Monday, 17 July 2017 11:58

ታሪከኛው ታሪካችን

Written by  ቤተማርያም ተሾመ betishk@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

ስለ ጊዜ በተነገሩ ፍልስፍናዎች ውስጥ በአንዱ፤ “ድሮ (ትናንት) የለም፣ አልፏል፣ ነገም የለም አልመጣም ያልተጨበጠ ብዥታ (Illusion) ነው። እውኑ እና እርግጡ ዛሬ፣ አሁን ብቻ ነው፡ ሲል ያትታል፡፡
ይሄ ምን ማለት ነው ? ይህ ድፍየና (Definition) በተለይ ታሪክ እግር ከወርች የኋሊት ከጠፈረን፣ የነገ ያልተረጋገጠ ተስፋና ፍርሀት  ዛሬ ላይ ግራ ለሚያጋባንና ለሚያስጨንቀን ሃበሾች ይሄ ፍልስፍና ምን ማለት ነው?
ዙሪያችን እንዲህ የሆነውና ቅጥ አምባሩ የጠፋው በትናንት ታሪካችን አይደለም እንዴ? እንዲህም እንዲያም ሆኖ  ደቁሶን ያለፈው ታሪካችን እንዴት ሆኖ ነው “ብዥታ” የሚሆነው? (Illusion የሚባለው?) አጣምመንና አወላግደን የሰማናቸው ታሪኮቻችን፣ ተደልዘውና ተቆራርጠው የተነገሩን ትናንቶቻችን እንዲህ ስላወላገዱን መስሎኝ ዛሬያችን እንዲህ የሆነው? እና እንዴት ሆኖ በምን ሒሳብ ነው ትናንት እንዲህ አፍጥጦብን ዛሬ ላይ እያየነው፣ ትናንት Illusion የሚሆነው ? በተለይ ለታሪከኛው ለሃበሻ?
ዛሬ የምንኖረው ትናንትን አይደለም እንዴ? እሺ ይባል? ትናንት የጫነብን ሸክም ዛሬ ላይ አጉብጦን ነገን መቅረጽና ማበጀት ተስኖን፣ ከቁጥጥራችን ወጥቶ የነገን ፍርሃት ዛሬ ተበድረን እየኖርነው አይደለም እንዴ? ለነገ ጭለማ ዛሬ እየቆዘምን  አይደለም እንዴ?  እህ…..እናስ?
ትናንት፣ ዛሬ፣ ነገ እውንና ተጨባጭ አልሆኑም? በተለይ ለእኛ ለታሪከኞቹና ለተስፈኞቹ ሃበሾች በደንብ አልተሰናሠሉም? እና ነገ ተጨባጭና እውን አልሆነም፤ ዛሬ ላይ አልተኖረም?፡፡ ከዛስ ከተጨባጭ ተሞክሯችንም እያጣቀስን፣ ይሄን እድሜ ጠገብ ፍልስፍና ተብዬ ውድቅ አላደረግነውም?  
ቁጣ ቁጣ ያለኝ ለምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ምናልባት ዛሬ ላይ አሳርና ፍዳ የሚያሳዩን ትናንት እና ነገ እንደ ተራ ነገር Ilussion የመባላቸው ተራ ፍልስፍና፣ ይሄንን ያህል ዘመን ገንኖ መኖሩ፣ በተለይ እኛን  ሃበሾችን ያላገናዘበ ተራ ፍልስፍና ይሄንን ያህል ዘመን ገንኖ መኖሩ፣ አበሳጭቶኝ ይሆናል፡፡ ለነገሩ ከፈላስፋቸው አንዱ፤ “ሐበሾች ከአለም ታሪክ ተገልለው አለምን እረስተው፤ አለምም እረስቷቸው የኖሩ ሕዝቦች” ብሎ ደፍይኖን የለ፡፡
(“ድፍየና” የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ቃል ሲሆን Definition የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ይተካል፤ ስለተመቸኝ ተውሼዋለሁ፡፡ ቆይ እዚህ ጋ ግን የ Definition ጽንሰ ሃሳብ በጥንታዊው አማርኛችን ውስጥ የለም ማለት ነው እንዴ? ወደ ቃል ብድር የሄድነው?)።
እንቀጥል፤ እናም ምን ለማለት ፈልጌ ነው… ፍልስፍናዎችን ሁሉ አንመን፤ ዝግ እና ቀስ ብለን መፍትሄ ያዘለ የገዛ እራሳችንን ፍልስፍና እናምጣ ፤እንደዚህ እንደ ላይኛው አይነት ባህልና እኛነታችንን ያላገናዘበ ፍልስፍና እንደወረደ አንጠጣ፤ ልምድና እውቀት መለዋወጥ ያባት ቢሆንም እንዲያው  ዝም ብለን ያገኘነውን ሳናላምጥ እንዋጥ፤ አንሰልቅጥ ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ ለምሳሌ ቢፒአሩም፣ ካይዘኑም፣ እና ሌሎችም ፍልስፍናዎች ጊዜ ተወስዶባቸው፤ ቀስ ተብለው ይታሹ፤በእኛው ልክ ይሰፉ፤ እንደወረዱ ተግተናቸው ሲያቅሩንና በቅጡ ሳንረዳቸው ወደ ሌላ ፍልስፍና፣ ወደ ሌላ ቃር እንዘላለን፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ እንደቅድሙ ፍልስፍና በስሱ አበሳጭተውን ብቻ ሳይሆን አበላሽተውን ስለሚያልፉ፡፡
እውነት ነው ነገን አልያዝነውም፤ወላፈኑና ጫናው ዛሬ ቢገርፈንም ፤ ትናንት የማይታረም፤ ያከተመለት፤ በነሲብ የሚጠበቅ፣ በ “ያመጣ ያምጣው” ፤ በአቦ ሰጡኝ የሚናፈቅ አይደለም፡፡ እንዲያውም የዛሬ ልፋትና መከራችን  እኮ ለተሻለ ነገ አይደል? ነገ ሕልም አይደለም ፤ነገ በመዳፋችን ላይ ነው፤ ነገን ዛሬ የምንሰራው፤ ዛሬ የምናበጀው፤ እንደወደድን የምንቀርፀው በእጃችን ያለ ሸክላ ነው፡፡(ያው መቶ በመቶ በቁጥጥር ስር እናውለዋለን!! ማለቴ ግን አይደለም ይቅር ይበለኝ እና)፡፡ እንዲያውም
ነገ ከቁጥጥሩ የወጣ ግለሰብ ለሱሳይድ
ነገ ከቁጥጥሩ የወጣ ሕብረተሰብ ለጄኖሳይድ የተጋለጡና የተመቻቹ ናቸው (ሳላውቀው አሪፍ ግጥም ሆነ) ፡፡
እና ምን እናድርግ ? (ምን ተሻለ?)
እንደኔ እንደኔ አሁንም ወደ ውስጥ እንመልከት ባይ ነኝ፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን “ለተሻለ ነገ ምን ብናደርግ ይበጃል?” ብለን “አንጐግል”  ጉግል ፍጹም አያውቀንም፡፡
እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን የገዛ ብልሹና ኃላፊነት በጐደለው መልኩ በተነገሩ ፤ተጨባጭነት በሌላቸውና በሳይንስ በማይደገፉ ታሪኮቻችን ሠለባዎች ነን፤ አራት ነጥብ።
በድብቅ አጀንዳ ታጅለውና በወገናዊነት ተጠርዘው፤ በተንኮልና ሆን ተብሎ ተጣምመው በሸር የተነገሩ አብዛኞቹ ታሪኮቻችን፤ የፈጠሩብን ጫና እና ያልተመለሰ (ምናልባትም ሊመለስ የማይችል) የማንነት ጥያቄ ብዥታ የፈጠረብን ሳንካ ዛሬን በግራ መጋባት እያኖረን ነው፡፡
የ“ከየት መጣሁ?” የ“ማን ምኔ ነው?” የ“ይህ ቦታ የማን ነው?” ውስብስብ ጥያቄ ሰርተን የማንጨርሰውን የቤት ስራ ዛሬ ላይ አሸክሞናል (እኛ ደግሞ ጥሎብን ታሪክ እንወዳለን) እናም በዚህ ጥልፍልፍ ማለቂያ አልባ ከባድ ጥያቄ ዛሬ ላይ ተወጥረን ማን ለነገ ይስራልን? ይባስ ብሎ ክፋቱ የ3 ሺህ ዘመን ባለታሪኮች መሆናችን ፤ታሪክን ፍለጋ 3ሺህ አመት የኋሊት መስፈንጠራችን፡፡ ነገን እንዴት እናብጅ? በየትኛው ጊዜ? የጊዜ መርከብ እያዳፋ ወዳሻው እንዲወስደን ፈቅደን መሪውን ሰጠነው፡፡ እናም ወደ አላበጀነው እና ወደማናውቀው ነገ እያጻፉ ይወስደናል፡፡ የነገ ፍርሃት ክፉኛ ያሳስበናል፤ ፈጥነን ካልነቃን ያው ቅድም እንደተጨዋወትነው የጊዜ መርከብ ጎትቶ ወይ ሱሳይድ፤አልያም ጄኖሳይድ ደሴት ላይ ይጥለናል፡፡ (የሰይጣን ጆሮ ይደፈን)፡፡
ስለዚህ እስቲ እንዲህ ባተሌ ያደረገንን ታሪካችንን እንመርምር፡፡ ለመሆኑ ታሪክስ ተጨባጭ  ተአማኒና ሳይንሳዊ ሊሆን ይችላል እንዴ? በተለይ የእኛው ጉራማይሌና ውንግርግር የታሪክ ነገራ ተጨባጭ (Objective)፤ ተአማኒ (Reliable) እና በተለይ ሳይንሳዊስ ነው ወይ?  እስቲ አንድ ቀላል ሙከራ እንስራ አንድ ቀላል ቀመር እንቀምር፡፡
እንጀምር ፡፡ የታሪክ ባለሙያ  አይደለሁም፤ የታሪክ ሰለባ እንጂ፡፡ ሙያዬ የነገሮችን እንቅስቃሴ፤ ባህርይና የእርስ በርስ መስተጋብር ተጨባጭና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዳይና እንድተነትን ያግዘኛል፡፡
ለምሳሌ ሀ=ለ, ለ=ሐ ስለዚህ ሀ=ሐ አይነት ማንም ማንበብ እና መጻፍ የሚችል ፍጡር የሚስማማበት ተጨባጭ የእውነታ (logic) እና የሙግት አካሄድ ነገሮች ሁሉ ሊዳኙ ይገባል ባይ ነኝ፤ ታሪክም ጭምር።
ይሄም ማለት፤የተፈጥሮ ሳይንስ አንድን ቀመር (Formula) ለመቀመር የሚከተላቸውን ሳይንሳዊ አካሄዶችና ሊካተቱ የሚገባቸውን ወሳኝ ግብአቶች (Parameters) መምረጥ፣ ከዛም የነዚህን ግብአቶች የእርስ በርስ መስተጋብር ከባህሪያቸው አንፃር በማጥናት እርስ በርስ ማሰናኘት ነው፡፡
በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በዚህ አካሄድ የሚጠኑት ግብአቶች (Parameters) የባህሪያቸው ወጥ መሆን እና ምናልባትም ውስኑነት የመቀመሩን ሂደት በተነፃፃሪ ቀላል ፤ውጤቱንም ተአማኒ አድርጐት ሊሆን ይችላል፡፡ በተቃራኒው የማህበረሰብ ሳይንስ እንዲህ ወደ ኋላ መቅረቱና ሊሰጠን ይገባው ከነበረው ጥቅም ኢምንት አለማበርከቱ፤ ከማህበረሰብ ጀርባ ያሉ ወሳኝ ግብአቶችን ከየማህበረሰቡ ባህርይ አንፃር ተንትኖና ወስኖ በወጥነት ማስቀመጥ ያለመቻሉ ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ፡-  የአንድ ማህበረሰብ ውልደት፣ እድገትና ጥፋት ከማህበረሰቡ ወግ፣ ልማድ ባህርይ፣ እምነት፡ አየር ንብረት፣ የቦታ አቀማመጥ ወዘተ አንፃር ተፈትሸው በዚህ ቀን እንዲህ ይሆናል፡፡ በዚህ ቀን ደግሞ እንዲህ ሆኖ ነበር፡፡ እንዲህ ካልሠራን ይህ ይመጣብናል፡፡ አይነት ሳይንሳዊና ተጨባጭ ትንተናዎች እና ትንበያዎች መኖር የለባቸውም?። በአንድ ማህበረሰባዊ ጉዳይ ላይ አስር የታሪክና የማህበረሰብ ሳይንስ ተንታኞች አስር አይነት መላምት፣ አስር አይነት ግምት ከሰጡ ይሄ ነሲብ እንጂ ምኑን ሳይንስ ሆነው? ታሪክ ተጨባጭ እና ሳይንሳዊ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ እንደኛ አይነቱ የታሪክ ጥገኛ የሆነ እና ከታሪክ ድርና ማግ የተሸመነ ማህበረሰብ፤ በነሲብና በመሠለኝ ጉንጭ አልፋ ክርክር ተተብትቦ  ውሃ በላው ማለት አይደለም?
እስቲ አንድ ቀላል ሙከራ እንስራ
በዚህ ሙከራ እንዲህ የወዘወዘንንና የ3ሺህ ዘመን (3 ሺህ የሚለው እራሱ አከራካሪ ነው መሰለኝ) የሰጠንን ታሪካችንን ተጨባጭነትና ተአማኒነት በተፈጥሮ ሳይንስ ምክንያታዊ አካሄድ እየፈተሽን አንድ ሒሳባዊ ቀመር እንቀምር እና ጉዳችንን እንመልከት፡፡
(ይህን አካሄድ እና  የሙግት ዘይቤ ከዚህ ቀደም “ሙስና ሙሶሎጂ እና ሙሶሜትሪ” በሚለው የሙስናን እና የማህበረሰብን ግንኙነት በሚተነትነው ጽሁፌ ተጠቅሜበታለሁ፤ ተቃዋሚ ስላልመጣ እግረ መንገዴን ባለቤትነቴ ይታወቅልኝ፤ ያው ለታሪክም ይቀመጥልኝ)፡፡
የታሪክ አዘጋገብና የታሪክ ነገራ (Reconstruction of history) እጅግ በሚበዙ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተና በብዙ ማህበረሰባዊ ቁሳዊ ጉዳዮች ተጽእኖ ውስጥ የወደቀ ዘርፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አጭርና ግልብ ዳሰሳ ውስጥ ሁሉንም ግብአቶች (parameters) ማካተት የማይሞከር ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ነው፡፡ ስለዚህ ጉልህና ከባድ ተጽእኖ አላቸው ብለን ያሰብናቸውንና እኛው ሐገር አሉ ብለን ያመንንባቸውን ግብአቶች ብቻ ተጠቅመን ሃሳባዊና ሐገራዊ ቀመራችንን እንቀምር ፡፡
ዋና ዋናዎቹ ግብአቶች (parameters) እነማን ናቸው?
የመጀመሪያው እና ዋናው ግብአት እራሱ ታሪክ ነው፡፡ (H) ብለን እንሰይመው፡፡ የታሪክን (H) ተአማኒነት በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ የሚጫኑ ግብአቶችን ደግሞ  ቀጥለን እንዘርዝር። ከዛም ከታሪክ ጋር ያላቸውን መስተጋብር (Relation) ደግሞ እንመርምር፡፡
1-ጊዜ (time) (T)

ጊዜ (T) እና የጊዜ እርዝማኔ ከታሪክ (H)ተአማኒነት ጋር የተገላቢጦሽ ዝምድና አላቸው፡፡ ይህም ማለት፤ ታሪኩ የተፈፀመበትን ጊዜ (T1) እና የአሁን ጊዜን (T2) ብንላቸው የጊዜ እርዝማኔ (T)  ማለትም (T2-T1) በተለቀ ቁጥር ታሪኩ ይርቃል፤ በታሪኩ ላይ ያለን ተአማኒነትም እየደበዘዘ ይሄዳል። ስለዚህ የመጀመሪያው ቀመር ታሪክንና ጊዜን እንዲህ ያጣምራቸዋል ይሄንንም ቀመር (Formula) 1 እንበለው፡፡
--------1
2-የታሪክ ዘጋቢው ወገንተኝነት ደረጃ  (P)  
ይሄ ግብአት ወሳኝ እና በተለይ በኛ ታሪክ ላይ ጽኑ አሉታዊ ጫናን ያመጣ ግብአት ነው፡፡ የዘጋቢው የነፃነትና የወገንተኝነት ደረጃ በታሪኩ ተአማኒነት ላይ በተለያየ መጠን አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል። ከሰብአዊ አመለካከት አንፃር ስናየው ደረጃው ይለያይ እንጂ ማንም ዘጋቢ ከወገንተኝነት ሊፀዳ እንደማይችል እርግጥ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክ (H) እና የዘጋቢው ወገንተኝነት ተገላቢጦሽ ዝምድና አላቸው፡፡ ሁለት እንበል፡፡
--------2
3-የተጨባጭ መረጃ (ሰነድ) (D) መኖር
ሰነድ ወሳኝ እና እጅግ ጠቃሚ ግብአት ነው (ካልተደለዘ)፡፡ ስለዚህ የተረጋገጠ የጽሁፍና ሌላ ቋሚ የቁሳቁስ ሰነድ (D) እና ታሪክ (H) የመሳ ለመሳ ግንኙነት አላቸው፡፡ ይህም ማለት እውነተኛና ሳይንሳዊ ሠነድ የቀረበለት ታሪክ፤ ለእውነታ የቀረበ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ቀጣዩ 3ኛ ቀመር ይፈጠራል፡፡

   ----------3         
እዚህ ላይ የታሪክን እውነተኛነት ለማጉላት ሆን ተበለው መረጃዎች ሊሰረዙና ሊደለዙ ስለሚችሉ ይህ ጉዳይ ከግምት ውስጥ መግባትና በከባድ ጥርጣሬ ሊታይ ይገባዋል፡፡ (ለነገሩ ደሞ ለመጠርጠር ከኛ በላይ ላሳር) ፡፡
4-የወቅቱ፤ የታሪክ ተቀባይ ማህበረሰብ የመረዳትና የማመዛዘን ደረጃ (I)
ይሄ ግብአት የኛው ጉድ ነው (I) ብለን እንሰይመው፡፡ ይህ ግብአት ማህበረሰባችን ከየትም አቅጣጫና ምንም አይነት የተነገሩ፣ የተፃፉ ታሪኮችን አሜን ብሎ የመቀበል አልያም በትእግስት የመመርመርን ሁኔታ፣ አዝማሚያና ዝንባሌ የሚያሳየን ነው፡፡ ይሄም ማለት አንድ መርማሪና ጠያቂ ማህበረሰብ ያፀደቀውና ያመነው ታሪክ፤ ወደ እውነታ የመጠጋቱ መጠን ከፍ ያለ ነው፤ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከታሪክ ዘገባ ጋር የመሳ ለመሳ ግንኙነት አለው ማለት ነው፡፡ አራት አትሉም፡፡
         ----------4
5-የመለኮት ጣልቃ ገብነት (Devine intervention) (R)
ይህ ግብአት ለእኛ  ለሃበሾች እንግዳ አይደለም። አብዛኞቹ ማጣቀሻዎቻችን በተለይም በእድሜ ሰንበትበት ያሉን የመለኮት ባህርይ የማላበስ ዘይቤ ተጠናውቶናል፡፡
ከተጨባጭ ምክንያታዊነት የራቁ መለኮታዊ ማስረጃዎች ታሪክን የማጣመምና እውነትን የመጋረድ አቅማቸው እጅግ ከባድ በመሆኑ፣ ከታሪክ ጋር ከባድ የተገላቢጦሽ ዝምድና አላቸው፡፡ ስለዚህ ታሪክ የማናወጥ ከባድነታቸውን በማገናዘብ  ከታሪክ ጋር እንዲህ ሊሠናኙ ይችላሉ፡፡
              
  -----------------5
ይህ ማለት እያንዳንዱ ማስረጃ የመለኮታዊ (supernatural) ባህርይ እጅግ የተጋነነና  አብዝቶ የተዛባ የእውነታ ጥመት ያስከትላል ማለት ነው፡

እነዚህ ግብአቶች በግርድፉ የተመረጡ እና ዋና ዋና የተባሉ ናቸው ተብለው የታመነባቸው ናቸው (በእኔ)፡፡፡
 በተለይም የገዛ ታሪካችንን ለመመርመር ታስበው ከሕብረተሰባችን ባህርይና ካለን ልምድ ተጨምቀው የወጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ግብአቶች ከታሪክ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከተቀመሩት 5 ቀመሮች በመነሳት አንድ ወጥ ቀመር ስንቀምር እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
  (ኒውክሊየር ፊዚክስ አስመሰልነው አይደል?)
ቀለል አድርገን እንየው፡፡ የግብአቶቹን ባህርይና ግብአቶቹ  ከታሪክ ጋር ያላቸው ተዛምዶ  ቀላልና የሚያግባባን ስለሆነ የግብአቶቹን ባህሪ በተጨባጭ ምክንያቶች እየፈተሽን የቀመራችንን ውጤት እንመልከት፤ ታሪካችንን እንሞግት፤ ከዛም ወይ ተጨባጭና እውነተኛ ታሪክ የሚዘገብበትን ሳይንሳዊ አካሄድ እንምረጥ (እንቀምር) አለበለዚያ የከበበንን የታሪክ ጥልፍልፍ እርግፍ አድርገን ትተን፣ ነገን አብረን እንገንባ፡፡ (እዚህ ጋ ኑ…… አብረን እንገንባ…… የሚለው ዘፈን ትዝ አለኝ) ቻው፡፡

Read 3858 times