Sunday, 16 July 2017 00:00

የገንዘብ እጥረት በግጭትና በአደጋ ቀጣና የሚኖሩ ሕፃናትን ትምህርት እየተፈታተነ ነው ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ 2 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ትምህርታቸውን ለመቀጠል ድጋፍ ይፈልጋሉ
በዚህ ዓመት ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 12 በመቶ ብቻ ነው የተገኘው
ዩኒሴፍ በሃምቡርግ ጀርመን ከተካሄደው የG-20 አገራት የመሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ፣ የገንዘብ እጥረት በግጭት ወይም በአደጋ ቀጣና የሚገኙ 9.2 ሚሊዮን ሕፃናትን ትምህርት እየተፈታተነ መሆኑን ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ዘንድሮ (2017) በአገር ውስጥ ከትምህርታቸው የተፈናቀሉትን 100 ሺህ ያህል ሕፃናት ጨምሮ 2.7 ሚሊዮን ሕፃናት ትምህርታቸውን ለመቀጠል ድጋፍ ይፈልጋሉ ብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከ369 ሺህ በላይ ስደተኛ ሕፃናት፣ የት/ቤት ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚፈልጉ አመልክቷል፡፡
ድርጅቱ፣ በድንገተኛ አደጋ ላይ ላሉ አገራት የትምህርት ፕሮግራም ከሚያስፈልገው 932 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ እስካሁን 115 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ከበጎ አድራጊዎች ማግኘቱን ጠቁሞ፤ የተጠየቀው ገንዘብ በሰብአዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ 9.2 ሚሊዮን ሕፃናት መደበኛና መደበኛ ያልሆነ መሰረታዊ ትምህርት መስጠት እንደሚያስችለው ገልጿል፡፡
“ያለ ትምህርት (ያለ እውቀት) እና የሙያ ክህሎት ያደጉ ሕፃናት፣ እጅግ አስከፊ የሆነውን ሕፃናት ያሉበትን ሁኔታ ከማባባስ በስተቀር ለአገራቸው ሰላም፣ ልማትና ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማበርከት አይችሉም” ብላለች፤ ወጣቷ የአሁኑ የዩኒሴፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሙዙን አልመለሃን፡፡ በሃምቡርግ - ጀርመን፤ በG-20 አገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ድርጅቱን ወክላ ስትናገርም፡- “በጦርነት ቀጣና ያደጉ ሚሊዮን ህፃናት፣ የሚከፍሉት ዋጋ እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ሕፃናት ት/ቤት መሄድ ካቆሙ በአእምሮና በአካል ደካማ ከመሆናቸውም በላይ ለተለያዩ መጥፎ አደጋዎች፣ ለልጅነት ጋብቻ፣ ለጉልበት ብዝበዛና ለወታደርነት ምልመላ ይጋለጣሉ” ብላለች- ሙዙን አልመለሃን፡፡
የዩኒሴፍ የትምህርት ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ክፍተት የተለያየ ሲሆን በኢራቅ 36 በመቶ፣ በሶሪያ 64 በመቶ፣ በየመን 74 በመቶ፣ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ 87 በመቶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የሕፃናትና የወጣቶች አጠቃላይ ትምህርት ከፍተኛ መሻሻል ቢደረግበትም የትምህርት ሲስተሙ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጋለጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ባለፈው ሁለት ዓመት በተከታታይ የተከሰተው ድርቅ፣ ተማሪዎች ከት/ቤት እንዲቀሩና የትምህርት ጥራት እንዲቀንስ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩት ት/ቤቶች ሲዘጉ፣ ተማሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና መምህራን ውሃ ፍለጋ ከሰፈራቸው መንቀሳቀሳቸውን፣ በ2008/09 መጨረሻ የትምህርት ዘመን ከ200 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የተዘጉ መሆናቸውን ዩኒሴፍ አመልክቷል፡፡
በያዝነው ሐምሌ ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያ ለ2017 የትምህርት ዘመን ለአደጋ በተጋለጡት አካባቢዎች ሕፃናትን በት/ቤት ለማቆየት ያስፈልጋል ተብሎ ከተጠየቀው 11.6 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የተገኘው 57 በመቶ ወይም 5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ዩኒሴፍ ገልጿል፡፡
Read 621 times