Sunday, 16 July 2017 00:00

የቀን ገቢ ላይ የተመሰረተው ግብር- ህጉና ችግሮቹ

Written by 
Rate this item
(24 votes)

    “ከግብር እና ከሞት ማንም አያመልጥም” ይሉ ነበር አሜሪካኖች፡፡ ቱጃሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ “ላወቀበት ብዙ መንገድ አለ” ይላሉ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የ916 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠማቸው በማሳየት ለ18 አመታት ያህል ይህ ነው የሚባል የፌደራል ታክስ እንዳልከፈሉ ይነገራል፡፡ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት በሚወዳደሩበት ወቅትም “የግብር ህጉን ክፍተቶች (loopholes) በመጠቀም አያሌ ረብጣዎችን ከግብር አድኛለሁ” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል፡፡ “ችግሩ የኔ ሳይሆን የህጉና የህግ አውጭዎቹ ነው፡፡” በማለትም ጣታቸውን ወደ ተፎካካሪያቸው የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን ቀስረው ነበር፡፡ በመሰረቱ ግብር ማጭበርበር (tax evasion) እንጂ ከግብር ማምለጥ (tax avoidance) ወንጀል አይደለም፡፡
በግብር ጉዳይ በመንግስትና በዜጎች መካከል እሰጥ አገባዎችን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ መንግስት ከግብር ብዙ ገቢ ለመሰብሰብ ሲጥር፣ ዜጎች በበኩላቸው፣ ከግብር ለማምለጥ ሲታትሩ፣ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በግብር ጉዳይ በዜጎችና በመንግስት መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ብዙ ዙፋኖች ተነቃንቀዋል፡፡ ትላልቅ ግዛቶች (empires) ወድቀዋል፡፡ ለግብፅ፣ ለሮምና ለስፔን ሰፋሪ ግዛቶች (empires) መፍረስ አንዱ ምክንያት በግብር ምክንያት የተቀሰቀሱ አመፆች እንደሆኑ ይነገራል።
ብሪታኒያ ከአትላንቲክ ማዶ ካለው ሰፊው ርስቷ የተቀነሰችው፣ የአሜሪካም አብዮት የፈነዳው በግብር ምክንያት በተፈጠረ እሰጥ አገባ መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በስኳር ላይ የተጣለው ግብር፣ የቴምብር ቀረጥና በሻይ ላይ የተጣለው ታክስ በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩትን ሰፋሪዎች አስቆጣ፡፡ በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ ሳንወከል በሚወጡ የግብር ህጎች መገዛት የለብንም (No taxation without representation) አሉ፡፡ በዚህ ሰበብ የተለኮሰው የአመፅ እሳት፤ ብሪታኒያን አንገብግቦ አስወጣት፤ ሰፋሪዎቹም ነፃ የአሜሪካን መንግስት መሰረቱ፡፡
የፈረንሳይ አብዮትም የፈነዳው ሀገሪቷ የተቆለለባትን ግዙፍ ዕዳ ለመክፈል ዜጎቿ ላይ የጫነችው እጅግ የበዛ ግብር የህዝቡን ቁጣ በመቀስቀሱ ነው፡፡ ከበርቴው ከግብር ነፃ ሲሆን፣ ገበሬውና የሰራተኛው መደብ በተጫነባቸው ከፍተኛ ግብር ክፉኛ ማቅቀዋል፡፡ ይህ ፍትሐዊነት የጎደለው የግብር ስርዓት፤ የፈረንሳይን አብዮት አስነስቶ፣ ሉዊስ 16ኛም ስልጣኑን ብቻ ሳይሆን ህይወቱን አጣ፡፡ ለእንግሊዝ አብዮት አንዱ መነሻም በግብር ምክንያት የተነሳ ብሶት ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በግብር ምክንያት በርካታ ንትርኮችና አለመግባባቶች በመንግስትና በዜጎች መካከል ተፈጥረዋል፡፡ ሰሞኑን በመዲናችን አዲስ አበባ በደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሚሰማው ብሶት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን የሚወጡት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን (ኢገጉባ) በቀን ገቢ ላይ ተመስርቶ በሚወስነው የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ይህ በግምት ላይ ተመስርቶ የሚከፈል የደረጃ “ሐ” ግብር፣ የአፈፃፀም ችግሮች ብቻ ሳይሆን ይህን ለመወሰን የመጡት የግብር ህጎችም የራሳቸው ክፍተቶች አሉባቸው፡፡
በተሻሻለው የግብር አዋጁ መሰረት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ ማለት አመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከ500 ሺህ ብር በታች የሆኑ ግለሰቦች ናቸው፡፡ የትኛውንም ያህል መጠን የሚያገኙ ድርጅቶች ግን እንደ ደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ ይቆጠራሉ፡፡ በቀድሞው የግብር አዋጅ ደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ ማለት አመታዊ ገቢያቸው ከ100 ሺህ በታች የነበሩት ናቸው፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግብር የሚከፍሉት አማካይ የቀን ገቢያቸው ተገምቶ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን (ኢገጉባ) ባስቀመጠው ቀመር መሰረት ነው፡፡ ደረጃ “ሐ” ለግብር አሰቸጋሪ (hard - to - tax) የሚሆኑ የስራ ዘርፎች የተሰባሰቡበት መደብ ነው፡፡ በዚህ መደብ ላይ የጣለው ግብር ምንጊዜም ከውዝግብ ርቆ አያውቅም፡፡
ከዚህ መደብ ሥር ያሉ ግብር ከፋዮችን የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ ማድረግ ለግብር ከፋዮቿም ሆነ መንግስት ግብርን ለመሠብሠብ የሚያደርገውን ወጪ በእጅጉ ያበዛዋል፡፡ ለዚህም ነው በቀን ገቢ ግምት ላይ የተመሠረተ ግብር እንዲከፍሉ የሚደረገው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ይህን ግብር ለማስፈፀም የወጡት አዲሱ የገቢ ግብር ደንብ ሠንጠረዥም ሆነ መመሪያ ቁጥር 123/2009 ችግሮች ይታዩባቸዋል፡፡ ለተፈጠረው የትመና ችግርም የየራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡
የአዲሡን የግብር አዋጅ መውጣት ተከትሎ፣ አዲስ የግብር ደንብ ተረቅቆ በዚህ ወር ይወጣል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ ረቂቅ ደንብ ደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የተሰማሩባቸውን የንግድ ዘርፎች ይዘረዝራል፡፡ ይህ ሠንጠረዥ ከጌሾና ብቅል ንግድ ጀምሮ እስከ ጀበና ቡና ንግድ ድረስ በአጠቃላይ ዘጠና ዘጠኝ የንግድ ዘርፎችን አካቶ ይዟል፡፡
ይህ ዝርዝር በሃገሪቱ ውስጥ ብሎም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎችን ያጠቃልላል ብሎ ማሠብ አይቻልም፡፡ ይህ የግብር ሰንጠረዥ የንግድ ሚኒስቴር ከተዘጋጀው የንግድ ፈቃድና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለመስጠት ከሚጠቀምበት የንግድ ስራ ፍቃድ መስጫ መደቦች መመሪያ (Ethiopian standard industrial classification) ጋር ቢጣጣም የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይህ የንግድ ሥራ ፍቃድ መስጫ መደቦች መመሪያ የራሡ የሆኑ ክፍተቶች ቢኖሩትም፣ ከሞላ ጎደል በሃገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ የንግድ ስራዎችን ያካተተ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በግብር ደንቡ ባለው ሠንጠረዥ ላይ ብቻ ተመስርቶ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብርን መሠብሰብ ብዙ ችግሮችን ያስከትላል፡፡
ደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የሚከፍሉት የግብር  መጠን የሚወሠነው የግብር ከፋዩን የቀን ገቢ መጠን ሊያሳዩ የሚችሉ አመላካቾችን (indicators) በመጠቀም ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ አመለካከቶች (indicators) ሙሉ ለሙሉ ተጨባጭ (objective) ናቸው ማለት አይቻልም። የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት የሚጠቀምባቸው መለኪያዎች ሙሉ ለሙሉ ተጨባጭ ካለመሆናቸው በተጨማሪ ገቢ በመገመት ሂደቱ ላይ የገማቾች የተለያየ ህላዓዊ ፍርድ (Subjectivity) ሲታከልበት በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያሉ ግብር ከፋዮች የተለያዩ መጠን ያለው ግብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ ይህ የቀን ገቢ መጠን ላይ የተመሠረተ ግብር በተቻለ መጠን ህሊናዊ ፍርድን (Subjectivity) እስካላስቀረ ድረስ እና ሳይንሳዊነትን እስካልተላበሠ ድረስ ኢ-ፍትሐዊ (in-equitable) ግብር መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡
ችግሩን የከፋ ያደረገው ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የቀን ገቢ ላይ የተመሠረተ ግብር ትመና የተካሔደው ከስድስት አመታት በፊት 2003 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ በነዚህ ስድስት አመታት ውስጥ የገቢያቸው መጠን የጨመረ የሚጠበቅባቸውን ግብር ሳይከፍሉ፣ የገቢያቸው መጠን ያሽቆለቆለ ግብር ከፋዮች በበኩላቸው፤ ያልተገባ ግብር ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ ‹‹ጭራሽ ከመቅረት ዘግይቶ መድረስ ይሻላል›› እንደሚባለው፤ ከስድስት አመታት በኋላም ቢሆን የግብር ክለሳ መካሔዱም አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን፤ በትመና ሥራው ላይ የተሠማሩ ሰዎችን በዘመቻ ካሠለጠነ በኋላ የትመና ሥራውንም በዘመቻ እንዲሠሩ ማድረጉ፣ እውነተኛ ገቢን እንዲሁም ግብርን ማንፀባረቅ አለመቻሉ፤ ቅሬታንም መፍጠሩ የሚያስገርም አይደለም፡፡
የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብ ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ በመያዝ የተወሰነባቸውን የቀን ገቢ እንዲሁም በዚያ ላይ የተጣለውን ግብር የማስቀየር (rebut) የማድረግ ዕድሉ በህግ ተደንግጎ ቢሠጣቸው ችግሩን በተወሠነ መልኩም ቢሆን መቀነስ ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት ዕድል የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይን የሒሳብ መዝገብ እንዲይዝ ያበረታታዋል፡፡ የያዙትን የሒሳብ መዝገብም በማየት ከደረጃ ‹‹ሐ›› ወደ ደረጃ ‹‹ለ›› እና ደረጃ ‹‹ሀ›› የተሸጋገሩ ግብር ከፋዮችን በቀላሉና በማያሻማ ሁኔታ መለየት ይቻላል፡፡ በአሁን ሰአት በደረጃ ‹‹ሐ›› ያሉ ግብር ከፋዮች ወደ ሌሎች የግብር ደረጃዎች መሸጋገራቸውን ግብር ሠብሣቢው መሥሪያ ቤት እንዴት እንደሚመዝን ማሠብ በራሡ ትልቅ ጥያቄ ያጭራል፡፡
ግብርን መደበቅ፣ በገቢ ትመና ወቅትም እቃዎችን መሰወር፣ ህፃናትን በሱቆች ላይ አስቀምጦ መሔድ፣ ሱቅ ዘግቶ መጥፋት እና የመሣሠሉት ችግሮች የሚፈጠሩት በግብር ከፋይ ዘንድ የግብርን ጥቅም ካለመገንዘብ በተጨማሪ ፍትሐዊ ያልሆነ ግብር መጫኑ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ተገቢነት የሌለውን ከፍተኛ ግብር በመፍራት ሱቁን ዘግቶ ቢጠፋ ምንም አያስገርምም፡፡
በገቢ ግብር ደንቡ ሠንጠረዥ ላይ የተቀመጠው አማካይ የትርፍ (Profitability rate) መቶኛ  በራሱ እንዴት እንደተወሠነ ግራ አጋቢ ነው፡፡ በሠንጠረዡ ላይ ያሉ የንግድ ዘርፎች አይከስሩም የማለት አንድታም ያለው ይመስላል፡፡ በደረጃ ‹‹ሐ›› ሥር ያሉ ግብር ከፋዮች እንደማንኛውም ነጋዴ የሚያጋጥማቸውን ትርፍም ሆነ ኪሣራ የረሳው ይመስላል፡፡
ይልቁንም በዚህ መደብ ያሉ አነስተኛ ግብር ከፋዮች የገጠማቸውን ኪሣራ በሒሳብ መዝገብ የሚያስረዱበት እድል ቢፈጠርላቸው፣ ኪሣራቸውንም እንዲያሸጋግሩ ቢፈቀድላቸው በርካታ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ በመያዝ፤ አሁን የተፈጠረውን ችግር መቀነስ ይቻላል፡፡ መንግስት ከአፈፃፀም ችግሮች በተጨማሪ የህጉንም ግድፈቶች በማየት የግብር ከፋዩን ቅሬታ ሊፈታ ይገባል፡፡

Read 11328 times