድል ያገኘ ወጣት በርክቷል፤.. ቁጥሩ፣ በእጅጉ ጨምሯል።
ታዲያ፣ በዚያው ልክ...
“ለትምህርቴ የሚመጥን፣ ደህና የስራ እድልና የኑሮ ደረጃ ማግኘት አለብኝ” የሚል አወንታዊ ስሜት የተላበሰ ተመራቂ ወጣትም፣ ቁጥሩ በእጅጉ ጨምሯል።
ተምሮ የተመረቀው ወጣት፣ በአብዛኛው... “ይገባኛል” ብቻ ሳይሆን፤ “ይግገባኛል” ባይ ነው። “ገብቶኛል፣ አውቄያለሁ” ብቻ ሳይሆን፣ “ለኔ ተገቢ የሆነው የስራ አይነት፣ ኑሮን የሚያሻሽል መሆን ይገባዋል” የማለት ዝንባሌን፣ ወይም ‘የይገባኛል ስሜት’ን የያዘ ነው - አብዛኛው ተመራቂ ወጣት።
በሌላ አነጋገር፣ እንደድሮው፣... ነባር የድህነት ኑሮን አሜን ብሎ ለመቀበል፣... በዝምታ ለመሸከምና እንደ እጣፈንታ እድሜውን በችጋር ለመግፋት፣ ብዙም ፈቃደኛ አይደለም። ይሄ ሁሉ፣ ጥሩ ለውጥ ነው።
ችግር የሚፈጠረው፤ ኑሮን የሚያሻሽል ዘዴና የስራ እድል ሲያጣ ነው። ያኔ፣... አንዳንዱ፣ በስሜትም ሆነ በስሌት ከስደት ጎርፍ ጋር ይቀላቀላል። አንዳንዱ፣ እዚሁ ሆኖ፣ መሰናክል በበዛበትና ተዘጋግቶ መፈናፈኛ በሚያሳጣ አገር፣ የቻለውን ያህል ለመንቀሳቀስ ይፍጨረጨራል፤ ይለፋል - ሌላ ጥሩ አማራጭ በማጣት። አንዳንዱ፣ አየርባየርም እየተቅለበለበ አልያም ከስር እየተሽሎከለከና እየሰረሰረ፣ የማምታታትና የማጭበርበር አቋራጭ መንገድ ለማግኘት ይቅበዘበዛል።
ከፊሉ ተስፋ ቆርጦ፣ ይላወሳል።
ከፊሉ ደግሞ፣ በቅሬታና በእሮሮ ተወጥሮ፣ “አንዳች ለውጥ” ይመጣ እንደሆነ ለማየት፣ ግራ ቀኝ ይወራጫል፣ ፊትና ኋላ እየተፈናጠረ ይደናበራል። ያምፃል፣ ይራበሻል።
አላወቀም እንጂ፣ ‘አንዳች ለውጥ’ ለማየት እየተደናበረ ሲራበሽ፣... ረብሻ የሚናፍቁ ነውጠኞች ይመቻቸዋል። ነውጠኞቹ፣ ሰበብ አያጡም። በዘር አልያም በሃይማኖት ማቧደን፣ በአገር አልያም በብሔርብሔረሰብ መፈክር፣ በባለስልጣንነት አልያም በተቃውሞ መሪነት፣ ሰማይ ምድሩን ያምሱታል። ባለፈው ዓመት እንዳየነው፣ የዘመናችን ቀውሶች በምን ሰበብ እንደሚጀመሩ፣ በየት አቅጣጫ ተባብሰውና ተቀጣጥለው አስፈሪ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው። በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር ምንድነው?
የተጠራቀመ የኑሮ ቅሬታ ሲበዛና ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ ሲታጣ፣ ቀውስ መፈጠሩ አይቀሬ ነው - ቀውሱን የሚለኩስ ሰበብ ሞልቷል።
እንደሚባባስና መያዣ መጨበጫ እንደሚያጣም፣ አያጠራጥርም። ውጥንቅጡ እየወጣ፣ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳይ እየደረሰ፣ ብዙም ሳይቆይ ወደ አስፈሪ ትርምስነት ይንደረደራል። ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ እስካላወቅን ድረስ፣ የቀውሱ መልክ እየተዘበራረቀ አገሬውን በነውጥ ለማዳረስ ከተስፋፋ በኋላ፣ ከመንታ አማራጮች ውጭ መሄጃ መንገድ ይጠፋል። ወይ፣ በበርካታ አገራት እንዳየነው፣ ‘ምንነቱ ያልታወቀ አንዳች ለውጥ ለማምጣት’ እየተደናበርን፣ አገሬው ወደለየት ትርምስና ለዓመታት መውጫ ወደሌለው እንጦሮጦስ ይወርዳል። አልያም፣... ‘ከትርምስ አድናችኋለሁ’ የሚል መንግስት፣ ከወትሮም በላይ በጉልበት የመግነን እድል ያገኛል። ይህም በበርካታ አገራት ታይቷል። ከእያንዳንዱ ቀውስና ብጥብጥ በኋላ፣ በጉልበት መግነን የሚፈልጉ ባለስልጣናት፣ እንዳሻቸው የመሆን ተጨማሪ ስልጣን ያገኛሉ - አገርን ለማረጋጋትና ከትርምስ ለማዳን።
በእርግጥም፣ ፈላስፋዋና ደራሲዋ አየን ራንድ እንደገለፀችው፣ ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ ሲጠፋ፣ መንታዎቹ የጥፋት አቅጣጫዎች... በአንድ በኩል ወደለየለት ትርምስ የሚያመራ አመፅ፣ በሌላ በኩል እየገነነ የሚሄድ መንግስት ናቸው። ደግሞስ፣ ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ ለመያዝ ያልቻለ ሰው፣ ምን ሌላ አማራጭ አለው? ያው፣ በትርምስ ዓመፅ ስንደናበር፣ በስልጣን መግነን ለሚፈልግ መንግስት እንመቸዋለን - “አገር ለማረጋጋት፣ በስልጣን መግነን ያስፈልጋል” ይላል። መንግስት በገነነ ቁጥር ደግሞ፣ የትርምስ ዓመፅ ማቀጣጠልና አገር-ምድሩን ማደበላለቅ ለሚፈልግ ነውጠኛ ይመቸዋል - “አንዳች ለውጥ ለማምጣት እንታገል” ይላል - (ምንነቱ የማይታወቅ ‘አንዳች ለውጥ’ ማለት፣ ከትርምስ ውጭ ትርጉም ባይረውም)። የትርምስ ዓመፅና ገናና መንግስት... እነዚህ ሁለቱ፣ እርስበርስ ‘ተመጋጋቢ’ ናቸው።   
ለዚህም ነው፣ መፍትሄ ሃሳብ የሌለና የማይገኝ በመሰለበት በዛሬው ግራ የተጋባ ዘመን፣ መጠኑ ቢለያይም፣ በየአህጉሩ የአለማችን አገራት እየተቃወሱ የሚገኙት። አንዳንዶቹ፣ ለይቶላቸዋል - መውጫ በሚያሳጣ ትርምስ እየተጫረሱ ናቸው (ከሶማሊያ እስከ ሶሪያ፣ ከየመን እስከ ሊቢያ ወዘተ...)። አልያም መፈናፈኛ የሚያሳጣ መንግስት ከቀን ወደ ቀን እየገነነባቸው ነው - (ከግብፅ እስከ ራሺያ፣ ከቬኔዝዌላ እስከ ፊሊፒንስ... ወዘተ)። የኛ አገር፣... ሁለቱንም የጥፋት መንገዶች እየሞካከረች፣ በየጊዜው የትርምስ ዓመፅንም እየቀመሰች፣ ከዚሁ ጎን ለጎን መንግስት እየገነነ የሚመጣበትንም ጊዜ እያየች ቆይታለች። ግን፣ ገና አልለየላትም። ይሄ፣ መፅናኛ ሊሆን ይችላል። ለጊዜ ብቻ!
ለማለት የፈለግኩትን በአጭሩ ለመግለፅ ይህንን እላለሁ፡
የኑሮ ቅሬታ በበዛበትና ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ የመያዝ ፈቃደኝነት በጠፋበት ዘመን፣... በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ኋላቀርና ድሃ አገራት ውስጥ፣... በነውጠኛ የትርምስ ዓመፅ እንዲሁም እየገነነ በሚሄድ መንግስት... ወደለየለት ጥፋት የመማገድ አደጋ እንደሚያጋጥም አትጠራጠሩ።
ታዲያ፣ ከዚህ አስፈሪ አደጋ ለመዳን፣ መጣጣር የለብንም?
ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ ለመጨበጥ፣ መመርመርና ማሰብ የለብንም?
እስከዚያው፣ የአደጋውን ፍጥነትና ጉዳት ለመቀነስ፣ የቻልነውን ያህል መሞከር፣... በተለይ ደግሞ፣ እስካሁን የዘረጋናቸውን መሰናክሎችና የተከልናቸው ጋሬጣዎችን በማስወገድ፣ ዜጎች ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ መንገዱን ለመክፈት መረባረብ የለብንም?
(በተቃራኒው፣ ‘የካርቦን ልቀት’ ለመከላከል በሚል አስቂኝ የተሳከረ የቅዠት ሃሳብ፣ የፋብሪካዎችና የስራ ግንባታዎች ሲታገዱ ዜና እንሰማለን - በአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አማካኝነት)።
የተማሩ ተመራቂ ወጣቶች፣... የየራሳቸውን ሕይወት በየራሳቸው ጥረት ከማሻሻል የበለጠ አንዳችም ቅዱስ ተግባር እንደሌለ እንዲገነዘቡና፣ ለስራ ፈጠራ እንዲተጉ ማነሳሳትና ማበረታታት የለብንም?
(ተማሪዎች ለስራ አለም እንዲዘጋጁ ከማድረግ ይልቅ፣ ‘የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የሚስተካከል ቅዱስ ነገር የለም’ በሚል መፈክር፣ 8 ሚሊዮን ተማሪዎች ለወደፊት የስራ ዓለም ምንም ፋይዳ በሌለው የክረምት ስምሪት እንዲጠመዱ ‘ትልቅ’ ዘመቻ ሲካሄድ እናያለን)።
ስራ የመፍጠር ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ወጣት ተመራቂዎች፣ በጥረት አለማቸውን እንዲያሳኩ መመኘትና በነፃነት እንዲሰሩ ማበረታታት ተገቢ የመሆኑን ያህል፤... በዚያው ልክ ለተመራቂ ተማሪዎች፣ ብዙ ሺ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ኢንቨስተሮችንም ማድነቅ፣ ማክበር፣ ያለመሰናክል በነፃነት የሚሰሩበት የሕግ የበላይነትን ለማስፋፋት መጣጣርስ የለብንም?
(በተቃራኒው፣ ኢንቨስተሮችንና የቢዝነስ ሰዎችን በጅምላ፣... ‘ኪራይ ሰብሳቢ’፣ ‘አጭበርባሪ’ እያልን ያለፋታ የውግዘት ዘመቻ እናካሂድባቸዋለን። ባሰኘን ጊዜ፣ የዋጋ ቁጥጥር እናውጅባቸዋለን። ባለ10 ፎቅ የቢሮ ሕንፃ የመገንባት ግዴታ ካሸከምናቸው በኋላ፣ ትንሽ ቆይተን ደግሞ፣ የቢሮና የመኖሪያ አገልግሎትን ካላቀላቀልክ፣ ህንፃ መገንባት አትችልም ብለን በድንገተኛ መመሪያ እንጠፍራቸዋለን። እንደ ስኳር ፕሮጀክት በመሳሰሉ የመንግስት ቢዝነሶች አማካኝነት በርካታ ቢሊዮን ብሮች በየዓመቱ ሲባክን ብዙም አያስጨንቀንም፤ በየዓመቱ ተጨማሪ ታክስ በኢንቨስተሮችና በነጋዴዎች ላይ መጫን ግዴታ እንደሚሆን አይገባንም። የሲሚንቶ ቢዝነስ ለዓመታት መንግስት በሞኖፖል (በጉልበት) ስለያዘው፣ ሲሚንቶ ብርቅ የነበረ ጊዜ ሩቅ አይደለም። በስድስት ወር ወረፋም አይገኝም፤ በዚያ ላይ ዋጋው ጣሪያ ሲነካ እናስታውሳለን። የሲሚንቶ እጥረት፣ በኢንቨስተሮች አማካኝነት ነው፣ ‘የድሮ ተረት’ የሆነው፤... ዋጋውም በግማሽ የቀነሰው። በዚህ ምክንያት፤ ስንትና ስንት ግንባታዎች እንደተሳኩ፣ ለስንትና ስንት ወጣቶች የስራ እድል እንደፈጠ ማሰብ ይቻላል። ታዲያ፣ እነዚህ ፋብሪካዎች ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ማካሄድ ነበረብን? ልንዘምትባቸው ይቅርና፣ ጨርሶ በሕልማችን ዝር ማለት ነበረበት? ‘በግዴታ፣ ለወጣቶች የስራ እድል ስጡ’ በሚል ዘመቻ፣ ለወጣቶች የስራ እድልን የሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶችን መሸርሸር!)
ያስገርማል።
የተማሩና የተመረቁ ወጣቶች ሲበራከቱ፣ መፍራትና መጨነቅ ሳይሆን፣ ብሩህ ዘመን ይመጣል የሚል ስሜት ሊፈጠርብን ይገባ ነበር።
ለወጣቶች ብዙ ሺ የስራ እድል የሚፈጥሩና ከአደጋ የሚያድኑን ኢንቨስትመንቶች እንዲበራከቱና እንቅፋት እንዳይገጥማቸው ከመጣርና ከመዝመት ይልቅ፤ በኢንቨስትመንቶች ላይ እንዘምታለን።
ይሄ፣ ይሄ... ከአደጋው በላይ፣... ይበልጥ ያስፈራል፤ ያስጨንቃል።

Read 3754 times