Thursday, 05 April 2012 13:10

የሆሊዉድ ፊልሞች ከቻይና የበጀት ድጋፍ እየጠየቁ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷ ዓለምን በመቆጣጠር ላይ የምትገኘው ቻይና፤ የሆሊውድን ትኩረት  እየሳበች ነው፡፡ የሆሊውድ ፊልሞች በእስያዊ ጭብጦች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ የተጠየቀ ሲሆን ቻይና በፊልም ሰሪ ኩባንያዎቿ አማካኝነት ለትላልቅ የሆሊዉድ ፊልሞች የበጀት ድጋፍ ማድረግ እንደጀመረች ቻይና ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል፡፡ የሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች በቻይና ገበያ በጣም መነቃቃታቸውን ያመለከተው ዘገባው፤ ከወር በፊት የአገሪቱ መንግስት በየዓመቱ ወደ ቻይና የሚገቡ ፊልሞችን ብዛት ከ20 ወደ 35 ማሳደጉ ትኩረታቸው እንዲጨምር ማድረጉን አመልክቷል፡፡

የሆሊውድ ፊልሞች የቻይና ገበያ በዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የዘገበው ቻይና ዴይሊ ኒውስ፤ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የገቢ መጠኑ ወደ 5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያድግና በዓለም አቀፍ ገበያ ሁለተኛ ደረጃን  እንደሚይዝ ጠቁሟል፡፡ በእስያ አህጉር ከ650 በላይ ዓመታዊ  የፊልም ኤግዚቢሽኖችና ፌስቲቫሎች የሚደረጉ መሆናቸውም ለሲኒማ ኢንዱስትሪው ገበያ እንደፈጠረ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

 

ይህ በዚህ እንዳለ የሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች ለሚሰሯቸው ትላልቅ ፊልሞች የቻይና ኩባንያዎችን የበጀት ድጋፍ እየጠየቁ ሲሆን ከቅርብ ዓመት ወዲህ በተሰሩት እንደ “ዘ ዳርክ ናይት”፤ “ኢንሰፕሽን” እና “ሃንጎቨር” ፊልሞች ላይ የቻይና ኩባንያዎች 45 በመቶ የሚደርስ የበጀት ድጋፍ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡

 

 

Read 938 times Last modified on Thursday, 05 April 2012 13:22