Monday, 17 July 2017 11:50

ዘመኑና ‘ነፍስ አባት’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እንደ በፊቱ “ኃጢአት ስለሠራሁ ይፍቱኝ!” ምናምን አይነት ኑዛዜ ነገር አሁን አለ እንዴ! መጠየቅ አለብና!…ዙሪያችንን የሚሆኑትንና የማይሆኑትን ነገሮች እያየን መጠየቅ አለብና! እንደው ተሳስቶ እንኳን “ኃጢአቶቼን ይቅር ቢለኝ እስቲ ለነፍስ አባቴ ልተንፍስው…” ብሎ  የሚናገር የጠፋ ነው የሚመስለው፡፡ አሀ…እንደዛ ቢሆን ክፋቱ፣ የድንጋይ ዘመን ባህርዩ ሁሉ ባይተወን እንኳን ይቀንስ ነበራ!
አንድ የምናውቀው ሰው… “ዘንድሮ የሚታመን የነፍስ አባት በቁጥር ቢሆን ነው” ሲል ነበር፡፡ ሉሲፈር ያልገባበት ቦታ፣ ያልተኛበት አልጋ፣ ያልተንፈላሰሰበት ወንበር የለማ! እናማ፣ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… የሚናዘዝ እንኳን ቢኖር ምናልባት “የዘመኑ ነገር ገብቶናል” የሚሉ፣ “የምንሰጠው ውሳኔ ከጊዜው ጋር የተጣጣመ ነው” የሚሉ የነፍስም ይሁን የምን አባቶች ካሉ አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለናል፡፡
እሱ፡— ኃጢአት ስለበዛብኝ ልናዘዝና ይፍቱኝ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡
እሳቸው፡— ጥሩ አድርገሀል፣ እስቲ ኃጢአቶቼ የምትላቸውን ነገሮች አንድ፣ ሁለት እያልክ ንገረኝ፡፡
እሱ፡— መቼም ባለትዳር መሆኔን ያውቃሉ…
እሳቸው፡— እኔው አጋብቼ፣ እኔው ባርኬ ባለትዳር መሆኔን ታውቃለህ ትለኛለህ!
እሱ፡— ይቅርታ አባቴ፣ አንዳንዴ እንደው በሆነ፣ ባልሆነው ስለሚያስለፈልፈኝ ነው፡፡
እሳቸው፡— እኮ አሁን ትዳሬን ልፈታ ነው ልትለኝ ነው?
እሱ፡— እሱን እንግዲህ ፈጣሪ ያውቃል፡፡ ይኸውልዎት በቀደም የመሥሪያ ቤት የእራት ግብዣ ላይ መጠጥ አብዝቼ ጠጥቼ ነበር..
እሳቸው፡— እና ሰክሬ ሰው አስቀየምኩ፣ ፍታኝ ነው የምትለኝ!
እሱ፡— እንደውም፣ ምን መሰለዎት፣ በቃ ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ፣ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጸሀፊ ጋር እ..እ…ምን መሰለዎት…
እሳቸው፡— እኮ ከእሷ ጋር ምን…
እሱ፡— ከእሷ ጋር ተኛሁ፡፡ አባቴ ያቺን በመሰለች ሚስቴ ላይ ሌላ ሴት ደረብኩ፡፡ እኔ…
እሳቸው፡— ቆይ ረጋ በል፣ ከዚች ሴትዮ ጋር አብራችሁ ስንት ጊዜያችሁ ነው?
እሱ፡— ኸረ ያቺን ምሽት ብቻ ነው! ከዛ በኋላ ሰላም ስላት እንኳን እየተሳቀቅሁ ነው…
እሳቸው፡— እና አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተሳሳትከው?
እሱ፡— አዎ…አንድ ጊዜ ተሳሳትኩ፡፡
እሳቸው፡— ስማ፣ ይሄ ታዲያ ምን ችግር አለው። ጊዜውን አታይም እንዴ! አየህ አንድ ጊዜ ከሆነ አንተ አውቀሀ የሠራኸው ኃጢአት ሳይሆን ዲያብሎስ በመጠጥ ተመስሎ መጥቶ አሳስቶህ ነው፡፡ ደግሞ ዘንድሮ ሁሉም ሰው በየጥጉ ከሚስቱ ውጪ እየተኛ አይደል እንዴ!  አንተ ከሰው አትለይ… ይልቅ ሌላ ኃጢአት የምትለው ነገር ካለህ ንገረኝ፡፡ ይሄኛው ዝም ብሎ ያላየኸው ድንጋይ አደናቅፎህ ተንገዳገድህ እንጂ ከአንድም በላይ ቢሆን እንደ ኃጢአት አይቆጠርም፡፡ ጊዜው ስለተለወጠ አብሮ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡
እናላችሁ…ነገራችን ሁሉ እንዲህ መላ ቅጡ ስለጠፋ ሰውዬአችን ግሳጼ እንኳን ላይደርስበት ይችላል፡፡ በሆነ ሰርኩላር በትእዛዝ መልክ የተላለፈ ይመስላል እኮ፡፡
“ከሚስትህ ሌላ አንድ፣ ሁለት መተከዣ ከሌለህማ ምኑን ኖርከው! መቼም ሰው በልቶ ጠጥቶ…”፣ “ባሌ ብለሽ እሱ ላይ ብቻ ሙዝዝ የምትዪ ከሆነ ያለፈው ስርአት ናፋቂ ነሽ…” (ቂ…ቂ…ቂ…) ምናምን አይነት ነገር የተባለ ነው የሚመስለው፡፡ እንደውም “እከሊት ለሰኞ፣ እከሊት ለማክሰኞ” እየተባለ ፕሮግራም በሚወጣበት ዘመን፣ በጎርደን ጂን ለመጣ ስህተት ተጠያቂው ዲያብሎስ ነው፡፡ በቃ፣ እሳቸው ብለዋላ!
ስሙኝማ… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ የባልና የሚስት ግንኙነት ከዘመን ጋር የተለዋወጠ አይመስላችሁም?
የትናንት ወዲያ ባልና ሚስት…
ባል ሲዞር ውሎ ይገባል፡፡
ባል፡- ማነሽ?
ሚስት፡- አቤት ምን አሉኝ?
ባል፡- መንገድ ሄጄ እግሬን እየቆረጠመኝ ነው
ሚስት፡- ውሀ አሙቄ ላምጣልዎት፡፡
ውሀ አሙቃ ታመጣና ወደ አጠባው ትገባለች፡፡ “ሂድና ስትዞር የዋልክበት ስፍራ እጠቡኝ በላቸው” ብሎ ‘ሽቅብ’ መልስ መስጠት የለም፡፡
የትናንት ባልና ሚስት…
ሚስት ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ትገባለች፡፡
ባል፡- የት ነበርሽ?
ሚስት፡- ቀበሌ ነዋ!
ባል፡- ቀበሌ እስካሁን ሰዓት ምን ትሠሪያለሽ?
ሚስት፡- ለዘማች ቀለብ ስናዘጋጅ፡፡
ባል ጭጭ፣ ዝም ብሎ ወደ አልጋው፡፡
“የምን ዘማች፣ የምን ዘመቻ ነው!”፣ “አንቺ ጄኔራል ነሽ! ፊልድ ማርሻል ነሽ!” ምናምን ብሎ ጭቅጭቅ የለም፡፡
የዛሬ ባልና ሚስት…
ሚስት ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ሞባይል ላይ ትደውላለች፡፡
ሚስት፡- ቤት ገብተሀል?
ባል፡- አልገባሁም፣ ትንሽ አመሻለሁ ልልህ ነው፡፡
ሚስት፡- እኔም ትንሽ ቆይቼ ነው የምመጣው፡፡
ባል፡- ቻዎ፣  ብዙ አታምሺ… (ምን?)
ሚስት፡- ቻዎ!
“የት ነው የምታመሺው?”፣ “እስካሁን የሚያቆይህ የትኛው ሥራ ነው?” ብሎ ጭቅጭቅ የለም፡፡
እናላችሁ… ጥናት ቢጠና እንዲህ ሊመስል ይችላል ብለን እንጠረጥራለን፡፡
እሱ፡— ደግሞ ሌላ ኃጢአት አለ…
እሳቸው፡— ደግሞ ምን አደረግህ፣  ከሌላዋ ጋርም ተኝቻለሁ ልትለኝ ነው?
እሱ፡— አይደለም፡፡ ከዓመት በፊት ገንዘብ በጣም ቸግሮኝ ከጓደኛዬ ምንም ነገር ሳያስፈርመኝ ሠላሳ ሺህ ብር ተበድሬ ነበር፡፡ በሁለት ወር እመልስለሀለሁ ብዬ ነው የወሰድኩት…
እሳቸው፡— እኮ የምከፍለው አጣሁ እያልክ ነው?
እሱ፡— እንደ እሱ ሳይሆን፣ ምን መሰለዎት…በቃ ገንዘቡ እንዴት አድርጎ ከእኔ ይውጣ…አሳሳኝ…
እሳቸው፡— ለመክፈል ጊዜ ስጠኝ አልከው፡፡
እሱ፡— አይደለም… ምን መሰለዎት፣ እየደጋገምኩ ስጠፋበት፣ ስልኩን አልመልስ ብል ‘ኸረ እባክህ ቤተሰቤ ከፍተኛ ችግር ላይ ነው፣ ገንዘቡን መልስልኝ’ ብሎ አማላጅ ላከብኝ…
እሳቸው፡— እና…
እሱ፡— ካድኩ፣ እንኳን ሠላሳ ሺህ ብር ሠላሳ ሳንቲም አልወሰድኩም ብዬ ሽምጥጥ አደረግሁ፡፡ እና በቃ ህሊናዬን እየቆጠቆጠኝ ነው..
እሳቸው፡— ቆይ ከሠላሳ ሺህ ብር ሌላ ወስደሃል?
እሱ፡— እንደውም፣ ያቺኑ ሠላሳ ሺህ ብር ብቻ ነው የወሰድኩት
እሳቸው፡— ይሄ ታዲያ ምን ችግር አለው፡፡ የአሁን ሠላሳ ሺህ ብር እኮ የትናንት ሦስት ሺህ ብር ነች፡፡ ደግሞ ሰዉ ሦስት አራት ሚሊዮን እየተበዳደረ ‘ሰጥቸዋለሁ፣ አልሰጠኝም’ ይባባል የለ እንዴ! ለሠላሳ ሺህ ብር ኃጢአት ትላለህ! በዚች ኃጢአት ከተባለ አገሩ ሁሉ ኃጢአተኛ ሊባል ነው፡፡ ይልቅ ሌላ ኃጢአት የምትለው ካለ ንገረኝ፡፡
እናላችሁ፣ ዘንድሮ መካካድ… አለ አይደል…በምድር ከወንጀልነት፣ በሰማይ ከኃጢአትነት ይልቅ ብልጥነት ሆኗል፡፡ አለ አይደል…‘ያበደረህ እኮ ትርፍ ስላለው ነው እንጂ ባይኖረው ኖሮ ሰባራ ሳንቲም አይሰጥህም ነበር’ አይነት ነገር ነው፡፡
ስሙኝማ… ዘንድሮ አንድ ነገር አለች… “ሁሉም የሚያደርገው አይደለም እንዴ!” የምንላት ነገር አለች፡፡ “ሁሉም ካደረገው እኔ መልአክ ነኝ! የመነንኩ ባህታዊ ነኝ! የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ያዥ ነኝ!” አይነት በልካችን የተሰፋች መውጫ ቀዳዳ አለች። እናማ… አንድ ጊዜ ቢያደናቅፍ ምን አለበት! ሰዉ መቶ አሥራ አንድ ጊዜ ይመላለስ የለ እንዴ!
የሰውየውን ‘ነፍስ አባት’ ፈልገን ማግኘት ሳይኖርብን አይቀርም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 5376 times