Sunday, 16 July 2017 00:00

እምቦጭ አረም የፈጠረው ከፍተኛ ስጋት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

አረሙ ጣናን አልፎ አባይ ገብቷል ተብሏል

በቅርቡ ወልቂጤና አርሲ ዩኒቨርሲቲዎች ዝዋይ በሚገኘው ሀይሌ ሪዞርት አገር አቀፍ ጉባኤ አካሂደው ነበር፡፡ የጉባኤው መነሻ ደግሞ የዝዋይ ሀይቅን ዙሪያ 75 በመቶ ከብቦ ህልውናውን አደጋ ላይ የጣለው “እምቦጭ” ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር “Water hysin” የተባለው መጤ አረም ነው፡፡ ይህ አደገኛ አረም ከአሜሪካ አማዞን ተነስቶ፣ በአፍሪካ በቪክቶሪያ ሀይቅ አቋርጦ፣ እስከ ቆቃ መድረሱንና ቀስ በቀስ የዝዋይ ሀይቅን ዳርቻ መክበቡን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቀረበው ጥናት ያመለክታል፡፡
አረሙ ሀይቁን ከከበበ በኋላ ቀደም ሲል ሀይቁ ከነበሩበት ችግሮች ማለትም የአበባ እርሻዎች ኬሚካል በመርጨት ከሚያደርሱበት ብክለት፣ ጭላሎ ተራራና ዘቢዳር ተራራ እየተራቆተ ከመምጣቱ የተነሳ እየተሸረሸረ የሚገባው አፈር ደለል ጥልቀቱን መቀነሱ፣ ለተለያዩ የመስኖ ስራዎች በውሃ ፓምፕ እየተሳበ የሚወጣው ውሃና መሰል ችግሮች ላይ እምቦጭ ተጨምሮ ሀይቁ እጅግ ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደሆነ ተጠቁሟል። በዚህ አረም ተነሳ በሀይቁ የሚገኙ የአሳ ዝርያዎች መበከላቸውንና እየጠፉ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ በሀይቁ የሚገኘው ጉማሬ እንኳን ትክክለኛ ባህሪውን በማጣት ወደ ቤት እንስሳት ባህሪ መቀየሩን አመልክቷል።
ይህን አረም ለማጥፋት ምን እናድርግ ከማን ጋር እንስራ፣ ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው፣ ምን ያህል በጀት ይመደብ፣ በሚሉት ዙሪያ ዩኒቨርሲቲዎች መክረውና ኮሚቴ አዋቅረው ኮሚቴው የሚያቀርብላቸውን መርሃ ግብር ተቀብለው ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ለመግባት ለነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል፡፡
እምቦጭ አረም በዝዋይ ሀይቅ ሳያበቃ፣ በአገር ደረጃ ትልቅ የሚባለውንና በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰኔ 2015 በ”ባዮስፌር ሪዘርቭ››ነት የተመዘገበውን ጣና ሀይቅን ህልውና እየተፈታተነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ዶክተር ዋሴ አንተነህ፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክተርና የጣና ሀይቅ ተመራማሪ ናቸው፡፡ አብዛኛውን የምርምር ዘመናቸውን በጣና ላይ እንዳሳለፉ ይናገራሉ፡፡ እንደ ዶ/ር ዋሴ ገለፃ፤ ጣና በርካታና አስጊ ፈተናዎች የተጋረጡበት ቢሆንም ከሁሉም እምቦጭ የተባለው መጤ አረም ግን ትልቁና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ነው፡፡ በዓለም ላይ 5 ሚ. ያህል ሀይቆች እንዳሉና ከነዚህ ሀይቆች መካከል 250 ያህሉ ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ አመቺ መሆናቸው በሳይንስ መረጋገጡን የሚናገሩት ዶ/ር ዋሴ፤ ከ250ዎቹ የተመረጡ ሀይቆች አንዱ ጣና ቢሆንም ይህንን ፀጋና ትልቅ የተፈጥሮ ሀብት ጠብቀንና ተንከባክበን ለመያዝ አለመታደላችንን  ይገልፃሉ፡፡
“የአብዛኞቻችን ችግር ጣናን ተዝቆ የማያልቅ ሀብት (unlimited resource) አድርገን ማሰባችን ነው” የሚሉት ተመራማሪው፤ ይህ የዋህነት እንደሆነ ይገልፃሉ። ከዚህ ቀደም ተመራማሪዎች ሀረማያ ሀይቅ በአግባቡ ካልተጠበቀ ከ15 ዓመት በኋላ ይደርቃል ብለው ሲናገሩ ተማርን የሚለውም ሆነ ሌሎች ሲስቁ እንደነበር ያስታወሱት  ዶ/ሩ፤ ጣናም ይህ እጣ ሳይገጥመው ከበርካታ ችግሮቹ ልንታደገው እንደሚገባ አበክረው ያሳስባሉ፡፡ ጣና ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ቢመስለንም ከእነ ቪክቶሪያና ታንጋኒካ ሃይቅ ጋር ስናወዳድረው ትንሽ ነው ይላሉ። አማካይ ጥልቀቱ 8 ሜትር፣  ስፋቱም ከ3ሺህ ስኩየር ኪ.ሜትር በላይ እንደሆነም ያብራራሉ። እንደተመራማሪው ገለፃ፤ ከተጋረጡበት ችግሮች ከጠበቅነው በእርግጥም ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ነው። ዩኔስኮም ሲመዘግበው በሰው ጉትጎታና ውትወታ ሳይሆን ባለው የተፈጥሮ ፀጋ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ጣና ዓለም አቀፍ የውሃ አካል ነው፤ መነሻው ከአባይም ይሁን ራሱ ጣና ይህ አያከራክርም” የሚሉት ዶ/ር ዋሴ፤ የጣናና የአባይ ጥቅም የሚገባንና ትርጉም የሚሰጠን ግብፆችና ሱዳኖች በዚያ በረሀ አገራቸው እንዴት እንደሚጠቀሙበት ብናይ ነበር በማለት ቁጭታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ጣና ኃይቅ ለክልሉም ሆነ ለአገር የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ያብራሩት ዶ/ሩ፤ በአሳ ህይወቱን የሚመራ 6 ሺህ አሳ አስጋሪ እንደሚኖርና እያንዳንዱ ቤተሰብ በአማካይ 5 ቤተሰብ ቢኖረው ጣና በዓሳ ብቻ ለ30 ሺህ ሰው የህይወት ዋስትና እንደሆነ ጠቁመው፤ በዓመት ከሀይቁ 10 ሺህ ቶን አሳ ይመረታል ብለዋል። በሀይቁ ውስጥ 28 ያህል የዓሳ ዝርያዎች የሚኖሩ ሲሆን ከነዚህ መካከል 20 ሺዎቹ በየትኛውም ዓለም የማይገኙና በጣና ብቻ ብርቅዬ ሆነው የሚኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከል ከ15-17 የሚደርሱት የዓሳ ዝርያዎች የዝግመተ ህይወት ለውጥ የሚያሳዩ አሳዎች በመሆናቸው ለየት ያደርጋቸዋል ያሉት ተመራማሪው፤ ይህንን የዝግመተ ህይወት ለውጥ በነዚህ አሳዎች ላይ ለመመራመር ከሩሲያ፣ ከጀርመን፣ ከኔዘርላንድና ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ተማራማሪዎች በብዛት ወደ ጣና እየመጡ  መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
 እነዚህ ተመራማሪዎች እነዚህን አሳዎች “Live Laboratory to Study Evolution” ብለው እንደሚጠሯቸውም ተናግረዋል፡፡ ጣና ሌላም የብዝሀ ህይወት ጥበቃ በጣም አስፈላጊ የሚባልበት ፀጋ አለው። ከ300 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች መገኛና ማረፊያ ነው። በተለይ በደንቢያ፣ ጎርጎራና ፎገራ እነዚህን አዕዋፋት ለመጎብኘት ቱሪስቶች ይጎርፉ እንደነበር የሚናገሩት ዶ/ር ዋሴ፤ ጣና እዚሁ ለተፈጠሩት አዕዋፋት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ዓለም ተሰደው ለሚመጡት (Migrant birds) ለሚባሉትና ለመራባት ወይም የተፈጠሩበት አገር ያለውን አስቸጋሪ የአየር ንብረት ለማሳለፍ አርፈው የሚሄዱበት፣ እንግዳ ተቀባይ ኢትዮጵያዊ ሀይቅ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ይህ ሁሉ የተፈጥሮ ፀጋው ዩኔስኮ በብዝሀ ህይወት መጠበቂያነት (Biosphere Reserve) እንዲመዘግበው አድርጎታል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ እምቦጭ የተባለው መጤ አረም፤ የአሳዎችንም ሆነ የአዕዋፋትን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ አሳ እንቁላሉን የሚጥለውና የሚራባው በሀይቁ ዳርቻ በሚበቅሉ ሳሮች ስር ሲሆን እነዚህ የሳር ዝርያዎች ዙሪያውን እምቦጭ በተባለው አረም ተተክተው ድራሻቸው ጠፍቷል፡፡ እምቦጭ ደግሞ ውሃው ላይ እንደ ብርድልብስ በመንሳፈፍ፣ በስሩ ያለውን ኦክስጂን እጅግ በጣም በማሳነስ፣ብዝሀ ህይወትን እያጠፋ የሚገኝ ሲሆን ከነዚህ መካከል የአሳ ዝርያዎች ዋነኛ የአደጋው ሰለባ እንደሆኑ በጥናት መረጋገጡን ተመራማሪው ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል አረሙ ያለበት ቦታ የውሃ ትነት፣ አረሙ ከሌለበት የሀይቁ የውሃ ትነት በ5 እጥፍ እንደሚበልጥ በምርምር እንደተደረሰበት ይናገራሉ። ‹‹Beautiful Devil›› (ውብ ሰይጣን) ተብሎ የሚጠራው ይህ አረም፤ ወይን ጠጅ ቀለም ያለው አበባ፣ ደማቅ አረንጓዴ ቅጠልና ማራኪነት ያለው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በፈረንጆች አማካኝነት እንደሆነ ያብራራሉ። ሳሙኤል ለተባለው ግድብ ዙሪያ ማስዋቢያ እንደሆነና ከዚያ በኋላ አዋሽ መግባቱን ጠቁመው፣ ከተለያዩ መላምቶች በስተቀር እንዴት ወደ ጣና እንደመጣ ግን በትክክል የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡
ጣና ገብቶ 4 ሺህ ሄክታር የሚሆነውን የሀይቁን ክፍል ከሸፈነ በኋላ የዛሬ ስድስት ዓመት መታወቁን የሚገልጹት ተመራማሪው፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሙሉ ትኩረቱን በጣና እና በጣና ተፋሰስ ላይ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። ህብረተሰቡን በማስተባበር አረሙን ለመቆጣጠር ብዙ ጥረት መደረጉን የሚናገሩት ዶ/ር ዋሴ፤ ይህን አረም ለመቆጣጠር የሰው ህይወት ማለፉን ጭምር ይገልፃሉ። ‹‹ማህበረሰቡ መስዋዕትነት ባይከፍልና ባይቆጣጠረው ጣና እስካሁን ሙሉ በሙሉ በዚህ አረም ይወረር ነበር›› ሲሉም አክለዋል፡፡ በጥናትና ምርምር የሚገኙ ውጤቶችን ለሚመለከታቸው ስናሳውቅና ስንጮህ ብንከርምም የሚሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም የሚሉት ተመራማሪው፤ ጉዳዩ የአገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ዝም ሊባል አይገባም ብለዋል፡፡ ከውጭ ተሞክሮ በመነሳት የአረሙን ድራሽ ያጠፋል የተባለ የጥንዚዛ ዘር ከውጭ መጥቶ በላብራቶሪ እየተራባ መሆኑን አጥኚው ይገልፃሉ። ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች፤‹‹ጥንዚዛው አረሙን በልቶ ሲጨርስ ምን ሊበላ ነው? ጥንዚዛው ሌላ መዘዝ ላለማምጣቱ ምን ዋስትና አለ?›› የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ዶ/ር ዋሴ ይሄንን በተመለከተ፣ ትኩረት ተሰጥቶት ከፍተኛ ምርምር እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
እምቦጭ አረም ከጣና አልፎ አባይ ገብቷል፤ አረሙ አባይ ገባ ማለት ግድቡ በሚያቁረው ውሃ ላይ ገብቶ በጉጉት የምንጠብቀው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሙሉ አቅሙ የታመለትን ግብ እንዳይመታ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ጠቅሰው፣ ስለዚህ ጉዳዩ በቸልታ ሊታይ አይገባም፤  ሁሉም ትኩረቱንና ዘመቻውን በ‹‹ውብ ሰይጣን›› ላይ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡


Read 1463 times