Sunday, 16 July 2017 00:00

የቴክኖሎጂ ግስጋሴ - በጎንደር ዩኒቨርሲቲ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“መንግስት የእንቦጭን ጉዳይ እንደ ብሄራዊ አጀንዳ ቢይዘው ጥሩ ነው”
ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ 11 ቴክኖሎጂዎችን አስተዋውቋል
በአገሪቱ ግዙፍ የምርምር ማዕከል እያስገነባ ነው

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 6536 ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ያስመረቀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ ቀዳሚ ነው የተባለ የቴክኖሎጂ ምርምርና ፈጠራ ማዕከል ግንባታም እየተጠናቀቀ ነው ተብሏል፡፡ ዘንድሮ 11 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያስተዋወቀው ዩኒቨርሲቲው፤ ስድስቱን በቀጥታ
ለተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶች አስተላልፏል፡፡ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ፕሮጀክቶችንም ተወዳድሮ በማሸነፍ እየሰራ እንደሚገኝ
የጠቆመ ሲሆን በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጤና ተቋማት የመረጃ አያያዝን ለማዘመን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የ3.5 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት መፈጸሙን አመልክቷል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የሚከበር ግዙፍ የትምህርት ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ባደረገው እንቅስቃሴ፣ ለከተማዋ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የ16 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በነዋሪው ዘንድከፍተኛ ተወዳጅነትን ላተረፈው ፋሲል ከነማ (አፄዎቹ) የስፖርት ክለብም የ4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ለከተማው ነዋሪዎች ያስገነባው ግዙፍ የሪፈራልሆስፒታልም ከዩኒቨርሲቲው ሰናይ ተግባራት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፓርትመንት በበኩሉ፤ በእንቦጭ አረም ከፍተኛ የመድረቅ ስጋት የተጋረጠበትን የጣና ኃይቅን
ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተርና የመካኒካል ኢንጅነሪንግ መምህር አቶ ሰለሞን መስፍን፤እንቦጭ አረምን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረትና በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡


 እንቦጭ አረምን ለማጥፋት እያደረጋችሁት ካለው ጥረት እንጀምር----
በጣና ላይ የተከሰተውን እንቦጭ አረም፣ በሰው ኃይል በእጅ ለማንሳት መሞከር የማይቻል ነው። የግዴታ ማሽን ያስፈልጋል፡፡ በቪክቶሪያ ኃይቅ ላይ ተከስቶ የነበረን እንቦጭ አረም ለማንሳት ጥቅም ላይ የዋለው ማሽን ነው፡፡ ከተንሳፋፊ ጀልባ ጋር ተገጣጥሞ የሚሰራ ማሽን ነው አረሙን ሊያነሳ የሚችለው፡፡ የጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተውን ይህን አረም ለማንሳትም  በራሳችን ተነሳሽነት፣ በዩኒቨርሲቲው የምህንድስና ክፍል ውስጥ አንዱን ማሽን ገጣጥመን እያጠናቀቅን ነው፡፡ ለዚሁ አረም ማጥፊያነት ብቻ ነው ይህ ማሽን የተሰራው፡፡
ማሽኑ እንዴት ነው አረሙን ለማጥፋት ጥቅም ላይ የሚውለው?
ከፊት ባለው (አካፋ መሰል) አካሉ ተንሳፋፊውን አረም እየጎተተ፣ ወደ ውስጥ በመቀረጣጠፍ ያስገባዋል፡፡ መሃል ላይ ባለው የማሽኑ ክፍል ደግሞ አረሙ ይፈጫል፣ የተፈጨው ተመልሶ ውሃው ላይ አይጣልም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ አረሙ በስሩም፣ በግንዱም የመራባት አቅም ስላለው፣ በቋት ተጠራቅሞ ከኃይቁ አካባቢ በራቀ ቦታ ላይ ይጣላል፡፡ በሌላው ሀገር መሰል አረምን ለማጥፋት ስራ ላይ የሚውሉ ማሽኖች፤ የተፈጨውን  አረም የማጠራቀሚያ የራሳቸው ቋት የላቸውም፡፡ ወደ ሌላ ጀልባ በመገልበጥ ነው የሚያጠራቅሙት፡፡ እኛ ግን ማሽኑ የራሱ ቋት እንዲኖረው አድርገን ነው የሰራነው፡፡
የዚህ አረም የጉዳት መጠን እንዴት ይገለጻል?
 አረሙ በባህሪው ከመሬት ጋር የሚገናኝ ስር የለውም፤ ዝም ብሎ ውሃው ላይ ነው እየተራባ የሚንሳፈፈው፡፡ በዚህ ሂደት ውሃውን እየመጠጠው በማድረቅ፣ ደረቅ መሬት እየፈጠረ ይሄዳል፡፡ በአሁን ወቅት የሃይቁን ዳርቻ ብንመለከት፣ በዚህ መንገድ አረሙ መሬት ፈጥሯል፡፡ አረሙ በባህሪው ውሃ ይወዳል፡፡ ውሃውን ደግሞ ቀድሞ ከነበረው ሦስት እጥፍ ነው የትነት መጠኑን የሚያሳድገው፡፡ ለዚያም ነው ሃይቆችን ሙሉ ለሙሉ የሚያደርቀው፡፡ ለምሳሌ ከአፍሪካ ታላላቅ ወንዞች አንዱ በሆነው ዛምቤዚ ወንዝ ላይ የተፈጠረው እንቦጭ አረም፣ የኃይል ማመንጫ ኃይሎች ሁሉ እንዲዘጉና እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡ ለኛም የህዳሴ ግድብ ይሄ አረም ትልቅ ስጋት ነው፡፡ ምክንያቱም በቀላሉ እየተንሳፈፈ ከዚህ ወደ ግድቡ መሄድ የሚችል ነው፡፡ ወደፊት ፕሮጀክቱ ሲጀምር ፈተና ነው የሚሆንበት፡፡
አረሙ የጤና ችግርም ያመጣል፡፡ በባህር ትራንስፖርት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ የዓሳ ሀብት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ዓሳዎች እንዳይራቡ ያደርጋል፡፡ የኦክስጅን ዝውውሩን ስለሚገታ መራባት አይችሉም፡፡ ለዓሣ አጥማጆችም ፈተና ነው የሚሆንባቸው፤ መረባቸውን መዘርጋት አይችሉም፡፡
አረሙ ከስሩ ሊጠፋ የሚችለው ምን ቢደረግ ነው?
አረሙን ማጥፋት አይቻልም፤ እንዳይስፋፋ ማድረግ ነው የሚቻለው፡፡ እኛ በሰራናቸው ማሽኖች ነው አረሙን መግታት የሚቻለው፡፡ እኛ የሰራነው አንድ ማሽን ነው፤ ነገር ግን አሁን በጎንደር አዋሳኝ ብቻ የተከሰተውን አረም ለማስወገድ ተመሳሳይ ስድስትና ሰባት ያህል ማሽኖች ያስፈልጋሉ። ምናልባት በባይሎጂካል መንገድ አረሙን የሚመገቡ ጢንዚዛዎችን በማምጣት በረዥም ጊዜ መስፋፋቱን መቀነስ ይቻል ይሆናል፤ ግን ይሄ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የኛ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶ/ር ሳሙኤልም በፈንገስ አረሙን መቋቋም የሚችል ንጥረ ነገር ለማዘጋጀት ሞክሯል፡፡ እነዚህ ምርምሮች በላብራቶሪ ሙከራ ደረጃ ውጤታማ ናቸው፡፡ ነገር ግን በመስክ ላይ በሚገባ መሞከር ያስፈልጋል። ሌሎች ሀገሮች ኬሚካልም ይጠቀማሉ፡፡ የኛ ግን ሃይቅ እንደመሆኑም ብዝሃ ህይወትን ስለሚጎዳ ኬሚካል መጠቀም አይቻልም፡፡
ግን አረሙ ከየት ነው የመጣው?
 አመጣጡ ላይ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ምክንያት እስካሁን አልቀረበም፡፡ መጀመሪያ የታየው መገጭ ወንዝ ላይ ነው፡፡ ግን ወደ ሀገር ውስጥ እንዴት እንደመጣ አይታወቅም፡፡ በእርግጥ ከኛ ቀድሞ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ በተለይ በቪክቶሪያ ሃይቅ ባለቤት ሀገሮች ነው የገባው፡፡ ግን ወደኛ ሀገር እንዴት እንደመጣ አይታወቅም፡፡ አንዳንዴ ከከተማ የሚመጡ ፍሳሾች እንዲህ አይነቱን አረም የመፍጠር እድል አላቸው፡፡ ከጎንደርም ሆነ ከሌሎች ከተሞች የሚለቀቁ ፍሳሾች ከጣና ሃይቅ ጋር መገናኘት የለባቸውም፡፡ ግን መነሻው ይሄ ፍሳሽ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ጥናትና ምርምሮች መካሄድ አለባቸው። በዋናነት የአረሙ መነሻ ደቡብ አሜሪካ ነው፡፡ አረሙ አበባ ያወጣል፡፡ በደቡብ አሜሪካ ይሄን አበባ ለቤት ማስዋቢያና ጌጣጌጥ ይጠቀሙበት ነበር። አሁን ይሄ አረም በዓለም ላይ ካሉ አስር አስከፊ አረሞች አንዱ ነው፡፡
በጣና ላይ የተከሰተው አረም በፈረንጆቹ 2014/15፣ 44 ሺህ ሄክታር መሸፈኑን የሚያመለክት መረጃ አለኝ፡፡ አረሙ ደግሞ ከ12 እስከ 18 ቀናት ውስጥ ራሱን በእጥፍ የማባዛት ባህሪ አለው፡፡ ይሄ በጣም አደገኛ ባህሪው ነው፡፡ እኛ ሀገርም ሆነ ሌሎች ሀገሮች ላይ ይሄ አረም ሃይቆችን አድርቋል። ጣና ላይም ይሄ የማይደገምበት ምንም ምክንያት የለም። ይሄን ጉዳይ ቢቻል መንግስት እንደ ብሔራዊ አጀንዳ ቢይዘው ጥሩ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውና ጥቂት የመንግስት አካላት ብቻቸውን ሊወጡት አይችሉም። ሌላ የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይሄን ጉዳይ የሚከታተል አካል በመንግስት ተቋቁሞ ቢሠራ መልካም ነው፡፡
የሰራችሁት ማሽን ምን ያህል አረም በቀን ያፀዳል?
 በሰዓት እስከ 5 ቶን ማስወገድ የሚችል ነው። አረሙ ውሃ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ማሽኑ ውሃውን እየጨመቀ ነው የሚፈጨው፡፡ ይሄን ማሽን የሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎችም አሉን፡፡ ሐምሌ መጨረሻ ላይ ማሽኑ ወደ ሀይቁ ተወስዶ ይሞከራል፡፡ ወደ ስራም ይገባል፡፡ ተጨማሪ ማሽን ይመረት ከተባለም ጨምረን እናመርታለን፡፡ አረሙን ለማጥፋት በሰው ኃይል ቢሞከር ውጤቱ እምብዛም ነው፡፡ አወጋገዱም አስተማማኝ አይደለም፡፡ አረሙ መልሶ ችግር እንዳይፈጥር በአግባቡ መወገድ አለበት፡፡
ታዲያ የተፈጨው አረም ሲጣል መልሶ ችግር አይፈጥርም?
የተለያዩ ሀገሮች ይሄን አረም ከሀይቁ ወይም ከውሃ አካሉ ካስወገዱት በኋላ ለተለያየ ነገር ይጠቀሙበታል፡፡ ከአረሙ ባዮጋዝ፣ ሜቴን ጋዝ ማግኘት ይቻላል፡፡ ከአረሙ ከሰልን ተክቶ ሊነድ የሚችል ብሪኬት መስራት ይቻላል፡፡ ኬንያዎች በቅርቡ ለዱባይ ማዳበሪያ ፋብሪካ ኤክስፖርት አድርገዋል፡፡ ለማዳበሪያ ምርት ይሆናል፡፡ ኬንያዎች ከኩባንያው ጋር ውል ገብተው፣ እየፈጩ ኤክስፖርት በማድረግ ገቢ እያገኙበት ነው፡፡ ቡና እና ሻይ ኤክስፖርት አድርገው ካገኙት ገቢ በላይ ከዚህ አረም አግኝተዋል፡፡ ለዚህ ነው መንግስት በዚህ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አለበት የምለው፡፡ በቅርቡ አስራ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ነው ከውጭ ያስገባነው፡፡ ይሄን ከሸጠልን ኩባንያ ጋር ለምን አረሙን ለመሸጥ አንዋዋልም? ይሄን መንግስት ማሰብ አለበት፡፡ ትልቁ ነገር ይሄን አረም ማስወገድ ቢሆንም የተወገደውን በዚህ መልኩ ለሀገር ጥቅም ማዋል ይቻላል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ምርምሮችና ፈጠራዎች ላይ እየተሳተፈ ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?
በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 38 የሚደርሱ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ተመርተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አዳዲስ ፈጠራዎችም አሉን፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች እኛ ጋር መቅረት የለባቸውም፤ ስራ ላይ መዋል አለባቸው የሚል እቅድ ይዘን ወደተጠቃሚዎችም እያደረስን ነው፡፡ በቅርቡ አራት የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ወደ ተጠቃሚዎች አድርሰናል፡፡ ለምሳሌ በቱሪዝም ጉዳይ የጀርመንና የአማርኛ ቋንቋ መተግበሪያ (Application) ሰርተናል፡፡ በተለይ ለአስጎብኚዎች ይሄ መተግበሪያ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ በአንድሮይድ ስልኮች ላይ በቀላሉ የሚጫን፤ ጀርመንኛን ወደ አማርኛ፣ አማርኛን ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ የሚቀይር መተግበሪያ ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን ለአስጎብኚዎች፣ ለዞኑ ቱሪዝም መምሪያ አስረክበናል፡፡ ሌላው የሰሜን ጎንደርና የደቡብ ጎንደርን የጉብኝት ቦታዎችና አንዳንድ ሆቴሎችን መገኛ የያዘ ዲጂታል ካርታ አዘጋጅተን አስረክበናል፡፡ ይህ ካርታ በህትመትም ይገኛል፡፡
የጎንደር፣ ላሊበላና አክሱምን የሚያገናኝ ካርታም በኛ የጂአይኤስ ባለሙያዎች ተሰርቷል፡፡ ይሄ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ከማስተዋወቅ አንፃር ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቱሪስቶች፤ ያለ ሰው እርዳታ ህንፃዎችን፣ ቤቶችን፣ ሆቴሎችን በአጠቃላይ የሚፈልጓቸውን ቦታዎች በቀላሉ ማግኘት የሚያስችላቸው የአሰሳ (Navigation) መተግበሪያ፣ የኛ ተማሪዎች ሰርተው ለጎንደር ከተማ አስተዳደር አስረክበናል፡፡
በፀሐይ ኃይል ብቻ የሚሰሩ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችንም ሰርተናል፡፡ በባዮ ጋዝና በሜቴን የሚነዳ መኪና ሰርተናል፡፡ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎቹ አሁን ሙከራቸው ተጠናቆ፣በኩባንያ ደረጃ መመረት ነው የሚቀራቸው፡፡ የሚያመርቱ ኩባንያዎች መፈጠር አለባቸው፡፡ እነዚህ ከመጡ እኛ ቴክኖሎጂውን ለማካፈል  ዝግጁ ነን፡፡ እኛም ራሳችን ይሄን የሚያመርት ኩባንያ መፍጠር አለብን፡፡ ሌላኛው ለተጠቃሚዎች ያደረስነው ቴክኖሎጂያችን፣ የላፕቶፕ ባትሪን የተመለከተ ነው። ብዙ ጊዜ የላፕቶፕ ባትሪ ውድ ከመሆኑም በላይ ሲያረጅ ያለው አማራጭ መጣል ብቻ ነው፡፡ እኛ ግን አያገለግልም የተባለውን ባትሪ በቀላሉ እየሞላን ወደ አገልግሎት መመለስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው የፈጠርነው፡፡ ለወደፊት እዚሁ ማምረት የሚቻልበት ሁኔታም እየተሰራ ነው፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ ዘንድሮ የ106 የዩኒቨርሲቲው መምህራንን ላፕቶፖች ባትሪ ሞልተናል፡፡ የዚህ ፈጠራ ባለቤት ዩኒቨርሲቲውና የሰሩት ግለሰቦች ናቸው፡፡
ቴክኖሎጂውን ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ላሉ ተጠቃሚዎች እንዴት ልታደርሱ አስባችኋል?
 ለህብረተሰቡ ማድረስ ጀምረናል፡፡ በጎንደር ከተማ የሚገኙ 20 ሥራ አጥ ወጣቶችንና ከዞኑም ወደ 28 ሥራ አጥ ወጣቶች፣ በድምሩ 48 ሥራ አጥ ወጣቶችን አሰልጥነን ወደ ስራ እንዲገቡ አድርገናል። ጎንደር ከተማ ላይ በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ያረጁ የላፕቶፕ ባትሪዎችን የሚሞሉ ወጣቶች አሉ። አንድ ባትሪ ከ1400 ብር በላይ ነው የሚሸጠው፡፡ ወጣቶቹ ግን በ500 ብር ነባሩን አዲስ አድርገው፣ ደንበኛው መልሶ እንዲጠቀምበት እያደረጉ ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ይውላል ተብሎ የሚታሰበውን የንፋስ ሀይል፣ ለከርሰ ምድር ውሃ ማውጫነት የሚያውል ቴክኖሎጂ አዘጋጅተናል፡፡ ሰሜን ደባርቅና ዳባት አካባቢ ከፍተኛ የንፋስ ፍጥነት አለ፡፡ አምባጊዮርጊስ አካባቢ በንፋስ ኃይል የሚሰራና 120 ሜትር ጥልቀት ውስጥ ያለን ውሃ ወደ ገፀ ምድር የሚያፈስ ፓምፕ ሰርተናል፡፡ እሱን በቅርቡ እናስመርቃለን፡፡ ይህ ከከርሰ ምድር የወጣ ውሃ ንፁህ ስለሆነ ለመጠጥም ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ለመፍጠሪያነት ይውላል፡፡
እኛም ለመስኖ ልማት የሚውል ሃይቅ ለመፍጠር አቅደን፣ ገበሬዎች የሚበዙበትን አካባቢ መርጠን ነው ፓምፑን የተከልነው፡፡ ውሃውን ለመስኖ እንዲጠቀሙ አቅደን ነው ይሄን ያደረግነው። ሁሉንም መጥቀስ ጊዜ ይወስዳል እንጂ እንደዚህ ያሉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺ 38 የቴክኖሎጂ ሽግግሮችና ፈጠራዎችን አዘጋጅተናል፡፡
የ3D ማተሚያ ማሽን፣ ዶክመንቶችን የማጠራቀሚያ አፕሊኬሽን፣ የፍ/ቤት ጉዳዮችን መከታተያ መተግበሪያ አፕሊኬሽን ሰርተናል፡፡ የፍ/ቤት መከታተያ መተግበሪያው በተለይ የሀገራችንን የፍ/ቤት አሰራር ለማዘመን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ባለጉዳዮች በቀጥታ ቀጠሮአቸውን እንዲከታተሉ ከማድረጉም ባሻገር በአንድ ጉዳይ ላይ ዳኞች ቢለዋወጡ እንኳ ቀጣዩ ዳኛ የቀድሞው ከቆመበት እንዲቀጥል በቀላሉ መረጃ የሚሰጠው ይሆናል፡፡
ከግብርና ጋር በተያያዘ ምርታማ ዘሮችን የማላመድ፣ ወተትን ከቅቤ በቀላሉ የሚለይ ማሽንም ሰርተናል፡፡ በቅርቡ ከተጠቃሚዎች ጋር ርክክብ እናደርጋለን፡፡ እስከ ሐምሌ 30 ሁሉም የተጠናቀቁ የምርምር ስራዎቻችንን ለተጠቃሚዎች የማድረስ እቅድ ነው የያዝነው፡፡ ለ2010 ደግሞ ሌሎች እቅዶች ይዘናል፡፡ ፓተንት ያገኘንባቸውን ቴክኖሎጂዎች በርካታ ኩባንያዎች  እንድንሸጥላቸው እየጠየቁን ነው፡፡ ለወደፊት በተገቢው መንገድ እንዲያገኙት ይደረጋል፡፡
አሁን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከላችሁ አነስተኛ ነው፡፡ ለወደፊት ምን ታስቧል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ግዙፍ የሚባለውን የወርክሾፕና የፈጠራ ማዕከል እየገነባን ነው፡፡ ግንባታውም በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በርካታ የምርምር ማዕከሎችን የያዘ ግዙፍ የምርምር ማዕከል ነው፡፡ በሀገራችን የእንስሳት ህክምና ሆስፒታል የለም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ግን ይሄን እውን ለማድረግ የእንስሳት ህክምና ሆስፒታልም እየገነባ ነው፡፡    Read 903 times